Friday, December 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በፕሮቪደንት ፈንድ ማኅበራዊ ዋስትና የታቀፉ የግል ሠራተኞች ወደ ጡረታ እንዲዛወሩ ሊወሰን ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

በፕሮቪደንት ፈንድ ወይም በሌላ ስያሜ በሚጠራ የማኅበራዊ ዋስትና ሥር የታቀፉ የግል ድርጅቶች ሠራተኞች የጡረታ ዐቅድ እንዲገቡ ሊወሰን ነው፡፡

ይህንኑ ለመወሰንና የግል ድርጅቶች ሠራተኞች የጡረታ ዐቅድ ሥርዓትን በድጋሚ ለማቋቋም አዲስ አዋጅ መረቀቁን ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የተረቀቀው አዋጅ ባለፈው ረቡዕ መስከረም 12 ቀን 2014 ዓ.ም. ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ መጽደቁን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በረቂቅ አዋጁ ከተካተቱት ድንጋጌዎች አንዱ የአዋጁ ተፈጻሚነት ወሰንን የሚያመለክት ነው፡፡ ረቂቅ ድንጋጌው እንደሚያመለክተውም ቀደም ሲል በፕሮቪደንት ፈንድ ወይም በሌላ ስያሜ በሚጠራ የማኅበራዊ ዋስትና ዐቅድ ተጠቃሚ የነበሩ ሠራተኞች፣ በአጠቃላይ በግል ድርጅት ሠራተኞች ጡረታ ዐቅድ የሚሸፈኑ ይሆናል፡፡

ረቂቅ አዋጁ ዝርዝር ሁኔታውን የተመለከተ ሌላ ድንጋጌ አልያዘም፡፡ ነገር ግን ዝርዝር አፈጻጸሙ በመመርያ እንደሚወሰን ይገልጻል፡፡

በ2003 ዓ.ም. የጸደቀው የግል ድርጅቶች ሠራተኞች የጡረታ ዐቅድ ከመጽደቁ አስቀድሞ ተመሳሳይ ድንጋጌ በረቂቅ አዋጁ ውስጥ ተካቶ የነበረ ቢሆንም፣ በፕሮቪደንት ፈንድ የማኅበራዊ ዋስትና የሚጠቀሙ ሠራተኞችና ተቋማት በወቅቱ ባሰሙት ከፍተኛ ተቃውሞ ድንጋጌው እንዲወጣና እንዲሻሻል መደረጉ ይታወሳል፡፡

ተሻሽሎ በጸደቀው ድንጋጌ መሠረትም አዋጁ በ2003 ዓ.ም. ከመታወጁ አስቀድሞ በተቋቋሙ የግል ድርጅቶች ሠራተኞች የጡረታ ዐቅድ ወይም ፕሮቪደንት ፈንድ ሽፋን ያላቸው ሠራተኞች በነበራቸው ዐቅድ ወይም የፕሮቪደንት ፈንድ ተጠቃሚነታቸውን ለመቀጠል ሊወስኑ ወይም በ2003 ዓ.ም. በወጣው የግል ድርጅቶች ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ ስለሚሸፈኑበት ሁኔታ ሊስማሙ እንደሚችሉ ፈቅዷል፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ አዋጅ ላይ በ2007 ዓ.ም. በተደረገው ማሻሻያ በፕሮቪደንት ፈንድ ዐቅድ የተሸፈኑ ሠራተኞችን ወደ ግል ድርጅቶች ሠራተኞች የጡረታ ዐቅድ ለማዘዋወር ረቂቅ ድንጋጌ ቀርቦ የነበረ ቢሆንም፣ በገጠመው ተመሳሳይ ተቃውሞ ሳይካተት ሙሉ በሙሉ ቀሪ ሆኗል፡፡

አሁን በድጋሚ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ለሚቋቋመውና የሥራ ዘመኑን ለሚጀምረው አዲሱ ፓርላማ የሚቀርብ የመጀመርያው ፈታኝ አዋጅ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች