Thursday, June 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በንግድ ዘርፉ ተዋናዮች ላይ በተወሰደ ዕርምጃ መሻሻል የጀመረው የዋጋ ንረት

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከወቅታዊ የዋጋ ንረቱ ጋር በተያያዘ በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በኩል እየተወሰዱ ያሉ ዕርምጃዎች ለውጥ እየታየባቸው መሆኑ ተጠቆመ፡፡ እየተስተዋለ ያለውን የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ለመከላከል ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ተግባር መግባቱን የሚያመለክተው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ መረጃ፣ በፌዴራል ደረጃ የተቋቋመው ዋጋ ማረጋጊያ በሚመለከት ሰሞኑን በኦሮሚያ፣ ደቡብ ሲዳማና አማራ ክልሎች፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ ዙሪያ ግብረ ኃይሉ በመዘዋወር በንግዱ ዘርፍ ያገኛቸውን ችግሮችና አሁናዊ ሁኔታዎች ለንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ሪፖርት አቅርበዋል፡፡ በዚህም መሠረት ምርት መደበቅ፣ ሱቅ መዝጋት፣ የሽያጭ ደረሰኝ ያለመስጠትና ቢሰጡም የሚሸጡበት ዋጋና ደረሰኝ ላይ የሚጻፈው ዋጋ መለያየት፣ የዋጋ ዝርዝር ያለመለጠፍና የደላሎች በሁሉም የግብይት ቦታዎች መግባት የተስተዋሉ ዋና ዋና ችግሮች ሆነው መገኘታቸውን በቀረበው ሪፖርት ላይ ተጠቅሷል፡፡ አቶ መላኩም፣ በአሁኑ ወቅት መንግሥት የህልውና ዘመቻ እያካሄደ ባለበት ወቅት፣ እንደዚህ ያለ የኢኮኖሚ አሻጥር መፍጠር በሸማቹ ማኅበረሰብ ላይ ኢኮኖሚያዊ ጫና ለመፍጠር የሚደረጉ እኩይ ተግራት ተቀባይነት እንደማይኖራቸው ማስታወቃቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡  

ለኑሮ ውድነቱ መባባስ እንደ ትልቅ ተግዳሮች ከሚጠቀሱት ጉዳዮች ውስጥ፣ በግብይት ሒደቱ የሕገወጥ ደላሎች ጣልቃ ገብነት አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፣ እነዚህና መሰል የሥርዓተ አልበኝት ችግሮችን ከሥሩ ለማድረቅ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከፌዴራል ፖሊስና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሠራና ይህም ውጤት እያመጣ ስለመሆኑ አስታውቋል፡፡  

እስካሁን በግብረ ኃይሉ በተወሰዱ ዕርምጃዎች ለውጦች ታይተዋል ተብለው ከተጠቀሱት ውስጥ፣ በኦሮሚያ ክልል ከኑሮ ውድነት ጋር ተያይዞ እየተወሰደ ባለው ዕርምጃ የዋጋ መረጋጋትና መቀነስ የታየ ሲሆን፣ አንዳንድ ምርቶች ላይ ከ200 እስከ 1,500 ብር ቅናሽ መታየቱ ተጠቁሟል፡፡

በከተሞች መጋዘኖች እየተፈተሸ ሕገወጥ የንግድ እንቅስቃሴ የመቆጣጠር ሥራዎችና የንግድ አሻጥሮችን የመለየት ሥራ መከናወኑንም በግብረ ኃይሉ እንቅስቃሴ የተመለከቱ መረጃዎች አመላክተዋል፡፡ በሕገወጥ እንቅስቃሴ ተሰማርተዋል የተባሉ ነጋዴዎች ላይ ዕርምጃ እየተወሰደ ሲሆን፣ ከሰሞኑም ከ50 ሺሕ ብር እስከ ሦስት ወራት በሚደርስ እስራት የተቀጡ ነጋዴዎች መኖራቸውን የግብረ ኃይል ኮሚቴው ሪፖርት አመላክቷል ተብሏል፡፡ በዚህም ምክንያት በተወሰኑ ከተሞች በአንዳንድ ሸቀጣ ሸቀጦች ላይ እስከ 1,500 ብር ድረስ የዋጋ ቅናሽ መታየቱን የሚያትተው ይኼው ሪፖርት የሌሊት ድብቅ ንግድ መበራከት፣ የገበያ ትስስር ችግርና የምርት እጥረት ደግሞ አሁንም በንግዱ ሥርዓት ላይ ማነቆ ሆነው እንደሚታዩ ተጠቅሷል፡፡  

በኦሮሚያ በተወሰደ ዕርምጃ ወደ 135 ሺሕ የንግድ ተቋማት ተፈትሸው፣ ከ10 ሺሕ በላይ በሚሆኑት ላይ የገንዘብና የእስራት ቅጣትን ጨምሮ የተለያዩ ሕጋዊ ዕርምጃዎች መወሰዳቸው ታውቋል፡፡ ዕርምጃው ሥርዓት አልበኝነትን መግታት፣ የኑሮ ውድነቱን ማረጋጋትና የዋጋ መቀነስ እንዲመጣ ጉልህ ሚና እያበረከተ መሆኑም እየተገለጸ ነው፡፡ በአዲስ አበባ የኢኮኖሚ አሻጥር በመፍጠራቸው 1,967 ንግድ ድርጅቶች ላይ ዕርምጃ መውሰዱን የከተማዋ ንግድ ቢሮ አስታውቋል፡፡ እንዲሁም የዋጋ ንረቱን ከመቆጣጠር ባለፈ በተወሰነ መልኩም ቢሆን አንዳንድ ምርቶች ላይ የዋጋ ቅናሽ መታየቱንና የበዓል ገበያው የተረጋጋ ሆኖ እንዲያልፍ የቁጥጥር ግብረ ኃይሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበረው ቢሮው አስታውቋል፡፡

በአዲስ አበባ ከ31,278 በላይ የንግድ ተቋማት መጎብኘታቸው የተገለጸ ሲሆን፣ በ1,967 ንግድ ድርጅቶች ላይ ሕጋዊና አስተዳደራዊ ዕርምጃዎች መወሰዱን ገልጿል፡፡ በቀጣይም በኢኮኖሚ አሻጥር ላይ በሚሳተፉ ሕገወጥ ነጋዴዎች ላይ የሚወሰደው ዕርምጃ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ ፕሬስ ሴክሬተሪያት ጽሕፈት ቤት መረጃ አመልክቷል፡፡     

በሚኒስቴሩ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ወ/ሮ አበባ ታመነ ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ ደግሞ፣ መንግሥት የኢኮኖሚ አሻጥርን ለመከላከል ያቋቋመው ግብረ ኃይል በሕገወጦች ላይ ተገቢውን አስተዳደራዊ ዕርምጃ በመጠቆም፣ የግብረ ኃይሉ ባደረገው መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ በኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ በሕገወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ የነበረ 250 ኩንታል ሰሊጥ፣ እንዲሁም በሐረሪ ክልል አራት መኪና ሽንኩርት አየር በአየር ሲሸጥ በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ተናግረዋል፡፡ በደቡብ ክልል በሃላባ ዞን ስምንት ሕገወጥ ደላሎች ላይ የእስራት ዕርምጃ መውሰዱንና በሕገወጥ መንገድ የተከማቸና ከፍተኛ ግምት ያለው ብረት መያዝም ከዚሁ ግብረ ኃይል እንቅስቃሴ ጋር የተያያዘ መሆኑ ተገልጿል፡፡  

እንዲህ ያሉ ዕርምጃዎች እየተወሰዱ ቢሆንም፣ አሁንም ገበያው በታሰበው ልክ እየተረጋጋ ያለመሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ እንደ ወ/ሮ አበባ ገለጻም፣ አስተማሪ ዕርምጃዎች ይወሰዱ እንጂ አሁንም በቀጣይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸው መሠራት የሚገባቸው ጉዳዮች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡ በተለይ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ እየተፈጠረ ላለው የኢኮኖሚ አሻጥር የአንባሳውን ድርሻ የሚይዘው በግብይት ሒደቱ ላይ ምንም እሴት የማይጨምሩ የሕገወጥ ደላሎች ጣልቃ ገብነት መሆኑን አመልክተዋል፡፡ እነዚህን ሕገወጥ አካላት አደብ ለማስያዝ በደቡብ ክልል በሃላባ ዞን የታየው በጎ ጅማሮ በሌሎች ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮችም ሊተገበር እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡  

ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከንግድ ሥርዓቱ ጋር በተያያዘ ‹‹እየወሰድኳቸው ናቸው›› ካላቸው ዕርጃዎች ባሻገር፣ ሕወሓት በሥልጣን በቆየባቸው ዓመታት በርካታ አሻጥሮች እንደተሠሩ በመግለጽ፣ እነዚህን አሻጥሮች ለመበጣጠስ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ማመልከቱ አይዘነጋም፡፡ በተለይ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ይህንን፣ ‹‹አሸባሪውና ዘራፊው ቡድን ሥልጣን ላይ በቆየባቸው 27 ዓመታት በርካታ የኢኮኖሚ አሻጥሮችን ሲሠራ ነበር፤›› ብለዋል፡፡

በነፃ ኢኮኖሚ ሥርዓት ሽፋን አንድን አካል ብቻ ተጠቃሚ የሚያደርግ ፖሊሲ ማውጣት፣ የመሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካን ብቻ ተጠቃሚ ለማድረግ፣ ተጨማሪ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች እንዳይገነቡ የሚያግድ ፖሊሲ እስከ ማውጣት የተደረሰበት እንደሆነ አቶ መላኩ ጠቁመዋል፡፡ ለኮንስትራክሽን የሚውሉ ግብዓቶችን በውስንና ለአሸባሪ ቡድን ታማኝ በሆኑ አካላት ብቻ ከውጭ እንዲመጡ መፍቀድ፣ በኢንቨስትመንት ሽፋን ሰፋፊ መሬቶችን በመያዝ ከባንኮች የብድር አገልግሎት መጠየቅና ብድሩን በተገቢው ዲሲፕሊን አለመመለስ ከተሠሩ አሻጥሮች ውስጥ ተጠቃሾች መሆናቸውንም መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

ይህንን የኢኮኖሚ አሻጥር የተረዳው የለውጡ ኃይል፣ ከለውጡ እዚህን ችግሮች ለመቅረፍ እንቅስቃሴ እያደረገ ባለበት ወቅት ይህ ጽንፈኛ በአገሪቱ ላይ በከፈተው ጦርነት የተፈለገው ውጤት እንዳልመጣ ያመለከቱት አቶ መላኩ፣ በአሁኑ ወቅት ይህንን የኢኮኖሚ አሻጥር ለመቀልበስና በአገሪቱ ላይ አላስፈላጊ ዋጋ ጭማሪ እንዳይፈጠር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከሚመለከታቸው ባለሀብቶች ጋር ስምምነት ላይ ተደርሷል ብለዋል፡፡ አሁን ያለንበት ወቅት አስከፊና ፈተና የበዛበት በመሆኑ በተለይ የአገራችን ባለሀብቶች ትርፍ ኅዳጋቸውን ከማሰብ ይልቅ አገርን ወደ ማዳን አንድምታ መሸጋገር እንደሚገባቸውም ማሳሰባቸው አይዘነጋም፡፡

ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርም እንዲህ ያሉ አሻጥሮችን ለመከላከል ኅብረተሰቡ መተባበር እንዳለበትና ጥቆማ መስጠቱንም እንዳያቆም እያሳሰበ ነው፡፡  

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች