– ከአክሲዮን ሽያጭ የገቢ ግብር ላይ የዋጋ ግሽበት ኪሳራ ተቀናሽ እንዲሆንም ተፈቅዷል
የንግድ ተቋማት በውጭ ገንዘብ ከፈጸሙት ግብይት ወይም የንግድ እንቅስቃሴ ጋር በተገናኘ የሚገጥማቸው የምንዛሪ ኪሳራ እንዲካካስ፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ወሰነ።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት ባካሄደው ስብሰባው፣ በሥራ ላይ የሚገኘው የገቢ ግብር ደንብ ላይ ተስተውለዋል ተብለው የተለዩ የሕግ ክፍተቶች ላይ በመወያያት የማሻሻያ ውሳኔዎችን አሳልፏል።
ከለተዩት ክፍተቶች መካከል አንዱም የንግድ ተቋማት በውጭ አገር ገንዘብ ግብይት ከፈጸሙ በኋላ በሚፈጠር የውጭ ምንዛሪ ምጣኔ ልዩነት፣ የሚደርስባቸውን የምንዛሪ ኪሳራ ማካካስ የሚችሉበት የሕግ አግባብ አለመኖሩና በዚህ የተነሳ በንግድ ተቋማቱ ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት ነው።
‹‹ከባንኮች ውጪ ያሉ ሌሎች የንግድ ሥራ ድርጅቶች ለካፒታል ንብረት ማፍሪያ የወሰዱትን ብድር በሚከፍሉበት፣ ወይም በውጭ ምንዛሪ ሌሎች የንግድ ሥራ እንቅስቃሴዎችን በሚያከናውኑበት ጊዜ የውጭ ምንዛሪ ኪሳራ ያጋጥማቸዋል፤›› ሲሉ አንድ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የሪፖርተር ምንጭ አስረድተዋል።
ምንጩ እንዳስረዱት በሥራ ላይ የሚገኘው የገቢ ግብር ደንብ በውጭ ምንዛሪ ግብይት የደረሰ ኪሳራ እንዲካካስ የሚፈቅደው፣ በውጭ ምንዛሪ ግብይት ለተገኘ ጥቅም ብቻ ነው።
ነገር ግን የንግድ ተቋማት ለካፒታል ንብረት ማፍሪያ የወሰዱትን ብድር በሚከፍሉበት ወቅት ወይም ሌላ ግብይት በውጭ ምንዛሪ ሲፈጽሙ፣ በምንዛሪ ለውጥ የሚደርስባቸው ኪሳራ ታሳቢ የሚደረግበት አሠራር አልነበረም ይላሉ።
እነዚህ ድርጅቶች የውጭ ምንዛሪ የማይዙ በመሆኑ ከግብይቱ የሚያገኙት ጥቅም ስለሌለ፣ ለከፍተኛ ችግር ሲዳረጉ መቆየታቸውንም ይገልጻሉ።
በመሆኑም ይህንን የሕግ ክፍተት ለማስተካከል በገቢ ግብር ደንብ ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ ተጠይቆ፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጉዳዩን ገምግሞ ማሻሻያው እንዲደረግ መወሰኑን ምንጩ ገልጸዋል።
በተፈቀደው ማሻሻያ መሠረትም በውጭ ምንዛሪ ግብይት ላይ ያጋጠመ ኪሳራ በሁለት ተከፍሎ ማካካሻ እንዲደረግበት መወሰኑን አስረድተዋል።
በዚህም መሠረት የውጭ ምንዛሪ ግብይቱ የተፈጸመው ከካፒታል ንብረት ግዥ ጋር በተያያዘ ከሆነ፣ የውጭ ምንዛሪ ኪሳራው የካፒታል ንብረቱ የተገዛበት ዋጋ ላይ ተደምሮ ለእርጅና ቅናሽ መሠረት እንዲሆን የሚፈቅድ ማሻሻያ በደንቡ ላይ እንዲደረግ ተፈቅዷል።
በሌላ በኩል የውጭ ምንዛሪ ግብይቱ የተፈጸመው ከካፒታል ንብረት ግዥ ጋር ባልተያያዘ ከሆነ፣ የውጭ ምንዛሪ ኪሳራው በግብር ዘመኑ እንደ ወጪ እንዲያዝ የሚፈቅድ ማሻሻያ እንዲደረግ መወሰኑን ምንጩ አስረድተዋል።
ሌላኛው በገቢ ግብር ደንቡ ላይ የታየው የሕግ ክፍተትና ማሻሻያ እንዲደረግበት የተጠየቀው ጉዳይ፣ ከካፒታል ዋጋ ዕድገት ጥቅም ላይ ከሚጣለው ግብር ጋር የተያያዘ ነው።
ለንግድ ሥራ የሚያገለግልን ሕንፃ ወይም አክሲዮን በሽያጭ በማስተላለፍ በሚገኝ የዋጋ ዕድገት ጥቅም ላይ የሚከፈለው የካፒታል ዋጋ ዕድገት ግብር አጣጣልን በተመለከተ የሚደነግገው የገቢ ግብር ደንብ፣ ሕንፃን በመሸጥ በሚገኝ የዋጋ (የካፒታል) ዕድገት ላይ የዋጋ ግሽበት ማስተካከያ ወይም ቅናሽ ተደርጎ በሚገኘው ዋጋ ላይ ግብር እንዲከፈል ሲፈቅድ፣ ከአክሲዮን ሽያጭ በሚገኝ የዋጋ ዕድገት ጥቅም ላይ የዋጋ ግሽበት ማስተካከያን አለመፍቀዱ ግብር ከፋዮች በእኩል እንዳይስተናገዱ ማድረጉን ምንጩ አስረድተዋል።
በመሆኑም ይህንን ችግር ለማስተካከል ማሻሻያ ድንጋጌ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ ተቀባይነት ማግኘቱን ገልጸዋል።
አክሲዮን የሚሸጡ ግብር ከፋዮች የአክሲዮን ሰነዱ ሲወጣ በተቆረጠለት ዋጋ፣ ወይም አክሲዮን ሰነዱ ላይ በተጻፈው ዋጋ (Par Value) እና በተሸጠበት ዋጋ መካከል ያለው ልዩነት ጥቅም እንደሆነ ተቆጥሮ ግብር እንዲከፍሉ ሲጠየቁ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
ይህ የግብር አጣጣል በብር የመግዛት አቅም መዳከም (በዋጋ ግሽበት) ምክንያት ግብር ከፋዩ ወይም ባለ አክሲዮኑ ሊያጣ የሚችለውን ገቢ ያላገነዛበ እንደሆነ የሚያስረዱት ምንጩ፣ በግብር አዋጁ መሠረት ግብር የሚጣለው ግብር ከፋዩ በትክክል አግኝቷል በሚባለው ጥቅም ላይ በመሆኑ በዚሁ አግባብ እንዲስተካከል መደረጉን ገልጸዋል።
ከአክሲዮን ሽያጭ የሚገኝ ጥቅም የዋጋ ግሽበት ማስተካከያ እንዲፈቀድ በሚያስችል አኳኋን በገቢ ግብር ደንቡ ላይ ያለው አንቀጽ እንዲሻሻል መወሰኑን የገለጹት ምንጩ፣ በዚህ ማሻሻያ መሠረትም ከአክሲዮን ሽያጭ በትክክል ተገኝቷል ሊባል የሚችለው ጥቅም በአክሲዮኑ የወቅቱ ዋጋና በተሸጠበት ገንዘብ መካከል ያለው ልዩነት እንደሚሆን አስረድተዋል።