Wednesday, July 24, 2024

የስድስተኛው አገራዊ ተረፈ-ምርጫና የፓርቲዎች ከምርጫው መውጣት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ከ400 በላይ የምርጫ ክልሎች ተከናውኖ፣ መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችል ድምፅ ያገኘው ፓርቲ ይፋ ከተደረገ እነሆ ሁለት ወራት ተቆጥረዋል፡፡ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በብዙኃኑ የምርጫ ክልሎች ተከናውኖ መንግሥት ሊመሠረት የቀናት ዕድሜ ሲቀረው ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. በፀጥታ ችግር፣ በፍርድ ቤት ውሳኔዎች እንዲሁም በምርጫው ሒደት በተለይም በመራጮች ምዝገባ ላይ በታዩ ምስቅልቅሎች ሳቢያ ድምፅ ባልተሰጠባቸው 47 የተወካዮች ምክር ቤት፣ እንዲሁም በ105 የክልል ምክር ቤት የምርጫ ክልሎች መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም. ይከናወናል፡፡

በሐረሪ ክልል፣ በደቡብ ክልል እንዲሁም በሶማሊ ክልል የሚከናወነው የስድስተኛው አገራዊ ተረፈ-ምርጫ፣ አስቀድሞ ታቅዶ የነበረው ጳጉሜን 1 ቀን 2013 ዓ.ም. ቢሆንም፣ በምርጫው ከሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ከተደረጉ ውይይቶች በተገኙ ግብዓቶች ወደ መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም. እንዲራዘም መደረጉን፣ በምርጫው ዝግጅት ላይ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሙዩኒኬሽን አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ መስከረም 10 ቀን 2014 ዓ.ም. በስካይላይት ሆቴል የምርጫውን ዝግጅት አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ምርጫ ጋር ጎን ለጎን የሚካሔድ የደቡብ ምዕራብ ሕዝቦች ክልል ሕዝበ ውሳኔ በአምስት ዞኖችና በአንድ ልዩ ወረዳ የሚከናወን ሲሆን፣ የዚህም ዝግጅት አንድ ላይ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡

በአጠቃላይ ለሦስቱም ዓይነት ምርጫዎች (ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለክልል ምክር ቤቶች፣ እንዲሁም ለሕዝበ ውሳኔው) 7,054 የምርጫ ጣቢያዎች የተመሠረቱ ሲሆን፣ ከ30 ሺሕ በላይ የምርጫ አስፈጻሚዎች ተመልክምለዋል፡፡ ካሁን ቀደም ምርጫ የማስፈጸም ልምድ የሌላቸውንና የማስታወሻ ሥልጠና የተሰጣቸውን ጨምሮ ለ26 ሺሕ የምርጫ አስፈጻሚዎች ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡

ከነሐሴ 26 ቀን 2013 ዓ.ም. እስከ ጳጉሜን 5 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ በተካሄደ የመራጮች ምዝገባ ከ7,686,549 መራጮች የተመዘገቡ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል 890,750 መራጮች በሕዝበ ውሳኔው ለመሳተፍ የተመዘገቡ ናቸው፡፡ በደቡብ ክልል ምዕራብ ኦሞ ዞን አዲስ የመራጮች ምዝገባ እንደተከናወነ የተገለጸ ሲሆን፣ ይኼም የሆነበት ምክንያት ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. በተደረገው ምርጫ በዞኑ ያለ ቦርዱ ዕውቅና ውጪ ተከፍተው የነበሩ 76 የምርጫ ጣቢያዎች እንዲዘጉ ተደርጎ ስለነበር ነው፡፡ በተመሳሳይ የመራጮች ምዝገባ ችግር አለበት ተብሎ ምዝገባው እንዲቋረጥ በተደረገባቸው የሶማሌ ክልል ሰባት የምርጫ ክልሎች የመራጮች ምዝገባ በድጋሚ እየተከናወነ ነው፡፡

የምርጫ ቁሳቁስ ሥርጭት ለመራጮች ምዝገባ የተከናወነ ሲሆን፣ እስከ መስከረም 11 ቀን 2014 ዓ.ም. ደግሞ የድምፅ መስጫ ቁሳቁስ ሥርጭት ይጠናቀቃል ሲሉ ሶሊያና ተናግረዋል፡፡

