Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉፐብሊክ ዲፕሎማሲን ለብሔራዊ ጥቅማችንና ለአገር ህልውና እንዴት እናጎልብተው?

ፐብሊክ ዲፕሎማሲን ለብሔራዊ ጥቅማችንና ለአገር ህልውና እንዴት እናጎልብተው?

ቀን:

በጌታቸው መኮንን

ዲፕሎማሲ ከወል ባህርይ አኳያ ዓላማና ይዘቱ በአገሮች/በመንግሥታት መካከል የሚካሄዱ ዘርፈ ብዙ የውጭ ግንኙነት እንቅስቃሴዎች የሚከናወኑበት የግንኙት ጥበብ ተጠቃልሎ የሚገለጽበት መሠረተ ሰፊ ፅንሰ ሐሳብ ሲሆን፣ አተገባበሩ ከሚከተላቸው ዓበይት አቅጣጫዎች አንፃር በሁለት ዋና ዋና መደዶች (tracks) ተከፍሎ የሚታይ እንደሆነ በጉዳዩ ላይ የተጻፉ ዋቢዎች በተመሳሳይ አኳኋን ያብራራሉ፡፡

ከዚህ አኳያ መደድ I (Track I) ዲፕሎማሲ ከጥንት ጀምሮ እስካለንበት ዘመን ድረስ ከፍ ሲል በተጠቀሰው ትርጓሜ መሠረት በመንግሥታት መካከል ሲካሄድ የቆየውንና በመካሄድ ላይ ያለውን ተለምዷዊ (መደበኛ) የግንኙነት መንገድ የሚመለከት ነው፡፡ መደድ II ዲፕሎማሲ ደግሞ ከዚህ ውጭ ያሉትንና እሰካለንበት ዘመን ድረስ በሰው ልጆች የሥልጣኔና የዕድገት ሒደት እየተፈጠሩ የተበራከቱትን ከላይ በተጠቀሰው ገዥ ትርጓሜ መንፈስ በአገሮች/በመንግሥታት (ዜጎቻቸውን ጭምር) መካከል የሚካሄዱ የተለያዩ የግንኙነት ዓይነቶችን (ፐብሊክ ዲፕሎማሲ፣ ኢኮኖሚክ ዲፕሎማሲ፣ ኮንፈረንስ ዲፕሎማሲ፣ ዲጂታል ዲፕሎማሲ፣ ፓርላሜንታዊ ዲፕሎማሲ…) የሚያጠቃልል እንደሆነ ይታወቃል፡፡

ምንም እንኳን የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ተግባራዊ እንቅሰቃሴ ለአገራችን እምብዛም እንግዳ ባይሆንም፣ የጋራ ግንዛቤ ለማሰጨበጥ የሚረዱ መሠረታዊ ነጥቦችን ማለትም ስለፐብሊክ ዲፕሎማሲ ጽንሰ ሐሳባዊ ምንነትና በፐብሊክ ዲፕሎማሲ ተፅዕኖ በመፍጠር ስኬታማ የሆኑ አገሮችን ከገለጽኩኝ በኋላ፣ ከዋነኛ ትኩረቴ አኳያ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ የኢትዮጵያን ህልውና ከማስጠበቅና የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች ለማራመድ የሚጠቅሙ ምክረ ሐሳቦችን እገልጻለሁ፡፡ ጥሩ ግንዛቤ እንደምታገኙበት ተስፋ አድርጋሁ፡፡

