Saturday, December 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ባህር ትራንስፖርት 10 ሚሊዮን ቶን ገቢና ወጪ ጭነቶችን ለማጓጓዝ እየሠራሁ ነው አለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የ240 የጭነት ተሸከርካሪዎችና የአምስት ሺሕ ኮንቴነሮችን ግዥ ሊፈጽም ነው

የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በተያዘው የበጀት ዓመት፣ ከአሥር ሚሊዮን ቶን በላይ ገቢና ወጪ ጭነቶችን ለማስተናገድ እየሠራ መሆኑን አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሮባ መገርሳ ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ የ2014 ዓ.ም. በጀት ዕቅድ ተዘጋጅቶና በሚመለከታቸው ሁሉም አካላት ውይይት ተደርጎበት በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ ፀድቆ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡ 

እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ፣ ድርጅቱ በተያዘው የበጀት ዓመት ከአሥር ሚሊዮን ቶን በላይ የገቢ ወጪ ጭነቶችን ለማስተናገድ ዕቅድ ይዟል፡፡ ከወጪና ገቢ ጭነቶች ውስጥ ከፍተኛ የሆነውን ድርሻ የሚይዘው የአፈር ማዳበሪያ ነው፡፡ ድርጅቱ ባለፈው የበጀት ዓመት ያጓጓዘው አጠቃላይ ገቢና ወጪ ጭነት 8.3 ሚሊዮን ቶን እንደነበር አቶ ሮባ አስታውሰዋል፡፡

በተያዘው ዓመት የሚጓጓዘው የአፈር ማዳበሪያ ሁለት ሚሊዮን ቶን እንደሚሆን ይጠበቃል ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ይህ ማዳበሪያ በተወሰነለት ጊዜ ግዥው ከተጠናቀቀ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት መርከቦችን አሰማርቶ ማጓጓዝ እንደሚጀምርና ለአርሶ አደሩም በጊዜው እንዲደርስ አስፈላጊው ዝግጅት እንደተደረገ አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በበጀት ዓመቱ የ240 ከባድ ጭነት ተሸከርካሪዎች ግዥ እንደሚፈጸም፣ ለ38 ተሽከርካሪዎች ግዥ ትዕዛዝ እንደተላለፈ አቶ ሮባ ተናግርዋል፡፡ ባለፈው የበጀት ዓመት ድርጅቱ ከ11 ሚሊዮን ዶላር በላይ በማውጣት 150 የከባድ ጭነት ተሸከርካሪዎችን መግዛቱ የሚታወስ ሲሆን፣ ድርጅቱ ባቡርም የሚጠቀምበት አማራጭ እንዳለ አስገንዘበዋል፡፡ አልፎ አልፎ ከሚያጋጥመው የፀጥታ ችግር በስተቀር ድርጅቱ በጥሩ ሁኔታ እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

‹‹በጁቡቲ ወደብ በኩልም አስፈላጊውን ዝግጅት እንዲያደርጉ ምክክሮችን  አድርገናል፤›› ያሉት አቶ ሮባ፣ በወደቡ በኩል በሥጋትነት ሊነሳ የሚችለው ጉዳይ ባሳለፍነው ዓመት አጋጥሞ በርብርብ ለማቃለል የተሞከረው ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተያያዘው ችግር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ባልተለመደ ሁኔታ ጂቡቲ ዝናባማ አገር እየሆነ መጥቷል ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ በወደቡ ያሉት አገልግሎቶች ለዝናባማ የአየር ፀባይ የተዘጋጁ ስላልሆኑ፣ የወደብ ማሽነሪዎች በተደጋጋሚ ጊዜ እንደሚበላሹና ተጨማሪ የወደብ ማሽነሪዎች እንዲገዙ ጥያቄ መቅረቡን ጠቁመዋል፡፡

ሌሎች የወደብ አማራጮችን ከመጠቀም ወደኋላ እንደማይባልና ወደ በርበራ መሄድም አስፈላጊ ከሆነ ዝግጅቶች ተደርገው የሚኬድ ይሆናል ብለዋል፡፡

ደርጅቱ በተያዘው የበጀት ዓመት ትኩረት ሰጥቶ ከሚሠራባቸው ጉዳዮች የመርከብ ዴሜሬጅን መቀነስ እንደሆነ ገልጸው፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ የመርከብ ማጓጓዣ ዋጋ ከሚታሰበው በላይ በመናሩ፣ የዓለምን የመርከብ ሥምሪት ቁጥጥር በአሜሪካና በቻይና ላይ በመውደቁ ያለውን ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ ወደብ የሚደርሱ ጭነቶችን በወቅቱ ማንሳት ወሳኝ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡

እንደ አቶ ሮባ ገለጻ፣ የመርከብ የጭነት ዋጋ ከዓመት በፊት ከነበረው አሥር እጥፍ ነው ያደገው፡፡ ይህም ታይቶ የማይታወቅ ነው ብለዋል፡፡ በወረርሽኙ ምክንያት በነበረው የእንቅስቃሴ ገደብ ምክንያት ሳይንቀሳቀሱ የቆዩ ጭነቶች በመኖራቸው ለማንሳት በሚደረገው ሒደት ወረፋዎች መብዛታቸውን፣ ባልተለመደ ሁኔታ ቻይና ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ መርከቦች ወረፋ እየጠበቁ መሆናቸው፣ በሁለትና በሦስት ቀናት መርከብ የሚስተናገድበት አሠራር እስከ 23 ቀናት እየፈጀ መሆኑ፣ በተለይ በቻይና አሁን የሞንሱን አየር ፀባይ ሌላው ችግር መሆኑን አውስተዋል፡፡

ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች የኮንቴይነር አቅርቦትን እንዳስተጓጎሉ የጠቀሱት አቶ ሮባ፣ ከዚህ ሁሉ በላይ የዕቃዎች ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እንዳደገና የዩሪያ፣ የድንጋይ ከሰልና የብረት ምርቶች ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ ታይቶበታል ብለዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ መርከብ መቆም የለበትም በሚል ትኩረት ተሰጥቶ፣ አቅምን በዚህ ላይ አጎልብቶ እየተሠራ እንደሆነ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስታውቀዋል፡፡

ከወደብ አገልግሎት አሰጣጥ አኳያ በሞጆ ደረቅ ወደብ በጥሩ ሁኔታ አገልግሎት የሚሰጥበት ሁኔታ ተመቻችቷል የተባለ ሲሆን፣ ጭነት ወደብ ላይ እንዳይቆይና በባቡር የሚመጣ ጭነት እንዲሁ በቶሎ እንዲራገፍ፣ በተለይም የአፈር ማዳበሪያን መቀበል የሚያስችሉ ሁለት መጋዘኖች ተሠርተው መጠናቀቃቸው ተመልክቷል፡፡

ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ የወጣበትና 34 ሔክታር መሬት ላይ ያረፈው ዘመናዊው የድሬደዋ ደረቅ ወደብ፣ በተያዘው የበጀት ዓመት ወደ ሥራ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡ በተያዘው የበጀት ዓመት ትልቅ ተግዳሮት ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው የመርከብ የማጓጓዣ ዋጋ ንረትና የኮንቴይነር እጥረት እንደሆነ ያስታወቁት አቶ ሮባ፣ በቅርቡ ከተገዙት አምስት ሺሕ ኮንቴይነሮች በተጨማሪ በቅርቡ አምስት ሺሕ ኮንቴይነሮች እንደሚገዙ አስታውቀዋል፡፡

የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ሌላው ችግር ሊሆኑ ከሚችሉ ጉዳዮች ተጠቃሹ እንደሆነ ያወሱት አቶ ሮባ፣ የጂቡቲ ወደብ ዕቃዎችን የማስተናገድ አቅም በጭነት መጠኑ ልክ አለማደጉ ሌላው ችግር እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ በወደቡ የሚስተናገዱ ጭነቶች መጠን በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ ቢሆንም፣ ማሽነሪዎች ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ በብልሽት ምክንያት የሚቆሙበት ሁኔታ እንደሚስተዋል ገልጸው፣ የማሽነሪና የአየር ሁኔታው ተጨማምሮ ስለማይቻል ይህ ጉዳይ ራሱን የቻለ ፈተና እንደሚሆን አስታውቀዋል፡፡

የአገሪቱ የግዥ ሥርዓት ችግር ሌላው ያልተፈታ መሠረታዊ ጉዳይ እንደሆነ የጠቀሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ግዥ በተፈለገው ጊዜ ስለማይካሄድ የመርከብ ጭነቶችን እንቅስቃሴ እንደሚያዛባና በተለይ የስንዴና የማዳበሪያ ግዥ ሒደት ትንሽ አስቸጋሪ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ የጭነት ተሸከርካሪዎች ቁጥር እጥረት እንደቀደሙት ጊዜያት ሁሉ የተለመደ መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸው፣ በአብዛኛው ወደ ወደብ የሚሄዱ ተሸከርካሪዎች የዕርዳታ እህል ጭነው አልተመለሱም እየተባለ ስለሆነ የዕርዳታ ፍላጎቱም እያደገ ከመሄዱ ጋር ተያይዞ ተጨማሪ ተሽከርካሪዎችን ማሰማራት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ አኳያ ያለው ብቸኛ አማራጭ ተጨማሪ ተሽከርካሪዎችን መግዛት እንደሆነ ታሳቢ ተደርጎ፣ መንግሥት 3,200 ያህል የጭነት ተሸከርካሪዎችን በተለያዩ ተቋማት አማካይነት እንዲገዙ ትዕዛዝ ሰጥቶ እየተሄደበት እንደሆነ አቶ ሮባ አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች