Wednesday, June 19, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የአፍሪካ መሪዎችና ሕዝቦች የፖለቲካ የኢኮኖሚና የማኅበረሰብ ርዕዮት ለአዲሱ መንግሥት ግብዓቶች

  • ኡጃማ (Ujama) – ኡቡንቱ (Ubuntu) – መደመር (Synergy)

በተስፋዬ ቦሩ (ዶ/ር)

የዓለም የማኅበረሰብና የኢኮኖሚ አወቃቀር ከአንዳንድ ሐሳባዊ ቲዎሪዎች (Dependency Theory) አንፃር ሲታይ በሦስት ይከፈላል፡፡ አንደኛው በጣም ኃያላን የሆኑ በኢኮኖሚና የዓለም ፖለቲካ አቋማቸው የፈረጠሙ በመካከለኛው (Core) ረድፍ የተሠለፉ አገሮችን ሲይዝ፣ ሌላኛው መካከለኛ (Semi Pheripherial) በማደግ ላይ ያሉና የኢኮኖሚ አወቃቀራቸው በአብዛኛው በመካከለኛና በፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት የሚገኙ ናቸው፡፡ ሌላኛው ጥግ (Peripherial) ላይ የሚገኙ በማኅበረሰብ ልማት በኢኮኖሚና በተለይ በሰው ኃይል ልማት አነስተኛ የሆኑ አገሮች/አኅጉሮችን የሚያካትት ነው፡፡ በመጨረሻው ረድፍ ላይ ተሠልፈው የሚገኙት አብዛኛዎቹ አገሮች በአፍሪካና በእስያ አካባቢ የሚኖሩ ሕዝቦችን ያቀፉ ሲሆን፣ እነዚህ አገሮች በጦርነትና ባልተረጋጋ የመንግሥትና የኢኮኖሚ መዋቅር ምክንያት ፍዳቸውን የሚያዩ ናቸው፡፡

 በተለይ የኢኮኖሚ ሥርዓቱ የተቀረፀው በጥግ የሚገኙ አገሮች የኃያል አገሮች የፖሊሲና የኢኮኖሚ ድጋፍ ጥገኞች ሲሆኑ፣ ያላቸውን የተፈጥሮ ሀብት ላደጉ አገሮች በመሸጥ በመሀል ረድፍ ከሚገኙ አገሮች በእነሱ ጥሬ ሀብት የተመረቱ ውጤቶችን እንዲጠቀሙ የሚጠበቅባቸው ናቸው፡፡ ለምሳሌ ቡና ወደ አደጉ አገሮች ልኮ ቼኮላት በውድ ዋጋ እንደመግዛት ማለት ነው፡፡ የሚገርመው እነዚህ በጥግ ረድፍ ያሉ አገሮች በተፈጥሮ ሀብት የታደሉ ነገር ግን ሀብታቸውን በወረቀት በመቀየር የሀብታም አገሮች ምፅዋት ጠባቂዎች መሆናቸው ነው፡፡ የራሳቸው የሚባል የኑሮና የማኅበረሰብ ዘይቤ ቢኖራቸውም እሱን ትተው ያደጉት አገሮች ባስቀመጡላቸው የኢኮኖሚ መርህና የአኗኗር ሕግጋት እንዲከተሉ ከፍተኛ ጫና ያረፈባቸው ናቸው፡፡ አፍሪካ ከነዚህ ጥግ ከሚባለው የኢኮኖሚ ሥርዓት ምድብ ውስጥ ስትሆን በውስጧ ያሉ ብዙ አገሮችም ሆኑ ዜጎች በአብዛኛው ከድህነት ወለል በታች በመሆን ዕድሜያቸውን የሚገፉ ናቸው፡፡ ነገር ግን ይሄን አካሄድ ብዙዎቹ አሜን ብለው ቢቀበሉም በታሪክ ምዕራፍ ይኼንን  ለመቀየር የተነሱ ጥቂት መሪዎችና የማኅበረሰብ ክፍሎች አሏት፡፡ ከነዚህ መሪዎች ውስጥ ግንባር ቀደሙ የታንዛኒያው ጁሊየስ ኒሬሬ ሲሆኑ፣ ታንዛኒያ ነፃነቷን ካወጀች በኋላ ኡጃማ (Ujama) የተሰኘ የማኅበረሰብና የኢኮኖሚ መርህ በመቅረፅ፣ ታንዛኒያ ከቅኝ ግዛት በፊት ትተዳደርበት በነበረው የማኅበረሰብና የኢኮኖሚ ሕግ መገዛትና ራሷን መገንባት አለባት የሚል አስተሳሰብ አበርክተዋል፡፡

ሌሎች ለዘመናት የቆዩ የአፍሪካ የማኅበረሰብ ዕሴቶች ቢኖሩም እንደ ኡቡንቱ ያለ በመላው አኅጉሪቱ ሊባል በሚችል መልኩ የተተገበረ የማኅበረሰብ ሕግ መገለጫም እንደማሳያም ተወስቷል፡፡ በቅርቡም በአገራችን በስፋት ሲነገርለት የሚስተዋለውና የራሱ ሕግጋት የተነደፉለት የመደመር ዕሳቤም በጥቅሉ ቀርቧል፡፡ የጽሑፉም ዓላማ አፍሪካ ለዘመናት የተጫነባትን የጭቆና ቀንበር ለመስበር መሪዎቿ ሕዝቦቿ በተግባር ባይሳካም ቢያንስ በሐሳብና በፍልስፍና ደረጃ  ምን አድርገዋል? የሚለውን ለመቃኘትና የነዚህን የሕዝቦችና የመሪዎች ምልከታ አንድነትና ልዩነትን በቁንፅል በማሳየት፣ አፍሪካ በተለይ ደግሞ አገራችን ኢትዮጵያ ከውስጥም ከውጭም እየደረሰባት ካለው ተፅዕኖና ችግሮችም አንፃር የራሷ የሆነ አመለካከትና የኑሮ ዘይቤ ከመቸውም በላይ ዛሬ ላይ እንደሚያስፈልጋት ለመግለጽም ነው፡፡ በተለይ በመስከረም የሚመሠረተው መንግሥት ሊያያቸው የሚገቡ የአፍሪካ ዕሴቶችን እንደማሳያ ለማንሳትና አገር በቀል የሆኑ የመሪዎች ፍልስፍናዎች መሪዎቹ ብቻ ሳይወሰኑ በስፋት ወደ መሬት እንዲወርዱ ማድረግ አስፈላጊነትን ለመጠቆም ነው፡፡

ኡጃማ (Ujama)

ትልቁ የዚህ ሐሳብ መነሻ አፍሪካ ከቅኝ ገዥዎቿ ዕቃ እያስመጣችና የእነሱ የኢኮኖሚ ጥገኛ በመሆን ለውጥ እንደማታመጣ በመተንበይ አኅጉሮች በራሷ አኗኗርና አያት ቅድመ አያቶች በኖሩበት የተፈጥሮ ሥርዓት ብትገዛ ሙሉ ነፃነቷን ከመጎናፀፏ ባለፈ ራሷን በዕድገት ጎዳና ልታስጉዝ እንደምትችል ቀድሞ የተመለከተ ራዕይ ነው፡፡ በዚህ ሐሳብ መሠረት ልማትና ዕድገት ሊመጣ የሚችለው አፍሪካ መሉ ነፃነቷን ስታረጋግጥና በራሷ መቆምን ስትጀምርና ከውጭ ዕርዳታና የካፒታል ፍሰት ነፃ ስትሆን ነው፡፡ ይኼም የተወሰነ ያህል የሶሻሊስት መርህ ተከታይ በመሆኑ ‹‹የአፍሪካ ሶሻሊዝም መነሻ›› የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን መሠረታዊ መርሆዎቹ ያረፉት በአፍሪካዊ ባህልና ማንነት ላይ የተመሠረቱ በደቦ የመሥራት፣ የማምረቻ ዓውዶችን በጋራ መጠቀም፣ የግል ይዞታን በመንግሥት እጅ ማዞርና የሕዝብ ግልጋሎቶችን በመንግሥት ድጋፍ ማዳረስ ነው፡፡ ይኼም የአንድን ፓርቲ የበላይነት በማስፈን ኃያል አገርን መገንባት በማለም በጁሊየስ ኔሬሬ የሚመራው ጠንካራ ፓርቲ (TANU Tanganikan Africa Nationional Union) እና የአገሪቱ መንግሥት ፖሊሲ እንዲሆን በ1967 የአሩሻ አዋጅ (Arusha Declaration) በመባል ተግባራዊም ተደርጓል፡፡ ይኼም የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሞዴል ነፃና አስገዳጅ የትምህርት ፖሊሲና ወጥ የሆነ የአመራር ሥርዓት (Leadership Code) በመፍጠር በጎሳ ያልተከፈለች አንድ አገር ለመፍጠር በመሞከር በብዙ የማኅበረሰብ ዕድገት መለኪያዎች ማለትም የጨቅላ ሕፃናት ሞትን በመቀነስ፣ የዕድሜ ጣሪያን በመጨመር፣ የዜጎች የመጀመርያና የአዋቂዎች የትምህርት ሽፋን ድርሻን በማሳደግና የአገሪቱን አንድነት በማስጠበቅ ስኬታማነቱንም ያስመሰከረ ፍልስፍናም ነበር፡፡ ነገር ግን ምርታማነትን በማሳደግና ታንዛኒያን ከድህነት በማውጣት ረገድ የታሰበውን ከዓለም አቀፍ ተመፅዋችነት በማላቀቅ ላይ ብዙ ውጤት አላስመዘገበም፡፡

ታንዛኒያ በዚህ የማኅበረሰብና የኢኮኖሚ ሕግ ከ1967 እስከ 1985 ድረስ ስትመራ ቆይታ ያው እንደ ሌሎቹ ጥግ ላይ ያሉ አገሮች አገር በቀል የሆነውን ኡጃማ ወደ መዋቅራዊ ማስተካከያ ፕሮግራም (Stractural Adjustment Program SAP) በመቀየር የንግድ ነፃነትንና ዓለም አቀፋዊነትን፣ ከጊዜ ጋር መለወጥና የግል ሀብት ማፍራት በሚሉ የምራባውያን አመለካከቶች  ለመተካት ተገዳለች፡፡ ነገር ግን ከኢኮኖሚው ስኬት ማጣት ባሻገር እንዲህ ዓይነት የአፍሪካ መሪዎች አፍሪካ ልትተዳደርበት የሚገባ የራሷ የሆነ የማኅበረሰብና የኢኮኖሚ ሕግጋት እንደሚያስፈልጋት ፍንትው አድርገው አሳይተዋል፡፡ በተለይ አፍሪካ አንድ ሊያደርጋት በሚችል የማኅበረሰብ ዕሴት ላይ ብትሠራ ከጎሳ ባለፈ አገራዊ/አኅጉራዊ  ዕይታን ሕዝቦች ሊጎናፀፉ የሚችሉበት ታላቅ ዕድል እንዳለም አመላካች ዕመርታዎች  የታዩበት ነው፡፡ የአፍሪካ መሪዎች ፍትሐዊነትና እኩልነት ላይ የተመሠረተ የማኅበረሰብና የፖለቲካ አካሄድ ላይ ትኩረት መስጠትን ሕዝቦቿ የሚጠብቁት ትሩፋቶች ከመሆንም ባለፈ በጋራ ሊጋሩት የሚችሉት የሞራል እሴቶችም መሆናቸውን ያረጋገጠ ነበር፡፡

የአፍሪካ ዜጎችም አንዱን ወንድም፣ ሌላውን እንደ ጠላት የሚተያዩበት የማኅበረሰብ መሠረት የሌለና አፍሪካ ላይ የመደብ ክፍፍሎች መሠረተ ቢስ እንደሆኑም ያሳየ ነው፡፡ ትልቁ መርህ ‹‹በወንድማማችነትና በአንድ አፍሪካ አምናለሁ›› የሚል ሲሆን፣ ቤተሰባዊነትን (Family Hood) የኡጃማና የአፍሪካ ሶሻሊዝም ልዩ መገለጫም አድርገው አቅርበውታል፡፡ አፍሪካ የዴሞክራሲ ሥርዓት ምንጭና ዴሞክራሲም ለዘመናት ስትተዳደርበት የነበረ የአኗኗር ዘይቤ እንደሆነም ዕውቅና የሰጠን ይኼንን ሥርዓት መመለስም የኡጃማ ዓብይ መሠረቶች ፍትሐዊነትና እኩልነትን ከማረጋገጥ አንፃር ወሳኝ እንደሆነም አበክሮ ያስቀምጣል፡፡

ኡቡንቱ (Ubuntu)

በሌላ በኩል ለብዙ ዘመናት በአፍሪካ ውስጥ በተለይ በደቡብ አፍሪካ የሰፈነው የማኅበረሰብ እሴት ኡቡንቱ (Ubuntu) ተብሎ ይጠራል፡፡ ይኼም አፍሪካውያን ከግለሰባዊ ማንነት ይልቅ ለማኅበረሰባዊነት የሚሰጡትን ታላቅ ትኩረት የሚያሳይ የአፍሪካ ፍልስፍና አካሄድ ነው፡፡ ይህም … የሰው ልጅ ሰው የሚሆነው በሌሎች ሰዎች ውስጥ/ትከሻ ላይ ነው፡፡ ሰው ለመሆን የሌሎች ሰዎችን ዕገዛም እንፈልጋለን… (ዴዝሞን ቱቱ)፡፡

ስለዚህም የአፍሪካ የባህል እሴት የሆኑት ደግነትን፣ ክብርን፣ ሰብዓዊነትንና ለሌሎች መኖርን ማስቀደም ለግል ጥቅም ሳይሆን ለፍትሐዊ ማኅበረሰባዊነት እንደሚጠቅም አበክሮ ያትታል፡፡ ብቻውን የሚኖር አፍሪካዊ ሊኖር ስለማይችል ማንነቱም ሊገለጽ የሚችለው በግለሰቡ ማንነት ብቻ ሳይሆን በሚኖርበት የማኅበረሰብ ክፍል የወል መገለጫዎች ነው፡፡ ከግለሰቦቹ የሚጠበቀውም ፍቅርና መከባበር እንዲሁም ማኅበረሰቡም ሊያሻሽሉ በሚችሉ የትብብር፣ የአካፋይነትና የተንከባካቢነት ባህሪያት ላይ ነው፡፡ ስለዚህ ኡቡንቱ የአፍሪካ የማኅበረሰብ ቡድን ሕይወት መሠረትና የእርስ በርስ ዝምድናን፣ የጋራ ሰብዓዊነትና ሰዎች ለሰዎች ያለባቸውን ኃላፊነት የሚገልጽ የኑሮ ዘይቤ ነው፡፡ ልክ እንደ ኔሬሬ ኡጃማ፣ ኡቡንቱ መከባበርን ለሰው ልጆች ክብር ታላቅ አጽንኦትን ይሰጣል፡፡ በተለይ አዎንታዊ በሆኑ ባህሪያት ላይ እንደ ፍቅር፣ ደግነት፣ ተካፍሎ መኖርንና የቡድን ሥራን ራስን በሌሎች ጫማ ውስጥ አድርጎ መመልከትን ያስቀድማሉ፡፡

አስገራሚው የኡቡንቱ መገለጫም አሉታዊ ባህሪዎች እንደ ጥላቻ ያሉ፣ የአጭር ጊዜ ትውስታ ያላቸውን በዕርቅና በመተው ሊፀዱ እንደሚችሉ በማመን ልጆችን የዚህ ዕውቀት እንዲኖራቸውም የሚቀርፅ ባህል መሆኑም ነው፡፡ ከባሰም አፍሪካ የራሷ የሆነ የሕግ አፈፃፀም ባህልና የፍርድ ሒደት ሲኖራት ይኸም ቢሆን ዕርቅንና ፍቅርን ከማኖር አንፃር የተዋቀረ ነው፡፡ ለተበዳይ ካሳ ለበዳይ ይቅርታን የማይነፍግ የፍርድ ሒደትም ነው፡፡

መደመር (Synergy)

በተመሳሳይ በእኛው አገር ተፀንሶ እያቆጠቆጠ የሚገኘው አፍሪካን የራሷ የሆነ የማኅበረሰብና የኢኮኖሚ አስተሳሰብ እንደሚያሻት የሚያስቀምጠው የመደመር (Synergy) ፍልስፍና ነው፡፡ መደመር ከኢትዮጵያውያን አኗኗር፣ ከተፈጥሮ ሕግና ከአፍሪካው የማኅበረሰብ (Community) አስተሳሰብ ተጣምሮ ከላይ እንደገለጽናቸው አስተሳሰቦች አፍሪካውያን ለአገር በቀል ችግሮች አገር በቀል መፍትሔና የኑሮ ዘይቤ እንደሚያሻቸው የሚጠቁም የሐሳብ ውልደትም ሆኖ እያደገ እየመጣ ነው፡፡

እንደ ኡጃማና ኡቡንቱ በግልጽ የማኅበረሰብ የጋራ (Communal) አመለካከትን በቀጥታ ባያወሳም የኔ (Individualistic) ከሚለው የምዕራባውያን ፈለግ ይልቅ የጋራ ግብ ማስቀመጥንና የብቸኝነትን ጉድለት ለመወጣት ተነሳሽነትን ማሳየትን ዓበይት የመደመር መሠረታውያን አድርጎ ያስቀምጠዋል (ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መደመር ቁጥር 1)፡፡ በተለይ የብቸኝነት ጉድለት የሚለው ከመሠረታዊ የኡቡንቱ አስተሳሰብ ‹ሰው ሰው የሚሆነው በሌላ ሰው ዕገዛ መሆኑን› አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ይኼም አገር በግል ዓላማ ብቻ ሳይሆን የጋራ ዓላማን አንግበው ለትልቅ አገራዊ ራዕይ በተሳሰሩ ዜጎች በጣምራ ልትገነባ የምትችል መሆኗንም አመላካች ነው፡፡

ይኼንንም የመደመር ዕሳቤ ልክ ኡጁማ እንደሚያስቀምጠው፣ ከጎሳ ይልቅ አንድ አገራዊ መንፈስን በመያዝ አንድነትን ማጎልበትን እንደ የመደመር እሴት አድርጎ ይተነትናል፡፡ እንደውም አገራዊ አንድነታችን የምርጫ ብቻ ሳይሆን የህልውና ማስጠበቅ ጉዳይ ጭምር ነው ብሎ ያስቀምጣል፡፡ ከላይ ከገለጽናቸው የአፍሪካውያን አመለካከቶች ለየት ብሎም ከማኅበረሰብ ወይም ከግለሰብ ተኮር ዋልታ ረገጥ ሐሳቦች ይልቅ ሁለቱንም ያማከለ ግለሰባዊ ነፃነትና የማኅበረሰባዊ ደኅንነትን ማረጋገጥ የዜጎችን ክብር ለማጎናፀፍም ሆነ ከጠባብ የጎጥና የጎጠኝነት ስሜት በማውጣት የመደመር ዕሴትን መጎናፀፍ እንደሚቻል ያሳስባል፡፡

ለኡጁማ ማክተም ትልቁ ምክንያት ተደርጎ ሲወሰድ የነበረው ከኢኮኖሚ አንፃር ዜጎችን ከተመፅዋችነት ማውጣት አለመቻሉና በተለይ ከከተማ ይልቅ በየሠፈሩ በሚመሠረቱ ባህላዊ መንደሮች (Villegization) የታንዛኒያን ኢኮኖሚ ማዋቀር የሚለው አመለካከት ላይ የተግባርም የሐሳብም ተቀባይነቱ እምብዛም አለመሆኑ ነበር፡፡ መደመር የዚህን ጉድለት ለመሙላት ዕድገትን ብቻ ሳይሆን ብልፅግናን እንደ እሴት በማስቀመጥ የዜጎችን የሥጋዊ፣ የስምና የነፃነት ፍላጎታቸውን በኢኮኖሚው ሁለቱም መዋቅር (Hard And Soft) ለሟሟላት እንደሚቻል ዕውቅና ይሰጣል፡፡

በፖለቲካም ከታንዛኒያው ኡጅማ መርህ በወጣ መልኩ ዴሞክራሲ የአንድን ፓርቲ የበላይነት ብቻ በማስቀጠል የሚገኝ ሳይሆን፣ ‹ቀጣይነትና አስተማማኝነት ያለው ነፃ የምርጫ አድማስ በማስፋት› የሚመጣ መሆኑን ሲያመላክት መቼም መምረጥ ካለ ከሁለት በላይ ፓርቲዎችን ተሳትፎ የሚጠይቅ በመሆኑ የአንድ ፓርቲ ማንገሥ ከሚለው አስተሳሰብም የተላቀቀ ፍልስፍናም ነው፡፡

የሦስቱ የማኅበረሰብና የመሪዎች የፍልስፍናና የአኗኗር ዘይቤዎች መልዕክት

ከላይ እንደማሳያነት የተነሱት ሦስት የማኅበረሰብና የመሪዎች የፍልስፍናና የአኗኗር ዘይቤዎች በብዙ መሥፈርቶች ተመሳሳይ እሴቶችን ያዘሉ ምልክቶች ሲሆኑ፣ ሁሉም ለአፍሪካዎች ችግር አፍሪካዊ የኑሮ ዘይቤና መፍትሔ አስፈላጊ መሆናቸውን ያሰምሩበታል፡፡ በተለይ አፍሪካ ከግል ፍላጎት ባለፈ በማኅበረሰብ እሴቶች የጎለበተችና የተዋቀረች አኅጉር መሆኗን ሕዝቦቿም በጋራ የመኖርን ልምድ በማካበት የቡድን ፍላጎትና የግለሰባዊ መብት በበለጠ ትኩረት ሲሰጡ እንደኖሩ ያሳያል፡፡ አፍሪካም ከሌሎች አኅጉሮች ልዩ የሆኑ እሴቶች እንደ ወንድማማችነት፣ ቤተሰባዊነት፣ ፍትሐዊነት፣ እኩልነትና ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ራስን በራስ የማስተዳደር ታላቅ አቅም ያላት አኅጉር መሆኗንም ይመሰክራል፡፡ አፍሪካ ከጥላቻ ይልቅ ወንድማማችነትን ከጦርነት ይልቅ ተግባቦትን፣ ከበደል ይልቅ ይቅርታን የሚያጎናፅፍ የዘመናት ሥርዓትና የፍትሕ አካሄድና ቱባ ባህል ባለቤትም መሆኗን ያሳዩናል፡፡

የአፍሪካ ችግር ምንጭ ራስን በራስ የማስተዳደር ልምድ ማነስም ሳይሆን የራስን ትቶ የሌላን የማምለክ አባዜ ላይ መውደቅ መሆኑንና ይኼንንም ከአያት ቅድመ አያት በተወረሰ ጥበብና የታሪክ ልምድ መቀየር እንደሚገባው አጽንኦት ይሰጠዋል፡፡ አፍሪካ በራሷ ልክ የተሰፋ የማኅበረሰብና የኢኮኖሚ መዋቅር መከተልን አሁን ካለችበት አዙሪት ልትወጣበት የምትችልበት ብቸኛ መንገድ ጠቋሚም ሲሆን በመሀል ረድፍ በተሠለፉ አገሮች በሚደረግላት የፖሊሲ መስመርና የኢኮኖሚ ምፅዋት ሩቅ ልትጓዝ እንደማትችልም በፊትም ሆነ አሁንም በተግባር እየታየ ያለ ጉዳይ ነው፡፡ አፍሪካውያን መሪዎች ከቅኝ ግዛት ለመላቀቅ እንደ አፍሪካ አንድነት ድርጅት (አአድ) ያሉ ውህድ ድርጅቶችን ባዋቀሩም ማግሥት ጥሩ ራዕይ ያለቸው አንዳንድ መሪዎችም የአፍሪካ ነፃነት ምሉዕ የሚሆነው ከቅኝ ግዛት ነፃ በመውጣት ብቻ ሳይሆን አፍሪካ ቀድሞ ከነበራት የማንነት ዕሴት ጋር የተጋመደ የማኅበረሰብና የኢኮኖሚ አመለካከትን ልታንፀባርቅ መሆኑን አስቀድመው ዓይተው ለመተግበር ጥረዋል፡፡ በትውልድ ቅብብሎሽ ይህ ሐሳብ ሲከስም ሲጎለብትም ነገር ግን ጨርሶ ሳይጠፋ እስከ ዛሬ ድረስ ቀጥሎ አፍሪካ የጋራ ራዕይና ግብን ስትነድፍ የደረሰችበት ዓውድም እየተንፀባረቀ የሚገኝ ነው፡፡

አፍሪካን አንድ ማድረግ በንግድ፣ በነፃ የሰዎች ዝውውር፣ በኢኮኖሚ ውህደት፣ በፀጥታና ሰላም፣ በመሳሰሉት የወደፊትና የአሁን የተጀመሩ የአፍሪካ የቤት ሥራዎች ሆነው ተቀምጠዋል፡፡ በ1996 የደቡብ አፍሪካ ሕገ መንግሥት ማርቀቂያ ላይ ታቦ ኢምቤኪ ‹‹እኔ አፍሪካዊ ነኝ›› (I am an African) በሚለው፣ ከማርቲን ሉተር ኪንግ እኩል የተቀመጠ ንግግራቸው ላይ አፍሪካ በምንም ሁኔታ ቢሆን መበልፀጓ እንደማይቀር ራዕያቸውን ያስቀመጡበት ነው፡፡ ይህ እኔ አፍሪካዊ ነኝ የሚለው ንግግር ዝም ብሎም የመጣም አይደለም፡፡ አንዳንድ አፍሪካዊነታቸውን ዘንግተው ዜግነታቸውን ቅኝ በገዛቸው አገሮች ማንነት ላይ በማድረግ አፍሪካን ሲክዱና ሲያዋርዱም በነበረበት ወቅት የተነገረ ትልቅ ትርጉም ያለውም ነው፡፡ በወቅቱ በዚሁ ጉዳይ የሚነሱት የማዕከላዊ አፍሪካ መሪ የነበሩት አፄ ቦካሳ፣ እኔ መጀመርያ ፈረንሣዊ ቀጥሎ የማዕከላዊ አፍሪካዊ ዜጋ ነኝ ብለው በይፋ ለሕዝባቸው ንግግር ያደረጉበትም ወቅትም የአፍሪካ መሪዎች ምን ያህል ስለማንነታቸው በኩራት መናገር እንኳ እንደማይችሉ ያሳየ ነበር፡፡

በልብ ወለዱ ዓለምም ይህንን የአፍሪካ በልጆቿ መዋረድ በግልጽ ያሳየው የሰርቅ ዳንኤል ‹‹ቆንጆዎቹ›› መጽሐፍ ነው፡፡ …አፍሪካ መቼ ነው ቀሚሷን ዝቅ የምታደርግና ጭኖቿን የምትሰበስብ፣ ኃፍረቷን የምትሸፍን… ብሎም ይጠይቃል፡፡ ስለዚህም አፍሪካ በልጆቿ ስትዋረድ፣ ዝቅ ስትል፣ ማንነቷን ረስታ በሌሎች ማንነት ለማጌጥ ስትማስን፣ ነገር ግን እሰከ ዛሬም ራሷን ሳትሆን ወይ ሌሎችን ሳትመስል ባተሌ እንደሆነች አለች፡፡ ይህንን ታሪኳን ለመቀየር የታተሩ ልጆቿም በውጭ ጫና፣ በብዙኃን አላዋቂነት ተፅዕኖ ምናልባትም በቅርብ ባሉ የትግል ገዶች ተጠልፈው ህልማቸው ሲዳፈን ኖራል፡፡ የታቦ ኢምቤኪም ህልም ከፖለቲካው መድረክ ላይ ብዙ ባይቆይም ወደ አካዴሚኩና መድረክ በለገሳቸው ቦታ ሁሉ አቅማቸውን ሲያስተጋቡ አሉ ኖረዋልም፡፡ እኚሁ መሪ በንግግር ብቻ ሳይሆን ከሥልጣን ጊዜ ማብቂያቸው በኋላም አፍሪካዊ የትምህርት ፖሊሲ ተቋም (Thabo MBKI Leadership Institiute) በመገንባት አፍሪካውያን ስላላቸው እሴትና የወደፊት የአፍሪካ መሪዎችን አቅም ለማነፅ ሲሞክሩም እናያለን፡፡ ስለዚህ ጥቂትም ቢሆኑ አሁንም ቢሆን አፍሪካ መስዋዕትነት ሊከፍሉላት ወይም እየከፈሉ የሚገኙ መሪዎች እንዳላት እናያለን፡፡  በኛም አገር ብዙ ቢያስከፍላችውም ለዚህ መስዋዕትነት የተዘጋጁ መሪዎችን እያየን ነው፡፡ …የአፍሪካ አንድነት ለአኅጉራችን መሠረት ነው፣ አብረን ለመሥራት ቃል ከገባን የሥነ ተፈጥሮ ሀብትና የሰው ኃይላችን አፍሪካ ወደ ታላቅነት ለማሻገር በቂ ናቸው፡፡ ‹‹የአፍሪካ ጊዜ አሁን ነው››  ዓብይ አህመድ፡፡

አገራችን  በአዲሱ  መንግሥትና  በሕዝባዊ መደረኮች ላይ ልትተገብረው የሚገባ አካሄድ በጥቂቱ

አገራችን ለአፍሪካ ነፃነት ፋና ወጊ የነበረችና ዛሬም የእጅ አዙር አገዛዝን ላለመቀበል አሻፈረኝ ካሉ ጥቂት የአፍሪካ አገሮች አንዷ ነች፡፡ ይኼም በብዙ መልኩ ከተራ የአገር ውስጥ ተቃውም እስከ መሀል ረድፍ ያሉ ኃያላን አገሮች ማስፈራሪያና ዕርምጃዎች እያስከተለ ቢሆንም ለጭቆና መቼም እጅ የማትሰጠው አገር የነብሩን ጭራ ይዛዋለች፡፡ የነብር ጭራ ከያዙም አይለቁምና ወደ ኋላ ተመልሶ የእጅ አዙር አገዛዝን መቀበሉም ለነፃነት የሚከፈለውን ዋጋ ያህል የሚጠይቅና እንደውም የጥቂት መሪዎችን የሥልጣን ዕድሜ ከማራዘም ባለፈ፣ የአገራችንንም ሆነ የአፍሪካን ከጥግ (Peripherial) መደብ ውስጥ ሊያላቅቅ የሚችልበት መንገድ ጠባብ ነው፡፡ ጉዞው ወደፊት መደብ ለውጥ ፍለጋም ሳይሆን የራስ ማንነትን ተገንዝቦ በልክ በተሰፋ የአስተዳደርና የማኅበረሰብ ቅኝት ውስጥ መጓዝም ነው፡፡ ለዕድገት፣ ለመበልፀግና ለዴሞክራሲያዊ ልማድ ለማስፈንም የነብሩን ጭራ ይዞ ጠንክሮ መራመድም አማራጭ የሌለው ነው፡፡