ፐብሊክ ዲፕሎማሲ የሚለውን ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ እ.ኤ.አ. በ1965 የተጠቀሙት ኤድመንድ ጉልዩን በአሜሪካ የተፍትስ ዩኒቨርሲቲ የዲፕሎማሲ ትምህርት ቤት ዲን ናቸው፡፡ ጉልይን በውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ቀረፃና ትግበራ ዜጋውን በማሳተፍ በሌላው አገር ሕዝብ ላይ መልካም ተፅዕኖ መፍጠር ይቻላል የሚል እምነት አላቸው፡፡ ከእዚሁ ጋር በተገናኘም ያለ መሣሪያ ተፅዕኖ የመፍጠርን (Soft Power) ወሳኝነት ከሚያቀነቅኑት ውስጥ የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ጆሴፍ ናይ ዋነኛው ናቸው፡፡ ፕሮፌሰር ናይ በዘመናዊው ዲፕሎማሲ የተሻለ መረጃ የሰጠ አሸናፊ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በኢኮኖሚም ሆነ በወታደራዊ ብቃት ማን ከማን ይበልጣል ብቻ ሳይሆን፣ በቂ መረጃ በመስጠት ቀድሞ አመለካከት መፍጠር የቻለው ማነው የሚለው በጣም ወሳኝ ሆኗል፡፡ የመጀመሪያ አስተሳሰብ ዘላቂ አስተሳሰብ የመሆን ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡ ተፅዕኖ ለመፍጠር ከሚያስችሉ መንገዶች ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ተጠቃሽ ነው፡፡

የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዘርፍ ተፅዕኖ ከሚፈጥርባቸው ውስጥ አንዱ ፖለቲካ ነው፡፡ በዚህም የሌላው አገር ሕዝብ፣ ፖለቲከኞች፣ ምሁራን፣ የተለያዩ ተቋማት ዘንድ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲውን አስመልክቶ አዎንታዊ አስተሳሰብ እንዲኖር ይረዳል፡፡ ሁለተኛው ማኅበራዊ ሲሆን የአገሩን ታሪክ፣ ባህል፣ ወግና የቱሪስት መስህቦች በሌላው ዘንድ እንዲተዋወቁ ያደርጋል፡፡ እንዲሁም በኢኮኖሚው መስክ ኢንቨስትመንት በመሳብ፣ ገበያ በመፍጠርና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማፋጠን አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ በፐብሊክ ዲፕሎማሲ ተፅዕኖ በመፍጠር ስኬታማ የሆኑ አገሮች ከዚህ በታች ተመላክተዋል፡፡

የቻይና ኢኮኖሚና ወታደራዊ ጥንካሬ በፐብሊክ ዲፕሎማሲው መስክ የመደገፉን አስፈላጊነት የመጀመሪያው ጠንሳሽ ፕሬዚዳንት ሁ ጂንታኦ ናቸው፡፡ በሰብዓዊ መብት አያያዝ የምትከሰሰው ቻይና ‹‹ስለራሷ መናገር አለባት›› (Talking Back) በሚል፣ ይህን ዘርፍ በተቋም ደረጃ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አቋቁማለች፡፡ ለዚህም ሁለት መንገዶችን ትጠቀማለች፡፡ አንደኛ የቤጂንግ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ በኢኮኖሚ ድጋፍ ላይ ያተኩራል፡፡ መንገድ፣ ባቡር፣ አውሮፕላን ማረፊያ፣ ወዘተ በሌላው አገር ሲገነባ ይህ ሥሌት ተወስዷል፡፡ ሁለተኛ በባህልና በመዝናኛ መስክ የቤጂንግ ኦሎምፒክ፣ የኮንፊሽየስ ትምህርት ቤት ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌላው ዓለም የሚስፋፉት ለዚህ ተግባር ነው፡፡

እ.ኤ.አ በ1947 ነፃነቷን ከተቀዳጀች ከሦስት ዓመት በኋላ በ1950 ህንድ የባህል ግንኙነት ምክር ቤት የተሰኘውን ተቋም መሠረተች፡፡ ተቋሙም በወቅቱ የተመሠረተው በሲቪክ ማኅበር መልክ ሆኖ ከህንድ መንግሥት በተሰጠው ሕጋዊ ፈቃድ፣ እንዲሁም የገንዘብና የማቴሪያል ድጋፍ በመታገዝ ነበር፡፡ የተቋሙ ዓላማዎችም ከሌሎች አገሮች ጋር የባህል ልውውጦችን ማካሄድና በህንድና በሌሎች አገሮች መካከል የጋራ መግባባት መፍጠር ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪም ምክር ቤቱ ለውጭ አገር ተማሪዎች በተለይም ከህንድ አጎራባች አገሮችና ከአዳጊ አገሮች ጭምር ለሚመጡ ባለሙያዎች የነፃ ትምህርት ዕድል መሰጠትን ያጠቃልላል፡፡  ከዚህም ሌላ ማዕከሉ በውጭ አገሮች ዩኒቨርሲቲዎች የህንድ የጥናት ማዕከላት እንዲቋቋሙና በተጓዳኝም ከልዩ ልዩ የጥናት ዘርፎች የተመረጡ ህንዳውያን ዶክተሮችና ፕሮፌሰሮችን ወደ ተለያዩ አገሮች በመላክ ስለህንድ ታሪክ፣ ፍልስፍናና የህንድ ቋንቋዎችን እንዲያስተምሩ የሚያደርግ ነው፡፡

