በገነት ዓለሙ
ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ የ2013 ዓ.ም. መስከረም ሲጠባ እንደተመኘነው የሰላምና የብልፅግና ዓመት ሆኖ አላለፈም፡፡ 2013 ዓ.ም. ውስጥ ያጋጠመን፣ ያናወጠንና የተጠናወተን ለብዙ ጊዜ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ችግር ሁሉ ሰበብና ምክንያት፣ መጋቢት 2010 ዓ.ም. የተጀመረው ዓለምን ጭምር ያስደመመው ለውጥ ውስጥ የተፀነሰና በዚያውም ላይ በሰፊው የተጠነሰሰ ተቃውሞ መሆኑ አሁን እያደር፣ እየዋለ ሲያድር እንደ እውነትና ንጋት ይበልጥ እየጠራና እየተረጋገጠ መምጣት ይዟል፡፡ መሰንበቻችንን የ2014 ዓ.ም. መስከረም እንደጠባ የመጀመርያው ሳምንት ውስጥ አደባባይ የወጣው ‹‹የሕወሓት ጽሕፈት ቤት [የ] መስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ሰነድ፣ ውሸት ነው፣ ‹የጠላት› ፍብረካና ፈጠራ ነው›› ካልተባለ በስተቀር፣ የሚገርምና የሚያስደነግጥ፣ የሚያስፈራራም ተጨማሪ ማረጋገጫና ማስረጃ ብቻ ሳይሆን የተፈጸመውና የተደረገው፣ የተጠረጠረውና የተፈራው ሁሉ የእምነት ቃል ጭምር ነው፡፡
የሕወሓት ጽሕፈት ቤት መስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ብሎ የፈረመበት፣ ‹‹የትግል ልዩ ምዕራፍ ዕድገቶችና የመከታችን ቀጣይ ስትራቴጂዎች፣ ሥልቶችና አቅጣጫዎች›› የሚል ርዕስ የሰጠው ‹‹ቁጥር ሁለት›› ብሎ የሰየመውና ሌላ መነሻ ሰነድ ስለመኖሩም በይዘቱ መግቢያ ላይ ጭምር የሚነገርለት፣ ‹‹ያለፈው ጊዜ ጽሑፋችን›› ተከታይ ነው፡፡ እሱን ይህ ጽሑፍ የሕወሓት ሰነድ ነው ወይ? ቋንቋው ለምን አማርኛ ሆነ? ጽሑፉ/ሰነዱ ‹‹አፈትልኮ›› ወጥቶ አሁን እኛ ጋ ደርሶ መወያያ ወይም መተዛዘቢያም ለመሆን ለምን ከመስከረም 2013 እስከ መስከረም 2014 ዓ.ም. ያለውን ጊዜ ወሰደ? ‹‹ቁጥር አንድ››ስ የታለ? የሚሉትን ጥያቄዎች መመለስ ቻልንም፣ አልቻልንም 2013 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ላይ ከባድና ግፈኛ ጥቃትና ክህደት የተፈጸመበት ዓመት መሆኑን፣ ከዚህ ‹‹ሰነድ›› ውጪ ብቻቸውን፣ በገዛ ራሳቸውና ራሳቸውን ችለው ያሉና የሚኖሩ ነባራዊ ማስረጃዎች ሞልተዋል፣ ተርፈዋል፡፡ ያጎደለንና እስካሁን ባካሄድነው የሸንጎና የአደባባይ ውሎ ላይ ‹‹ያስረታንና›› ክፉኛ የጎዳን፣ የደረሱብንንና የምናውቀውን ስለድርጅታችን ሰንደን እዩልኝ ስሙልኝ አለማለታችን ወይም ይህን ማለት አለመቻላችን ነው፡፡ ወይም በዚህ ረገድ በተቃራኒ ወገን በመበለጣችን ነው፡፡
ሴፕቴምበር 10 ቀን፣ በእኛ ጳጉሜን 5 ቀን 2013 ዓ.ም. ‹‹የኢትዮጵያንና የኤርትራን ሕዝብ›› እንቁጣጣሽ መልካም አዲስ ዓመት ያሉት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን መስከረም 7 ቀን የፈረሙት ፕሬዚዳንታዊ ትዕዛዝ (የተባለ የሕግ ዓይነት)፣ የአገሪቱ የገንዘብ ሚኒስቴር ከዚያው አገር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በመመካከር በኢትዮጵያ ላይ በፕሬዚዳንታዊ ትዕዛዙ በክፍል ሁለት (ሴክሽን 2) በብዙ ንዑስ አንቀጾች የተዘረዘሩትን፣ አንዱን ወይም ከአንድ በላይ የሆኑ ማዕቀቦች እንዲቀጥሉ ያዛል፡፡ ለጊዜው አሁን እዚህ ላይ የማዕቀቡን ‹‹ፍትሐዊነት›› የፍረጃንና የዳኝነቱን አግባብነት፣ ወዘተ አላነሳም፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ላለ አገር ከሰማይ ከምድር የከበደ አደጋና ጥፋት ማስከተል የሚችሉት እነዚህ የ‹‹ቅጣት›› ዕርምጃዎች በእንግሊዝኛ ‹‹ሳንክሸንስ›› የሚባሉት ናቸው፡፡ ‹‹ሳንክሸን›› የሚባለውን ቅጣት ዛሬ በአማርኛችን አሻሽለን ወይም አማርኛችን ‹‹ተሻሽሎ›› ማዕቀብ ብሎት ነው እንጂ፣ የአገራችን ፖለቲካ ወይም የውጭ ግንኙነት ቋንቋ ሳንክሽንን በንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ዘመን ሲጠራው የኖረው ጭቆና ብሎ ነው፡፡ ዛሬም ኢትዮጵያ ላይ እንዲወሰድ በፕሬዚዳንት ባይደን ‹‹ኤክዝኪዩቲቭ ኦርደር›› የተወሰኑት የማዕቀብ ዓይነቶች ጭቆና መባል የሚያንሳቸው ናቸው፡፡
ጭቆናው/ማዕቀቡ ከሚጣልባቸው በፕሬዚዳንታዊ ትዕዛዙ ክፍል አንድ ኤ ሥር ከተዘረዘሩት ሰባት የጥፋት ዓይነቶች ውስጥ ለምሳሌ የመጨረሻዎቹ ሁለት በቅደም ተከተል (6) ዴሞክራሲያዊ ሒደቶችን ወይም ተቋማትን፣ (7) የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት የሚያሰናክሉ ድርጊቶችና ፖሊሲዎች ናቸው፡፡ የአሜሪካ መንግሥት ለጣለው/ለሚጥለው ማዕቀብ ወይም ጭቆና መነሻና ምክንያት የሆነው፣ አሁንም ለጊዜው የማዕቀብ አድራጊውን ባለመብትነት ትተን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የደረሰው ወይም ደረሰ የተባለው የሰብዓዊነትና የሰብዓዊ መብቶች ቀውስ ነው፡፡ ይህንን ‹‹ሒውማኒቴሪያን እና ሒውማን ራይትስ›› ቀውስ ምን አመጣው? ሁለት ሰነዱ ውስጥ የተጠቀበሱ፣ ሰነዱም ባይኖር ሰነዱ ውስጥ ባይጠቀሱም ከሰነዱ ውጪ ራሳቸውን ችለው ያሉና የሚኖሩ ቁም ነገሮችና ፍሬ ነገሮች አሉ፡፡ አንዱ ምርጫ ነው፡፡ ሁለተኛው የኢትጵያን መከላከያ የሚመለከተው ጥቃትና አደጋ ነው፡፡
‹‹ምርጫ›› ለኢትዮጵያ ብርቅና አዲስ ነገር ሆኖ አያውቅም፡፡ በ2010 ዓ.ም. የመጣው ለውጥ ግን የተቀጣጠለውና የተጀመረው የኦባማ/ባይደን አስተዳደር እንደሚያውቀው፣ በተለይም ደግሞ ወይዘሮ ሱዛን ራይስ የምርጫ 2007 ውጤት፣ ስኬትና ዴሞክራሲያዊነት ‹‹የነገረ እናት› ሆነው በወቅቱ በዓለም ፊት እንደመሰከሩት፣ በዚህ ምርጫ መቶ በመቶ ያሸነፈው ፓርቲ በ2008 ዓ.ም. መስከረም ወር መጨረሻ ላይ በመሠረተው መንግሥት ላይ ኅዳር የጀመረው የሕዝብ ተቃውሞ ከፍቶና ገፍቶ መጥቶ ነው፡፡ ለውጡንና ሽግግሩን ለማምጣት ከ2008 ዓ.ም. ኅዳር ጀምሮ እስከ መጋቢት 2010 ዓ.ም. ያለውን ጊዜ ቢወስድም፣ ለውጡን ያመጣው ተቃውሞ ግን መቶ በመቶ የሕዝብ ድምፅ አሸናፊ የተባለው ፓርቲ መንግሥት በመሠረተ በሁለት ወራት ውስጥ ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ‹‹ምርጫ›› እና የሕዝብ ይሁንታና ፍላጎት ተገጣጥመው አያውቁም የሚባለው በዚሁ ምክንያት ነው፡፡
በዚህ ምክንያት ከለውጡ በኋላና በሽግግሩ ሒደት ውስጥ የሚደረግ ምርጫ የሚጨነቀውና የሚጠበበው ጊዜ በመቁጠርና በማክበር ላይ ሳይሆን፣ ምን ዓይነት ዝግጅቶችን አሟልቶ፣ የትኞቹን ቅድመ ሁኔታዎች አስቀድሜ አሳክቼ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ላድርግ ብሎ ዴሞክራሲን የማደላደል ሥራዎች ውስጥ ይመደባል፡፡ ከዚህ አንፃር የምርጫ 2012 ታሪክ፣ ወግና ንትርክ በመላው ዓለም የታወቀ ነው፡፡ ድንገት ኮቪድ-19 መጥቶ ዋናውን የዴሞክራታይዜሽን ጉዳይ በቀጥታ፣ በግልጽና ፊት ለፊት ተጋፍጠን፣ አፍረጥርጠን እንድንመልሰው ሰበብ ሆኖ ማለፊያና መሹለኪያ ሰጥቶን ዋናውን ጉዳይ አድበስብሰን እንጂ፣ ጥያቄው ኮቪድ-19 ያረዘመው የአምስት ዓመት የጊዜ ወይም የሞት ቀጠሮ አይደለም፡፡
ከዚህ መሠረታዊ የአንድ አገርን ድኅረ ግጭት ምርጫ ቅደም ተከተሎች የመሰደርና የማደላደል፣ እንዲሁም የምርጫን ቀን በመቁረጥ (እነዚህ ሁለቱን ‹Election Sequencing and Timing› ይሏቸዋል) ጉዳይ ጋር፣ ምናልባትም ከዚህም በላይ የምርጫ ሥራና ሥልጣን የመንግሥት ባለመብት የሥልጣን አካል ጉዳይ አለ፡፡ ይህና ተመሳሳይ ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች በተለይም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በማፍረስ ወንጀል መከሰስ ‹‹ብሔራዊ ስፖርቱ›› ለነበረ፣ እንዲሁም ‹የገዛ ራስህን ሕገ መንግሥት ራስህ ማክበር አልቻልክም› የሚል ተቃውሞ ቀስፎ ይዞት ለኖረ ገዥ ፓርቲ በጭራሽ ሊጠፉት/ሊሳሳትባቸው የማይገቡ ርዕሰ ጉዳዮች ናቸው፡፡ በሕገ መንግሥቱ ሆኖ መብቱንና ጥያቄውን የሚያስከብርና የሚያቀርብ ወገን (ፓርቲም ይሁን ግለሰብ ወይም ሌላ ድርጅት) የፌዴራሉን መንግሥት የምርጫም ሆነ የመከላከያ ሥልጣን እነጥቃለሁ ሊል አይችልም፡፡ በሁለቱም ጉዳዮች የሆነው ግን ይህ ነው፡፡ ከምርጫው ጉዳይ እንጀምር፡፡ የምርጫውን የብቻ ዕርምጃ በሕገ መንግሥታዊ ማዕቀፍ ውስጥ መከላከልና ‹‹መመከት›› ቀርቶ በተያያዘው የድጥ ጉዞ በዚያው አዳላጭ መንገድ ውስጥ ከድጡ ወደ ማጡ ገብቶ ስለ‹‹ዲፋክቶ ሀገር ላይ›› በኩራት ያወራል፡፡ ‹‹በኢ-አገራዊነት ውስጥ [ሆኖ] የአገራዊነት (ዲፋክቶ) ግንባታ… ነክሰን መፈጸም ይገባናል ይላል፡፡ ለምን በሙሉ እንዳለ አንጠቅሰውም፡፡
ሁሉን አቀፍ ተቋማዊ አቅም የገነባች ትግራይ (ዲፋክቶ ትግራይ)
‹‹ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን ለማፍረስ የክልሎች ሉዓላዊ ሥልጣን ነጥቆ አገርን እያተራመሰ የሚገኘውን የዓብይን ቡድን በፅናትና በጥንካሬ በመመከት፣ የራስን ዕድል በራስ የመወሰንና አስተዳደር መብቶችን ለማንኛውም ኃይል አሳልፈን እንደማንሰጥ፣ ከጠላት ጋር ግንባር ለግንባር የሚያስተናንቀን የምርጫ ጉዳይም ቢሆንም ይህንን መክተን ምርጫውን አካሂደን፣ ሕጋዊ መንግሥታችንን መሥርተን፣ ብቸኛው ሕገ መንግሥታዊ ክልል ሆነን፣ በከፊል አገራዊነት (ዲፋክቶ) ክልል ውስጥ ነው ያለነው፡፡ በዚህ መሠረት የክልላችን የተለያዩ ተቋማዊ አቅሞችን ብዙዎቹን ጉዳዮች ራሱን ችሎ እያሳለጠ ቆይቷል፡፡ በትግራይ ካስቀመጥናቸው ዕቅዶች/ትንቢቶችን የዲፋክቶ ስቴት ሒደት ተጠናክሮ መጥቷል፡፡
‹‹በዚህ መሠረት የትግራይ መሠረታዊ ተቋማዊ አቅማትን በዚህ ቅኝት እየተመራ ጎልብቶ እንዲወጣ፣ በተጨባጭ ጥናትና ዝርዝር የሥራ ዕቅድ ተንተርሰን መሥራት አለብን፡፡
‹‹ከላይ እስከ ታች የሚኖረን አደረጃጀትም ከዚሁ የሚመነጭና ይህንን እንዲያገለግል ማድረግ፣ በተለይ በፀጥታና ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳይ ዙሪያ ከቀረጥና ግብር መሰብሰብ፣ ሦስተኛ ወገን ግንኙነት፣ እንዲሁም ንግድና ኢንቨስትመንት፣ መገናኛ ብዙኃንና የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን እያሟላን የምንሄድበትን እነዚህን በሙሉ ግምት ውስጥ ያስገባ የትግራይ ሕገ መንግሥት በሙሉ ጥናትና ዕውቀት በመመሥረት የሚያስተካከልበትን ሁኔታ መፍጠር፡፡ ይህ ማስተካከያ ሁለት መንገድ ሊኖረው ይችላል፡፡
‹‹በቀጣይ የሚፈጠረው አስተማማኝ ዘላቂ ጉዞ ጋር ሊያያዝ (ሊቆራኝ ይችላል፡፡ ወይም ደግሞ አሁን ባለው ፌዴሬሽን ሥር በመሆን የቀደመውን ማስተካከልም ይቻላል፡፡ ወጣም ወረደ በኢ-አገራዊነት አጥር ውስጥ ሆነን ነገር ግን የአገራዊነት (ዲፋክቶ) ግንባታ የሚሳለጥበትን ተቋማዊ ግንባታ ላይ ጠንክረን) ነክሰን መፈጸም ይገባናል፡፡››
ስለመከላከያም ሰነዱ ምን እንደሚል እንመልከት፡፡ ሰነዱ በአገራዊ ሁኔታዎች [ውስጥ} የተፈጠሩት ያላቸውን አዳዲስ ክስተቶች›› በሚገልጽበት ክፍሉ…
ደጋግሞና በመላ ጽሑፉ ውስጥ ጠላት ብሎ የሚጠራውን ለውጡን የሚመራውን መንግሥት በሁሉም መልክና ዘርፍ ውድቀት እያጋጠመው እንደሆነ፣ መውደቂያውም እንደተቃረበና የቀረው አንድ ሐሙስ መሆኑን፣ ሌላው ቀርቶ ዕድሜውን የሚያራዝምበት የፀጥታ መዋቅሩ/መከላከያውም ላይም ቢሆን ሕዝብ እምነት እያጣ፣ እያገለለው መሄዱን ይገልጽና ለማንኛውም ግን የመከላከያው ኃይል ‹‹ሊሠራበት›› ይገባል ይላል፡፡ ‹‹ሁሉንም ዓይነት አማራጭ ተጠቅመን የዚህ ኃይል [የጠላት ኃይል] መሣሪያ ሆኖ እንዳይቀጥል ማድረግ አለብን፤›› ሲል ወስኗል፡፡ ተጨማሪ እንጥቀስ፡፡
‹‹ይሁን እንጂ ጠላት በዚህ ረገድ ያለው አቅም ገና አልተዳከመም፡፡ ሁሉንም ትቶ ኃይልን ተጠቅሞ ነው ሁኔታዎቹን ለመቀየር እየጣረ የሚገኘው፡፡ እርግጥ ነው ጠላት ህልውናውን ጠብቆ እንዲቆይ እያደረገው ያለው የፀጥታና ደኅንነት መዋቅር ነው፡፡ ቀጣይ ዘላቂ ህልውናውን ለማደላደል ሲል በፀጥታ መዋቅር ዙሪያ ትልቁን ዝጅግጅት እያደረገ ነው፡፡ የቆየው የአገር መከላከያ ኃይል በተለይ በትግራይ ያለውንና የተላመደውን ኃይል አድርግ የተባለውን ሊያደርግ አይችልም ብሎ በጥርጣሬ እየተመለከተ በአዲስ ኃይል ለመተካት እየሞከረ ነው፡፡ በአገር ደረጃም የነበረውን ኃይል ለመቀየር እጅግ በጣም ብዙ ቁጥር ያለው አዲስ ኃይል ወደ ማሠልጠኛ ማስገባት ጀምሯል፡፡ ቀደም ሲል ማደራጀት የጀመረውን የሪፐብሊካን ኃይልም እያጠናከረው ነው፡፡ በኦሮሚያ ያለው ልዩ ኃይልም በሁሉም መልኩ እንዲታጠቅና እንዲጠናከር እያደረገ ነው፡፡ በአማራም ተመሳሳይ ሥራዎችን እየሠሩ ነው፡፡ የኢሳያስ ኃይልም ቀላል የማይባል ኃይል ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ አድርጓል፡፡ በሥልጠና፣ በስለላ፣ በሰው ኃይል ሥምሪት እየተደረገ ያለው መደጋገፍ ጠላት ሌላው አቅሙ ወይም ችሎታው ከፍ እንዲል የሚያደርግ ነው፡፡ ከዚህ ተነስተን ጠላት በወታደራዊ ድጋፍ በኩል ገና አልተዛባም/አልተዳከመም፡፡ እዚህ ላይ ነው የተንጠላጠለው፡፡ እርግጥ በሌሎቹ ዘንድ ያለው ለውጥ በዚህ ወታደራዊ ክንፍ በኩልም የሚወሰን የሆነው የኃይል ሚዛን መቀየር ካለበት ግን በፖለቲካዊ፣ በኢኮኖሚዊና በዲፕሎማሲያዊ ሒደት የሚያጋጥሙ መዛባት በወታደራዊ ክንፍ በኩል ተመሳሳይ ውጤት/ክስተት መምጣት ከቻለ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ረገድ ወሳኝ ሥራ ይጠይቀናል፡፡ ይህንን ለማድረግ ከሁሉም በፊት ሊሠራበት የሚገባው የመከላከያ ኃይል ነው፡፡ ሁሉንም ዓይነት አማራጭ ተጠቅመን የዚሁ ኃይል መሣሪያ ሆኖ እንዳይቀጥል ማድረግ አለብን፡፡››
ይህ የተባለው ገና አሁን በዚህ ዓመት በመስከረም ወስጥ ያገኘነው የመስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም. የሕወሓት ሰነድ ነው፡፡ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ግን አንድ አስደንጋጭ ነገር ሰምተናል፡፡ ይህንን የሰማነው በዚያው ዕለት ከመንፈቀ ሌሊት በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በፌስቡክ ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ነው፡፡
‹‹ሕወሓት በትግራይ በሚገኘው የመከላከያ ካምፕ ላይ ጥቃት አድርሷል፡፡ ሰሜን ዕዝንም ለመዝረፍ ሙከራ አድርጓል፡፡ ይህ ሠራዊት ከሃያ ዓመታት በላይ የትግራይን ሕዝብ ሲጠብቅ የቆየ ሠራዊት ነው፡፡ በቦታው የሚገኘውም የትግራይን ሕዝብ ከጥቃት ለመከላከል ነው፡፡ ሕወሓት ግን እንደ ባዕድና እንደ ወራሪ አገር ሠራዊት ቆጥሮ፣ የመከላከያ ሠራዊቱን ለመምታትና ለመዝረፍ ተነስቷል፡፡ በዳልሻህ በኩልም ጦርነት ከፍቷል፡፡
‹‹መንግሥት የትግራይ ሕዝብ እንዳይጎዳ በማሰብ፣ ጦርነት እንዳይፈጠር የትዕግሥቱ ጫፍ ድረስ ታግሷል፡፡ ጦርነት የሚቀረው ግን በአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ አይደለም፡፡
‹‹የመከላከያ ሠራዊታችን በኮማንድ ፖስት እየተመራ አገሩን የማዳን ተልዕኮውን እንዲወጣ ትዕዛዝ ተሰጥቶታል፡፡ ቀዩ መስመር የመጨረሻው ነጥብ ታልፏል፡፡ አገርና ሕዝብ ለማዳን ሲባል ኃይል የመጨረሻው አማራጭ ሆኗል፡፡
‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ነገሮችን በሰከነ መንፈስ እንዲከታተል፣ በየአካባቢው ሊከሰቱ የሚችሉ ትንኮሳዎች በንቃት እንዲቃኝና ከመከላከያ ሠራዊታችን ጎን እንዲቆም ጥሪ አቀርባለሁ፡፡››
ከዚያ በኋላ በውድቅት ሌሊት ውስጥ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ይህንኑ መግለጫ ቢያቀርብም፣ ከነገሩና መርዶው ለኢትዮጵያውያን የተነገረውና አብሯቸውም የቆየው በዚሁ ለስላሳነት ነው፡፡
ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ይህ ሆኖ ከዚያ አንስቶ እየታየና እየተገላለጠ በመጣው እውነት መሠረት፣ የወረራ ትርጉም ውጫዊና ውስጣዊ ተብሎ መስተካከል ያስፈልገው ይሆን የሚል ‹‹የቸገረው›› ሰው ጥያቄ ማስነሳቱም አልቀረም፡፡ የዚህ ዓይነት እንግዳ ልምድ ፊትም የታየ፣ ወደፊትም የሚደገም ስለመሆኑ ቢያጠራርም፣ ኢትዮጵያ ግን ከባድና ግፈኛ ጥቃትና ክህደት፣ እንዲሁም ወረራ የተፈጸመባት አገር መሆኗን የሚያከራክርም፣ የሚያጠራጥርም አልነበረም፡፡
በአንድ ሉዓላዊ አገር ውስጥ ዋና ብቸኛ ገዥ ሆኖ የቆየ፣ በስተኋላ ላይ ዋና ገዥነቱ ጥቂት ከመቀነሱ በቀር በብዙ ሥፍራ እንዲያውም በመላ አገሪቱ የሠራ አካላት ውስጥ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መረብ የነበረውና ያለው፣ በክልሉ ላይም የተደላደለና የአዲሱ ለውጥ ንፋስ ያልነካው የማይበገር ገዥነት ያለው ቡድን በገዛ አገሩ የፀጥታና የመከላከያ አካላት ውስጥ ሚስጥራዊ ከዳተኞችን ከፌዴራል ማዕከል እስከ ክልል ማዕከል ድረስ አዘጋጅቶ፣ አካባቢዊ ፖሊስንና ልዩ ኃይልን የቡድናዊ ፍላጎቶቹ ሌሎቹ አድርጎ ጥርጣሬ በሌለበት ሁኔታ ውስጥ በገዛ አገሩ ላይ ወረራ ሲያካሂድ ማየት ለዓለምም ለኢትዮጵያም እንግዳ ነገር ቢሆንም፣ የተፈጸመውና የሆነው ግን ይኼው ነው፡፡ የአንድን አገር የመከለከያ ኃይል የተወሰነ የዕዝ ማዕከልን በፈጣንና በሚስጥራዊ እንቅስቃሴ ቆርጦና አደንዝዞ ማዕከላዊ ሥልጣንን መቆጣጠር የመንግሥት ግልበጣ የተለመደ ባህርይ ነውና አያስገርምም፡፡ ሕወሓት የፈጸመው ግን የመንግሥት ግልበጣ አይደለም፡፡ ከዚህም የከፋ ነው፡፡ በተለይም በሚገዛው ሕዝብ ዘንድ በበጎ ሕዝባዊ ሥራው የተከበረና የተወደደ የመከላከያ ዕዝ ላይ ጨካኝና ሥውር የበቀል ጭፍጨፋ ፈጽሞ፣ በተዘረፈ መሣሪያ የአገሪቱን ቀሪ የታጠቀ ኃይል ድብቅ መትቶና አገሪቱን ራሷን ‹‹መገልበጥ›› የተለመደ ነገር አይደለም፣ እንግዳ የሆነውም ይኼው ተግባር ነው፡፡
የውስጥ ወረራው ባልተጠበቀ ፍጥነትና በአጭር ጊዜ (ኅዳር 19 ቀን 2013 ዓ.ም.) ከተቀለበሰ በኋላ፣ በተለይም በትግራይ ክልላዊ መስተዳደር ውስጥ የተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር ባቀረበው የውሳኔ ሐሳብና ጥያቄ መሠረት የፌዴራል መንግሥት ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም. የወሰደውን የተናጠል የተኩስ አቁም ዕርምጃ፣ ከዚያ በኋላ የሆነውን በዝርዝር መተንተንና ማጥራት የዚህ ጽሑፍ ዓላማ አይደለም፡፡ በዚህ ውስጥ ግን ተድበስብሶ መታለፍ፣ ተድበስብሶ ሲታለፍም ዝም መባል የሌለበት የሕግና የፍሬ ነገር ጭምር የሆነ አንድ ጉዳይ ላንሳ፡፡ ይህ የማነሳው ጉዳይ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ደረጃ እንኳን፣ በዚሁ በመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ ንግግር ውስጥ እንኳን ዝም ብሎ እንደ ዋዛ ሲታለፍና በተለይም በዋናው ጸሐፊው ንግግር ውስጥ የሚያከራክር ነገር ሆኖ ዝም ሲባል የታዘብኩ ይመስኛል፡፡
የፀጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ከተሰበሰበባቸው በርካታ ውይይቶች መካከል፣ ይህንን ጽሑፍ ሳዘጋጅ የመጨረሻው ሐሙስ እ.ኤ.አ. ኦውገስት 29 ቀን 2021 መሆኑን አውቃለሁ፡፡ በዚህ በሰባ ድስተኛው ዓመት 8843ኛው የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ከአባላቱ ውጪ ንግግር ካደረጉት መካከል አንዱ፣ የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጽሐፊ ናቸው፡፡ ሚስተር አንቶንዮ ጉተሬስ ሰሜናዊ ኢትዮጵያ ውስጥ የተጀመረው ግጭትና ጦርነት እየተስፋፋ መሄዱን፣ ይህም ያስከተለው የሰብዓዊንና የሰብዓዊ መብት ችግር እየከፋና እየሰፋ መሄዱን የገለጸበትና የሚመለከታቸውን ሁሉ የተማፀኑበት ነው፡፡ እዚህም ጉዳይ ውስጥ የእኔ ጉዳይ ከዚህ ጽሑፍ ከያዝኩት ዓላማ አኳያ የዛቻው የንግግር ይዘት ዝርዝር አይደለም፡፡ አንቶኒዮ ጉተሬስ በዚህ ከፍተኛ ቁም ነገርና አጣዳፊ አቤቱታ /ምልጃ/ስሙና በያዘ ንግግራቸው ውስጥ፣
‹‹On these Issues, I have been in contact with Prime Minister Abiy Ahmed. I also received a letter on this matter from the president of the Tigray region, as elected at the time, in response to may appeal which was also addressed to the president of the Security Council. ሲሉ ሰምቻለሁ፡፡
በፀጥታው ምክር ቤትም ይፋዊ ሪከርድ ይህንን መዝገብ ዓይቻለሁ፡፡ በዚህ የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ የፀጥታው ምክር ቤት ንግግር እንደገለጸው የትግራይ ክልል (ሪጅን) ፕሬዚዳንት ደብዳቤ የጻፉላቸው ሰው ማን ናቸው ብሎ መጠየቅ ነገር የማዳነቅ፣ ወይም የአንድን ወገን መከራከሪያ የማዳነቅ ጉዳይ አይደለም፡፡ የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት ማነው የሚለው ጥያቄ ዝም ብሎ ቀላል መልስ የሌለው መሆኑን የሚያወዛግብ አለመሆኑን የራሳቸው የዋና ጸሐፊው ንግግር/በጽሑፍ ተዘጋጅቶ የቀረበ ንግግር ያሳብቃል፣ ያጋልጣል፡፡ (The President of Tigray region, as elected at the time) ጳጉሜን 4 ቀን 2012 ዓ.ም. ስለተደረገው የትግራይ ክልል ምርጫ በተመለከተ ከዚህ ቀደም ሲል የምርጫና የመከላከያ ነገር አሁን ባለው ሕገ መንግሥት ማዕቀፍ ውስጥ፣ የፌዴራሉ (የማዕከላዊው) መንግሥት ሥልጣን መሆኑ ገልጸናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪና በላይ የሆነም ነገር አለ፡፡ ጥቅምት 24 የሆነውን ነገር ምክንያት በማድረግና ከዚሁ ቀን በኋላ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 62(9) እና የፌዴራል መንግሥት በክልል ጣልቃ የሚገባበትን ሥርዓት ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 359/95 አንቀጽ 14/2/ለ መሠረት የክልሉን ምክር ቤትና የክልሉን ከፍተኛ የሕግ አስፈጻሚ አካል አግዶ ለፌዴራል መንግሥቱ ተጠሪ የሆነ ጊዜያዊ አስተደደር እንዲቋቋም ወስኗል፡፡ ይህ የተወሰነው ጥቅምት 28 ቀን 2013 ዓ.ም. ነው፡፡ ይህንንም ተፈጻሚ የሚያደርግ የትግራይ ክልላዊ መስተዳደር ጊዜያዊ አስተዳደር የሚኒስትር ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 479/2013 ከኅዳር 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የፀና እንዲሆን ተደንግጓል፡፡
እናም ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. የትግራይ ክልላዊ መስተዳደር በ2007
ዓ.ም. ጠቅላላ ምርጫ ውጤት መሠረት የተቋቋመ መስተዳድር ይሁን ወይም በጳጉሜን 4 ቀን የተናጠል ምርጫ የተመሠረተው መንግሥት፣ እነዚህ ወይም ከሁለቱ አንዱ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥቅምት 28 ቀን በሰጠው ውሳኔ ትይዩ በምትኩ ጊዜያዊ አስተዳደር ተቋቁሟል፡፡ በዚህ ምክንያት በኢትዮጵያ ያለው ጦርነት፣ የትግራይ ክልልን ጨምሮ በሌሎችም ግንባሮች የተተለኮሰውና የተቀጣጠለው ጦርነት ያሳሰበው የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ ከጦርነቱ ‹‹ተሳታፊዎች›› ጋር ያለውን ግንኙነት በገለጸበት በዚህ ነባይ ሊባል በሚችል ንግግር ውስጥ እንኳን፣ ቢያንስ ቢያንስ ማስተካከያ ሊደረግበት የሚገባ የኢትዮጵያ ጥቅም አለ፡፡ የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ዛሬ (ከሰኔ 21 ቀን 2013 በኋላ) ‹‹በስደት ላይ››ም ቢሆን በጥቅምት 28 ቀን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔና የፌዴራል መንግሥት በክልል ጣልቃ የሚገባበትን ሥርዓት ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 359/1995 መሠረት የተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደሩ ነው፡፡ እንዲህ ያለ ሥርዓት ጦርነቱ ከመጀመሩ በክልሉና በፌዴራል መንግሥት መካከል የተፈጠረውና ከሕገ መንግሥቱ ውጪ መፍትሔ እየፈለገ ያለው የአመፅ የወረራ ድርጊት ከመፈጸሙ በፊት በወጣ ሕግ የተቋቋመውና የተዘረጋ ነው፡፡ አዲሱ ‹‹አሀዳዊ›› እና ‹‹የአንድነት›› መንግሥት ያወጣው ሕግ ነው እንዳይባል አዋጅ ቁጥር 395/1995 በሕወሓት በራሱ የበላይነት ዘመን የወጣ ፌዴራል መንግሥቱ በክልል ጣልቃ ገብቶ፣ የክልሉን ምክር ቤትና የክልሉን ከፍተኛ የሕግ አስፈጻሚ አካል አግዶ ለራሱ ለፌዴራል መንግሥት ተጠሪ የሆነ እስከ ሁለት ዓመት ተኩል ድረስ ሊቆይ የሚችል ጊዜያዊ አስተዳደር ማቋቋም የሚያስችል ሕግ ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ሕገ መንግሥታዊነትን፣ ፌዴራላዊነትን፣ ዴሞክራሲያዊነትን፣ ሪፐብሊካዊነትን ለመጠበቅ የተሰጠ የፌዴራል መንግሥቱ ሥልጣንና ግዴታ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ይህንን የመሰለ አቻ ሥልጣን በክልል ደረጃ ሊጤን ይገባል ብሎ በክልል ደረጃ ‹‹ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ተግባር ሲፈጸም፣ ወይም የወረዳው አስተዳደር የአካባቢውን ፀጥታና ደኅንነት መቆጣጠር ሲያቅተው፣ ወይም በሕግ የተሰጠውን ሥልጣንና ተግባር በአግባቡ ሊተገበር አልቻለም ብሎ ሲወስን፣ የትግራይ ክልል ምክር ቤት የወረዳውን ምክር ቤት ወይም ሥራ አስፈጻሚውን አካል በማፍረስ የሽግግር አስተዳደር በማቋቋም፣ የሽግግሩ ወቅት የሚቆይበትን ጊዜ ይወስናል፤›› ብሎ ይህን የመጀመርያውን ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ያደረገው የትግራይ ክልል በ1998 ዓ.ም. ነው፡፡
ይህ ጽሑፍ በእርግጥም የሕወሓት ጽሕፈት ቤት የመስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም. አቅጣጫ ግምገማ አይደለም፡፡ ጊዜውና አቅሙ ባለመፍቀዱ እንጂ ይህ ጉዳይ ዝርዝር ግምገማ አያስፈልገውም፣ አይገባውም ብዬ አይደለም፡፡ የዚህ ጽሑፍ ወሰን እዚህ ዝርዝር ግምገማ ውስጥ አልገባም/አላስገባም ቢልም፣ አንዳንድ ዓይን ያወጡ ጉዳዮችን ግን በዚሁ በተገኘው ጊዜና አቅም ውስጥ ማየት እንገደዳለን፡፡
አንደኛውና የመጀመርያው የሕገ መንግሥታዊነት ጉዳይ ነው፡፡ ዓመቱን በሙሉ እንዲያ በፀጥታው ምክር ቤት ውስጥ ተወጥረን በተያዝንበት ሁኔታ እንኳን እንደ ህንድ ያሉ ለእግዜር ያለና ለሕግ የበላይነት የሚታገሉ አባላት፣ የኢትዮጵያ ጉዳይ መፍትሔ ማግኘት ያለበት ‹‹With in the sounds of the Constitution›› (በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ነው) እለያ ተከራክረውልናል፡፡ በብቸኛ የገዥነት ዘመኑ እኔን የመሰለ ለሕገ መንግሥት የታመነ የለም ሲል የኖረው ሕወሓት፣ ዛሬ በስትራቴጂ ስለጊዜያዊ መንግሥት ምሥረታ፣ ስለዘላቂ ጉዞ፣ ስለሽግግር መርህ የሚናገረው ምንና የትኛውን ሕገ መንግሥት ይዞ ነው?