አገራችንም የአፍሪካ ዋና ከተማ፣ የአፍሪካዊነት ግንባር ቀደም መግለጫ እንደመሆኗ ከአፍሪካዊ ማንነት ተፀንሶ የተወለደው ፅንሰ ሐሳብ አሁን ካለበት በጥቂት አመራሮች ራዕይና አረዳድ መወሰን ተላቆ እንደ ወንጌል በስፋት ሊሠራጭበት የሚችልበት መንገድ ሊታሰብ የሚገባ ነው፡፡ ልክ ታቦ ምቤኪ እንደተከተሉት የራሱ የሆነ የአካዴሚ ማዕከልና የትምህርት ካሪኩለም ተቀርፆ ለሚመጣውም ላለውም ትውልድ ካልተሠራጨ፣ የጋን ውስጥ መብራት ሆኖ የመቅረት አደጋውም ላቅ ያለ ነው፡፡ እንደ አፍሪካ ኢትዮጵያም የወንድማማችነትና የፍቅር አንዱ ለአንዱ የመኖርና የራስ የማኅበራዊ ዕሴቶች ያሏት ከመሆኑ አንፃር፣ እነዚህን የማጉላትና ለሚቀጥለውም ትውልድ አውቀውት እንዲያድጉና አድገውበትም እንዲኖሩበት፣ ኖረውበትም እንዲያረጁበት  ከሥሩ የማነፅ ሒደት ላይ ልዩ ትኩረት ያሻል፡፡

በተለይ አገራችንን ቆልፎ ከያዛት ከጎሳና ከዘር ማንነት ላይ የመወሰን አባዜ ወደ አገራዊ ብሎም አኅጉራዊ አንድነት የማሸጋገሪያ ሐሳብ ላይም ወደፊት በሚካሄደው የብሔራዊ የውይይት መድረኮች፣ የዕርቅና ይቅርታ ፕሮግራሞች ላይ ኅብረተሰቡ በስፋት ሊነጋገርበት የሚገባም ነው፡፡ በነዚህ መደረኮች ላይ ሊያራርቁን ሳይሆን ሊያግባቡን የሚችሉ ሐሳቦችና ትርክቶች ላይም ትኩረት ማድረጉም ታላቁ የቤት ሥራ ነው፡፡ ልክ ሩዋንዳ ውስጥ ስለ ሁቱና ቱትሲ ግጭት ማውሳት እንደማይቻለው በኛም አገር ግጭትን የሚቀሰቅሱና ልዩነትን በሚያሰፉ የኋላ ታሪኮች ላይ ጊዜ ማጥፋትንም በጥብቅ ቁጥጥር ሊደረግበት የሚገባም ነው፡፡ በተለይ የመንግሥት ቁጥጥር ያለበት በማይመስለው የሚዲያዎች አካሄድ ላይ የሚደረገው ክትትልና የሕግ ማዕቀፍ ቀረፃ ከመቼውም ጊዜ በላይ ጠንከር ብሎ መቀጠል አለበት፡፡

ለዘመናት ሲጠየቁ የነበሩ የማኅበረሰብ ጥያቄዎች የቋንቋ፣ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ፣ የመሬት ፖሊሲ፣ የክልል፣ የድንበርና ሌሎችም ላይ ኅብረተሰቡን ያሳተፉ ቁርጥ ያለ ምላሽ የሚሰጥባቸው የተደራጀ አወቃቀርና ሥርዓቶችንም መዘርጋት የመንግሥትን ብቃት ማሳያ ከመሆንም በላይ የሕዝብ ጥያቄዎችን ላለማንከባለልና የግጭትም መንስዔ እንዳይሆኑም ከማሰብ አንፃር አዎንታዊ በመሆኑ የአዲሱ መንግሥት የቤት ሥራዎችም ሆነው መያዝ ይገባቸዋል፡፡

የመሪዎች ራዕይ እንዳለ ሆኖ ራዕዩንና ቃሉን ሊተገበሩና ሊያሠራጩ የሚችሉ ከልብ የተጠመቁና ወንጌሉን የተቀበሉ ደቀ መዛሙርት መኖርም የግድ ያደርገዋል፡፡ ቃሉ መደመር ተግባሩ ሌላ እንዳይሆንም በተለይ የመንግሥት ኃላፊነት ላይ ያሉና የሚሾሙ አመራሮች የመሪዎችን ራዕይ የሚጋሩና ወደ ተግባር ሊቀይሩ የሚችሉ መሆናቸውን እርግጠኛ መሆንም አስፈላጊ ነው፡፡ በሁለት ቢላዋ የመብላት ልማዳቸው የሚቋጭበት ጊዜም ሊያከትም ይገባል፡፡ በጎሳና በዘር ድልድል ከሚለገስ ሹመት ይልቅ በብቃትና ከአገርም አልፎ አኅጉራዊ ራዕይ ያላቸው ሹመኞች ማብዛቱ የአኅጉሩን ባያሳኩ እንኳ የአገሪቱ አንድነት ላይ የራሳቸውን አሻራ ማኖር የሚችሉበት አጋጣሚ ሊፈጥር ይችላል፡፡ አለበለዚያ በነበረው አካሄድ የኖረን ችግር መፍታት እንደ ዕብደት ይቆጠራል የሚለውን የኖረ አባባል መድገምም ይሆናል፡፡

አፍሪካ የራሷ የሆነ የኢኮኖሚ መዋቅር ልትከተል ይገባል ብለው የተነሱ እንደ ኡጃማ ያሉ አመለካከቶች በብዙ መለኪያዎች በጤና፣ በትምህርት፣ የዕድሜን ጣሪያ በመጨመር፣ የአገር አንድነትን በማስጠበቅ የመሳሰሉት አዎንታዊ ሚና እንደነበራቸው ታሪክ ያሳያል፡፡ ይህም አገር በቀል የኢኮኖሚ አካሄዶች በተገቢው ከተተገበሩ በማኅበረሰብ ሕይወት ላይ ያላቸው ውጤት አበረታች እንደሆነም ይመሰክራል፡፡ ከኢኮኖሚ ዕድገት ጋር ተያይዞ ያለው ክፍተት ዛሬም በአገራችን ላይ ምልክቶቹ ስላሉ (የዋጋ ንረት፣ ሥራ አጥነት፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና ዕዳ ወዘተ.) ከፖለቲካው እኩል ኢኮኖሚውንም እውነተኛ አገር በቀል ሆኖ ዕድገትን በሚያስቀጥል ሁኔታ ማዋቀሩም የሚቀጥለው መንግሥት ትልቁ የቤት ሥራም ሆኖ ይቀጥላል፡፡  የተፈጥሮ ሀብቶችን በአግባቡ ከመጠቀምና የኢኮኖሚው ማርሽ ቀያሪ እንዲሆኑ ማድረግም የኢኮኖሚው ሞተርና የእውነተኛ አገር በቀል አካሄድም ነው፡፡ ተፈጥሮን የማስዋብና መልሶ መገንባት አፍሪካውያን እስከ ኖቤል ሽልማት (Wanagari Mathai Green Belt Movement) ያገኙበት ታላቅ ገደል ከመሆንም ባሻገር፣ ለአፍሪካ ልማት ቁልፍ ሚና እንዳለው የታየበት በመሆኑም አሁን ያለው መንግሥት በጀመረው የአረንጓዴ አሻራ (Green Legacy) አቅጣጫ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም የሚጠበቅ ነው፡፡

በአጠቃላይ ከቃልም በላይ በድርጊት የሚገለጽ አኅጉራዊና አገራዊ የመሪዎች የአመራር ፍልስፍናዎች በአመራሩ ፖሊሲዎች ውስጥ መኖሩም በቁርጠኝነት ሊጤን የሚገባው ነው፡፡ ከአገር አልፎም አኅጉራዊ ዕይታን የማጎልበት አካሄድ ጥሩ ጅማሮ በአዲሱ መንግሥት ቀጥሎ አፍሪካ የራሷ ገንዘብ፣ የራሷ ጦር፣ ድንበር አልባና የጋራ ገበያ እንዲሁም ሌሎችም እንዲኖራት በሚደግፉ ጥምረቶች ላይ ግንባር ቀደም ሚና መጫወቱም ጠቃሚ ነው፡፡ በዲፕሎማሲው መስክም የታዩ ክፍተቶችን በመሙላት የአገር ገጽታ ግንባታን ማጎልበትም ዋነኛ አቅጣጫ መሆኑም አይቀሬ ነው፡፡ በተለይ ግን አፍሪካም ሆነ አገራችን ያላቸውን የኑሮ ዘይቤዎች፣ የማኅበረሰብ ልማዶች፣ የጋራ ዕሴቶች ላይ ያተኮሩ መድረኮች፣ የፖሊሲ መዋቅሮች፣ የትምህርት ፖሊሲዎች፣ የአመራር ሥርዓቶች (Leadership Codes) የግጭት አፈታት ባህላዊ ሥርዓቶችና ፍርዶች፣ የሥነ ጥበብ ሥራዎች መገንባትም የግድ ይሆናል፡፡ ሸክሙ ብዙ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ለአገር ሰላምን የማስፈን ሒደቱ በሁሉም ርብርብ ከዳር ደርሶ ዜጎች በሰላም የሚኖሩባት አገር መፍጠሩ በጋራ የሁላችንም አስተዋጽኦ የሚሆንም ነው ኡቡንቱ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles