Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርበግድቦች ምክንያት ሰው ሠራሽ ሐይቅ ሲፈጠር የዝናብ መጠን ስለሚጨምር ዝግጅት ያስፈልጋል

በግድቦች ምክንያት ሰው ሠራሽ ሐይቅ ሲፈጠር የዝናብ መጠን ስለሚጨምር ዝግጅት ያስፈልጋል

ቀን:

በግድቦች ምክንያት ሰው ሠራሽ ሐይቅ ሲፈጠር የዝናብ መጠን ስለሚጨምር ዝግጅት ያስፈልጋል

በመታሰቢያ መላከ ሕይወት

ይህንን ጽሑፍ ለማዘጋጀት ያነሳሳኝ ዋናው ምክንያት ዘንድሮ በቻይና ከፍተኛ የሚባል በታሪክ ተመዝግቦ የማያውቅ ዝናብ ዘንቦ ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት እንደደረሰ በዋና ዋና የዜና ምንጮች የተገለጸ ሲሆን፣ ለዚህ ችግር እንደ ዋና ምክንያት ተደርጎ የተወሰደው (በሳይንቲስቶች ማብራሪያ መሠረት) በአገሪቱ እየተካሄደ ያለው የግዙፍ ግድቦች ግንባታና ከዚያው ጋር ተያይዞ በተፈጠረው ከፍተኛ የውኃ ክምችት ምክንያት በገጸ ምድርና በከባቢ አየር ውስጥ ከፍተኛ እርጥበት በመሆኑ እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ቻይና እንደሚታወቀው በዓለም ትልቁ የሚባለው 22,400 ሜጋ ዋት የሚያመነጭ ግድብና በቅርቡ ያስመረቀችው 1,600 ሜጋ ዋት የሚያመነጩ ግድብ ባለቤት ስትሆን፣ እነዚህ ግድቦች በዓለም አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡ ናቸው፡፡

ሳይንቲስቶቹ ግን አስቀድመው በተገቢው መንገድ ያላጠኑት ያልተጠበቀ ክስተት በመፈጠሩ፣ በክረምት ወቅት ቻይና ውስጥ የሚጥለው ዝናብ መጠኑ እየጨመረ መጥቷል፡፡ ምንም እንኳን ቻይናዎች እነዚህን ሁለት ግዙፍ ግድቦች መገንባት በመቻላቸው ከፍተኛ መጠን ያለው የካርቦን ልቀት ማስወገድ ቢችሉም፣ በሚጥለው ከፍተኛ ዝናብ ምክንያት ያልጠበቁት ችግር እየገጠማቸው ነው፡፡

በግድብ ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው ውኃ ሲጠራቀም የዝናብ መጠን እንዴት ይጨምራል የሚለውን ጉዳይ እንመልከት፡፡

በመጀመርያ ደረጃ ዝናብ ለመፈጠር ምን ዓይነት ሁኔታዎች መፈጠር አለባቸው? የሚለውን ማየቱ ጠቃሚ ነው፡፡ ዝናብ የሚፈጠረው በውቅያኖስ ወለል ላይ በሚያርፈው የፀሐይ ብርሃን ምክንያት ከፍተኛ ትነት ሲነሳ፣ ከዚያም ትነቱ ወደ ላይኛው የከባቢ አየር ክፍል በሚተንበት ጊዜ ላይኛው የከባቢ አየር ክፍል በጣም ቀዝቃዛ በመሆኑ ትነት የነበረው ውኃ ክብደት ማግኘት ይጀምርና ወይም (Condensation) ይፈጥርና ወደ መሬት ወይም ወደ ውቅያኖስ ይዘንባል፡፡ ወይም በትነት መልክ ያለው ውኃ በንፋስ ይገፋና (እንደ ወቅቱ ሁኔታ) ወደ የተለያየ ቦታ ይጓዛል፡፡

በክረምት ወቅት ወደ አገራችን የሚገባው ከፍተኛ መጠን ያለው እርጥበት በወቅቱ የህንድ ውቅያኖስና የፓስፊክ ውቅያኖስ የባህር ወለል ሙቀት ስለሚጨምር፣ በተጨማሪም የንፋስ አቅጣጫ ወደ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ቦታዎች በመሆኑ ይህ እርጥበት ያዘለ ንፋስ ኢትዮጵያ ግዛት በሚደርስበት ጊዜ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ቦታዎቸ ምክንያት ወደ ላይኛው የከባቢ አየር ክፍል ስለሚገፋ፣ የበለጠ ይቀዘቅዝና ዝናብ ሆኖ መዝነብ ይጀምራል፡፡

አንዳንድ ጊዜ በጣም ወደ ከፍተኛው የከባቢ አየር ክፍል ስለሚገፋ በረዶ ሆኖ የሚወድቅበት ጊዜ አለ (Nature does not respect man made boundary) ይባላል፡፡ ተፈጥሮና የአየር ንብረት ከሰው ልጆች ትዕዛዝ ውጪ በራሷ መንገድ ያሰኛትን ታደርጋለች፡፡ ሰው የሠራው ድንበር ተፈጥሮን አግዳትም፡፡

ዝናብን ለመፍጠር ከውቅያኖስ የሚነሳው እርጥበት ብቻ ሳይሆን፣ ከጥቅጥቅ ደኖችና በአገሮች ውስጥ ካሉ እርጥበት ካላቸው ቦታዎች ሁሉ እርጥበት ወደ ከባቢ አየር ስለሚተን፣ እነዚህ ትነቶች ተደምረው በሚፈጥሩት ጠንካራ ወይም ዝናብ አምጪ ደመናዎች ምክንያት ዝናብ ይፈጠራል፡፡

ብዙ ጊዜ ከፍተኛ ተራሮች ባሉበት ቦታ በጣም የሚቀዘቅዘው በተራራው ዙሪያና በተራራው አናት ላይ ሁልጊዜ እርጥበት (Moisture) ያለ በመሆኑ የፀሐይ ብርሃን ወደ መሬት መውረድ ቢችልም፣ የፀሐይ ሙቀት ግን ከፍተኛ ቦታዎች መድረስ አይችልም፡፡ ምክንያቱም በዓይን የማይታይ ደመና ወይም እርጥበት በመኖሩ የፀሐይን ሙቀት ወደ ምድር እንዳይደርስ ያደርገዋል፡፡

በተቃራኒው በጣም ዝቅተኛ በሆነ ቦታ እርጥበት በአመዛኙ የሌለ በመሆኑ የፀሐይ ብርሃን በቀላሉ ወደ ምድር መድረስ ስለሚችል ሙቀትም፣ ብርሃንም ሁል ጊዜ ይኖራል፡፡

በግድብ ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው ውኃ ሲጠራቀም በፊት ደረቅ የነበረ መሬት አሁን ከፍተኛ የሚባል እርጥበት ስለሚኖረው ‹‹Moisture›› መፈጠር ይጀምራል፡፡ በዚህን ጊዜ በፊት ያልነበሩ ዕፅዋቶች መብቀል ይጀምራሉ፡፡ ብዝኃ ሕይወት ይስፋፋል፡፡ በሐይቁ ዙሪያ ደግሞ ዓመታዊ ምዝን የአየር እርጥበት በአንድ ወይም ሁለት ዲግሪ መቀነስ ይጀምራል፡፡

በሐይቁ ዙሪያ ከፍተኛ የሆነ የውኃ ሥርገት ይፈጠራል፡፡ ከግድቡ የሚነሳው መጠኑ ከፍተኛ የሆነ እርጥበት ከውቅያኖስ ከመጣው እርጥበት ጋር በሚደመርበት ወቅት (ሐይቁ ከመፈጠሩ በፊት ኢትዮጵያን አልፎ ወደ ሌላ አገር ይሄድ የነበረው ደመና) ክብደት ያገኝና ወደ ዝናብነት ይለወጣል፡፡ ይህ ሁኔታ ወደ ፊት እስከ ምዕራብ አፍሪካ ያሉ አገሮች የዝናብ መጠን ቀነሰብን ብለው ቅሬታ ሊያቀርቡ የሚገደዱበት ሁኔታ ሳይፈጥር አይቀርም፡፡

በሌላ አነጋገር ኢትዮጵያ ውስጥ እየተገደቡ ያሉት ግድቦች ደመና ወደ ዝናብነት የመለወጥ አቅም ይፈጥራሉ ማለት ነው፡፡

እስካሁን ባለኝ መረጃ ዓባይ ግድብ ተገድቦ ሲልቅ ሊኖር ስለሚችለው የዝናብ መጠን መጨመር፣ ወይም በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ወደፊት በርካታ ግድቦችን ኃይል ለማመንጨት፣ ጎርፍ ለመቆጣጠር፣ ለመስኖ ሥራ፣ ለከተሞችና ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚሆን ውኃ ስታጠራቅም ሊፈጠር ስለሚችለው የአየር ንብረት ለውጥ የተባለ ነገር መኖሩን፣ ወይም የተጠና ጥናት መኖሩን የሰማሁት ነገር የለም፡፡ ነገር ግን ጉዳዩ አሳሳቢ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

በድሮ ዘመን ከተጻፉ መጻሕፍት መረዳት እንደሚቻለው፣ በአሁኑ ጊዜ ዝቅተኛ የውኃ መጠን ያላቸው ወንዞቻችን ድሮ የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ከፍተኛ የነበረ በመሆኑ፣ የወንዞቹ የመሙላት መጠንም ከፍተኛ እንደነበረ ተደጋግሞ ተጽፏል፡፡ ስሜን ተራራ የበረዶ ክምር እንደነበር የተጻፉ ሰነዶች አሉ፡፡

አሁን ኢትዮጵያን በደን ለመሸፈን የተሳካ ሥራ ከሠራን፣ በርካታ ግድቦችን ከገደብን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚጥለው ዝናብ መጨመሩ ስለማይቀር ሱዳኖችና ግብፆች እስካሁን እንደሚሉት በግድቡ ምክንያት የውኃ እጥረት ይገጥመናል ሳይሆን፣ ከመጠን ያለፈ ውኃ እያመጣብን ነው ማለታቸው አይቀርም፡፡

እንደሚታወቀው በክረምት ወቅት ከህንድና ከፓስፊክ ውቅያኖስ የሚመጣው እርጥበት ኢትዮጵያ ከፍተኛ ተራሮች ጋር ሲደርስ ወደ ላይኛው የከባቢ አየር፣ ማለትም ከፍተኛ ቅዝቃሴ ወዳለው ከፍታ ሲገፉ ደመና ይሆንና ወደ ኢትዮጵያ ውስጥ ይዘንባል፡፡ ወይም ደግሞ ጉዞውን በንፋስ እየተገፋ ወደ ምዕራብ አፍሪካ እስከ አትላንቲክ ውቅያኖስ ይጓዛል፡፡ አልፎ አልፎ እስከ ምሥራቃዊው የሰሜን አሜሪካ ክፍል በመጓዝ ብዙ ውድመት ያስከትላል፡፡

በአትላንቲክ ውቅያኖስ በተደጋጋሚ የሚፈጠረው ‹‹ሔሪከን›› ተብሎ የሚጠራው  የባህር ማዕበል ወይም ወጀብ በአብዛኛው የሚፈጠረው፣ ወይም መነሻው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ተራሮች ናቸው፡፡ ግድቦች በሚሠሩበትና ውኃ መያዝ በሚጀምሩበት ጊዜ የሚፈጠረው ሐይቅ ብቻ ሳይሆን፣ በሐይቁ ዙሪያ እስከተወሰነ ኪሎ ሜትር ድረስ እርጥበት ይኖራል፣ ልምላሜ ይኖራል፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያው ጣና ሐይቅና በዙሪያው ያለውን ልምላሜ መመልከት ይበቃል፡፡

እዚህ ላይ የግድ መታወቅ ያለበት ነገር በርካታ ግድቦች በገነባንና ሰው ሠራሽ ሐይቅ በተፈጠረ ቁጥር ኢትዮጵያ የምታገኘው ዝናብ ሲጨምር፣ ተጠቃሚ ትሆናለች እንጂ ብዙ አገሮች ውስጥ እንደምናየው ይዞት የሚመጣው ጉዳት የለም፡፡ ምክንያቱም ውኃው በፍጥነት ወደ ሸለቆዎች ውስጥ ስለሚገባ በንብረት ላይ የሚደርሰው ጉዳት አይኖርም፡፡ ጉዳት የሚያደርሰው ሸለቆ የሌላቸው፣ ወደ ግዛታቸው የገባውን ውኃ ገድበው መያዝ የማይችሉ አገሮች ወይም የውኃ ባንክ የሌላቸው ጎረቤቶቻችን ናቸው፡፡

በተጨማሪ ሳይንቲስቶች በተደጋጋሚ እንደሚነግሩን በከባቢ አየር ሙቀት መጨመር ምክንያት ከውቅያኖሶች ተነስቶ ወደ ኢትዮጵያ የሚገባው እርጥበት ያዘለ አየር በሚቀጥሉት ጊዜያት እስከ 20 በመቶ ሊጨምር የሚችል ሲሆን፣ እኛ ደግሞ አሁንና ወደፊት በምንገነባቸው ግድቦች ምክንያት በከፍተኛ መጠን እርጥበት መያዝ አቅም ስለምንፈጥር፣ ወደፊት ባሉት ዓመታት ሊኖር የሚችለው የዝናብ መጠን እየጨመረ ይሄዳል እንጂ መጠኑ የሚቀንስበት ሁኔታ አይፈጠርም፡፡ ይህ ጉዳይ በዓባይ ግድብ ምክንያት የድርድሩ አጀንዳ መሆኑን የሰማሁት ነገር የለም፡፡ ካልሆነ ግን አጀንዳ መሆኑ ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ሰው መላ ኢትዮጵያን በአውሮፕላን ቢጎበኝ በደቡብ የአገራችን ክፍል ካልሆነ በስተቀር ጥቅጥቅ ያለ ደን ማየት ብዙም አይቻልም፡፡ አብዛኛው ሰሜኑና የሰሜን ምዕራብና ምሥራቃዊ ክፍል በደን የተሸፈነ መሬት ማየት ያስቸግራል፡፡ ይህ የሆነበት ዋናው ምክንያት መንግሥት ዜጎች የደን ባለቤት መሆን የሚችሉበት ሥርዓት መዘርጋት ባለመቻሉ፣ በደኖች ልማት ዜጎች በባለቤትነት ስሜት መሥራት ባለመቻላቸው፣ ደን የማልማት፣ ባለቤት የመሆን፣ ቆርጦ የመሸጥ ወይም ደኑን አልምቶ ሳይቆረጥ ለሌላ ወገን በመሸጥ ተጠቃሚ መሆን የሚችሉበት ሥርዓት ባለመኖሩ የአገራችን ደን ሊያገግም የሚችልበት ሁኔታ እስካሁን አልተፈጠረም፡፡ ወደፊት ይህ ሁኔታ ከተቀየረና ዜጎች ደን የማልማት መብታቸው ከተከበረ፣ አገራችን ያሏትን ተራራማ ቦታዎች ሁሉ በደን በመሸፈን ተጨማሪ ዝናብ እንድታገኝ ማድረግ በጣም ቀላል ነው፡፡

አሁን በዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እየተመራ ያለው ችግኝ የመትከል ተግባር ዛፉን በባለቤትነት ስሜት የሚንከባከበው ሰው ባለመኖሩ ገንዘብ ማባከኛ ከመሆኑ በቀር ለአገር ምንም የሚፈይደው ነገር የለም፡፡ እኔ በምኖርበት አካባቢ ባለፉት ዓመታት የተተከሉት ችግኞች ሙሉ በሙሉ በከብቶች ተሰባብረዋል፣ ወይም ቀንጭረው ቀርተዋል፡፡ በተጨማሪም የደን ልማት ሳይንስን ተከትለው የተተከሉ ባለመሆናቸው መቼም አድገው ዛፍ አይሆኑም፡፡

በትልልቅ ሰው ሠራሽ ሐይቆች ምክንያት እርጥበት ካለ ዛፍ እንኳን መብቀል ባይችል፣ ሥር መብቀሉ ስለማይቀር የተፈጥሮ ሚዛን እንዲጠበቅ ታላቅ ጠቀሜታ አለው፡፡ ሳር ደግሞ የከብቶች ምግብ ነው፡፡ እኛ ሰዎች ደግሞ ከብቶቹ የማንበላውን ሳር ወደ ሥጋ ስለሚለውጡልን የምግብ ዋስትናችን እየተሻሻለ ይሄዳል፡፡ እኛ ኢትዮጵውን ያልተዘመረለት አንዱና ትልቁ ሀብታችን ሳር ነው፡፡ ኢትዮጵያ በአፍሪካ በሳር ሀብት አንደኛ ነች፡፡ ለዚህ ነው በከብቶች ብዛት አንደኛ የሆንነው፡፡

በብዙ አገሮች የሳር ሀብት አለ፡፡ ነገር ግን በረዶ የሚጥል ከሆነ ወይም የተራዘመ የበጋ ወቅት ካለ ሳር ማግኘት ስቸግራል፡፡ እኛ ኢትዮጵያውን ዓመቱን ሙሉ ከብቶቻችን ሳር መጋጥ ይችላሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ገበሬዎች የግጦሽ መሬት አጥር እያጠሩ፣ ውኃ እያጠጡ፣ የሳር ሀብት እንዲጨምር የማድረግ አሠራር አልተጀመረም፡፡ ነገር ግን ዓመቱን ሙሉ ሳር እያመረተ ለገበያ ያቀርባል፡፡ የግጦሽ መሬት የመንከባከብና የማልማት ባህል ቢዳብር ደግሞ የአገራችን የሥጋ ምርት በከፍተኛ ሁኔታ ሊጨምር ይችል ነበር፡፡

መንግሥት የገጠር መሬት ባለቤትነትን ማክበር ባለመቻሉ፣ አገራችን በከፍተኛ ሁኔታ ተጎጂ ሆናለች፡፡ ገበሬው በይዞታው ሥር ያለን መሬት በማንኛውም ጊዜ ማልማት፣ ለልጆች ማውረስ፣ መሸጥ መለወጥ እችላለሁ ብሎ ስለሚያምን እጁ ላይ የገባን ገንዘብ መሬቱ ላይ ኢንቨስት እያደረገ መሬቱ የተሻለ ዋጋ እንዲወጣ እያደረገ አይደለም፡፡ እኔ በግሌ ኢትዮጵያ ውስጥ በግለሰብ ደረጃ የለማ የደን መሬት መኖሩን አላውቅም፡፡ አገራችንን ክፉኛ የጎዳት የተፈጥሮ ሀብት ዕጦት ሳይሆን በተከታታይ ወደ ሥልጣን የመጡ ከደረጃ በታች የሆኑ መሪዎች ናቸው፡፡

በአጠቃላይ የግለሰብ ታሪክ ሠሪነትን፣ የግለሰብ ለአገር ዕድገት ትልቁን ድርሻ እንዳለው ያልተገነዘበ መንግሥት መቼም ውጤት ማስመዝገብ አይችልም፡፡ አሁን እየሠራናቸው ያሉና ወይም ወደፊት ልንሠራቸው ያሰብናቸውን ግድቦች ከደለል ልንታደግ የምንችው እያንዳንዱ የመሬት ክፍል ባለቤት ኖሮት፣ ባለቤቱ ተግቶ እየሠራና መሬቱ እንዳይሸረሸር ማድረግ ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ማንም ሰው በይዞታው ሥር ያለን መሬት አንድ ግራም አፈር እንድትሸረሸር አይፈልግም፡፡

ሌላው ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ መንግሥትና ክልሎች በየወንዙና ጅረቱ ቁመታቸው ከአንድ ሜትር እስከ አምስት ሜትር ከፍታ ያላቸው ትንንሽ ግድቦች በመገደብ፣ ደለል ማጥመድና በበጋ ወቅት ገበሬዎች የተከማቸውን ደለል እየወሰዱ መሬታቸው ላይ እንዲበትኑ በማድረግ የማዳበሪያ ወጪን መቀነስ ከመቻሉም በላይ ግድቦቻችንን የአገልግሎት ዘመን በከፍተኛ ደረጃ መጨመር ይቻላል፡፡

አንድ ተወዳጅ አባባል አለ፡፡ ‹‹ተፈጥሮ ሰዎች ኖሩም አልኖሩም መቀጠል ትችላለች፣ ሰዎች ግን ያለ ተፈጥሮ መኖር አይችሉም፤››፡፡ እኛ በአሁኑ ጊዜ እያደረግን ያለነው ለህልውናችን መሠረት የሆነውን ተፈጥሮን ባለቤት በማሳጣት እያወደምነው ነው፡፡ መሪዎቻችን ይህንን አባባል መቶ ጊዜ ቢነገራቸውም አይገባቸውም፡፡ ሌላው መሪዎቻችን ላለፉት 50 ዓመታት ያልገባቸው ነገር መሬት ባለቤት ሲኖረውና መሸጥ፣ መለወጥ ሲጀምር እጅግ በርካታ የሥራ ዕድልና ከፍተኛ የታክስ ገንዘብ የማመንጨቱ ጉዳይ ነው፡፡ አንድ ሰው የገጠር መሬት ለመግዛት ሲያስብ መጀመርያ ዕቅድ ይዞ ነው ወደ ግዥ የሚሄደው፡፡ ያንን ዕቅዱን ሥራ ላይ ለማዋል የሰው ጉልበት ስለሚያስፈልገው ሰው ይቀጥራል፣ የሥራ ዕድል ይፈጥራል፡፡ መሬቱን ሲገዛ ደግሞ የታክስ ገቢ ለክልሉ ያመነጫል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ የልማት እንቅስቃሴ የግድቦች ግንባታ ነው፡፡ ነገር ግን የጎንዮሽ ክስተቶች በአግባቡ እየተጠኑ ነው ማለት አይቻልም፡፡ በእንግሊዝኛ አጠራር (Undsirable Effect or Unforseen Condition) የሚባለው ሁኔታ ሰፊ ሥራ የሚፈልግ ጉዳይ ነው፡፡ ብዙ አገሮች በቀላሉ ወደ ልማት የሚወስዳቸው የተፈጥሮ ሀብት አላቸው፡፡ ነዳጅ፣ ቱሪዝም፣ የተለያዩ ማዕድናት፣ ወዘተ ኢትዮጵያ ደግሞ ግድቦችን በመገንባት በቀላሉ ሀብት መፍጠር ትችላለች፡፡ አንድ ግድብ ተገድቦ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ በኋላ፣ ከአምስት እስከ አሥር ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ዕዳውን ከፍሎ ይጨርሳል፡፡ ከዚህ በኋላ በጣም በዝቅተኛ ወጪ ከፍተኛ ትርፍ የሚያስገኝ የልማት ዘርፍ ነው፡፡

ነገር ግን ኢትዮጵያ ግድብ ገንብታ ኃይል ማመንጨት የቻለችው ወንዞች ስላሏት ሳይሆን፣ ወንዞቹ ጥልቅ በሆነ ሸለቆ ስለሚያልፉና በቀላል ውኃን ማከማቸት ስለሚቻል ነው፡፡ ብዙ አገሮች ከእኛ ወንዞች የሚበልጡ ከፍተኛ የውኃ መጠን ያላቸው ወንዞች አሏቸው፡፡ ሸለቆዎች ግን የሏቸውም፡፡ ኢትዮጵያ 65 በመቶ የአፍሪካ ከፍተኛ ቦታዎች ባለቤት ነች፡፡ አፄ ምኒልክ በዙሪያቸው ያለውን ከፍተኛ ቦታና በተወሰነ ደረጃ ዝቅተኛ ቦታዎችን ሰብስበው የኢትዮጵያ ግዛት አድርገዋል፡፡ ይህ ትውልድ በአፄ ምኒልክ አመራር ምክንያት እጃችን የገባውን መሬት አልምተን፣ እሴት ጨምረን፣ ለልጆቻችን ማውረስ ሲገባን፣ አፄ ምኒልክን በመሳደብ ጊዜያችንን እናባክናለን፡፡ ቤታችን ገብተን መብራት ስናበራ መብራቱ አፄ ምኒልክ ወረው ከያዙት ቦታ መንጭቶ እንደሚመጣ እንኳን መገንዘብ ተስኖናል፡፡

ግድብ የሚገደበው ለበርካታ ምክንያቶች ነው፡፡ ኃይል ለማመንጨት፣ ጎርፍ ለመቆጣጠር፣ ለመስኖና ለከተሞች አገልግሎት የሚውል ውኃ ለማግኘት፣ ለመዝናኛ የሚሆን ሐይቅ ለመፍጠር፣ ዓሳ ለማርባት፣ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆን ከፍተኛ መጠን ያለው ውኃ ለማግኘትና ደለል ለመያዝ ወይም ለማጥመድ፣ ወዘተ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ከላይ የተጠቀሱትን ሁሉንም ዓይነት ግድቦች መገንባት ይቻላል፡፡ ሁሉም ደግሞ ከፍተኛ የሚባል ጥቅምና መለስተኛ የጎንዮሽ ጉዳቶች አሏቸው፡፡ ከእነዚህም አንዱ የተለያዩ ነፍሳቶች በቀላሉ ስለሚራቡ የተለያዩ የጤና ችግሮች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ ሰው ሠራሽ ሐይቆች በሚፈጠሩበት ቦታ ሌላው ትልቁ ጥቅም በውኃው ዙሪያ በርካታ ሰዎችን በማሥፈር አዲስ የኢኮኖሚ ዞን ወይም ቀጣና መፍጠር መቻሉ ነው፡፡ ውኃ ካለ ሕይወት አለ፡፡ ውኃው ደግሞ ጨዋማ ያልሆነ በመሆኑና ለሰው ልጆች ፍጆታ ስለሚውል በቀላሉ ጥቅም ላይ ማዋል ይቻላል፡፡

በርዕሱ እንደተጠቀሰው ወደፊት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚዘንበው ዝናብ መጠን የሚጨምር ከሆነ፣ ገበሬዎችም አዲስ የሚከሰተውን የዝናብ አዘናነብ ወቅት ተከትለው መጓዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ምናልባት ዝናቡ እስከ ጥቅምት ሊዘልቅ ይችላል፡፡ እየደረቀ ያለን ሰብል ከዘነበበት ችግር ሊፈጠር ይችላል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በሰው ሠራሽ ድርጊቶች ተፈጥሮ እየተናጋ ነው፡፡ እኛ የምንገነባው ግድብም በተወሰነ ሁኔታ ተፈጥሮን ሊያናጋ ይችላል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተፈጠረው ከፍተኛ መጠን ያለው የካርቦን ልቀት መሠረት ዕፅዋቶችን እየመጠጡ ወደ ኦክስጂን ከሚለውጡት የካርቦን መጠን በላይ እየተፈጠረ በመሆኑ፣ ደንን ማልማት በመላው ዓለም የሞት የሽረት ጉዳይ ሆኗል፡፡ የዓለማችንን 20 በመቶ ኦክስጂን የሚያመርተው የብራዚል ጥቅጥቅ ደን በከፍተኛ ውድመት ላይ ነው፡፡ በሰው ሠራሽ የተፈጥሮ ሚዛን መዛባት ምክንያት ብዙ አገሮች በየዓመቱ በሰደድ እሳት፣ በጎርፍ አደጋ፣ በበረዶ ክምር ከፍተኛ ውድመት እየደረሰባቸው ነው፡፡ የዓለማችን ኃያሏ አገር አሜሪካ በየዓመቱ በሰደድ እሳት ትነዳለች፡፡

የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ወደፊት በተከታታይ በሰው ሠራሽ ችግር በሚፈጠረው የተፈጥሮ ሚዛን መናጋት፣ ኢትዮጵያ ብዙም ጉዳት ይደርስባታል ብዬ አላምንም፡፡ ምክንያቱም ከፍተኛ የዝናብ መጠን በሚፈጠርበት ጊዜ (አቅም በፈቀደ መጠን ቶሎ ቶሎ በርካታ ግድቦችን ከገነባን) የጣለው ከፍተኛ ዝናብ ወደ ሸለቆዎች እየገባ፣ ከዚያም በግድቦች ውስጥ የሚጠራቀም ከሆነ በኢኮኖሚ ላይ እምብዛም ጉዳት አያደርስም፡፡

አዲስ አበባን ብንመለከት አልፎ አልፎ ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ ይዘንባል፡፡ በተደጋጋሚ የሚደርሰው ችግር የመንገድ መዘጋጋት ነው፡፡ ይህ የሚሆነው የውኃ መፍሰሻ ቱቦዎች በቆሻሻ ስለሚዘጉ ውኃው ለብዙ ጊዜ መንገድ ላይ ስለሚቆይ እንጂ፣ ከተማዋ ዘቅዛቃ በመሆኗ በርካታ ሸለቆ ያላቸው ወንዞች በመኖራቸው ውኃው በፍጥነት ሸለቆ ውስጥ እየገባ ወደ አዋሽ ይጓዛል እንጂ ምንም ጉዳት አድርሶ አያውቅም፡፡ በተቃራኒው ካርቱም ከተማ ለጥ ያለ ሜዳ ላይ ስለተገነባች በየዓመቱ ከፍተኛ ኪሳራ የሚያስከትል አደጋ ይደርሳል፡፡

በአጠቃላይ አንድ አገር ሀብታም ከሚያደርጋት ነገር አንዱ ወኃን የመያዝ ብቃት ነው፡፡ ግድብ መገንባት ደግሞ ውኃ የመያዝ ብቃትን ያሳድጋል፡፡ ወደፊት መገንባት ከሚገባቸው ግድብ ዓይነቶች አንዱ እንደ ዓባይ ላሉ የአገራችን ዝቅተኛ ቦታ የተገነቡ ግድቦች በበጋ ወቅት ውኃ እንዳያጥራቸው ከፍተኛ ቦታ ውኃን አከማችቶ በመያዝ፣ በበጋ ወቅት የተከማቸውን ውኃ በመልቀቅ ታች ያለው ግድብ በቂ ውኃ እንዲኖረውና በቂ ኃይል ማመንጨት እንዲቻል የማድረግ ተግባር ነው፡፡ ይህ ተግባር የአዋጪነት ጥናት ምን ሊሆን እንደሚችል መረጃው ባይኖረኝም ሳስበው ጥሩ ሐሳብ ይመስለኛል፡፡

ኢትዮጵያ ባላት ከፍተኛ ቦታዎች ምክንያት ደመና አምርታ ለራሷና እስከ ምዕራብ አፍሪካ ላሉ አገሮች ዝናብ እንዲፈጠር ምክንያት የሆነች አገር ነች፡፡ በሰሜን ላሉት ሱዳንና ግብፅ ደግሞ ደመናውን ወደ ውኃ (ዝናብ) ቀይራ ትልክላቸዋለች፡፡ እነሱ ግን አንድም ዓይነት ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ሙከራ ሳያደርጉ ሁሌም እንቅፋት ይፈጥራሉ፡፡

ግብፅና ሱዳን ኢትዮጵያ መጥተው አንድ ችግኝ ተክለው አያውቁም፡፡ በዓባይ ተፋሰስ ዙሪያ ላሉ ገበሬዎች መሬታቸውን በአግባቡ እንዲይዙ የገንዘብ ድጋፍ አድርገው አያውቁም፡፡ ኢትዮጵያ መንግሥት ግብፅና ሱዳን ስለመብታቸው ብቻ ሳይሆን ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ግፊ ማድረግ አለበት፡፡

የዓባይ ወንዝን ልክ እንደ ዕድር ላም እንውሰደውና ዕድርተኞቹ ተሠልፈው ወተት ማለብ ብቻ ሳይሆን ያለባቸው፣ ላሚቷ የምትፈልገውን ነገር ሁሉ በአግባቡ ማድረግ ስላለባቸው፣ ይህ ተግባር በሦስቱም አገሮች እንዲከበር ጥረት ማድረግ ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ የዓባይ ወንዝ ከ300 ሚሊዮን በላይ ለሆኑ አፍሪካውያን የሕይወት መሠረት ነው፡፡ በመሆኑም ተገቢውን እንክብካቤ ማድረግ ግድ ይላል፡፡ በየዓመቱ ይዞት የሚሄደው ደለል መጠን እየጨመረ እንጂ ሲቀንስ አልታየም፡፡ አሁንም በድጋሚ እያንዳንዱ የመሬት ክፍል ባለቤት ይኑረውና ተንከባካቢ አግኝቶ ከደለል የፀዳ ውኃ ብቻ ዓባይ ወንዝ ውስጥ ይግባ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...