አገር በቀል ኢኮኖሚን ለመተግበርና ለማጎልበት ያስችላል የተባለውን መሪ ዕቅድ የሚተገበረው በተያዘው ዓመት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እያንዳንዱ ዘርፍ ለአገራዊ ኢኮኖሚው ያበረክታል ተብሎ የታመነበት ዕቅድ ተቀምጧል፡፡ ኢኮኖሚውን በተሻለ ደረጃ ከፍ ያደርገዋል ተብሎ የታመነበት ይህ አገር በቀል የኢኮኖሚ መሪ ዕቅድ እንደ ከዚህ ቀደሙ ተመሳሳይ ዕቅዶች ፍሬ አልባ እንዳይሆን ወይም በታቀደውና በተገኘው ውጤት መካከል እጅግ የሰፋ ልዩነት እንዳይኖረው የሁላችንም ምኞት ነው፡፡ የቀደመው ውጥን ከውጤት አንፃር ሲለካ ፈጽሞ ለግቡ የቀረበ ያለመሆኑ በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም፣ በአግባቡና በልክ ያለመወጠኑ አንዱ ነው፡፡ ከግቡ ለማድረስ የሚያስችሉ ወሳኝ የሆኑ ሥራዎች ቀድመው ዝግጅት ያልተደረገባቸው መሆኑም ሌላው ችግር ነው፡፡
የቀደሙት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዶች እጅግ የተለጠጡ ከመሆናቸውም በላይ ዕቅዶቹን ከግብ ለማድረስ የሚያስችሉ አሠራሮች ያልነበራቸው፣ በየዘርፉ ብቁ የሥራ መሪዎች ያልተመደበላቸው ነበሩና ዕቅዶቹ የፕሮፓጋንዳ መሣሪያዎች ሆነው እንዲቀሩ አድርጓቸዋል፡፡ አዲሱን አገር በቀል የኢኮኖሚ ውጥን እንዳይስተጓጎል የቀድሞዎቹ ዕቅዶች ለምን እንዳልተሳኩ በመፈተሽ መማርያም ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ከቀድሞ አሠራርና ዕሳቤ በመውጣት አዲሱን ዕቅድ ለማስፈጸም ያስችላሉ የተባሉ አሠራሮቸን ቀድሞ ማዘጋጀትን ሁሉ ይጠይቃል፡፡ በተለይ በየዘርፉ ዕቅዱን ለማስፈጸም የሚያስችል አቅም ያላቸውን ባለሙያዎች በሚገባ መዝኖ ማስቀመጥን ይጠይቃል፡፡
የሥራ መሪዎች እንደ ከዚህ ቀደሙ በኮታና በፖለቲካ አመለካከታቸው ተመሥርቶ የሚሾሙ ከሆነ፣ አሁንም ዕቅዱን ለመፈጸም አንችልም፡፡ በአዲሱ መንግሥት ምሥረታ በጥብቅ ሊታሰብባቸው የሚገቡ ጉዳዮች መካከልም ውጤት በምንጠብቅባቸው በማንኛውም የሥራ ዘርፎች ሥራቸውን የሚሠሩ የሥራ መሪዎችን በጥንቃቄ መመደብ ቁልፍ ጉዳይ መሆን አለበት፡፡
በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች የሚሾሙ ቱባ ባለሥልጣናትም ሆኑ ባለሌላ ሹመኞች በየተመደቡበት ዘርፍ የማስፈጸም አቅማቸውንና ሥራውን ታች ወርደው ሊሠሩ የማይችሉ ከሆነ የትናንቱ ነገር ይደገማል፡፡ አፈር መንካትና ከአርሶ አደሩ ጋር ወርዶ መሥራትን፣ አርብቶ አደሩ ጋር በመሄድ የእንስሳት ሀብት እንደደረሱ የሚያስችል አሠራር እንዲፈጠር የሚያደርግ ካልሆነና ቢሮው ቀጥ የሚል ተlሚ ይዞ የትም አይደርስም፡፡
የአገር በቀል ኢኮኖሚ ውጥኑ ታሳቢ ያደረገው የግል ዘርፉን ጭምር በመሆኑ ኩባንያዎች አለብን የሚሉትን ችግር በአዳራሽ ሰብስቦ በማናገር ብቻ ሥራ እንደተሠራ የሚቆጥሩ ተlሚዎች ላለንበት ጊዜ አይመጥኑም፡፡ በየኢንዱስትሪው በመዞር የመስክ ቅኝት በማድረግ ችግሮቹን በተጨባጭ በማየት አፋጣኝ ምላሽ የሚሰጥ ሥልጣን እንዳለው የሚያምኑ የሥራ መሪዎች እስካልፈጠርን ድረስ በየትኛውም ዘርፍ ይደረስበታል የተባለውን ውጤት ማምጣት ዘበት ይሆናል፡፡
በተለይ ዛሬ አገራችን ካለችበት ችግር አንፃር አገራዊ ኢኮኖሚውን የማጎልበት እንደተባለውም አገር በቀል ኩባንያዎችን ከፍ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎችን መሥራት ይጠበቃል፡፡ ይህንንም የአገር ጉዳይ ከግምት ውስጥ በማስገባት በቁጭትና በወኔ የሚሠሩ ሁነኛ ባለሙያዎችን ማፍራትና አጠቃላይ የሥራ ባህላችንም መቀየር አለበት፡፡
ግልጽ የሆነ አሠራር በማስቀመጥ ሁሉም ሹመቶች በሠሩት ሥራ ልክ ተመዝግነው በቦታው መቀጠል አለመቀጠላቸው የሚወሰንበት አሠራር ሊኖር ይገባል፡፡
ሌላው መታሰብ ያለበት የአገር በቀል ኢኮኖሚው ውጥን በታሰበው መንገድ እንዲቀጥል ማድረጉ አንድ ጉዳይ ሆኖ፣ አሁን ካለው ወቅታዊና አገራዊ ሁነት አንፃር ዕቅዱን በተወሰነ ደረጃ በመከለስ በተለይ ወሳኝ ለሚባሉ ዘርፎች በልዩ ትኩረት እንዲሠራባቸው ማድረግም ተገቢ ነው፡፡
ለምሳሌ ከውስጥም ሆነ ከውጭ ሊፈጠሩብን በሚችሉ ጫናዎች አገሪቱ የሚያስፈልጋትን የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ያስችላሉ የተባሉ ሁሉንም አማራጮች መጠቀምና በአንስተኛ ወጪ የተሻለ የውጭ ምንዛሪ ሊያስገኙ የሚያስችሉ ዘርፎች በልዩ ክትትል ግባቸውን እንዲመቱ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ከውጭ ምንዛሪ ግኝት ጋር በተያየዘ ሌላው መፍትሔ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርት እንዲተኩ በቀዳሚነት መሠራት ያለበትን በማድረግ የሚያውለውን ውሳኔ ማሳለፍና ይህንንም መተግበር ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን የሚተኩና የሚያመርቱ አገር በቀል ኩባንያዎችን በመለየት የበለጠ አምራች የሚሆኑበትን ሁኔታ ማመቻቸት ዜጎችም እነዚህን ምርቶች እንዲጠቀሙ ማበረታታት የግድ ይሆናል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ በቀላሉ ሊተኩ የሚችሉ ምርቶችን ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ በሕግ ክልከላ ማድረግም ጠቃሚ ነው፡፡ ሊተኩ የሚችሉ ምርቶችን ከውጭ በሕግ እንዲቆሙ እንዳይገቡ በማድረግ ፈታኝ የሚባለውን ጊዜ ለመሻገር አጋዥ ይሆናል፡፡ ዛሬ በቀላሉ በአገር ውስጥ የሚገኙ ተመሳሳይ ምርቶችን ከውጭ የምናስገባበትና የውጭ ምንዛሪ የምናባክንበት አቅም ላይ ያለመሆናችንን በመረዳት፣ በዚህ ላይ ጠንከር ያለ ዕርምጃ መወሰድ አለበት፡፡ ይህ ወቅታዊ ችግራችንን ለመወጣት ብቻ ሳይሆን ለዘለቄታውም አገር በቀል ኩባንያዎች አቅምን ለማጎልበት ይረዳል፡፡
አገር ውስጥ በቀላሉ ሊመረቱ የሚችሉ ምርቶቻችን ለይቶ ማስቀመጥና ለእነዚህ ምርቶች የውጭ ምንዛሪ እንዳይፈቀድ ማድረግም ይችላል፡፡ የውጭ ምንዛሪ የሚፈቀድ ከሆነ አይደለም ግባችንን ለመምታት አሁን ያለንበትን ችግር ለመስማት የሚከብድ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ሁኔታዎች እስኪስተካከሉ በራሳችን አቅም የሚመረቱ ምርቶችን ተብለጭላጭ ዕቃዎችን ገታ በማድረግ እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ምርቶች ማስገባት ያስፈልጋል፡፡
ስንዴ ለመግዛት የሚወጣውን ወጪያችን ለመቀነስ አሁን የተጀመረውን የበጋ ስንዴን በመስኖ ማምረትን አጠንክሮ መሥራትና ሌሎችንም የእርሻ ምርቶችን በተመሳሳይ መንገድ እንዲመረቱ ማድረግ ብዙ ለውጥ ያመጣል፡፡ ባዶ መሬትን በትብብር ከሠራንበት አገር ለመጠምዘዝ እንቅልፍ እያጡ ያሉ የአገር ጠላቶች አደብ ማስገዛት ይቻላልና የራስ አቅም ማጠንከር ተገቢ ይሆናል፡፡ ይህም መሪ ዕቅዱን ዳር ለማድረስ ይረዳል፡፡