Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየአማራ ሕዝብ ለምን በክራንቻ ከመጎርደም አልዳነም?

የአማራ ሕዝብ ለምን በክራንቻ ከመጎርደም አልዳነም?

ቀን:

ሁሴን አዳል መሐመድ (ዶ/ር)

ሥጋ በል እንስሳት አጥንትን የሚጎረዳድሙበትና ከአጥንት ላይ የተጣበቀ ሥጋ የሚግጡበት ክራንቻ (Carnassials) የሚባል ስለታማ ጥርስ አላቸው፡፡ የላይኛው ቅድመ መንጋጋ (Premolar) እና የታችኛው መንጋጋ (Molar) ጥርሶች አንድ ላይ ክራንቻ ጥርሶች ይባላሉ፡፡ በዚህ ጥርስ አማካይነት በእንስሳው ሁለት የፊት እግሮች ጠበቅ ብሎ የተያዘ አጥንት የላይኛው ክራንቻ ከታችኛው ክራንቻ ጋር እንደ መቀስ በመጫወት (በመፋጨት) ይጎረዳደማል፡፡ ከአጥንቱ ጋር የተጣበቀ ሥጋ እየተነጨ ወደ ጉሮሮ ይላካል፡፡

‹‹የብሔር ፖለቲካ›› የመሬት ባለቤትነትን በብሔረሰብ ስም በመቆጣጠር በቡድን ለተደራጁ ጥቂት ፖለቲካ አደሮችና ጥገኛ ከበርቴዎች መሬት በሥልት የሚያከፋፍል፣ ብዙኃኑን ነባር/መጤ፣ ወዳጅ/ጠላት በማባባል ዜጎችን የሚነቅልና የሚተክል፣ የዜጎችን በአገራቸው የተለያዩ አካባቢዎች በነፃነት ተንቀሳቅሰው የመኖርናብት የማፍራት መብት ነፍጎ በድህነት የሚያማቅቅ የአዲስ ገዥ መደብ የሸፍጥ ፖለቲካ ነው፡፡ ገዥ መደቡ ሕዝብን ከፋፋይና ኋላቀር ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› በመሣሪያነት ተጠቅሞ የመንግሥትና የፓርቲ መዋቅርን ጓዳና ሳሎን በማድረግ ከሚሰበስበው ኪራይ፣ በሁለቱም መዋቅሮች በማፈራረቅ ለሚሰገስጋቸው የገዥ መደቡ አባላት የተልዕኮ አስፈጻሚነት ድርሻ እንደ ችሎታቸውና ተሳትፎአቸው ያከፋፍላል፡፡ በአንፃሩ የፖለቲካው ደጋፊ ላልሆኑ ዜጎች ሁሉንም ዓይነት ዕድልና የመግቢያ በር ይዘጋባቸዋል፡፡

በአገራችን ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› የገዥ መደብ ድብቅ ርዕዮት ‹‹ጨቋኝ ብሔር›› ብሎ የፈረጀውን የአማራ ብሔረሰብ ትውልድ ለአገሩ ባይተዋር ማድረግና ሌሎች የኢትዮጵያ ብሔረሰቦችን አነሳስቶ በትውልዱ ላይ ማዝመት ነው፡፡ ስለሆነም ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› ቀስት የተነጣጠረበት አማራነትና የአማራ ሕዝብ ዘመን ሊሽረው የሚችል የማይመስል የመከራ ዶፍ ወርዶበታል፡፡ በዚህ ዘመን አማራ ተብሎ የተፈረጀ ኢትዮጵያዊ ሁሉ በሥጋ በል እንስሳ ክራንቻ ውስጥ ገብቶ እንደሚደቅ አጥንት፣ በገዛ አገሩ ውስጥ እየኖረ መጤ የተባለ፣ የህልውና አደጋ የተጋረጠበት ‹‹በብሔር ፖለቲካ›› ክራንቻ በጥብቅ የተያዘ ሕዝብ ነው፡፡ የትሕነግ የፈጠራ ሥራ ውጤት የሆነው ይህ ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› በአገራችን አድማሱን እያሰፋ በሄደ መጠን በአማራ ሕዝብ ላይ የሚደርሰው ተፅዕኖም አድማሱ በዚያው ልክ እየሰፋ ሄዷል፡፡ እሾህን በእሾህ መንቀል በሚመስል ፈሊጥ ፖለቲካው የሚያደርስበትን ጉዳት በተመሳሳይ ግብረ መልስ መቀልበስ ይቻላል የሚሉ ጥቂት የአማራ ብሔረሰብ ተወላጆች፣ ‹‹ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ›› እንዲሉ ከጊዜ በኋላ በቁጭት ስሜት በመገፋፋት ‹‹የአማራ ብሔር ፖለቲካ ፓርቲ›› ለማቋቋም ሞክረዋል፡፡

በአማራ ሕዝብ ላይ በደረሰው ከልክ ያለፈ ግፍና በደል ምክንያት ‹‹የአማራ ብሔርተኝነት›› ትግል ፈር ቀዳጅ የነበሩት ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ ካቋቋሙት የመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት (መአሕድ) ወዲህ፣ የአማራ ሕዝብ መብትን መከበር አጀንዳ አድርገው የተነሱ ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ቢኖሩም ‹‹የአማራ ሕዝብ ሁለንተናዊ መብቶች፣ ጥቅሞችና ፍላጎቶች በዘላቂነት ተከብረው ማየት›› የሚል ራዕይ በመንደፍ፣ የአማራ ብሔርተኝነት ትግልን በስፋት ማነቃቃት የጀመረው የአማራ  ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሰኔ 2-3 ቀን 2010 .ም. ከተመሠረተ ወዲህ ገና ሦስት ዓመታት ብቻ ሆኖታል፡፡ ይሁን እንጂ በኅብረ ብሔራዊነትናኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብ ቅኝት የታነፀውን ሰፊውን የአማራ ሕዝብ ‹‹በብሔር የፖለቲካ ፓርቲ›› ማዕቀፍ ውስጥ በቶሎ አደራጅቶ ውጤታማ የሆነ ፈጣን እንቅስቃሴ ማድረግ ቀላል አልሆነም፡፡ ባለፉት 30 ዓመታት በአማራ ሕዝብ ስም በሚነግዱ አስመሳዮችና ከብሔረሰቡ በወጡ ተላላኪዎችና አድርባዮች ጭምር የአማራ ሕዝብ ‹‹በዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት›› የሸፍጥ ፖለቲካ በመገነዝ ተዘናግቶ እንዲቆይ ስለተደረገ ‹‹የአማራ ብሔርተኝነት›› ትግል ቶሎ የማይሰማ የእንጀራ ምጣድ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ‹‹በብሔርተኝነት ትግል›› ጥርስ አብቅለው እንደ ነቀሉት የትግሬናኦሮሞ ‹‹የብሔር ድርጅቶች›› ሁሉ፣ የአማራ ሕዝብን ስም ይዞ የተመሰረተው ‹‹ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ›› (ብአዴን) የአማራ ሕዝብን  ትግል ‹‹በአማራ ብሔርተኝነት›› ትግል  ዓውድ ማስኬድ ነበረበት፡፡ ዳሩ ግን የፓርቲው ፖሊት ቢሮ አማራ ባልሆኑ  ሰርጎ ገቦች ቁጥጥር በመውደቁ፣ ‹‹ከብሔርተኝነት›› ትግል በፊት የይስሙላ ‹‹ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት›› ስብከት እየተቀነቀነ በአማራ ሕዝብ ‹‹የብሔርተኝነት ፖለቲካ›› ትግል ቁማር ተጫወቱበት፡፡ 

በመሆኑም ‹‹እህት ድርጅቶች›› ተብዬዎች ስላጭበረበሩት ዕውነተኛ ‹‹የአማራ ብሔርተኝነት›› ትግልን የማነሳሻው ወቅት እንዲረፍድ ተደረገ፡፡ ‹‹እህትማማቾች›› ነን የሚሉ ሌሎች የብሔረሰብ ድርጅቶች በየደረጃው ባለው የፓርቲና የመንግሥት መዋቅር ቁልፍ ቦታዎች ላይ የራሳቸውን ሰዎች በመመደብ  ለአማራ ሕዝብ የፈጠሩለትን ድርጅት ድብቅ ዓላማቸውን ለማሳካት እንዲችሉ ወደ አማራ ሕዝብ ዘልቆ መግቢያ በር አድርገው ተጠቀሙበት እንጂ፣ የአማራ ሕዝብ የፖለቲካ ሥልጣን ባለቤት እንዲሆንና መብቱን ለማስከበር እንዲጠቀምበት አድርገው አልመሩትም፡፡ የፖለቲካ ትግል የሚጠይቁ ወሳኝ የሆኑ የአማራ ሕዝብ የፖለቲካ ጉዳዮችን በወቅቱ ለይቶ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመፍታት ካለመቻሉ የተነሳ፣ በአማራ ሕዝብ ጉዳይ የፖለቲካ ውሳኔ ሰጪዎች የነበሩት ራሳቸው ሰርጎ ገቦቹ እንጂ ከአማራ ሕዝብ አብራክ የተገኙ የአማራ ሕዝብ ዕውነተኛ ተወካዮች አልነበሩም፡፡ የአገሪቱን ሕገ መንግሥት ከማፅደቅ፣ በውስጥ የአስተዳደር ወሰኖች ጉዳይ ላይ ከመወሰን፣ በብሔራዊ ሀብት ክፍፍልና ሥርጭት፣ እንዲሁም በሌሎችም የአማራ ሕዝብ ወሳኝ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ የአማራ ሕዝብ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ተሳትፎ አድርጎ ጥቅሙን አላስጠበቀም፣ መብቱንም አላስከበረም፡፡ ይህን በማረጋገጥ ድርጅቱ  (ብአዴን) የተላላኪነት ሚና ብቻ ሲጫወት እንደቆየ የድርጅቱ ሊቀመንበርና የክልሉ ምክር ቤት  ምስክርነት መስጠታቸው ይታወሳል፡፡ በዚህ የተነሳ የአማራ ሕዝብ መሠረታዊ መብቶቹንና አንጡራ ይዞታዎቹን ማስከበር ባለመቻሉ ‹‹ሰዶ ማሳደድ›› እንዲሉ፣ መብቱን ለማስከበርና ክብሩን ለማስመለስ መሥራት የሚኖርበት  ከባድ ትግል የሚጠይቅ ተንከባላይ የቤት ሥራ ተከማችቶ ቆይቶታል፡፡  ለዚህም ነው የአማራ ሕዝብ ለረዥም ጊዜ በክራንቻ ውስጥ ሆኖ ሲፈጭ ቆይቷል ለማለት የሚያስደፍረው፡፡  

ሌሎች ብሔረሰቦች ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› ያስገኘላቸውን ጥቅም ሲያጣጥሙ በተቃራኒው አማራነት ‹‹አማራ በመሆን›› (በትውልድ) እና ‹‹አማራ በመባል›› (በትስስር) የሚገኝ ለአማራ ሕዝብ ጉዳት የሚያስገኝ ዕዳ ሆኗል፡፡ ስለሆነም በአማራነት የተፈረጁ ሁሉም የአገሪቱ ዜጎች በዚህ የሚያደቅ ክራንቻ ውስጥ ገብተው በመድቀቅ እየጠፉ ነው፡፡ ትውልዳቸው ከአማራ ብሔረሰብ የሚመዘዝ ሰዎች ‹‹አማራ በመሆን›› የሚገኝ አማራነት ተሰጥቷቸዋል፡፡ በትውልድ አማራ ሳይሆኑ የአማራ እሴቶችን ያጎለበቱ የሌሎች ብሔረሰቦች ተወላጆች፣ ‹‹አማራ በመባል›› የተሰጣቸውን አማራነት ተላብሰዋል፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎን የአማራ  ናቸው የሚባሉትን እሴቶች የተጋሩ በትውልድ አማራ ያልሆኑ ሌሎች ዜጎች፣ በአማራነት ተፈርጀው ለትውልደአማራ የተከፈተው ክራንቻ እነሱንም ፈጭቷቸዋል፡፡ ዘር ማጥፋት ከተካሄደባቸው አንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች ለምሳሌ ማይካድራ የተጠናቀሩ አስረጂዎች  እንዳመለከቱት፣ የአማራ እሴቶችን የተላበሱ በትውልድ የሌላ ብሔረሰብ አባላት የዚህ ክራንቻ ሰለባ ሆነዋል፡፡ ለሥራና ለኑሮ ወደ ማይካድራ ሄደው በአማራ ኅብረተሰብ ውስጥ የተገኙ የወላይታ፣ሲዳማ፣ጉራጌ፣ ወዘተ ብሔረሰብ ተወላጆች በሌላ ክልል ውስጥ ግፍ እንደ ሚፈጸምባቸው የአማራ ተወላጆች እነዚህም ‹‹ከኑግ ጋር የተገኘ ሰሊጥ›› በመሆን ለአማራ ሕዝብ የመጣው ግፍና መከራ ተቋዳሽ ሆነዋል፡፡ የመንግሥት የሥራ ቋንቋ የሆነውን አማርኛ በመናገራቸው ብቻ፣ በትውልድ አማራ አለመሆናቸው ከሞትና ከጣዕር አላዳናቸውም፡፡ አማራ ናችሁ ተብለው የሚፈጩት ‹‹የአማራ እሴት›› ተብሎ በሴራና በተንኮል የተፈረጀውን የአማርኛ ቋንቋ በመልመዳቸው ነው፡፡ ዜጎቹ በመፈጫ ቀጠናው  ውስጥ የተገኙት በኢትዮጵያ አገራቸው ተማምነው ኢትዮጵየያዊነት በፈጠረው ሰፊ ገበያ ለመጠቀም ወደ አካባቢው በመንቀሳቀሳቸው ነው፡፡

‹‹የአማራ ነው›› ተብሎ በፖለቲካ የተፈረጀውን ‹‹የአማራ እሴት›› የተጠቀመ ኢትዮጵያዊ ሁሉ በክራንቻ ስለተፈጨ፣ ‹‹አማራ መሆን›› እና ‹‹አማራ መባል›› እኩል የጉዳት ሰለባ አድርጓል ማለት ይቻላል፡፡ ክራንቻው በአማራነት በኩል ኢትዮጵያን ፈጭቷል፣ እየፈጨም ይገኛል፡፡ ‹‹ባጎረስኩኝ እጄን ተነከስኩኝ›› እንዲሉ ቀደም ሲል ኢትዮጵያን ለመገንባት አስተዋጽኦ ያበረከተው ‹‹የአማራነት እሴት›› ዋጋ ቢስ ተደርጎ ቀጥሏል፡፡ የአሁኑ የአማራ ትውልድ ከአማራ እሴት ገንቢዎች አብራክ የወጣ ትውልድ መሆኑ ‹‹ነፍጠኛ አማራ›› አስብሎት የማይገባው ፖለቲካዊ ጫና ተደርጎበታል፡፡
‹‹ሸዋ፣ ወሎ፣ ጎጃም፣ ጎንደር ለሚኖረው ሕዝብ የአማራ ማንነት መጠሪያ የሰጠነው እኛ ነን›› የሚለውን የትሕነግ ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ መግለጫ ወደ ጎን ትተን፣ ሰፊ ሥርጭት ያለው የአማራ ሕዝብ ሸዋ፣ ወሎ፣ ጎጃም፣ ጎንደርና ሌሎች የአገራችን ኢትዮጵያ አካባቢዎች ውስጥ ይኖራል፡፡ የዚህ ነባራዊ ሁኔታ መኖር በውስጡ ንዑስ ብዝኃነት እንዲኖረው በማድረጉ፣ ከአማራነት የጋራ ማንነት ጎን ለጎን ከአያት ቅድመ አያት የተወረሰ የጋራ ሥነ ልቦናና የጎለበተ አማራጭ የጋራ ማንነት አለ፡፡ እንደ ሌሎች ጽንፈኛ ብሔርተኛ ሆኖ ለመውጣት ለአማራ ውስጠ ፖለቲካ ያስቸገረው አንዱ ምክንያት ይህ ንዑስ ብዝኃነትና በውርስ የተረከበውን እሴት ለመካድ የሚቸገር ሕዝብ መሆን ነው፡፡

ይሁን እንጂ እነዚህ ንዑስ ማንነቶች ኢትዮጵያዊነትን የሚያጠናክሩ እንጂ አትዮጵያዊነትን የሚሸረሽሩ ወይም የሚሸራርፉ አይደሉም፡፡ ቀደም ባለው ዘመን እንደ ታየው ብሔረሰቦችን እንደ ሲሚንቶ በማያያዝ ኢትዮጵያ አንድነቷ ተጠብቆዘለዓለም በክብር እንድትኖር ይረዳሉ እንጂ፣ ለአንድነቷ መዳከምና መፈራርስ አሉታዊ አስተዋጽኦ አያበረክቱም፡፡ ዜጎች ፍትሕናኩልነት በሰፈነበት ሥርዓት ዴሞክራሲያዊ መብታቸው ተከብሮ፣ የሥልጣን ባለቤትነታቸው ተረጋግጦ፣ ራሳቸው በመረጧቸው ሰዎች እየተዳደሩ  በአብሮነትና በአንድነት እንዲኖሩ እንጂ በብሔረሰብ ዘውግ በመከፋፈል በቋንቋ ግድግድ አጥር ተለያይተው በጠላትነት እየተያዩ ወደ መለያየት ለማምራት በጉርብትና እንዲኖሩ አይገፋፋም፡፡ በየደረጃው በሚፈጠር የብሔረሰቦች መተሳሰር (መደራረብ) የምትገነባ በፅኑ የአንድነት መሠረት ላይ የተዋቀረችብረ ብሔራዊ ኢትዮጵያን የሚገነቡ እንጂ፣ ተለያይተው በመኖር በፌደሬሽን ምክር ቤት ላይ የሚወደስና በየዓመቱዳር 10 ቀን በሚከበረው የብሔረሰቦች ፌስቲቫል በሚቀርብ የብሔረሰቦች የባህል ትርዒት የሚዘከር የላላ የይስሙላ አንድነት የሚፈጥሩ የብሔረሰቦች ስብስብ ከመሆን ይታደጋል፡፡  

በአንፃሩ በሌሎች የአገራችን ክፍሎች የሚገኙ ትውልደ አማራዎች በአካባቢው የሚኖሩት ኢትዮጵያዊነትን መድኅን አድርገው ነው፡፡ መጤነባር መባባል ያስከተለውን መገለል ተቋቁመው ከአካባቢው ጎሌ (Dominant) የኅብረተሰብ ክፍል ጋር ተሰናስለው ለመኖር ጥረት የሚያደርጉ የአገሪቱ ዜጎች ናቸው፡፡ ከሌላው የኅብረተሰብ ክፍል ጋር ተቀላቅለው የሚገኙበትም ምክንያት ታሪካዊ ዳራ አለው፡፡  በአማራ ክልል ውስጥ እንደሚኖረው አማራ ሁሉ፣ በሌሎች ክልሎች የሚኖሩ ትውልደአማራዎች ‹‹በብሔር ፖለቲካ›› ዓውድ ውስጥ ገብተው መማሰን የማይፈልጉት ለኢትዮጵያዊነት ስለሚሳሱ እንጂ፣ አማራነት ከሌላው ብሔረሰብ ዝቅ ያለ ክብርና ሞገስ ስላለው አይደለም፡፡ አያት ቅድመ አያቶቻቸው ኢትዮጵያን ከሌሎች ብሔረሰቦች ጋር መሥርተው ለአሁኑ ትውልድ ያስረከቡት  በዘር ልዩነት ዓውድ እያሰቡ ስላልነበር ልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸውም የእነርሱን ፈለግ በመከተል፣ አገሪቱን ለመጪው ትውልድ ከዘር ልዩነት ዕሳቤ ውጭ ለማስረከብ ፅኑ ፍላጎት ስላላቸው ነው፡፡ አማራ የአያት ቅድመ አያቶቹን ማኅበረሰባዊ ባህርይ አይለቅም፡፡ አያት ቅድመ አያቶቹ ሌላውን የማግለልና የማስወገድ ዝንባሌ ቢኖራቸው ኖሮ በእነሱ ጎሌነት ወቅት በሕይወት የሚተርፍ ብሔረሰብና አሁን ቋንቋውንና ባህሉን ጠብቆ የብሔረሰብ ማንነቱ ተከብሮ የሚኖር የሌላ ብሔረሰብ ትውልድ አይገኝም ነበር፡፡  በሌሎች ክልሎች በሚኖረው የአማራ ብሔረሰብ አባላት ላይ በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን እየደረሰ ያለው ዘርን መሠረት ያደረገ ጥቃት የአሁኑ የአማራ ሕዝብ ትውልድ አያት ቅድመ አያቶች በጥንት ጊዜ ያሳዩትን መልካም ሥነ ምግባር ይፃረራል፡፡

አሁን ያለው ተጨባጭ ሁኔታ በጥሞና ሲገመገም በአማራነት የሚደርሰው መፈጨት ዋና ዓላማው አማራነትን ፍለጋ (እነሱ እንዳሉት ከአማራ ጋር ሒሳብ ለማወራረድ) ስለሆነ  በሸዌነት፣ወሎየነት፣ጎጃሜነት፣ጎንደሬነት፣ ከክልሉ ውጪ በሚኖር፣ ክርስቲያን/ሙስሊም፣ ወዘተ አማራነት ‹‹በብሔር ፖለቲካው›› ክራንቻ ከመፈጨት ማምለጥ አይቻልም፡፡ አማራነትን በጠላትነት የፈረጀ  አረመኔ፣ አማራጭ ማንነትን ተመልክቶ በርኅራኄ አያልፍም፡፡ ከዚህ ጥግ ውጪ ማሰብ መታለል ይሆናል፡፡ በወለጋናቤኒሻንጉል ጉምዝ የሚፈጨው አማራ ወሎየ ወይም ጎጃሜ  ነው፡፡ ግን ወሎየነቱና ጎጃሜነቱ ከመፈጨት አላዳነውም፡፡ ‹‹የብሔር ፖለቲካው›› የኢትዮጵያዊነትን ዣንጥላ በመቦጫጨቁ የተነሳ  በወሎየነቱ ወይም በጎጃሜነቱ ምክንያት ከአካባቢውብረተሰብ ተገልሎ የመከራ ዶፍ ሲወርድበት፣ የሚጠለልበት ዛፍ  አላገኘም፡፡ በዚህ ተጨባጭ ሁኔታ ውስጥ የሚገኝ ሕዝብ በአንድነት ሆኖ የተባበረ ክንዱን በጎርዳሚው ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› ክራንቻ ላይ ከማሳረፍ በስተቀር የተሻለ ሌላ  አማራጭ የለውም፡፡  በግንባር ቀደም መደረግ ያለበት ክራንቻው ሊጎረድም የተነሳውን አማራነት አለማስጎርደም ነው፡፡ አማራ በዜግነቱ በአገሩ የመኖር መብት አለው፡፡ ክራንቻው አማራነትን ጎረደመ ማለት ኢትዮጵያም ተጎረደመች ማለት ነው፡፡ ይህንሳቤ የማነሳው የአማራ ማንነትን ከአማራ ክልል  ጋር በማዛመድ አይደለም፡፡  አማራነት ከአማራ ክልል  የገዘፈ መሆኑንና በክልሉ ውስጥ የሚኖረውን ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ተቀባይነት ባለው መንገድ በአማራነት ለመግለጽ ያለውን አስቸጋሪነት እገነዘባለሁ፡፡ 

ለሁላችንም የሚመች አማራጭ የአገር አስተዳደራዊ  አወቃቀር በመግባባት አበልፅገን ተግባራዊ በማድረግ የጋራ ዋስትናችን የሆነችውን እምየ ኢትዮጵያ በጋራ ለማስቀጠል፣ በአሁኑ ወቅት ከውስጥና ከውጭ ያሰፈሰፉ ጠላቿን በጋራ መመከት ቀዳሚ ኃላፊነታችን ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› የመጨረሻ ዕድገቱን ሲያጠናቅቅ መዳረሻው የት እንደሆነ ትሕነግ የደረሰበት የዕድገት ደረጃና ውጤቱ በቂ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ለማንኛውም አማራ የሆነ እንዲሁም አማራ የተባለ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሁሉ ክንዱን አስተባብሮ በቅድሚያ ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› ክራንቻን መስበርና ማፈራረስ አለበት፡፡ አሁን በአገራችን የሚታየው ሕዝባዊ እንቅስቃሴ የሚጠቁመው ፍንጭ ይህንኑ ነው፡፡ ለህልውና ትግሉ በድል መቋጨት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ያለ ብሔረሰብ ልዩነት ከጫፍ እስከ ጫፍ አንድ ልብ መካሪ፣ አንድ ቃል መስካሪ ሆኖ መንቀሳቀሱ የሚያስተላልፈው መልዕክት ከፖለቲከኞቹ መጋረጃ በስተጀርባ ያለውን የሕዝቡን ፅኑ ፍላጎት በግልጽ ያሳያል፡፡ ይህም ፍላጎት የአንድነትና የአብሮነት ፍላጎት ነው፡፡

‹‹የብሔር ፖለቲካ›› ክራንቻው መሰበር አለበት፡፡ ክራንቻው ይሰበር ካልን ደግሞ መሰበር ያለበት ሙሉ በሙሉ ነው፡፡ የላይኛው ቅድመ መንጋጋ ወይም የታችኛው መንጋጋ ወይም የግራው ክራንቻ ወይም የቀኙ ክራንቻ ብቻ መስበር  አይበቃም፡፡ ኢትዮጵያ እርስ በርስ እየተፋጩ የሚያደቋት በውስጥና በውጭ የበቀሉ ክራንቻዎች አሉባት፡፡ ግብፅና ሱዳን ከሌሎች የአገራችን ታሪካዊ ጠላቶቿ ጋር የተባበሩ የውጭ ክራንቻዎች ናቸው፡፡ የእነሱ ተላላኪ ባንዳዎች ደግሞ የውስጥ ክራንቻዎች ናቸው፡፡ አገራችን የእነዚህን በቅንጅት የሚሠሩ ክራንቻዎችን ተፅዕኖ  በዘላቂነት ለመቋቋም አንዱና ዋናው መፍትሔ፣ የውስጥ ችግሮቿን ክብደትና በምትገኝበት የጂኦ ፖለቲካ አካባቢ ያንዣበበውን ዓለም አቀፍ ግፊት በመገምገም በሁሉም ረገድ የተሟላ  ዝግጅት ያለው ወታደራዊ አቅም ስትፈጥር ነው፡፡  አገራችንን ሊያደቅ አሰፍስፎ የተነሳውን የውስጥና የውጭ ክራንቻ ለመስበር ሁሉም ዜጋ  ለአገሩ ዘብ መቆም አለበት፡፡ የውስጥም ሆነ የውጭ ክራንቻ ትኩረቱን ይበልጥ ያደረገው  በአማራነትና በኢትዮጵያ ላይ ስለሆነ፣ ‹‹አማራ በመሆን›› እና ‹‹አማራ በመባል›› የተፈረጀ ዜጋ ሁሉ ‹‹ኢትዮጵያ የእኛም አገር ናት›› ከሚሉ ሌሎች ዜጎች ጋር ለህልውና ትግሉና ከዚያም በኋላ ለሚመጣ ማንኛውም አገራዊ ግዳጅ ዝግጁ መሆን ይኖርበታል፡፡ በየደረጃው በሚዘጋጁ የዝግጁነትልጠናዎች ላይ በነቂስ በመሳተፍ ራስን የመከላከልና የአካባቢ ደኅንነት ጥበቃ ተግባር በንቃት ማከናወን፣ መታጠቅ፣ እንዲሁም የልዩ ኃይልና የመከላከያ አባል ለመሆን መመዝገብና ሠልጥኖ መሰማራት ወቅቱ ለዜጎች ያቀረበው የህልውና ዘመቻ ጥሪና መወጣት ያለብን የጋራ አገር የማስቀጠል ኃላፊነት ነው፡፡ ኢትዮጵያ በክብር ለዘለዓለም ትኑር!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...