- የከተማ አስተዳደሩን አስፈጻሚ አካላት መልሶ ለማደራጀት የተዘጋጀውን ረቂቅ አዋጅ አፅድቋል
አዲስ የተመሠረተው የአዲስ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት በመሥራች ጉባዔው፣ የከተማዋን ከንቲባ ምርጫ ጨምሮ የተለያዩ ውሳኔዎችንና የአስፈጻሚ አካላትን መልሶ ለማደራጀት የተዘጋጀውን ረቂቅ አዋጅ በማፅደቅ በይፋ ሥራ ጀመረ፡፡
ምክር ቤቱ የመጀመሪያውን መሥራች ጉባዔውን ዕድሳት በተደረገለትና ማዘጋጃ ቤት ውስጥ በሚገኘው የቴአትርና የባህል መሰብሰቢያ አዳራሽ፣ ማክሰኞ መስከረም 18 ቀን 2013 ዓ.ም. አከናውኗል፡፡
አዲሱ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ከዚህ ቀደም የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩትን ወ/ሮ ቡዜና አልቃድርን በቀጣይ አምስት ዓመታት የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤትን በአፈ ጉባዔነት እንዲመሩ የመረጠ ሲሆን፣ ወ/ሮ ፈይዛ መሐመድ ደግሞ በምክትል አፈ ጉባዔነት ተመርጠዋል፡፡
ምክር ቤቱ ከአፈ ጉባዔና ከምክትል አፈ ጉባዔ ምርጫው በመቀጠል ከተማዋን ለቀጣይ አምስት ዓመታት የሚመሩትን ከንቲባ የመረጠ ሲሆን፣ በዚህም መሠረት ያለፉትን አንድ ዓመት የከተማዋ ምክትል ከንቲባ በመሆን ያገለገሉትን ወ/ሮ አዳነች አቤቤን በቀጣይ አምስት ዓመታት አዲስ አበባ ከተማን በከንቲባነት እንዲመሩ በሙሉ ድምፅ መርጧል፡፡
ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በአዲሱ ምክር ቤት ቀርበው ቃለ መሃላ በፈጸሙበት ወቅት ባደረጉት ንግግር፣ የከተማዋን ዕድገት ለማሳካት የኅብረተሰቡን አዳጊ ፍላጎት ታሳቢ በማድረግ በትጋት እንደሚሠሩ ገልጸው፣ በከፍተኛ ድህነት ውስጥ የሚኖረውን፣ የኑሮ ውደነት ዋነኛ ገፈት ቀማሽ የሆነውንና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚኖረውን የከተማዋን ነዋሪ ሕዝብ ከድህነት ለማውጣት በቁርጠኝነት እንሠራለን ብለዋል፡፡
ከንቲባዋ በንግግራቸው እንዳመላከቱት የአዲስ አበባን የመሠረተ ልማት፣ የመኖሪያ ቤት አቅርቦት፣ የውኃ፣ የመብራትና የስልክ አገልግሎቶችን ለማሳደግ በትጋት እንደሚሠራ አስታውቀው፣ ለወጣቶችና ለሴቶች ልዩ ትኩረት በመስጠት ርብርብ እንደሚደረግ፣ የሥራ ፈጠራና ኢንዱስትሪ ልማት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ፣ በከተማዋ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር በቁርጠኝነት እንደሚሠራ፣ ሕዝቡ የሚሳተፍባቸው የተለያዩ አደረጃጀቶች ተግባራዊ እንደሚደረጉ አስታውቀዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ጥራትና ተደራሽ የሆነ የጤና ሥርዓት ተግባራዊ እንደሚደረግ በንግግራቸው ያወሱት ወ/ሮ አዳነች፣ ጥራቱ የተጠበቀ ትምህርት ተግባራዊ በማድረግ፣ አረጋውያንን ታሳቢ ያደረጉ ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ተደራሽ እንዲሆኑ በማድረግ አዲስ አባባን የባህል ማዕከል ለማድረግ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ገልጸዋል፡፡
ምክር ቤቱ በነበረው የመጀመሪያ ቀን ውሎ የከተማ አስተዳደሩን አስፈጻሚ አካላት መልሶ ለማደራጀት በተዘጋጀውና 101 አንቀጾች ባሉት ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎች አሳልፏል፡፡
በምክር ቤቱ ቀርቦ የፀደቀው ረቂቅ አዋጅ ባለፈው ምክር ቤት 61 የነበሩትን አጠቃላይ የአስፈጻሚ አካላት በአዲሱ ምክር ቤት 46 አድርጎ ያቀረበ ሲሆን፣ የካቢኔ አባላት ቁጥርን እንዲሁም በከንቲባዋ እንደ አስፈላጊነታቸው የሚሰየሙ ሌሎች ተቋማትን ጨምሮ አዳዲስ የካቢኔ አባላት የሆኑ ተቋማትን የያዘ ነው፡፡
ረቂቅ አዋጅ ከመፅደቁ በፊት በምክር ቤቱ አባላት የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየት የቀረበበት ሲሆን፣ ከዚህም ውስጥ ረቂቁ ቀደም ብሎ ለአባላቱ ቀርቦ ሰፊ ውይይቶች ሊደረጉበት እንደሚገባ፣ የአስፈጻሚ አካላት ስያሜ ድቅል መሆን ከሥራ ባህሪያቸው አንፃር ተመሳሳይ ተግባራት የሚያከናውኑ ተቋማት ቢዋሀዱ፣ የተቋማት አመራር ስብጥር በሃይማኖት፣ በብሔርና በፆታ ረገድ ምጣኔው ምን ይመስላል? የሚሉት ይገኛሉ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባና ምክትል ከንቲባ በመሆን የተመረጡት ወ/ሮ አዳነች አቤቤና አቶ ጃንጥራር ዓባይ በቀረቡት ጥያቄዎች ላይ ምላስ ሰጥተዋል፡፡ ቀደም ሲል ወደ 60 የሚጠጉትን መዋቅሮች ቁጥራቸው ዝቅ እንዲል የተደረገው በዋናነት ተበታትነው ሲሰጡ የነበሩትን አገልግሎቶች ለመሰብሰብ እንደሆነ፣ ምንም እንኳን እንደ መንገድና ትራንስፖርት ያሉት አገልግሎቶች የአንድነት ባህሪ ቢኖራቸውም ተቋማቱ የሚያከናውኗቸው ተግባራት ሰፊ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ በተናጠል እንዲሠሩ የተደረገበትን ሁኔታ አስረድተዋል፡፡
ከዚህ በሻገር በቀጣይ የሚደረጉ የአዋጅ ማፅደቅና ተያያዥ ጉዳዮች አዲስ በተመሠረተው ምክር ቤት ሰፊ ውይይት እንደሚደረግባቸውና የኅብረተሰብ ተሳትፎ ግብረ መልስ ላይ የተመረኮዘ እንደሚሆን የተጠቀሰ ሲሆን፣ ሆኖም ረቂቅ አዋጁን በማዘጋጀት ሒደት ላይ ከፍተኛ የዘርፍ ባለሙያዎች የተሳተፉበት ተጠቁሟል፡፡
አዲሱ ምክር ቤት የከተማ አስተዳደሩን አስፈጻሚ አካላት መልሶ ለማደራጀት የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ በ126 የድጋፍ፣ በአንድ ተቃውሞና በአንድ ድምፀ ተዓቅቦ አፅድቋል፡፡