Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናሦስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ከሶማሌ ክልል ምርጫ ራሳቸውን አገለሉ

ሦስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ከሶማሌ ክልል ምርጫ ራሳቸውን አገለሉ

ቀን:

‹‹ፓርቲዎቹ ራሳቸውን ከምርጫው ማግለላቸው ምንም ተፅዕኖ አያመጣም››

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ድምፅ ያልሰጡ ክልሎች መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም. እንዲመርጡ በተወሰነው መሠረት፣ በሶማሌ ክልል በሚደረጉ የሕዝብ ተወካዮችና የክልል ምክር ቤቶች ምርጫዎች የሚፎካከሩ ሦስት የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ራሳቸውን አገለሉ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ከምርጫው ራሳቸውን ያገለሉት የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ)፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) እና የነፃነትና ዕኩልነት ፓርቲ (ነዕፓ) ሲሆኑ፣ እነዚህ ፓርቲዎች ከምርጫው መውጣታቸው ብልፅግና ፓርቲ ብቻውን በክልሉ በሚደረገው ምርጫ እንዲሳተፍ ያደርገዋል፡፡

ኦብነግ ከምርጫው ዓርብ መስከረም 7 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ለምርጫ ቦርድ ከመራጮች ምዝገባ ጋር የተገናኙ ችግሮችን አስታውቆ እንደነበረና መፍትሔ ሊያገኝ ስላልቻለ ከስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ራሱን ማግለሉን አስታውቋል፡፡ ፓርቲው የምርጫ ካርድ የተሠራጨው ለሕዝቡ ሳይሆን ለገዥው ፓርቲ ካድሬዎችና ደጋፊዎች ነው ብሏል፡፡

በአንድ ክልል ጦርነት እየተካሄደ በሌላው ሰላም ሊኖር ስለማይችል ሁሉም የግጭቱ ወገኖች ጦርነቱን ማቆም አለባቸው በማለት በትግራይ የሚካሄደውን ጦርነት አጣቅሶ ያስታወቀው ኦብነግ፣ ከመራጮች ምዝገባ ጋር የተያያዙ ችግሮችን የፖለቲካ ፓርቲዎች ለቦርዱ በተደጋጋሚ ያስታወቁ ቢሆንም ቦርዱ ምላሽ ሊሰጣቸው እንዳልቻለ ወቅሷል፡፡ በዚህም በሶማሌ ክልል ለነፃና ለገለልተኛ ምርጫ የሚያስፈልገውን ቅድመ ሁኔታ እንዲሟላ አላደረገም ብሏል፡፡ ስለዚህም ምርጫው ለሦስት ወራት እንዲራዘም ሲደረግ በሕዝቡ ዘንድ ተፈጥሮ የነበረው ተስፋ፣ ቦርዱ የመራጮችን ምዝገባ ከእነ ችግሮቹ በማስቀጠሉ እንዲንኮታኮት አድርጓል ይላል የኦብነግ መግለጫ፡፡

ኢዜማና ነዕፓ በጋራ መስከረም 9 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጡት መግለጫ፣ ‹‹በሶማሌ ክልል ውስጥ በተካሄደው የመራጮች ምዝገባ ሒደት ችግር ያዘለ ከመሆኑም በላይ፣ ሕግና የምርጫ ሥርዓት የጣሰ ከመሆኑ በላይ የምርጫውን ምንነት ትርጉም የሚያሳጣና ለአንድ ወገን ያዳላ በመሆኑ፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከዚህ በፊት ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያቀረብናቸው ቅሬታዎች ሊፈቱ ባለመቻላቸውና የምርጫውን ሒደት ተዓማኒነት የሚያሳጣ ስለሆነ ከምርጫው ራሳችንን አግልለናል፤›› ብለዋል፡፡

ፓርቲዎቹ ራሳቸውን ከምርጫው ለማግለል፣ ‹‹ከዚህ በፊት ተሰርቆ የነበረው የምርጫ ቁሳቁስ በአዲስ እንዲተካ የጠየቅን ቢሆንም፣ አሁን ግን ቀድሞ ተዘርፎ በነበረው ካርድ ወደ ምርጫ በመገባቱ ምርጫው ተዓማኒነት አይኖረውም፡፡ በተጨማሪም የምርጫ ጣቢያ ያልተቋቋመባቸው አካባቢዎች ምርጫ ጣቢያ እንዲቋቋም ጠይቀን የነበረ ቢሆንም፣ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጠው ምላሽ አጥጋቢ አይደለም፤›› የሚለውን እንደ አንድ ምክንያት አቅርበዋል፡፡

ፓርቲዎቹ አክለውም ባለው የመረጃ ክፍተት ሳቢያ ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ለእያንዳንዱ የምርጫ ክልል ምን ያህል የመራጮች ካርድ እንደመጣ ግልጽ አለመሆኑ ችግር ፈጥሯል ያሉ ሲሆን፣ ቁሳቁሱን እያጓጓዘ ያለው የወረዳና የቀበሌ መስተዳድር መዋቅር በመሆኑ፣ ለአንድ ዕጩ በየምርጫ ክልሉ የራሱን ታዛቢ እንዲኖር ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከ15 ቀናት በፊት ማሳወቅ አለበት የሚለውን መርህ በመጣስ የምርጫውን ነፃና ፍትሐዊነት ጥያቄ ውስጥ ያስገባ ነው ብለዋል፡፡

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሙዩኒኬሽን አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ ሰኞ መስከረም 10 ቀን 2014 ዓ.ም.  በሰጡት መግለጫ፣ የእነዚህ ፖለቲካ ፓርቲዎች በተለይም የኦብነግ ከምርጫው ራሳቸውን ማግለል በምርጫው ሒደት ላይ ምንም ተፅዕኖ እንደማይኖረው ያስታወቁ ሲሆን፣ በተለይ ኦብነግ ዕጩ ለማስመዝገብ ችግር አለብን ሲል በማዕከል ዕጩ ማስመዝገብ እንዲችል አድርገናል ብለዋል፡፡ ከመራጮች ምዝገባ ጋር በተያያዘም ችግር ታየ በተባለባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ምክንያት ሙሉ የምርጫ ክልሎች ተዘግተው ማጣራት እንዲከናወን ተወስኖ እንደነበረ፣ ለአጠቃላይ የማጣራት ሥራው እስከ አምስት ሚሊዮን ብር ድረስ ወጪ እንደተደረገ በመጠቆም፣ ለሶማሌ ክልል ከተሰጠው ትኩረት አንፃር ፓርቲዎቹ ራሳቸውን ማግለላቸው ያሳዝናል ብለዋል፡፡

የምርጫዎቹን ውጤት እስከ መስከረም 30 ቀን 2014 ዓ.ም. ለማሳወቅ ዝግጅት ተደርጎ እየተሠራ እንደሚገኝ የጠቆሙት ሶሊያና፣ ምርጫ በተከናወነ በአሥር ቀናት ውስጥ ውጤት ይፋ ይደረጋል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...