ሕወሓት በጅምላ ጭፍጨፋና በረሃብ አደጋ ውንጀላ የሐሰት ክስ አማካይነት የምዕራባውያንን ከዕቀባ/ጭቆና እስከ ጦር ጣልቃ ገብነት ዕርምጃ እየደለለ፣ ኢትዮጵያን በማዳን ስም የሚፈልገው ምንድነው? ሥልጣን መልሶ መያዝ? ይህ ብቻ አይመስልም፡፡ ሕወሓት ለዚያውም በእሱ ብሶ ኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ሰላምና ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ የሚሰፍነው የራሳችንን ዕድል በራሳችን በመወሰን መብታችን፣ በነፃ ፍላጎታችን፣ በሕግ የበላይነትና በራሳችን ፈቃድ ላይ የተመሠረተ አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ የመገንባት ቁርጥ መነሳሳታችን ሁሉ (ይህ ሁሉ የሕገ መንግሥቱ መግቢያ ነው) ለካስ ከእኔ የብቻ ገዥነት ውጪ አይሆንም በሚል ሥሌትና ጥናት ኢትዮጵያን ‹‹ኢምፓየር›› ብሏታል፡፡ በስትራቴጂና በጥናቱም ‹‹የዚህች አገርና የትግራይ ሕዝብ የመጨረሻ ጉዞ›› ያለ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ወደ ሊዝ ፌዴራሊዝም የሚያስኬድና የሚያደርስ ሕገ መንግሥት ኢትዮጵያ ከዚህ በኋላ በግዛታዊነት አንድነት (ኢምፓየር) አንድ ዕርምጃ መራመድ አትችልም ብሎ፣ ኢትዮጵያን ብዙ ትንንሽ አድርጎ የመበጣጠስ ፕሮጀክት ነድፎ መጥቷል፡፡ ኢትዮጵያን በመበታተን ተበቅሎም ሌላ ‹‹አገር› የማትረፍ ተግባር መፈጸም የሚቻል ይመስለዋል፡፡
‹‹ለኢትዮጵያ የግዛት አንድነት ከአንደበት ወግ በላይ እቀረቆራለሁ የሚል በፀጥታው ምክር ቤትም ከዚያ ውጪም ባሉ መድረኮች የሚናገር የመንግሥት መሪ/አካል ሕወሓትን ሂድ ወግድ ማለት አለበት፡፡ የኢትዮጵያ እያለም የአካባቢውና የአኅጉሩ የሰላም ጠንቅ እየሆነ የመጣው በትክክለኛ ስሙ ባለመጠራቱ መሆኑን አስረግጦ ማወጅ አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብም አሁን እንደሚያደርገው/እንዳደረገው አገርን የማዳን ተግባር ፌዴራላዊ ዴሞክራሲን መሠረት ከማስያዝ፣ ለውጡንና ሽግግሩን ዘላቂ አድርጎ ከማስሄድ ተልዕኮ ጋር ያጣጣመ አደራና ግዳጅ የሰጠን መሆኑን ለአንድ አፍታ ሳይረሳ አንድ ሆኖ ዕንቢ ለጣልቃ ገብነት ማለት አለበት፡፡
በመጨረሻም በተሰናበትነው የ2013 ዓ.ም. ዓመት አገራችን ግፈኛና ከባድ ክህደትና ጥቃት ተፈጽሞባታል፡፡ ይህንን በኢትዮጵያ ሰሜናዊ የመከላከያ ዕዝና ክምችት ላይ የደረሰውን ክህደትና ጥቃት ዩኤንዲፒ በየካቲት 9 ቀን 2013 ዓ.ም. ለመንግሥታቱ ድርጅት በላከው ማስታወሻ እንዲመሰክር የኢትዮጵያ መንግሥት ወታደራዊ ዕርምጃ ለምኖ፣ ‹‹ተለማምኖ››፣ ቀስቅሶ፣ ቆስቁሶ የመጣው (ፕሮቮክ ያደረገው ዓብይ በዚያ የእኩለ ሌሊት የፌስቡክ ማስታወሻቸው የገለጹትን ዕርምጃ) ትግራይ ያለውን የኢትዮጵያን የመከላከያ ሠራዊት የሰሜናዊ ዕዝ ጠቅላይ መምርያ ሕወሓት ማጥቃቱና መያዙ ነው ብሎታል፡፡ የትም ቦታ በዓለም ዙሪያ የጦርነት ተግባር የሚባልና የትኛውንም አገር ለማዳንም ወታደራዊ ምላሽ የሚያስከትል ተግባር ነው ብሎም ምስክርነቱን የሰጠለት አሳፋሪ ድርጊት ነው፡፡
በረሃብ አደጋና በጅምላ ጭፍጨፋ ክስና ውንጀላ፣ በማዕቀብና በሥውር ሴራ አንቀጾች ላላችሁ የሚሉንን ዓለም አቀፋዊ ኅብረተሰብ የኢትዮጵያ መንግሥትንና ሕወሓትን የሚያይበትና የሚመዝንበት መለኪያ ፍርደ ገምድልነትን ያለው ነው (ባለ Doble standared ነው) በማለት የሚያወግዘው የዩኤንዲፒ ማስታወሻ፣ ‹‹There is no evidence of any early actin taken by the international community to stem what is known to be a 2-year-old cancer in Ethiopians body – politic›› ይላል፡፡ ደድ ወደገግደድ መማማተት አለበተት፡ አየአኢተትየዮፐፕየያ፣ አእየያያመም የአከካበባባወውነና የሐአኀኅገጉረሩ የሰለላመም ጠነንቀቅ አእየሀሆነ የመጠጣወው በተትከክከክለኘኛ ሰስመሙ በባለመጠረራተቱ መሀሆነኑነን አሰስረገግጠጦጦ
ፈርዶብን ፎሬይን ፖሊሲ በየካቲት 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ዕትሙ ላይ ለዚያውም አንጋዶና አንሸዋሮ ካሳወቀን በላይ እኛ የማናውቀው፣ የዓለም አቀፋዊው ኅብረተሰብም በዝምታ ሴራ ያድበሰበሰው ወይም የቀበረው ይህ የልማት ድርጅቱ ምስክርነትና ማስታወሻ ግን፣ ዛሬም ከሌሎች ተጨባጭ ማስረጃዎቻችን ጋር ከመስከረም የሕወሓት ‹‹ሰነድ›› ውጪና በገዛ ራሱ ህልውና የሚኖር ምስክራችን ነው፡፡
ኢትዮጵያ ያን የመለሰለ ከባድ ክህደትና ጥቃት የደረሰባት አገር ናት፡፡ በ2013 ዓ.ም. ያን ያህል ክህደትና ጥቃት ተፈጽሞባትም በሚያስደንቅ ጀግንነት የተረፈች አገር ናት፡፡ እንዲህ ያለ ከባድና ግፈኛ ክህደትና ጥፋት ተፈጽሞባት የተረፈች አገር አይዞሽ መባል ቢቀር፣ አተራረፉ ብቻውን ክብርና ምሥጋና ሊሰጠው የሚገባ በሆነ ነበር፡፡ በጦርነት ውስጥ ተዘውትረው በሚታዩት በፍርስራሽ መዋጥ፣ የብዙ ሕዝብ መማቀቂያ ዕልቂት ሳይደርስ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ፈጥኖ መከናወኑ፣ በዚህም ቅልጥፍና ሕዝቦቿንና የአፍሪካ ቀንድን ከመታመስ ማራቋ በራሱ ‹እንኳን ደስ አለሽ!›፣ ‹እንኳን ለዚህ አበቃሽ!› የሚያስብል የጀብድ ሥራ ነበር፡፡
በዚህ ውስጥ ኢትዮጵያ ከመቶ ሚሊዮን ሕዝብ በላይ የያዘ አገረ መንግሥቷን ለማትረፍ በወሰደችው ዕርምጃ ወስጥ ጥፋት ቢገኝ እንኳን፣ ሚዛናዊ ፍርድ የሚያውቅ ጥፋቷን የሚፈርደው በተሰነዘረባት ከባድ ጥቃትና ከዚያ ለማምለጥ ባካሄደችው ጠንቃቃ ጥረት ውስጥ እንጂ፣ ተገኘ የተባለውን ጥፋት ራቁቱን በወሰደ ወይም ተጠቂነቷንና ለሕዝቦቿ ያላትን ኃላፊነት እንዳለ አድርጎ በደመሰሰ ፍርደ ገምድል ዓይን መሆን አልነበረበትም፡፡ 2013 ዓ.ም. ያሳለፍነው ይህን በመሰለ ክስ፣ ውንጀላና ማሳፈሪያ ነበር፡፡
2014 ዓ.ም. እንደጠባም በአሜሪካ መንግሥት የእንቁጣጣሽና የእንኳን አደረሳችሁ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ስጦታ የማዕቀብ/የጭቆና ዕርምጃ ሆኖ አረፈው፡፡ አንድ መቶ ዓመት ሊሞላው ሩብ ያህል ጊዜ በቀረው ከ76 ዓመታት በፊት የመንግሥታቱ ድርጅት የተቋቋመው ከሁለት አውዳሚ ጦርነቶች በኋላ፣ የመረረ ጦርነቶችን ለመከላከልና ለማስቀረት ነበር፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ቻርተር አንቀጽ አንድ ለሰላም ሥጋትና ጠንቅ የሆኑ ለመከላከልና ለማስወገድ የወልና የጋራ ዕርምጃዎችን (Effective Collective Measures) ይደነግጋል፡፡ በ2013 ዓ.ም. የካሌንደር ዓመት ውስጥ አሥር ያህል በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የተጠራ የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ተካሂዷል፡፡ በየትኛውም ስብሰባ የጋራ/የወል ዕርምጃ የወሰደ ስምምነት በጭራሽ አልነበረም፡፡ ሌላው ቀርቶ ውሳኔ መስጠት ይቅርና ድምፅ የመስጠት ሙከራ ያደረገ ስብሰባ ተዋጥቶለት አያውቅም፡፡ እንዲያውም የራሱ የፀጥታው ምክር ቤት ‹‹ፕሮስ ቨርባሎች›› እንደሚያሳዩት፣ ከሞላ ጎደል በሁለም ስብሰባዎች የተናጠል ማለትም ‹‹ዩኒላተራል ሳንክሽን›› የተወገዘበት ነው፡፡ የፀጥታው ምክር ቤት የወልና የጋራ ማዕቀብ ሁሉ ፍትሐዊ ነው ባይባልም፣ የአሜሪካ መንግሥትና የሌሎችም አገሮች የተናጥል ማዕቀቦች ሁሉ ‹‹ሸንጎ ሲረቱ…›› ያለ ሕግና ያለ ኃፍረት የሚወስዱት የተሸናፊነት ዕርምጃ ነው፡፡ ብዙዎቹ የጉልበተኛ አገር የ‹‹መብት›› እና ‹‹ነፃነት›› ተሟጋቾች በእንዲህ ያለ ጉዳይ ብዙ ጊዜ አማረልን ብለው ቀብራቸውን በሚደፍቁበት የጂኔቫው የሰብዓዊ መብቶች የመንግሥታቱ ድርጅት አዳራሽና ሥርዓት ውስጥ የተናጠል ማዕቀብ ሲሻሻል ራፖርተር የሚባል እንዳለ፣ የተናጠል ማዕቀብ ሕገወጥ እንደተባለ ‹‹አያውቁም›› አይባልም፡፡ 2014 ዓ.ም. የጀመርነው ይህንን ጭምር እየታገልን ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