Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህል‹‹ጊፋታ›› የወላይታ አዲስ ዓመት መግቢያ

‹‹ጊፋታ›› የወላይታ አዲስ ዓመት መግቢያ

ቀን:

‹‹ዮዮ ጊፋታ››  የወላይታ ባህል አዋቂዎችና ጥበበኞች የጨረቃን ዑደት ስሌት መሠረት በማድረግ ማኅበረሰቡ ከክረምት ወደ በጋ፣ ከጭጋጋማ ድባብ ወደ ብርሃናማ ዓውድ፣ ከአሮጌ ዓመት ወደ አዲስ ዓመት የሚደረገውን ሽግግር የሚያበስሩበት ነው፡፡ የአዲስ ዓመት ዕቅዳቸውና ጥረታቸው እንዲሳካ አምላክን የሚማፀኑበት የተስፋና የተምሳሌት በመሆኑ ጊፋታ በየዓመቱ ይከበራል፡፡   

የወላይታ ብሔር ዘመን የሚቆጥረው የጨረቃ ዑደትን ተከትሎ መሆኑን የሚገልጹት የጊፋታ አባት አቶ ኢያሱ ገጀቦ ናቸው፡፡

‹‹ጨረቃ የወር ዙረቷ 29 ቀን ይፈጅባታል፡፡ ይሄም ግማሽ ጨረቃ እና ግማሽ የፀሐይ ዙረትን ይቆጥራሉ፡፡ በአካባቢው የሚቆመውን ገበ በመቁጠር፣ በዓመቱ 364ኛ ቀን ላይ በሚውለው እሑድ ጊፋታ የሚውልበት ይሆናል፡፡ የወላይታ ብሔር ጊፋታን አንድ ብሎ የሚቆጥረው ከዕርድ ዕለት ጀምሮ ነው፤›› በማለት አቶ ኢያሱ ያስረዳሉ፡፡        

- Advertisement -

ጊፋታን የጀመረው የወላይታ ብሔር በኦሞ ሸለቆ ከሚኖሩት ቀደምት ሕዝቦች አንዱ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በወላይታ ዙሪያ የሚገኘው ‹‹ሞቼ ቦራጎ›› ዋሻ ከሰባ ሺሕ ዓመት በፊት የወላይታ ብሔር ይኖር እንደነበር ታሪክ አዋቂዎች ያወሳሉ፡፡ ሰለዚህም የወላይታ ብሔር ከዋሻ ወጥቶ በጋራ መኖር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ 30 ቀን ድረስ እያከበረ ያሳልፋል፡፡ ጊፋታን ከሃይማኖታዊ በዓላት ጋር ሲያያዝ ይስተዋላል፡፡ ሆኖም  ጊፋታ ከየትኛውም ሃይማኖታዊ ክንውኖች ጋር እንደማይያያዝና የወላይታ የትኛውም ተወላጅ በዓል እንደሆነ አቶ ኢያሱ ያስረዳሉ፡፡

የጊፋታ በዓል ማዕድ

ያከባበር ሥርዓት

ጊፋታ የራሱ የሆነ ያከባበር ሥርዓት አለው፡፡ ቁጠባ አንደኛው መገለጫ ነው፡፡ ይሄም በዓሉ በሚከበርበት ቀን ዕርድ ከተከናወነ በኋላ በእርጥብ ቆዳ ላይ ተቀማጭ ብር በማዋጣት፣ በሚደረግ የቁጠባ ሥነ ሥርዓት ነው፡፡ በቁጠባው ሴቶችም የምግብ ቅቤ ሲቆጥቡ፣ ወንዶች ገንዘብ ይቆጥባሉ፡፡

ጊፋታ መቃረቡ ከሚገለጽበት መንገድ አንዱ የጉልያ ሥርዓት ይጠቀሳል፡፡ ይሄም በአካባቢው ያሉ ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 30 የሚደርሱ ወጣቶች የጉልያ ሥነ ሥርዓት ያከናወናሉ፡፡ ጉልያ ማለት ወጣቶቹ ለደመራ የሚሆን እንጨት የሚለቅሙበትና የሚያዘጋጁበት ወቅት ነው፡፡ ጊፋታ መድረሱንና አለመድረሱን በአካባቢው የሚገኙ ሽማግሌዎች ተሰብስበው መች ቀን ላይ እንደሚውል አስልተው ከወሰኑ በኋላ ለንጉሡ ያሳውቃሉ፡፡ ንጉሡም ለአካባቢው ነዋሪ ካሳወቁ በኋላ በጉልያ ሥነ ሥርዓት ደመራና  የደመራ ቦታ ማዘጋጀትና ለጉልያ ምሰሶ ጉድጓድ መቆፈር እንዲሁም የተለያዩ ጭፈራዎች በወጣቶች ይከናወናሉ፡፡  ጉልያ በወጣቶች ከደመቀ በኋላ በእናቶች የሚከናወነው የእንሰት መፋቅ ሥነ ሥርዓት ይገኝበታል፡፡ በዚህም አባወራዎች ያዘጋጁትን እንሰት ለእናቶች እንዲፍቁ ይሰጣሉ፡፡

እናቶችም እንሰቱን ከልጆች፣ ከጎረቤት ሴቶች ጋር በጋራ ሆነው የእንሰት መፋቂያ (ወተታንና ማይሊያን) ይዘው እንሰቱን መፋቅና ማዘጋጀት ይጀመራሉ፡፡ ጊፋታ የዕርቅ፣ የሰላም እንዲሁም ለታላቅ የሚሰጥ በዓል ነው ተብሎ የሚታመን ሲሆን የመጀመርያ የወላይታ ወርም ጊፋታ ተብሎ ይጠራል፡፡

ጊፋታ ከመከበሩ ቀደም ብሎ አካባቢን ማፅዳት፣ ቤት ማደስና የዕርቅ ሥራ ትልቅ ቦታ አላቸው፡፡ በዚህም መሠረት የአካባቢው ሕፃናት ተሰብስበው፣ ሠፈር ቀዬውን ማፅዳት፣ ቤት ውስጥ የቆሸሸ ሰንበሌጥ፣ ሳጠራ እንዲሁም የከብቶች በረት ሳይቀር ይፀዳል፡፡

ጊፋታ የእርቃ በዓል መሆኑን ተከትሎ ለዕርቅ ቅድሚያ ይሰጣል፡፡ የተጣሉ ባለትዳሮች፣ ቤተሰቦች፣ ጎረቤቶች እንዲሁም የአካባቢው ሰው የሚታረቅበት ወቅት ነው፡፡ በጊፋታ ዕዳ ኖሮበት ያልከፈለ ካለም ያለበትን መክፈል ይኖርበታል፡፡ ከዚህም ባሻገር አዲስ ጎጆ ለመቀለስ የተጫጩም ካሉ ለቤተሰብ የሚያሳውቁበት ወቅት ነው፡፡

በጊፋታ የበሬ ግዥ የራሱ የሆነ ሥነ ሥርዓት ሲኖረው አንዱ ከሦስት ወር በፊት ግዥ የሚፈጽሙበት ሒደት ነው፡፡  በሬውን የሚገዛው ቡድን ዓምና የተዋጣውን ገንዘብ ይዞ ከገበያ ሙክት በሬ ገዝቶ ይመለስና በአካባቢው በሚኖር ሰው እንዲቀለብ ይደረጋል፡፡

ጊፋታ ከመድረሱ 15 ቀናት በፊት ሦስት ገበያዎች ይቆማሉ፡፡ እነዚህ ገበያዎች ከወትሮ ለየት ያሉ ይሆናሉ፡፡ ገበያዎቹም ቦቦዳና ጎሻ ገበያ በመባል ይጠራሉ፡፡

የሀራይቆ ገበያ ማኅበረሰቡ የጊፋታ በዓልን ታሳቢ አድርጎ ምርት በገፍ የሚያቀርብበትና የጋማ ከብትም ወገባቸው እስኪጎብጥ ድረስ ስለሚሸከሙ፣  ‹‹የጋማ ከብት የሚያጎብጥ›› ገበያ ተብሎ ይታወቃል፡፡ ሌላኛው ቦቦዳ ገበያ ሲሆን ገበያው ጥሩ መዓዛ ያለው ገብያ ተብሎ ይጠራል፡፡ በዚህም ገበያ ሁሉም ሰው በአቅሙ የሚያስፈልገውን የሚገዛበት ነው፡፡

በጎሼ ገበያ ደግሞ ሁሉም ገበያተኛ ቁርስ ሳይበላ በማለዳ የሚያቀናበትና የሚገዛው ነገር ሁሉ አዲስና የሚያምር የሚሆንበት ቀን ነው፡፡ በጎሼ ለሕፃናት ልብስ፣ ሎሚ፣ እንዲሁም ሴቶች የሚቀቡትን እንሾሽላ የሚገዛበት ነው፡፡

ከዚህም ባሻገር በጊፋታ የመጨረሻ ወይም መዳረሻ የዕርድ ቀን ላይ የሚውል ‹‹ቃያ›› የሚባል ገበያ አለ፡፡ ቃያ ገበያ ከሌሊቱ 10 ሰዓት እስከ ጠዋቱ 2 ሰዓት ድረስ የሚቆይ ገበያ ሲሆን በዕለቱም የተረሱ ግን መገብየት ያለባቸው ነገሮች የሚሸመትበት  ነው፡፡

የጊፋታ በዓል ማዕድ

ምግብ

ሌላኛው በጊፋታ የምግብ ሥነ ሥርዓትም የራሱ የሆነ ሥርዓት ሲኖረው ጊፋታ የሚከበርበት ቀን ከመቃረቡ በፊት እሑድን ማለማመጃ ምግብ ይዘጋጃል፡፡ በጊፋታ ቀን ቁርጥና ባህላዊ መጠጥ የሆነውን ቦርዴ ይጠጣል፡፡

በጊፋታ ለበዓሉ ድምቀት የሚውል ቅቤ፣ ሠንጋ በሬ፣ አልባሳት፣ ጌጣ ጌጦች፣ የስፌት፣ የሽክላ፣ የብረታ ብረት ምርቶችና ሌሎች ግባቶች የበዓሉ ድምቀት ናቸው፡፡

የዘንድሮ የጊፋታ በዓልም በወላይታ ዞን ሶዶ ከተማ በደማቅ ሥነ ሥርዓት ተከብሮ አልፏል፡፡ ቀድሞ በዞኑ ነዋሪዎች በድምቀት ይከበር የነበረው ጊፋታ፣ ዘንድሮ በኮቪድ-19 ወረርሽኝና አገሪቷ ያለችበት ሁኔታ በርካታ ሰዎች በተገኙበት ማክበር ባይቻልም በዓሉን በተለያዩ መሰናዶች ታስቦ እንዲውል ተደርጓል፡፡

መስከረም 15 ቀን 2014 ዓ.ም. በወላይታ ሶዶ የተከበረው ጊፋታ፣ በዓሉን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት ሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ለማስመዝገብ ሒደት ላይ መሆኑን የወላይታ ዞን ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል፡፡ በመድረኩም ሲሞፖዚየም አሰናድቶ እንዴት በዓሉን ማሳደግና በዩኔስኮ ማስመዝግብ እንደሚቻል ሲመክር ቆይቷል፡፡

   

   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...