በአፍሪካ ደቡብ አፍሪካውያን ለፐብሊክ ዲፕሎማሲ ሌላ አይደለም የኔልሰን ማንዴላን ተክለ ሰውነት ሳይቀር ይጠቀማሉ፡፡ ለ20 ዓመታት ያህል ደቡብ አፍሪካ ኖሩ የሚባሉትን ማህተመ ጋንዲን ሳይቀር እንደ ራሳቸው ይጠቀማሉ፡፡  የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኡቡንቱ (አንድነትና ትብብር ማለት ነው) በሚል ስያሜ የ24 ሰዓት የሬዲዮ ፕሮግራም አለው፡፡ ዲፕሎማቶች ብቻ ሳይሆኑ ምሁራን፣ ተማሪዎች፣ ባለሀብቶች፣ ወዘተ በውጭ ፖሊሲ ላይ ይከራከራሉ፡፡ በግብፅም ፒራሚዱም፣ ሲፊንክስም ሆነ ኦፔራው፣ ስዊዝ ካናልም ሆነ ናይል ለዚሁ ተግባር የሚውሉ ሲሆን፣ የአል አህራም ጋዜጣና የጥናት ኢንስቲትዩት፣ የካይሮም ሆነ የአልዓዛር ዩኒቨርሲቲ፣ እንዲሁም የቀድሞ ዲፕሎማቶችን የሚያቅፈው ካውንስል የሌትና የቀን ተግባር በፐብሊክ ዲፕሎማሲ የግብፅን ብሔራዊ ጥቅም ማስከበር ነው፡፡ በተለይም ግብፅ ዓባይ ላይ፣ ጥቅም ላይ፣ አሳሪውም ታሳሪውም መንግሥት የማይናወጥ የጋራ አቋም አላቸው፡፡ ምሁሩ፣ ተማሪው፣ ነጋዴው፣ አርቲስቱ፣ አትሌቱ፣ ጋዜጠኛው፣ ዘፋኙ፣ ሰዓሊው፣ ሼኩ፣ ቄሱ፣ ወዘተ እንደዚያው፡፡ ግብፅ በዚህ ዓመት በመጭው ጥቅምት ወር መጨረሻ ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ከተውጣጡ መሪዎችና ምሁራን ጋርም ሦስተኛውን የህዳሴ ግድብ ለማደናቀፍ የሚያስችል የውኃ ኮንፍረንስ እንደምታካሂድ መረጃዎች እየወጡ ነው፡፡

በተጨማሪም የ55 የአፍሪካዊያን ምሁራን ስብስብ ነኝ የሚል ቡድን በአፍሪካ ኅብረት ወይም በምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) በኩል፣ ቀደም ሲል ምዕራባውያኑ ሲገፉት የነበረውን የኢትዮጵያን መንግሥት ፓርላማችን ሽብርተኛ ቡድን ብሎ ከፈረጀው ሕወሓት ጋር ለድርድር እንዲቀመጥ የሚያስገድደውን የጣልቃ ገብነት ስትራቴጂ እየገፋው ነው፡፡ እኛም የግብፅንና የምሁራኑን አካሄድ ከወዲሁ ሊመክቱ የሚችሉ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ሥልቶችን መንደፍ ይጠበቅብናል፡፡ የሊሴ ገብረ ማሪያም ትምህርት ቤት፣ የጣሊያን የባህል ማዕከል፣ የብሪቲሽ ካውንስል፣ ጐቴ ኢንስቲትዩት  አዲስ አበባ የከተሙት የዜጎቻቸውንና የአገሮችን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር መሆኑ አይዘነጋም፡፡ አዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ የፓን አፍሪካን ስሜት የሚያስተጋባ የአፍሪካ የባህል ማዕከል ወይም ሚዲያ መፍጠር አያስፈልገን ይሆን? በጸሐፊው ዕይታ ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ቻይና፣ ኳታር ዓለምን ከተቆጣጠረው የአሜሪካና የእንግሊዝ አስተሳሰብና ትንተናን (Anglo-Saxon Narratives) ለመመከት የራሳቸውን ዓለም አቀፍ ሚዲያ አቋቁመዋል፡፡ ሌሎች ስለእኛ ባቀረቡት ትንተና እስከ መቼ እንፈረጃለን? ኢትዮጵያ ስለራሷ መናገር አለባት፡፡

የፐብሊክ ዲፕሎማሲ በኢትዮጵያ በተቋም ደረጃ አይከናወን እንጂ፣ ባልተደራጀ መልክ አልተካሄደም ማለት አይደለም፡፡ በአፍሪካዊያን ዘንድ አገራችን ያገኘችው ከበሬታ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የአትሌቶቻችንን የኦሎምፒክ አስደማሚ ድል፣ የሕዝብ ለሕዝብ ኪነት ሥምሪት፣ በአኅጉራዊና በዓለም አቀፍ መድረኮች ያላት ዲፕሎማሲያዊ ተደማጭነት፣ የአገራችን የሰላም ማስከበር ሚና፣ ወዘተ በመስኩ የተደረጉ የሚታዩና የሚዳሰሱ የፐብሊክዲ ፕሎማሲ እንቅስቃሴዎች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በመከላከያ ተቋማት ይሰጡ የነበሩ የፀረ ቅኝ አገዛዝ፣ የፀረ አፓርታይድ ወታደራዊ ሥልጠናዎች፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለአፍሪካዊያን ወገኖቻችን የሰጡት ነፃ የትምህርት ዕድል በፐብሊክ ዲፕሎማሲ መስክ ከነበሩት በጐ ጅምሮች ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በየሳምንቱ የሚወጣው ‹‹የአፍሪካ ቀንድ በሳምንቱ›› ኅትመት በውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ዙሪያ የሚያጠነጥን የቴሌቪዥን ፕሮግራም ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በተጨማሪም አገራችን ኢትዮጵያም ብሔራዊ ጥቅሟን በብቃት ከማራመድና ከማስጠበቅ አኳያ የፐብሊክ ዲፕሎማሲን ሥራ በአግባቡ በተደራጀና በተቀናጀ አኳኃን የማካሄድ ዓላማና ዕቅድ ያላት በመሆኑ፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካይነት የፐብሊክ ዲፕሎማሲ የልዑካን ቡድን ወደ ግብፅ አምርቶ መመለሱ አንድ ዕርምጃ ነው፡፡ ጉብኝቱ ‹‹ከወዮላችሁ›› ወደ ‹‹እንገናኝና እንወያይ፣ እንተባበር፣ መፍትሔ በጋራ እንፈልግ…›› ስሜት መሸጋገሩን ያሳየ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በካርቱም ዩኒቨርሲቲ በናይል ላይ ውይይት መካሄዱ፣ ኢትዮጵያ በምዕራብ አፍሪካ በተከሰተው ኢቦላ ምክንያት የጤና ባለሙያዎችን መላኳ ዲፕሎማሲያዊ ትርጉሙ ግዙፍ የሆነ ተግባር ነው፡፡ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ካውንስል በመመሥረት በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮችና ሁነቶች ላይ በኤምባሲዎች አማካይነት በመካፈል፣ የባህል ማዕከላት በማቋቋም (ኒው ደልሂ፣ ብራስልስ) የከተሞች የተቋማትና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግንኙነቶችን በማመቻቸት ጉልህ እንቅስቃሴ አድርጋለች፡፡ በአሁኑ ወቅትም የነጩ ፖስታ ጎርፍ ለነጩ ቤተ መንግሥት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ በግለሰቦችና በአሜሪካ ኢትዮጵያ ዜጎች የሕዝብ ጉዳዮች ኮሚቴ ደረጃ እየተከናወነ ያለው ተግባር ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡

በሌላ በኩል ግን የውጭ ትልልቅ ሚዲያዎችን ጉድኝቶች፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችና ተቋማት (think tanks) በሚፈለገው መጠን አለመጠቀም ወይም አለመቅረብ ድክመት እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል። የ‹‹think tank››ን ቁጥር ስንመለከት በዓለም ላይ ስምንት ሺሕ ሁለት መቶ አርባ ስምንት በላይ ‹‹think tanks›› እንዳሉ ‹‹Think Tanks and Civil Societies Program (TTCSP’s) Global (Think Tank) የመረጃ ቋት ያሳያል፡፡ በዓለም ላይ ካሉ የልህቀት ማዕከላት ውስጥ ከሰሃራ በታች ባሉ አገሮች የሚገኙት ስድስት መቶ አሥራ ሁለት ናቸው፡፡ ከተመረጡት ጋር መሥራት በአገራችን ላይ ሊፈጠሩ የሚችሉ አሉታዊ ትርክቶች ለመቀነስና የአገራችንን ገፅታ ግንባታ ለማጎልበት ይጠቅማል፡፡ ተፅዕኖ ለመፍጠርም ያስችላልና፡፡ እንደ አዲሰ የተቋቋመው ስትራቴጂያዊ ጉዳዮች ኢንስቲትዩት የተባለው ‹‹think tank›› በመጀመሪያ በአገራችን ካሉ የምርምር ተቋማት ‹‹think tank›› አብሮ በጣምራ በመሥራት፣ ከሌሎች የዓለም አቀፍ ‹‹think tanks›› ጋር ለመሥራት አጋርነትን እሴቱ በማድረግ ተፅዕኖ ፈጣሪ ለመሆን ራዕይ ሰንቆ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡

ፐብሊክ ዲፕሎማሲ የኢትዮጵያን ህልውና ከማስጠበቅና የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች ለማራመድ ከዚህ የሚከተሉት ምክረ ሐሳቦች ገቢራዊ ቢደረጉ መልካም ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ እነዚህም በተለያዩ መስኮች ስለኢትዮጵያ አዎንታዊ ትርክት መፍጠር፣ ትርክቶቹን በተከታታይና በሰፊው እንዲሠራጩ መሥራት፣ ከወዳጅ አገሮች ጋር ዘላቂነት ያለው ስትራቴጂካዊ ትስስርና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ ጥምረት (alliance) እንዲፈጠር ማስቻል፣ ደጋፊ የዓለም አቀፍ ትስስር እንዲኖር ማገዝ፣ ከሌሎች አገሮች ትምህርትና ምርምር ተቋማት ጋር የምክክር መድረኮችን ማመመቻቸት፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችና ተቋማት (think tanks)፣ እንዲሁም ከትልልቅ የውጭ ሚዲያዎች ጋር ጠንካራ ግንኙነት መመሥረትና በጋራ መሥራት፣ ከሌሎች አገሮች የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድኖች ጋር የሥራ ጉድኝት መፍጠርና በዚህ ዓመት አዲስ የመሚሠረተው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፓርላሜንታዊ ዲፕሎማሲ ተግባራትን እንዲያከናውን ማድረግ፣ በአጭር፣ በመካከለኛና በረዥም ጊዜ ምን መደረግ እንዳለበት የሚገልጽ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስትራቴጂ መንደፍ፣ ለዚህም በቂ በጀትና ሥራውንም ሴራውንም የሚያውቅ ባለሙያ አስፈላጊ መሆኑን በፅኑ ማመን፣ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድንን አቅም ለማጎልበት የሚያግዝ የአቅም ግንባታ መርሐ ግብር ሥልት ቀይሶ ያለማሰለስ ተግባራዊ ሊደረግ የሚችልበትን ሁኔታ ማመቻቸት፣ በአገራችን ተቀማጭ የሆኑ የውጭ አገር የዜና አውታሮች ዘጋቢዎች በውጪው ዓለም ዘንድ ያላቸውን ተዓማኒነትና ተቀባይነት ከግምት ውስጥ በማስገባት የተለየ ትኩረት ስጥቶ ማቅረብ፣ በተለያዩ አግባብነት ያላቸው ኦፊሴላዊ ሥነ ሥርዓቶች ላይ እንዲገኙ መጋበዝ፣ የወዳጅነትና የመተመማን ስሜት መፍጠር፣ በተለያዩ ምክንያቶች (በስደት ወጥተው፣ በጉዲፈቻ ተወስደው፣ ውጭ አገር ተወልደው አድገው፣ በዓለም አቀፍ ድርጅቶችና በልዩ ልዩ መሰል ተቋማት ተቀጥረው፣ ወዘተ) ከአገራቸው ርቀው ዜግነታቸውን ቀይረውም ሆነ ሳይቀይሩ የራሳቸውን የፖለቲካ አመለካከትና እምነት በማራመድ ጭምር ባሉበት የውጭ አገር ሥራና ኑሮዋቸውን ያደረጉና ለአገርና ለወገን ጠቃሚ አስተዋፅኦ ሊያበረክቱ የሚችሉ ባለሙያዎች (ምሁራን፣ የኪነ ጥበብ ሰዎች፣ ወዘተ…) በጠቅላላ ከግላዊ የአመለካከት ልዩነቶች ባሻገር፣ የወል ባህርይ ባላቸው መሠረታዊ የአገር ጉዳዮች ዙሪያ እንዲሰባሰቡ ለማስቻል ብርቱ ጥረት ማድረግ፣ ከኢትዮጵያ ሄደውም ሆነ ውጭ አገር ተወልደው ያደጉ፣ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያላቸው ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሆኑ ወጣቶች ከአገራቸው ጋር ያላቸው ትስስር እንዳይላላ የጋራ መግባቢያ የሆኑትን ቋንቋዎች ባሉበት ሊማሩ የሚችሉበትንና ከአገራቸው ታሪክና ባህል ጋር ሊተዋወቁ የሚችሉበትን ሁኔታ መፍጠር፣ ከመካከላቸው ከፍተኛ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ያሉና ፍላጐት ያላቸው ወጣቶች በኢትዮጵያ ላይ የምርምር ሥራቸውን እንዲሠሩ አስፈላጊ ሁኔታዎችን ማመቻቸት፣ በአገር ቤት የነፃ ትምህርት ዕድል ሊመቻችላቸው የሚፈልጉ ካሉ ተግባራዊ ሊደረግ የሚችልበትን ሁኔታ መፈተሽ፣ እንዲሁም እነዚህ በውጭ አገር ነዋሪ የሆኑ ወጣት ተማሪዎች የዕረፍት ጊዜያቸውን ኢትዮጵያ ውስጥ የሚያሳልፋባቸው ‹‹Summer Camps/Youth Camps›› ሊቋቋሙ የሚችሉበትን ሁኔታ በማጥናት ተፈጻሚ ሊደረግ የሚችልበትን መንገድ መፈለግ፣ ወገናዊ አለኝታነታቸውን ኮትኩቶ በአስተማማኝ መንገድ ማሳደግ በእጅጉ ጠቃሚ ይሆናል፡፡

በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘመን የፐብሊክ ዲፕሎማሲ የዲጂታል ዲፕሎማሲን ይጠቀማል፡፡ የመረጃ መኖርና የመረጃው ተደራሽነት ‹‹የኃይል ዲፕሎማሲን›› ሁሉን አድራጊነትና አይተኬነት ቀንሶታል፡፡ ይህ አስተሳሰቦችን በማሳመን የመለወጥ ፖለቲካ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተፈላጊ በሆኑ የማኅበራዊ ሚዲያዎች በዕውቀት መጠቀም የግድ ይላል፡፡ ዲፕሎማሲና ቴክኖሎጂ ተመጋጋቢ ሆነዋል፡፡ ከዓለም ሕዝብ አብዛኛው ታዳጊና ወጣት መሆኑና ይህም የኅብረተሰብ ክፍል የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ በመሆኑ፣ ቴክኖሎጂ መጠቀም ለፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስኬት አስፈላጊ ነው፡፡ ሶሻል ሚዲያን ተጠቅሞ የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ ተፅዕኖ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ይህም መሆን ያለበት በብልኃት፣ በጥበብና ሥነ ምግባርን በጠበቀ መንገድ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት መንግሥት እያሰበ ያለውን ተመላላሽ አምባሳደር (Laptop Ambassador) ጥቅምና ጉዳቱን መለየት አሰፈላጊ ነው፡፡ ምክንያቱም ከመንግሥታት በተጨማሪ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተዋናዮች (Non-state Actors) በፖለቲካውና በዲፕሎማሲ ገበያ፣ በወታደራዊው ሽኩቻ፣ እንዲሁም በኢኮኖሚያዊ መሳሳብ ሚና ስላላቸው የሚታሰበው ተመላላሽ አምባሳደር (Laptop Ambassador) የመንግሥት ለመንግሥት ግንኙነቱን ሊሸፍን ይችል ይሆናል እንጂ፣ መንግሥታዊ ካልሆኑ የዲፕሎማሲ ተዋንያን ጋር የሚኖረውን ዲፕሎማሲያዊ መስተጋብር ወስኖ ጥቅማችንን እንዳይገድበው ከወዲሁ መጠንቀቁ አይከፋም፡፡ አገሪቱ አሁን ያሏትን ወደ 60 የሚጠጉ የኤምባሲና የቆንስላ ጽሕፈት ቤቶች እንደገና በማዋቀርና ቁጥራቸውን ለመቀነስ የታሰበው መንገድ መልካም ቢሆንም ማለት ነው፡፡

መደምደሚያ

በተግባርና በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ ከቀደምት ዓመታት አነሳሱ ጀምሮ በሒደት እያደገ፣ እየተሰፋፋና ሥር እየሰደደ የመጣው የፐብሊክ ዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ፣ በተለይ በአሁኑ ጊዜ አገሮች የውጭ ፖሊሲያቸውን በሌሎች ወገኖች ዘንድ ተደማጭነት እንዲኖረው ለማድረግ ከተለምዷዊው ዲፕሎማሲ ጎን ለጎን የተጠናከረ ጥረት የሚያደርጉበትና ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ የተቀነባበረ ትግል የሚያደርጉበት ዓይነተኛ መሣሪያቸው እንደሆነ በገሃድ እየታወቀ የመጣ እውነታ ነው፡፡ አገሮች ብሔራዊ ጥቅሞቻቸውን በተሟላ መንገድ ለማራመድ የፐብሊክ ዲፕሎማሲን ሥራ ማካሄድ አማራጭ የሌለው መሆኑን በመገንዘብ፣ በዚህ አቅጣጫ ያለ ማሰለስ በስፋት በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡

ፐብሊክ ዲፕሎማሲ የአንድ ቀን ተግባር አይደለም፡፡ ውጤቱም በአንድ ጊዜ አይገኝም፡፡ ግቡ አመለካከት መለወጥ ነው፡፡ አንድ አገር ጠንካራ ኢኮኖሚና የመከላከያ ሠራዊት ለመገንባት እንቅልፍ የምታጣውን ያህል እልህ አስጨራሽ ነው፡፡ ምክንያቱም ወታደራዊ የበላይነት በሐሳብ የበላይነት ካልተደገፈ የትም መድረስ አይቻልም፡፡ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ሲፈለግ የሚከናወን ሳይፈለግ የሚተው ምርጫ አይደለም፡፡ የመንግሥት ለመንግሥት ግንኙነት ከሕዝብ ጋር በሚደረግ ግንኙነት መታገዝ አለበት፡፡ አገራችንም በዚህ መጓዝ ይኖርባታል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በውጭ ፖሊሲና ዲፕሎማሲ የማስተርስ ዲግሪ፣ እንዲሁም በመልቲ ካልቸራሊዝም የማስተርስ ዲግሪ ሲኖራቸው፣ በስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ኢንስቲትዩት ተመራማሪ ናቸው፡፡ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...