- የ5ጂ አገልግሎት በቅርቡ ሊጀመር ይችላል ተብሏል
ከተጀመረ አራት ወራት ባስቆጠረው የቴሌ ብር የሞባይል ገንዘብ ዝውውር አገልግሎት፣ ለአንድ ቢሊዮን ብር የተጠጋ የገንዘብ ዝውውር መፈጸሙን ኢትዮ ቴሌኮም አስታወቀ፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም ይህንን ያስታወቀው ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የ4ጂ ኤልቲኢ አድቫንስድ አገልግሎት በምዕራብ ሪጅን በሚገኙት ከተሞች ማለትም በጊምቢ፣ በነቀምቴ፣ በደምቢዶሎ፣ በባኮና በሻምቡ ባስጀመረበት ሥነ ሥርዓት ላይ ነው፡፡
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩ፣ በፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽ ያልሆኑ ዜጎችን ታሳቢ በማድረግ ይፋ የተደረገው የቴሌ ብር የሞባይል ገንዘብ ዝውውር አራት ወራት አስቆጥሯል ብለዋል፡፡
ለቴሌ ብር አገልግሎት 9.5 ሚሊዮን ተገልጋዮች እንደተመዘገቡ የተገለጸ ሲሆን፣ በቴሌኮም ኢንዱስትሪውና በሌሎች አገሮች እንደታየው በአገልግሎቱ አንድ ሚሊዮን የሚደርሱ ደንበኞችን ለማፍራት አንድ ዓመት የሚደርስ ጊዜ ይወስዳል ተብሏል፡፡ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ኢትዮ ቴሌኮም ግን በሞባይል ገንዘብ ዝውውር አገልግሎቱ በአራት ወራት ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ የደንበኛ ቁጥር ለማግኘት መቻሉን ገልጸዋል፡፡
ቴሌ ብር ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የተንቀሳቀው የገንዘብ ዝውውር አንድ ቢሊዮን ብር መጠጋቱን ያስረዱት ወ/ሪት ፍሬሕይወት፣ ቁጥሩም በትክክል ሲገለጽ 938 ሚሊዮን ብር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ስምንት ባንኮች የቴሌ ብር አገልግሎት ለመስጠት ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር እንደተዋዋሉ ተገልጾ፣ ከሌሎች ቀሪ ባንኮች ጋርም አገልግሎቱን ለመጀመር ንግግር እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ኩባንያው 85 በመቶ በመልክዓ ምድራዊ ሽፋንና በመላው አገሪቱ 95 በመቶ ተደራሽነት ስላለው፣ ደንበኞች በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል ለሚያደርጉት የገንዘብ ዝውውር እንቅስቃሴ የቴሌ ብር መጀመር አመቺ ዕድል የፈጠረ እንደሆነ ወ/ሪት ፍሬሕይወት አስረድተዋል፡፡
ኩባንያው በመላው ኢትዮጵያ ለሚገኙ 665 ትምህርት ቤቶች ከ600,000 በላይ ደብተሮች፣ ለ50,000 ድጋፍ ለሚሹ ተማሪዎች የትምህርት መርጃ መሣሪያዎች ድጋፍ ማስጀመርያ መርሐ ግብር በነቀምት ከተማ እንዲሁ ይፋ አድርጓል።
በተያያዘም የ5ጂ ኔትወርክ አገልግሎትን እ.ኤ.አ. በ2022 ይጀምራል ብለን አቅደን ነበር ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፣ ምናልባት ከተጠቀሰው ጊዜ ቀደም ብሎ አገልግሎቱን ይፋ ለማድረግ እንደሚቻል የተደረገው ዝግጅት ያመላክታል ብለዋል፡፡ በቅርቡም ይህንን ዜና ደንበኞች የሚሰሙበት አጋጣሚ እንደሚኖር ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም ከፍተኛ የደንበኞች ቁጥር እያፈራበት ባለው የሞባይል ገንዘብ ዝውውር አገልግሎት አማካይነት፣ ዓለም አቀፍ የሐዋላ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለውን ቅድመ ዝግጅት ማድረጉንና ለዚህ የሚያስፈልገውን ፈቃድ ብሔራዊ ባንክ እንዲሰጠው መጠየቁን መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን፣ አገልግሎቱን ለመስጠት የሚያስችለውን ፈቃድ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንዳገኘ በሳምንቱ መጨረሻ ተዘግቧል፡፡
ግንቦት 3 ቀን 2013 ዓ.ም. በወዳጅነት አደባባይ ቴሌ ብር ይፋ በተደረገበት መድረክ ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ የሞባይል ገንዘብ ዝውውር አገልግሎትን ለማስጀመር ብዙ ዋጋ ተከፍሏል ብለው ፣ ይህም መንግሥት የውጭ ቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢዎችን በአገር ውስጥ እንዲሳተፉ ሲጋብዝ ከቴሌኮም አገልግሎት ሁለት ሦስተኛ የሆነ ገቢ ያስገኛል የሚባለውን የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ለአንድ ዓመት በብቸኝነት በኢትዮ ቴሌኮም ብቻ እንዲሰጥ መፍቀዱ አንዱ እንደሆነ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም አገልግሎቱ በሒደት ለሌሎች አዲስ ገቢ የቴሌኮም ኩባንያዎች የሚከፈትበት ሁኔታ እንዳለ አስታውቀው ነበር፡፡