ቦርዱ የቁሳቁስ ሥርጭትን አስመልክቶ ማክሰኞ መስከረም 11 ቀን 2014 ዓ.ም. ለሪፖርተር በላከው ማብራሪያ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም. በሐረሪ ክልል፣ በሶማሌ ክልልና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ለሚያካሂደው ምርጫና ሕዝበ ውሳኔ ለድምፅ መስጫና ለኦፕሬሽን ሥራዎች የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችን ከማዕከል ወደ ምርጫ ክልሎች አሠራጭቶ አጠናቅቋል፤›› በማለት፣ ‹‹ሥርጭቱ ዓርብ መስከረም 7 ቀን 2014 ዓ.ም. የተጀመረ ሲሆን ሐረሪ ክልል፣ ሶማሌ ክልልና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የሚሠራጩትን ቁሳቁሶች የጫኑ ተሽከርካሪዎች አዲስ አበባ ከሚገኘው የቦርዱ ጊዜያዊ መጋዘን መስከረም 11 ቀን 2014 ዓ.ም. ወደ ምርጫ ክልሎች ተንቀሳቅሰው ጨርሰዋል። በአዲስ አበባና ቅርብ አካባቢዎች ለሐረሪ ተወላጆች ለተከፈቱት ምርጫ ጣቢያዎች የሚሠራጩትን ቁሳቁሶች ደግሞ፣ የድምፅ መስጫ ቁሳቁስ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች መድረስ ያለበትን የጊዜ እርዝማኔ ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ የሚጠናቀቅ ይሆናል፤›› ሲሉ አስታውቋል፡፡

ሆኖም ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ያልተካሄዱና በዚህኛው ዙር ይከናወናሉ ሲል ቦርዱ አስታውቆ የነበረው በቤንሻንጉል ጉምዝ በመተከልና በካማሺ ዞኖች የሚገኙ የምርጫ ክልሎች፣ እንዲሁም የደቡብ ክልል የጎፋ ዞን የቁጫ ሕዝብ ልዩ የምርጫ ክልል አሁንም ድምፅ አይሰጥም፡፡

በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ካማሺና መተከል ዞኖች በተደጋጋሚ ሲከሰት የነበረው የንፁኃን ጥቃት አሁንም ሊረግብ ያልቻለ ሲሆን፣ በክልሉ የሚንቀሳቀሰው በተለይም የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አባላት ሕዝቡ በመጠለያ ጣቢያዎች እንደሚገኝ፣ በምርጫው የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር 22 እንደሆነ፣ እነዚህ ፓርቲዎች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 210 ዕጩዎችን፣ ለክልል ምክር ቤቶች ደግሞ 1,236 ዕጩዎችን ማቅረባቸውን ሶሊያና አስረድተዋል፡፡

ይሁንና በተለይም በሶማሌ ክልል ያለው የምርጫ ሒደት ፍትሐዊና ነፃ ሊሆን አይችልም ያሉ ሦስት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከምርጫው ራሳቸውን አግልለዋል፡፡ እነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦብነግ)፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) እንዲሁም የነፃነትና ዕኩልነት ፓርቲ (ነዕፓ) ናቸው፡፡

ኦብነግ ከምርጫው ራሱን እንዳገለለ ዓርብ መስከረም 7 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ለምርጫ ቦርድ ከመራጮች ምዝገባ ጋር የተገናኙ ችግሮችን አስታውቆ እንደነበረና መፍትሄ ሊያገኝ ስላልቻለ ከስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ራሴን አግልያለሁ ብሏል፡፡

ፓርቲው የምርጫ ካርድ የተሠራጨው ለሕዝቡ ሳይሆን ለገዢው ፓርቲ ካድሬዎችና ደጋፊዎች ነው በማለት ራሱን ከምርጫው አግልሏል፡፡

በአንድ ክልል ጦርነት እየተካሄደ በሌላው ሰላም ሊኖር አይችልምና ሁሉም የግጭቱ ወገኖች ጦርነቱን ማቆም አለባቸው በማለት የትግራይ ጦርነትን አጣቅሶ የሚያሳስበው መግለጫው፣ ከመራጮች ምዝገባ ጋር የተያያዙ ችግሮችን የፖለቲካ ፓርቲዎች ለቦርዱ በተደጋጋሚ ያስታወቁ ቢሆንም ቦርዱ ምላሽ ሊሰጣቸው እንዳልቻለ በማንሳትም ወቅሷል፡፡ በዚህም በሶማሌ ክልል ለነፃና ገለልተኛ ምርጫ የሚያስፈልገውን ቅድመ ሁኔታ እንዲሟላ አላደረገምም ብሏል፡፡ ስለዚህም ምርጫው ለሦስት ወራት እንዲራዘም ሲደረግ በሕዝቡ ዘንድ ተፈጥሮ የነበረው ተስፋ ቦርዱ የመራጮችን ምዝገባ ከነ ችግሮቹ በማስቀጠሉ እንዲንኮታኮት አድርጓል ይላል የኦብነግ መግለጫ፡፡

ሆኖም በቅርቡ የትጥቅ ትግል ትቶ ወደ ሰላማዊ ትግል የተቀላቀለው ኦብነግ ይኼንን ውሳኔ ማስተላለፍ ቀላል እንዳልነበረ አምኗል፡፡

ኢዜማና ነዕፓ በጋራ መስከረም 9 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጡት መግለጫ፣ ‹‹በሶማሌ ክልል ውስጥ በተካሄደው የመራጮች ምዝገባ ሒደት ችግር ያዘለ ከመሆኑም በላይ ሕግና የምርጫ ሥርዓት የጣሰ ከመሆኑ በላይ የምርጫውን ምንነት ትርጉም የሚያሳጣ ለአንድ ወገን ያዳላ በመሆኑ፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከዚህ በፊት ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያቀረብናቸው ቅሬታዎች ሊፈቱ ባለመቻላቸውና የምርጫውን ሒደት ተዓማኒነት የሚሳጣ ስለሆነ ከምርጫው ራሳችንን አግልለናል፤›› ብለዋል፡፡

ፓርቲዎቹ ራሳቸውን ከምርጫው ለማግለል፣ ‹‹ከዚህ በፊት ተሰርቆ የነበረው የምርጫ ቁሳቁስ በአዲስ እንዲተካ የጠየቅን ቢሆንም፣ አሁን ግን ቀድሞ ተዘርፎ በነበረው ካርድ ወደ ምርጫ በመገባቱ ምርጫው ተዓማኒነት አይኖረውም፡፡ በተጨማሪም የምርጫ ጣቢያ ያልተቋቋመባቸው አካበቢዎች ምርጫ ጣቢያ እንዲቋቋም ጠይቀን የነበረ ቢሆንም ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጠው ምላሽ አጥጋቢ፤›› አይደለም የሚለውን እንደ አንድ ምክንያት አስቀምጠዋል፡፡

በተጨማሪም በየደረጃው መዋቀር የነበረበት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መዋቅር ከመንግሥት መዋቅር ጋር የተዋሀደ በመሆኑና የምርጫ አስፈጻሚዎች የምርጫ ቁሳቁስ አስዘርፈው በሕግ መጠየቅ ሲገባቸው፣ አሁንም ምንም ዓይነት ማሻሻያ ሳይደረግ በዛው መንገድ በመቀጠሉ የምርጫውን ፍትሐዊነትና ተዓማኒነት የሚያሳጣው እንደሆነ፣ እንዲሁም ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቀረቡ የምርጫ ቁሳቁስ ድልድል ሒደት፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች ምልመላና ሥልጠና ሒደት፣ ስለመራጮች ምዝገባ ሒደትና የጊዜ ሰሌዳ አለማስቀመጥና አሁንም በዚያው ሒደት የቀጠለ በመሆኑና በቦርዱ በኩል የሠለጠኑ ሠልጣኞች ሳያውቁ የምርጫ ቁሳቁስና ሰነድ በወረዳና በቀበሌ የመንግሥት መዋቅር ሠራተኞች እጅ በመግባቱ፣ ይኼም ለገዢው ፓርቲ ብቻ የሚያገለግል በመሆኑና አሁንም በዚያ መንገድ መቀጠሉን በመጥቀስ ከሰዋል፡፡

ፓርቲዎቹ አክለውም፣ ባለው የመረጃ ክፍተት ሳቢያ ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ለእያንዳንዱ የምርጫ ክልል ምን ያህል የመራጮች ካርድ እንደመጣ ግልጽ አለመሆኑ ችግር ፈጥሯል ያሉ ሲሆን፣ ቁሳቁሱን እያጓጓዘ ያለው የወረዳና የቀበሌ መስተዳድር መዋቅር በመሆኑ በመርሁ መሠረት ለአንድ ዕጩ በየምርጫ ክልሉ የራሱን ታዛቢ እንዲኖር ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከ15 ቀናት በፊት ማሳወቅ አለበት የሚለው መርህ በመጣስ የምርጫውን ነፃና ፍትሐዊነት ጥያቄ ውስጥ ያስገባ ነው ብለዋል፡፡

ሶሊያና በመግለጫቸው የእነዚህ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በተለይም የኦብነግ ከምርጫው ራሳቸውን ማግለል በምርጫው ሒደት ላይ ምንም ተፅዕኖ እንደማይኖረው ያስታወቁ ሲሆን፣ በተለይ ኦብነግ ዕጩ ለማስመዝገብ ችግር አለብን ሲሉ በማዕከል ዕጩ ማስመዝገብ እንዲችሉ አድርገናልም ብለዋል፡፡ የመራጮች ምዝገባ ጋር በተያያዘም ችግር ታየ በተባለባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ምክንያት ሙሉ የምርጫ ክልሎች ተዘግተው ማጣራት እንዲከናወን የተወሰነ እንደነበረና ለአጠቃላይ የማጣራት ሥራው እስከ አምስት ሚሊዮን ብር ድረስ ወጪ እንደተደረገ በመጠቆም፣ ለሶማሌ ክልል ከተሰጠው ትኩረት አንፃር ፓርቲዎቹ ራሳቸውን ማግለላቸው ያሳዝናል ብለዋል፡፡

የእነዚህ ተረፈ-ምርጫዎች ውጤት እስከ መስከረም 30 ቀን 2014 ዓ.ም. ለማሳወቅ ዝግጅት ተደርጎ እየተሠራ እንደሚገኝ የጠቆሙት ሶሊያና፣ የሕዝበ ውሳኔ ውጤቶችም በቦንጋ ከተማ ተሰብስበውና ተደምረው በተመሳሳይ በአሥር ቀናት ውስጥ ይፋ ይደረጋሉ ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -