Saturday, April 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የእንግሊዙ ዲያጆ ኩባንያ ንብረት የሆነው ሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካ በሐራጅ ሊሸጥ መሆኑ ተሰማ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ፋብሪካው ለሐራጁ ምክንያት የሆነው የ3.7 ቢሊዮን ብር የግብር ዕዳ እንደሆነ ተጠቁሟል
  • ፋብሪካው በበኩሉ የግብር ግዴታውን እየተወጣ እንደሆነ በመግለጽ መረጃውን አስተባብሏል

የእንግሊዙ ኩባንያ ዲያጆ ንብረት የሆነው ሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካ ከገጠመው ችግር ጋር በተያያዘ፣ የተከማቸበትን ከፍተኛ የግብር ዕዳ መክፈል ባለመቻሉ በሐራጅ እንዲሸጥ መወሰኑ ተሰማ።

በዲያጆ ኩባንያ ባለቤትነት ሥር የሚገኘው ሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካ ላለፉት ዓመታት በገጠመው ችግር የተነሳ የሚፈለግበትን የንግድ ትርፍ ግብር፣ የኤክሳይስ ታክስና የተጨማሪ እሴት ታክስ ለመንግሥት መክፈል እንዳልቻለ ሪፖርተር ከታማኝ ምንጮቹ ያገኘው መረጃ ያመለክታል። 

ሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካ ... 2017 እስከ ጁላይ 2021 ድረስ የተከማቸበት አጠቃላይ የግብር ዕዳ ማለትም ፍሬ ግብር፣ መቀጫና ወለድን ጨምሮ 3,692,163,231 ብር መድረሱን መረጃው ያሳያል። 

 

የኩባንያው ዕዳ ወደ ተጠቀሰው መጠን ከመድረሱ አስቀድሞ ዕዳውን እንዲከፍል ተጠይቆ ሊከፍል ባለመቻሉየገቢዎች ሚኒስቴር የከፍተኛ ግብር ከፋዮች ሕፈት ቤት፣ የታክስ አስተዳደር አዋጁ በሚሰጠው ሥልጣን መሠረት የፋብሪካውን ሀብትና ንብረት ለመያዝ እንደሚገደድ በማስታወቅ፣ ለኩባንያው ማስጠንቀቂያ መስጠቱን መረጃው ይገልጻል። 

ይሁን እንጂ ፋብሪካው በሚፈለግበት የግብር ዕዳ ምክንያት ሀብትና ንብረቱ በገቢዎች ሚኒስቴር ቢያዝ የመዘጋት ዕድል የሚያጋጥመው በመሆኑና ይህም በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ የፋብሪካውን ሠራተኞች ከእነ ቤተሰቦቻቸው ለችግር የሚያጋልጥመሆኑበተጨማሪም ፋብሪካው ለኢኮኖሚው ሲያደርግ የነበረውን አስተዋጽኦ የሚያቋርጥ እንደሚሆን በመንግሥት በመታመኑ ሳይተገበር ቀርቷል።

‹‹የፋብሪካው ባለቤት የእንግሊዙ ኩባንያ ዲያጆ ፋብሪካው ባጋጠመው ችግር ምክንያት ሥራ በማቆሙ ያለ ሥራ ለተቀመጡ ሠራተኞች በየወሩ ከአንድ ሚሊዮን ፓውንድ በላይ እየከፈለ እንደሚገኝ፣ መንግሥት ፋብሪካውን ቢረከብ እንኳ ይህንን ወጪ በየወሩ መሸፈን አስቸጋሪ ስለሚሆን ዕርምጃ መውሰዱ ለመንግሥት ተመራጭ አልነበረም፤›› ሲሉ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን ገልጸዋል። 

ችግሩን ለመፍታት ከገንዘብ ሚኒስቴርና ከገቢዎች ሚኒስቴር የተወከሉ አመራሮች ከዲያጆ ኩባንያ ተወካዮች ጋር የመፍትሔ አማራጮች ላይ ሲመካከሩ መቆየታቸውን አስረድተዋል። 

ሜታ አቦ ፋብሪካ የግብር ዕዳውን መክፈል ባለመቻሉ በሕጉ መሠረት በሐራጅ መሸጥ የነበረበት ቢሆንምፋብሪካውን 3.7 ቢሊዮን ብር ዕዳው ጋር ጨምሮ የሚገዛ ባለሀብት ሊቀርብ እንደማይችል በተደረጉ የተወሰኑ ሙከራዎች መረጋገጡን ምንጮች ይገልጻሉ። 

ቢራ ፋብሪካው ካለበት የግብር ዕዳ ውስጥ መቀጫና ወለዱ ተነስቶለት እንዲከፍል የተወሰነ ቢሆንም፣ ፋብሪካው ባለበት የጥሬ ገንዘብ እጥረት ምክንያት ይህንን ማድረግ እንዳልቻለ ምንጮች ገልጸዋል። 

ከዲያጆና ከፋብሪካው አመራሮች ጋር በተደረገ ውይይት ፋብሪካው በአሁኑ ወቅት ያለው የተጣራ ሀብት 60 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ ብቻ መሆኑን ማስታወቃቸውን አክለዋል።

ሌላኛው አማራጭ የነበረው መንግሥት ፋብሪካውን ተረክቦ እንዲያስተዳድር የሚል እንደነበርነገር ግን ከልምድ እንዲሚታየው ሽያጩን ለማከናወን ከሁለት ዓመት ያላነሰ ጊዜ የሚፈጅ በመሆኑና ይህም በመንግሥት ላይ የወጪ ጫና እንደሚያሳድር ከግምት ውስጥ በማስገባት ተቀባይነት ማግኘት አለመቻሉን ገልጸዋል።

የመጨረሻውና ብቸኛው አማራጭ ፋብሪካው ያለበትን አጠቃላይ ዕዳ በመንግሥት ምሕረት እንዲሰረዝ አድርጎ፣ ፋብሪካውን ለሌሎች ባለሀብቶች መሸጥ እንደሆነ ምንጮች ገልጸዋል። 

ይሁን እንጂ በኩባንያው ላይ ከሚፈለገው የግብር ዕዳ ውስጥ የኤክሳይስ ታክስና የተጨማሪ እሴት ታክስ በታክስ ሕጎች በተደነገገው መሠረት ኩባንያው ከማኅበረሰቡ የሰበሰበው በመሆኑ፣ ይህንን የግብር ዕዳ ቀሪ ማድረግ የሕጋዊነት ጥያቄ እንደሚያስነሳ አስረድተዋል።

ነገር ግን በዚሁ ማዕቀፍ ውስጥ የተሻለ መፍትሔ የያዘ የውሳኔ ሐሳብ ለመንግሥት መቅረቡን ምንጮቹ አስረድተዋል።

 

የተሻለ የተባለው የመፍትሔ አማራጭም ኩባንያው ባለፉት ዓመታት ባገኘው ትርፍ ላይ ሊከፍል ይገባ የነበረው 860.3 ሚሊዮን ብር የትርፍ ግብር ወለድና መቀመጫውን ጨምሮ በመንግሥት ምሕረት ቀሪ እንዲሆንበተጨማሪም ኩባንያው ባልከፈለው የኤክሳይስና የተጨማሪ እሴት ታክስ ላይ የተጣለው መቀጫና ወለድ በመንግሥት ምሕረት ቀሪ እንዲሆን በማድረግ ፋብሪካውን እንዲሸጥ የሚል እንደሆነ ምንጮች ጠቁመዋል።

በዚህ መንገድ ኩባንያው እንዲሸጥ በመወሰን ፋብሪካውን ለመግዛት ፍላጐት ያላቸው የውጭ ወይም የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ተበረታትተው ፋብሪካውን ሊገዙ እንደሚችሉ፣ ከሽያጩ የሚገኘውን ገንዘብም ምሕረት ላልተደረገበት የኤክሳይስና የተጨማሪ እሴት ታክስ ዕዳ መክፈያ እንዲውል የሚል ነው።

በዚህ መንገድ ከተወሰነ ኩባንያው ለመንግሥት መክፈል የሚጠበቅበት የኤክሳይስና የተጨማሪ እሴት ታክስ ዕዳው 942 ሚሊዮን ብር እንደሆነ ምንጮች አስረድተዋል።

በዚህ አማራጭ ላይ መግባባት ከተደረሰ በኋላ የውሳኔ ሐሳብ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅረቡን የገለጹት ምንጮችምክር ቤቱም በፋይናንስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 648/2009 (እንደተሻሻለ) አንቀጽ 13 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የውሳኔ ሐሳቡን ተቀብሎ ከሜታ አቦ ፋብሪካ ላይ የሚፈለገው የንግድ ትርፍ ግብር ዕዳ ከነእ ወለድና መቀጫው፣ እንዲሁም ባልተከፈሉ የኤክሳይስና የተጨማሪ እሴት ታክሶች ላይ የተመዘገበው ወለድና መቀጫ በምሕረት ቀሪ እንዲሆን መስከረም 12 ቀን 2014 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ መወሰኑን ምንጮች ገልጸዋል።

ጉዳዩን አስመልክቶ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካ ኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ሲሳይ ዘሪሁን፣ መረጃውን ሙሉ በሙሉ አስተባብለዋል፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ ሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካ የተጠቀሱት ችግሮች እንደሌሉበት፣ ኩባንያውም ባለፉት ሁለት ዓመታት በግብር ከፋይነቱ በመንግሥት መሸለሙን አስታውሰዋል፡፡

ሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካ በመንግሥት ባለቤትነት የተመሠረተና ለዓመታት በመንግሥት ይዞታ ሥር ከቆየ በኋላ፣ መንግሥት ወደ ግል ይዞታ ለማዘዋወር ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ በወጣው ጨረታ ያሸነፈው ዲያጆ የተባለው የእንግሊዝ ኩባንያ ... 2012፣ 225 ሚሊዮን ዶላር እንደገዛው ይታወሳል።

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች