Monday, March 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየነውጠኞች መንገድና የአፍሪካ ቀንድ ወቅታዊ ሥጋት!

የነውጠኞች መንገድና የአፍሪካ ቀንድ ወቅታዊ ሥጋት!

ቀን:

በንጉሥ ወዳጅነው 

ሕወሓት መራሹ የአገራችን ፅንፈኛ ኃይል አካሄዱ ሁሉ አገርን ብቻ ሳይሆን፣ ቀጣናውንና አፍሪካንም የሚበጅ እንዳልሆነ እየታየ ነው፡፡ ሌላው ሁሉ ቢቀር በፖለቲካ ሥልጣን ጥያቄ ሰበብ፣ በዚህ ዘመን የማይበረታታውን አውዳሚ ጦርነት ለኩሷል፡፡ በከፈተው ጦርነት በርካታ ዜጎች ሞተዋል ቆስለዋል፡፡ የአገር ሀብት፣ የግለሰቦች ንብረትና ማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ልማት ወድሟል፡፡ ሴቶችና ንፁኃን፣ ሕፃናትና አረጋዊያን በዚህም በዚያም ተሰቃይተዋል፡፡ ዕድሜያቸው ያልደረሰ ወጣቶችን ወደ ጦርነት ማግዷል፡፡

ይህ ነውጠኛ ኃይል አገራችን የምትገኝበትን ምሥራቅ አፍሪካም ቢሆን ሰላም የሚሰጥ እንዳልሆነ እየታየ ነው፡፡ በአንድ በኩል ከኤርትራ መንግሥት ጋር የፈጠረው ጠላትነት፣ በሌላ በኩል ከሱዳን መንግሥት (ከጀርባ ግብፅም አለችበት) ጋር የጀመረው ከኢትዮጵያ መንግሥት ተቃራኒ የሆነ ሽርክና የቀውስ ማባባሻ ምድጃዎች ናቸው፡፡ ከጂኦ ፖለቲካዊ ርቀት አኳያ እንፋሎቱ ለኬንያና ለሶማሊያ የራቀ ቢመስልም፣ ደቡብ ሱዳንና ጂቡቲም ቢሆኑ የጁንታው አካሄድ አደገኛ እንደሆነ የሚስቱት አይደለም (በተቃራኒው ሕወሓት ምሥራቅ አፍሪካ የዓብይ መንግሥትን አይቀበልም ብሎ የሚያምን ዋሾ መሆኑን በቅርቡ ይህ በሆነው ሰነዱ ተጋልጧል)፡፡

በመሠረቱ ጥንታዊው የአፍሪካ ቀንድ ብዙ ውጣ ውረድ፣ ውጥረትና ሥቃይ በታሪክ ያልተለየውና አሁንም የማያጣው አካባቢ ሆኖ ዘመናትን የዘለቀ ነው፡፡ ቅኝ ገዥዎችም ለምዝበራ እንዲመቻቸው እየነጣጠሉ ሲያባሉት የኖረና ዛሬም ጠባሳው ያልተወገደለት የምድር አካል ነው፡፡ የአፍሪካ ቀንድ በዋናነት ስድስት ገደማ አገሮችን የያዘ በቀይ ባህር፣ በኤደን ባህረ ሰላጤ፣ በህንድ ውቅያኖስ ዳርቻ የተዘረጋ ድንበር ያለው በመሆኑ ተፈጥሯዊ ወሳኝነቱን ለመቀራመት የማይቋምጥም የለም፡፡

ከገልፍና ከዚያም ባሻገር ከሚገኙ ሕዝቦች ጋር ለሺሕ ዓመታት የዘለቀ ጠንካራ የንግድ ትስስር መሥርቶ የኖረ ቅይጥ ሕዝብ መገኛ መሆኑም ይታወቃል፡፡ ሲራራ ነጋዴዎች ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ በተዘረጋው የንግድ መስመር እየተመላለሱ ሲነግዱ የኖሩበት አካባቢ በመሆኑም፣ በውስጡም ሆነ ከውጭ ዘራፊዎችና ነውጠኞች ያሰፈሰፉበት ቀጣና መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ለዚህ ቀጣና መረጋጋትና ሰላም አገራችን የስበት ማዕከል የመሆኗን ያህል፣ ከዚህች አገር የሚነሳ ችግር ደግሞ ብዙዎቹን እንደሚነካካም ጥርጥር የለውም፡፡

ቀጣናው ሁለቱንም ታላላቅ እምነቶች የክርስትናና የእስልምና ሃይማኖቶች በማለዳ የተቀበሉ ሕዝቦች መገኛ፣ ከስድስት ሺሕ ኪሎ ሜትር በላይ በመጓዝ ግብፅ የሚደርሰው የናይል ወንዝ የሚነሳበት፣ በታሪክና ቅርስ ካለው ዕምቅ አቅም ባሻገር ጂኦ ፖለቲካዊ መገኛውም ሆነ ያልተነካው የተፈጥሮ ሀብቱ የባዕዳን መራኮቻ መሆኑ ብቻ አይደለም ሥጋቱ፡፡ ከዚህ ባልተናነሰ ሕዝብ የማይፈልጋቸውና ብዙኃኑ ያልመረጣቸው የፖለቲካ ሲራራ ነጋዴዎችም ሥልጣን ይዘው ለመበዝበዝ ጦር የሚሰብቁበት ነው፡፡

እንደ አልሻባብ፣ የደቡብ ሱዳን አማፂያን፣ ሕወሓትና ኦነግ ሸኔ ዓይነት ኃይሎች ተነስተው፣ በፖለቲካ ጥያቄ ሰበብ አካባቢውን የሚያተራምሱበትና ለውጭ ኃይሎች ቅጥረኞች ሆነው በነውጥ ንፁኃንን የሚፈጁበት ሁኔታ እየተፈጠረ ይገኛል፡፡ ለዚህም ነው ዛሬም ድረስ ቀጣናው ድርቅ፣ ድህነት፣ የእርስ በርስ ጦርነት፣ ስደትና የዜጎች መንገላታት ያልተለየው ሆኖ የቀጠለው፡፡

የሕወሓትና አጋሮች አካሄድም የዚሁ የኪሳራ መንገድ አካል ለመሆኑ ከትግራይ ሕዝብ ባሻገር ዛሬ በሰሜን ወሎና በአፋር ሕዝብ ላይ የተፈጠረው ከፍተኛ የድርቅ ሥጋት፣ በሰሜን ጎንደር፣ በወለጋና በቤንሻኒጉል ጉምዝ ተደጋግመው የታዩት ዘር ተኮር የንፁኃን ዜጎች ጥቃቶች ጉልህ ማሳያ ናቸው፡፡ ይህን ድርጊት ተባብሮ አለማውገዝና አለመኮነን ነው አደጋውን የሚያከፋው፡፡

ለዘመናት የሚያግባባና ጠንካራ የማኅበረ ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር መፍጠር ተስኖት የቆየው፣ እንዲሁም የመነጣጠልና የመዘነጣጠል መጥፎ የታሪክ ጓዝ ተሸክሞ እዚህ የደረሰው የአፍሪካ ቀንድ አሁን ሕወሓትና ሸኔን የመሰሉ አዋኪዎች እንደ ተጋረጡበት የሚያሳየውም ይኼው ድርጊታቸው ነው፡፡ እነዚህ ጦርነትን የመረጡ የውስጥ ኃይሎች ለኢትዮጵያ የብልፅግና ጉዞ ዋነኛ እንቅፋት መሆናቸው እንደ ተጠበቀ ሆኖ፣ ምዕራባዊያንና የአገራችን አንዳንድ ባላንጣዎች በእጅ አዙር ቀጣናውን ከማሾር ፍላጎታቸው በመነጨና ታዛዥ አሻንጉሊት መንግሥት ለመጣድ በማሥላት ተባባሪ ሲሆኗቸው ይታያል፡፡

በእርግጥ በአብዛኛው አክራሪ ካፒታሊስቶች በኢትዮጵያም ሆነ በቀጣናው ራሱን የቻለና በብዙኃኑ ተቀባይነት ያለውና ጠንካራ መንግሥት እንዲኖር አይፈልጉም፡፡ የቀጣናው አገሮች ትብብርና የጋራ ፖለቲካዊ መስተጋብር መጠናከርንም የሚያዩት በጥርጣሬ ነው፡፡ በተለይ በእነ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተጀመረው የመደመር ዕሳቤና የኢኮኖሚ ውህደት መንፈስ ከምኞታቸው ተቃራኒ የሆነ አመለካከት አድርገው ነው የሚያስቡት ማለት ይቻላል፡፡

ይህንንም በየአገሩ እየገቡ በፖሊሲ ሰበብ መንግሥታትን ለመጠምዘዝም ሆነ የየአገሮቹን ሀብት ለመመዝበር የሚያውካቸው ስለሆነ ብቻ አይደለም የሚጠሉት፡፡ ይልቁንም ሕዝብ የተቀበለውና ጠንካራ መንግሥት በተለይ በኢትዮጵያ ከተመሠረተና ተጠናክሮ ከወጣ ቀስ በቀስ እንደ ቻይና፣ ቱርክ፣ ሩሲያ፣ ኢራን፣ ሰሜን ኮሪያና… መሰል አገሮች አንሰማህም የሚሉና የምሥራቅ ሽርክና የሚፈጥሩባቸው እንዳይሆኑ ይሰጋሉ፡፡ ለዚህም ነው ዛሬ መሬት ላይ ባለው እውነት የኃይል አማራጭና የጥፋት መንገድን የተከተለው የአገራችን አማፂ ኃይል ሃይ ባይ ያጣው፡፡ የዕርዳታ ድርጅቶችን ንብረት ሳይቀር እየዘረፈ ጭምር እየዘረፈ ያለው፡፡ ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡

ለነገሩ ጥንትም ቢሆን ምሥራቅ አፍሪካ ለባዕዳን ቀኝ ገዥዎች ቅርምት ሲጋለጥ፣ በየአካባቢው ምንደኞች እየተቀፈቀፉ ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ የአካባቢው አገሮች  ተመሳሳይ ወይም የጋራ የሆነ የቅኝ ግዛት ታሪክ እንኳን እንዳይኖራቸው የተደረጉት ከፋፍሎ ለመብላት በተዶለተባቸው ሴራ ነበር፡፡ ያ ታሪካዊ ክስተት ደግሞ በአንድ አገረ መንግሥት ጉዞ በጀመሩ ሕዝቦች መካከልም ከአክራሪና ከነጣጣይ ፍልስፍና ጋር ያበሩ (ሕወሓትና ሸኔ)ን የመሰሉ አፍራሽ ኃይሎች ወልዷል፡፡

ከቅኝ ገዥዎች ብዝበዛ ማክተም በኋላ፣ ቢያንስ ባለፉት 50 ዓመታት በቀጣናው በአዙሪት መልክ የሚመላለሰው ሁኔታ አባባሉን ያረጋግጣል፡፡ ከአፍሪካ ቀንድ አገሮች ውስጥ ሦስቱ (ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ) ዘመናትን ተሻግሮ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም መፍትሔ ሊገኝለት ያልቻለ ከባድ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ተዘፍቀው ነበር የቆዩት፡፡ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን፣ ኢትዮጵያና ኤርትራ፣ ሶማሊያና ኢትዮጵያ እንደ አገር ብዙዎች ያለቁበትንና ግዙፍ ሀብት የወደመባቸው ጦርነቶችን አስተናግደዋል፡፡ አሁን ደግሞ በአገራችን በጥቂት ፅንፈኞች ገፋፊነት ቀጣናውንም እስከ መረበሽ የሚደርስ ጦርነት ተከስቷል፡፡

በነገራችን ላይ በፖለቲካ አለመግባባትና በዴሞክራሲ ዕጦት ግጭቶች ይነሳሉ፡፡ በታሪክና በብልፅግናቸው የታወቁት እነ ሊቢያ፣ ሶሪያና የመን ሲፈራርሱም ዓይተናል፡፡ በዚህ ቀጣና የነገሠው ሰይጣናዊ ዕሳቤ ግን ፖለቲከኞች  “የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት” (በጉልበትም ቢሆን) የሚሉት ስታሊናዊ ፍልስፍናና የቁም ቅዠት ላይ የተጣበቀ ነው፡፡

ለአብነት ያህል በሕግ ሳይሆን በጦርነት የተዋለዱት ኤርትራና ደቡብ ሱዳን የዓለም የቅርቦቹ አገሮች ቢሆኑም፣ እምብዛም የተሳካ የአገር መንግሥት ግንባታ ላይ አልደረሱም፡፡ እንዲያውም ከቀውስና ከመከራ ያልወጡ አገሮችን በማዋለዱ የሕመም ምልክት ተደርጎ የሚወሰድ ለጋ ምዕራፍ ላይ ነው የሚገኙት፡፡ አሳዛኙ ነገር ደግሞ ከስድስት ሚሊዮን ያነሰ ሕዝብ የሚኖርበት የትግራይ ክልልን ቢያንስ ላለፉት 30 ዓመታት ያስተዳደረው ሕወሓት ለመገንጠል መተናነቁና አገር ማስጨነቁ  ነው፡፡

ይህን የማይበጅና እኩይ ተግባር የኢትዮጵያ ሕዝብ ይቅርና ራሳቸው የትግራይ ተወላጆች ሙሉ በሙሉ ሳይደግፉት፣ ወያኔ ብቻውን ከትጥቅ ትግል ዘመኑ ጀምሮ ከሕዝቡ ጋር የፈጠረውን መስተጋብር በአሉታዊ መንገድ ለጥፋት በማዋል የ“ዲፋክቶ”ና፣ የተነጣይነት አገርነት ትርክት ውስጥ መክተቱ በትግል መሸነፍ አለበት፡፡ ከዘለዓለማዊ ግጭትና ጦርነት ቀጣናውን ስለማያስወጣም ተገዶ ወደ ጠረጴዛ ሊመጣ የግድ ነው፡፡

ይህ ዝንባሌ ለምሥራቅ አፍሪካም ጠንቅ ነው፡፡ በተለይ የአፍሪካ ቀንድ ዥንጉርጉር ገጽታና ዘወትር በቋፍ ሆኖ የሚያስጨንቅ የደኅንነት ሁኔታ ውስጥ እንደ መሆኑ፣ ሌሎች ጥገኞችንም አብዝቶ የሚቀፈቅፍ ድርጊት ነው፡፡ የአንዱ ተፅዕኖው ለሌላው እንደ ሚተርፍ አብነቱ በኢትዮጵያ የሕወሓት/ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት በሕዝብ ቁጣ ሲመታ፣ በሱዳንም የአልበሽርን የ30 ዓመታት አገዛዝ ለማሽቀንጠር ገፊ ምክንያት እንደ ነበር ስናስታውስ ነው፡፡ በኤርትራም ተመሳሳይ ንቅናቄ መታየቱ አይካድም፡፡ ሒደቱ ያበቃለት ባይሆንም፣ በየአገሩ የሚስተዋለው ፀረ ዴሞክራሲን የመፀየፍ ዕርምጃ ተጠናክሮ መቀጠሉ የሚቀር አይመስልም፡፡

በእርግጥ አንዳንድ ተንታኞች እንደሚሉት ይህ ትስስራዊ ተፅዕኖ የሚፈጥረው፣ የአፍሪካ ቀንድ አገሮችንና በየአገሪቱ የሚኖሩ ሕዝቦች ጥንታዊና በደም፣ በቋንቋ፣ በባህልና በታሪክም የተሳሰሩ በመሆናቸው ነው፡፡ የመልክዓ ምድር፣ የሥነ ሕዝብ፣ የፖለቲካና የባህል ልዩነታቸው እንደ ተጠበቀ ሆኖ ከቅኝ ገዥዎች አንስቶ፣ የውጭ ኃይሎች ተዕፅኖም ለመከፋፈልና ለግጭት ሲያጋልጣቸው መቆየቱም  አይዘነጋም፡፡

በተለይ በተለይ ዛሬም ድረስ ከቀጣናው ውጪ ያሉ ኃይሎች ‹‹የውክልና ፖለቲካ›› ተዋናዮችን በቀላሉ ለማግኘት ተኝተው እንደማያድሩ ማሰላሰል ተገቢ ነው፡፡ አሁን ከእነ ሕወሓት ጀርባ ግብፅና ሱዳን አሉ ቢባል እንኳን፣ አብዛኛው የኒዮሊብራል ኃይል ወኪል፣ ሚዲያ ወይም ፖለቲከኛ እንዴት ሊሠለፉ ቻሉ መባል አለበት፡፡

አብዛኛው ዓለምም ሆነ ራሳቸው አማፅያንና ፅንፈኞችም እውነቱን ይካዱት እንጂ፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በሚጠቀሰው መረጃ 350 ሚሊዮን ከሚደርሰው የቀጣናው ሕዝብ 68 በመቶ የሚሆኑት ወጣቶች መሆናቸው ይታወቃል፡፡ እነዚህ ወገኖችም በየወሩ በአሥር ሺዎች ወደ አውሮፓና መካከለኛው ምሥራቅ ለመሰደድ ሲዳክሩ ነው የቆዩት፡፡ በሜዲትራንያን ባህርና በየበረሃው በየጊዜው የሞት ፅዋን እየተጎነጩ  እስከ ዘለዓለሙ የሚያሸልቡ ታዳጊዎች መገኛም ይህው መከረኛ ቀጣና ሆኖ እንደ ቆየ አይዘነጋም፡፡ አሁን ደግሞ አብዛኛውን ኢትዮጵያዊ ወጣት ወያኔ ወደ ጦርነት ሲማግደው ለትውልዱ እንድናዝን ያስገድዳል፡፡

በመሠረቱ የዚህ ቀጣና ዋነኛ ችግር የፖለቲከኞች ስግብግብነት የፈጠረው ነው፡፡ የየአገሮቹ የእርስ በርስ ግጭትና በየራሳቸው ውስጥም የተንሰራፋው ፀረ ዴሞክራሲያዊነት፣ ሌብነትና ምዝበራ፣ ብሎም ዘረኝነትና ድህነት ሁሉ ወጣቱን ከችግር እንዳይወጣ እያደረገው ነው፡፡ ለስደቱም ሆነ ለኋላቀርነቱ ትልቁን በር እየከፈተ ያለው ችግርም የእልህና የዕብሪት አዙሪት ተብትቦ የያዛቸው ፅንፈኞችና ነውጠኞች እየበረከቱ፣ ሕዝቡም እየታገላቸው ስላልሆነ ነው፡፡ የሕወሓትንም ሆነ የሸኔን ድርጊት ያስታውሷል፡፡ እውነት ለመናገር ኢትዮጵያ ውስጥ አዲስ ዓይነት የለውጥ ጅምር ሲታይ ለጤናውም ቢሆን አዲስ ተስፋ፣ በተለይ በኢኮኖሚ የመተሳሰር ዕድል እንደሚፈጠር ታምኖ ነበር፡፡ አገራችንንም ሆነ ቀጣናውን ሲያምሱት የነበሩት ዘረኝነትና የእርስ በርስ ግጭቶች፣ ብሎም የአገረ መንግሥት መዳከም እንደሚቀረፉም ብዙዎች ገምተው ነበር፡፡ አሁን በኢትዮጵያ የተጫረው የውስጥ እሳት ግን ቢያንስ ኤርትራንና ኢትዮጵያን በጦርነት ስሜት ውስጥ አቆይቷል፡፡ ሱዳንም የማትወጣበት የግጭት አዙሪት ውስጥ ገብታለች፣ ከኢትዮጵያ ጋር፡፡

ይህ ሁኔታ ደግሞ በተናጠልም ሆነ በጋራ የቀጣናውን ኢኮኖሚ አዳክሞታል፡፡ የጦርነት ኢኮኖሚ እሳት የሚባለው ሀብት ቀላል ባለመሆኑም ድቀት መፈጠሩ አይቀሬ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም አስከፊ የምሥራቅ አፍሪካ ገጽታ የነበረውን ችግር ለመቅረፍም ሆነ  ለማስታገስ ሙከራ ስታደርግ የነበረችውን ኢትዮጵያውያን ለባሰ ችግር እየዳረጋት ስለሆነ ችግሩን ለመቅረፍ መረባረብ ግድ ይላል፡፡

ሌላው ቀርቶ ስምንት አባላት ባሉት “ኢጋድ“  የተሰኘው የቀጣናው መንግሥታት የጋራ የምክክር መድረክም የታሰበውን ያህል ውጤታማ አደረጃጀት ለመሆን አልቻለም፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ ችግርም ሆነ የነውጠኞች አካሄድ በአፋጣኝ ይገታ ዘንድ፣ በተለይም በሰላማዊ መንገድ መፍትሔ ያገኝ ዘንድ፣ አኅጉራዊም ሆነ ዓለም አቀፍ ተቋማት መረባረብ ነው የሚጠበቅባቸው፡፡ አሁን እንደሚታየው ኃያላን አገሮች አመፀኞችን አሸናፊ ለማድረግ መፍጨርጨራቸው የሚበጅ አይሆንም፣ በፍፁም፡፡

ኢትዮጵያ ምንም እንኳን በቀድሞ ዘመናት እንዳለመታደል ሆነ ከእርስ በርስ መናቆር ወጥታ ለትውልድ ተሻጋሪ የሚሆን ሐሳብ ያላቸው ዘመናዊ መሪዎችን አግኝታ ነበር ባይባልም በቅኝ ያልተገዛች ለረጅም ዘመናት የዘለቀ ግዛት አፅንታ የኖረች፣ ለጠንካራ እምነትና ሥነ ምግባር ምሰሶ ሆና የቆየች ነች፡፡ ይህ ነባራዊ ሀቅም ማዕከላዊና ወሳኝ የቀጣናው አገር አድርጓት ቆይቷል፡፡ ይህንን ፀጋ ማናወጥም ሆነ እንዲናጋ ማድረግ ከወንጀል በላይ ወንጀል ነው፡፡

በእርግጥ ነውጠኞች ይህ መልካም የአገር ገጽታ እንዲቀጥል አይፈልጉም፡፡ የአገራችን ታሪካዊና ቀጣናዊ መሪነት ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚችለው ግን ተወደደም፣ ተጠላም ጀግኖች ልጆቿ በሚከፍሉት ዋጋ ነው፡፡ የአገር ሰላም፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲና ፈጣን ልማት ሲረጋገጥ በመሆኑ ኢትዮጵያዊያን ከዳር እስከ ዳር ለዚህ መቆም አለባቸው፡፡  ከሁሉ በላይ አገራዊ አንድነቱን የጠበቀ አገረ መንግሥት ለመገንባት የትኛውንም ተፅዕኖ ለመቋቋም መዘጋጀት የግድ ይላል፡፡

ከሁሉ በላይ አገራችን የራሷንም ሆነ የአካባቢውን ሰላምና ማረጋጋት ዕውን ማድረግ የምትችለው፣ ጠንካራና የማይናወጥ ሠራዊት ስትገነባ ነው፡፡ እንኳን ዛሬ በፊትም ቢሆን ኢትዮጵያ ከራሷ ግዛት አልፎ ለጎረቤቶቿ የሰላም ዋስትና መሆን የቻለ የመከላከያ ሠራዊት እንደ ነበራት የታወቀ ነው፡፡ ይህን ሀቅ አጠናክሮ ለማውጣት ደግሞ አሁን የምንገኝበት ወሳኝና ታሪካዊ ወቅት፣ ወጣቱን ከዳር እስከ ዳር ለአገሩ ሉዓላዊነት እንዲነሳ ማድረጉ ጠቃሚ ክስተት ነው፡፡

ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የኢትዮጵያ መንግሥት በተሃድሶ መንፈስ ወደ ሥልጣን ሲመጣ የበለጠ ትኩረት የሰጠው፣ ለጎረቤት አገሮች ወዳጅነትና አጋርነት መሆኑም ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል ነው ያለበት፡፡ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲን በማሻሻል ዜጋ ተኮርና በሰጥቶ መቀበል ላይ የተመሠረተ እንዲሆን የተደረገው ጥረትም፣ በበለጠ መተማመንና ሰጥቶ መቀብ መርህ ማደግ አለበት፡፡ ይህ ከሆነ በየአካባቢው የሚገኙ ነውጠኞችን ለመተጋገል ተባባሪ የሚሆንና ሥጋቱን የሚረዳ ጎረቤት አይታጣም፡፡

በመሠረቱ የቀጣናው ጉዳይ በአንድ አገር ብቻ ሳይሆን፣ በሁሉም አባል አገሮች በጥንቃቄ ሊታይ የሚገባው ነው፡፡ ምክንያቱም በአንድ በኩል የአፍሪካ ቀንድ ሕዝቦችና መንግሥታት፣ ለመገመት አስቸጋሪና ትርጉም የለሽ የሆነ ስትራቴጂካዊ አሠላለፍ ከሚያስከትለው ቀውስ በጋራ መጠበቅ ይገባል፡፡ ከፊታቸው የተዘረጋውን አደገኛ ጎዳና በጥንቃቄ መጓዝም ይኖርባቸዋል፡፡ በሌላ በኩል በአፍሪካ ቀንድ የውክልና ጦርነት ማካሄድ ቀላል ነገር መስሎ የሚታያቸው ከቀጣናው ውጪ የመጡ ኃይሎች፣ ራሳቸውን ከስህተት ለመጠበቅ የአካባቢውን ታሪክና ፖለቲካ በውል እንዲረዱ የማድረግ ጠንካራ ትብብር መጀመር አለበት፡፡ ይኼ ደግሞ እነ ሕወሓትን ማክሰሙ አይቀርም፡፡

ያለ ጥርጥር የአፍሪካ ቀንድ መንግሥታት ከእርስ በርስ ጥርጣሬ ወጥተው የሕዝባቸውን ልብ የሚገዛ ብሔራዊ ፕሮጀክት መቅረፅ የሚችሉትም ይኼን ሲያደርጉ ነው፡፡ ለአብነት ያህል እንደ ዋና ዋና መንገዶች፣ የጋራ ወደብ አጠቃቀም፣ የኃይል አማራጭና መሰል ልማቶች፣ እንዲሁም የፀረ ኮንትሮባንድ፣ ሕገወጥ የመሣሪያ ዝውውርና የዕፅ ዝውውር ዓይነት ውንብድናዎችን ተጋግዘው ለመመከት የሕግ የበላይነትና የአገሮች ደኅንነት መረጋገጡ አስፈላጊ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በሕገወጥ መንገድ ሥልጣን ለመያዝ ጦርነትና ጉልበትን የሚመርጡ ኃይሎችን በአንድ ቋንቋ ማውገዝም ይጠበቅባቸዋል፡፡

በሌላ በኩል ደሃም ብንሆን በአፍሪካ ቀንድ የራሳቸውን ፍላጎት ለመጫን የሚንቀሳቀሱ፣ ከቀንዱም ሆነ ከአፍሪካ ውጪ የሚመጡ ተዋናዮች እጃቸውን በቀላሉ ለማስገባት ቀዳዳ እንዳያገኙ መትጋት ያስፈልጋል፡፡ የእርስ በርስ ችግሮች ሲፈጠሩም በመነጋገር የመፍታት ባህል መለመድ አለበት፡፡ የራሱ የአፍሪካ ቀንድ እጥረቶችና የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ተባብረው፣ አካባቢውን የደኅንነት ሥጋት የማይለየው ቀጣና እንዳያደርጉት ኢጋድና የተናጠል መንግሥታት ቀን ከሌት ሊተጉ የግድ ነው፡፡

በአጠቃላይ የአፍሪካ ቀንድ አገሮች፣ ከቆዩበት የመርገምት አዙሪት ወጥተው፣ በፀጋ አዙሪት ለመሽከርከር ከፊታቸው የተጋረጡ እንቅፋቶችን በተናጠልም በጋራም ታግለው ማስወገድ ይኖርባቸዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ በየአገሪቱ እያቆጠቆጠ የመጣውን አጉራ ዘለልነት በሕግና በሥርዓት መዳኘት ብቻ ሳይሆን፣ ከአገር አልፎ በቀጣናው ትርምስ ለመጋበዝ ጭምር ወደኋላ የማይሉ ሕወሓትን የመሰሉ ኃይሎችንም ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ማድረግ ለነገ የማይባል የጋራ ሥራ መሆን አለበት፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...