Saturday, December 9, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪዎች በስድስት ወራት ውስጥ የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት እንደሚፈቀድላቸው ታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ የቴሌኮም አገልግሎት ለመስጠት አዳዲስ ፈቃድ የሚወስዱ ተቋማት፣ በስድስት ወራት ውስጥ የሞባይል የገንዘብ አገልግሎት ፈቃድ መውሰድ እንደሚችሉ ታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ የኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን ሁለተኛውን የቴሌኮም ፈቃድ ለመስጠት ማክሰኞ መስከረም 18 ቀን 2014 ዓ.ም. ጨረታ ያወጣ ሲሆን፣ ይኼንን ጨረታ የሚያሸንፍ ድርጅት የሞባይል የገንዘብ አገልግሎት ፈቃድ ወስዶ መሥራት የሚፈቅድ መሥፈርት በጨረታው ተካትቷል፡፡

የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ለመስጠት ግን የቴሌኮም አገልግሎት ጨረታ የሚያሸንፈው ድርጅት ከስድስት ወር በኋላ ለብሔራዊ ባንክ ይኼንን ፍላጎቱን የሚገልጽ ጥያቄ አቅርቦና ባንኩ የሚጠይቀውን ክፍያ በመፈጸም ወደ አገልግሎቱ እንደሚገባ፣ የኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ባልቻ ሬባ (ኢንጂነር) ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ይኼንን የሚገዛ መመርያም በብሔራዊ ባንክ ተሻሽሎ እንደሚዘጋጅ ጠቁመዋል፡፡

ይኼ ውሳኔ የተላለፈውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከመጀመሪያው የቴሌኮም አገልግሎት ጨረታ አሸናፊ ድርጅት ጋር ውል በታሰረበት መድረክ፣ በአንድ ዓመት ውስጥ አገልግሎቱ ከውጭ ለመጡ የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ክፍት እንደሚደረግ በተናገሩት መሠረት፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ ያቀረበውን ምክረ ሐሳብ ተከትሎ ነው ሲሉም ባልቻ (ኢንጂነር) ተናግረዋል፡፡ በዚህም መሠረት የጨረታ ሰነዱ ተሻሽሎ የወጣ ሲሆን፣ ውሳኔው ካሁን ቀደም በመጀመሪያው የጨረታ ሒደት ላይ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሲነሱ የነበሩ ጥያቄዎችን የመለሱ እንደሆኑም አስረድተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የአምስተኛው ትውልድ (5G) አገልግሎት መስጠት የሚያስችላቸውን ሞገድ ለመስጠት በጨረታ ማስታወቂያው ቃል የተገባ ሲሆን፣ ይኼ እንዲሆን ከአሁን ቀደም በጨረታ የተሳተፉ ድርጅቶች ጥያቄ አቅርበው ነበር ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ሞገዱ ለአዲስ ገቢም ሆነ ለነባር አገልግሎት ሰጪዎቹ ይሰጣል ብለዋል፡፡

የሁለተኛው ፈቃድ ሰነድ ሽያጭ ከመጀሪያው ዋጋ በሃምሳ በመቶ ቀንሶ በ7,500 ዶላር የሚሸጥ እንደሆነ በማስታወቂያው ላይ የተነገረ ሲሆን፣ ይኼ የሆነበት ምክንያትም በመጀመሪያው የፈቃድ አሰጣጥ ሒደት ላይ ገንዘቡ በዛ የሚል ቅሬታ ያቀረቡ ተጫራቾች በመኖራቸውና በርካታ ተጫራቾች በዚህኛው ሒደት ተሳታፊ እንዲሆኑ በማለም የተላላፈ ውሳኔ መሆኑንም፣ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር  አብራርተዋል፡፡

ያለፈው የጨረታ ሒደት የመጀመሪያ እንደ መሆኑ መጠን መንግሥት ከግብይት አማካሪውና ከሌሎች አማካሪዎች ጋር በትብብር ያደረገው ጥረት የተሳካ ነበር ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በወቅቱ የሞባይል ፋይናንስ አገልግሎት እንደ ፖሊሲ አይፈቀድም ተብሎ የነበረ ቢሆንም፣ የጨረታው ሒደት እንዲህ ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች እንዲታዩና እንዲፈቱ ለማድረግ ጠቅሟል ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በመጀመሪያው የጨረታ ሒደት የ5G ሞገድ ፍኖተ ካርታ ተሠርቶ ነው የሚደለደለው የሚል አቅጣጫ ተይዞ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ቴክኖሎጂው እየተስፋፋ በመሆኑና ኢትዮ ቴሌኮምም በዚህ ዘርፍ ለመሰማራት ጥያቄ እያቀረበ ስለሆነ በዚህ የጨረታ ሒደት እንዲካተት ተደርጓል ብለዋል፡፡

ፈቃድ የመጀመሪያ፣ ሁለተኛና ሦስተኛ እየሆነ ሲሄድ ዋጋው ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ እንደሚኖር ያከሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ከዚህ ሊገኝ የሚችለው የገንዘብ መጠን ከመጀመሪያው የቴሌኮም አገልግሎት ፈቃድ ጋር ትይዩ ተደርጎ የሚገመት አይደለም ብለዋል፡፡ ስለዚህም ራሱን የቻለ የዋጋ ግመታ ተሠርቶ ለመንግሥት መቅረቡን ተናግረዋል፡፡

ነገር ግን ከአሁን ቀደም አገልግሎት ለማግኘት ጨረታ ያሸነፈው ግሎባል ፓርትነርሺፕ ፎር ኢትዮጵያ የተባለው ጥምረት ከከፈለው 850 ሚሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ይጠበቃል ከተባለ፣ በርካታ የፖሊሲ ማሻሻያዎች ሊደረጉ እንደሚገባ ያወሱት ባልቻ (ኢንጂነር)፣ ይኼም የቴሌኮም መሠረተ ልማት ገንብተው የሚያከራዩ ድርጅቶች እንዲገቡና እንዲሠሩ መፍቀድን ሊያካትት ይችላል ብለዋል፡፡ ሆኖም በአገር ውስጥ ያሉትን አገልግሎት ሰጪዎችንም ሆነ የሚመጡትን እኩል ተጠቃሚ የሚያደርገው፣ አሁን ባለው አካሄድ መቀጠልና አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ብቻ መፍቀድ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

ሆኖም ለመጀመሪያው የተደረገው ክፍያ ለዋጋ ግመታ ያገለግላል እንጂ፣ ያኔ ይኼንን አግኝተናልና አሁን እንደዚህ እንጠብቃለን ለማለት አያስችልም ባይ ናቸው፡፡

ለዚህ ጨረታ የወጣው ማስታወቂያ የኢትዮጵያ መንግሥት፣ በኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለሥልጣንና በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል የሁለተኛውን አዲስ የቴሌኮሙኒኬሽን ፈቃድ የጨረታደት በነሐሴ ወር 2013 .ም. ለመጀመር ታቅዷል ይላል፡፡

በኢትዮጵያ ከኢትዮ ቴሌኮም በተጨማሪ የቴሌኮም አገልግሎቶችን ለመስጠት በወጣው ጨረታ 850 ሚሊዮን ዶላር በማቅረብ ያሸነፈው ዓለም አቀፍ ጥምረት ለኢትዮጵያ የተባለው የአገልግሎት ሰጪዎች ስብስብና የኢትዮጵያ ኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (/) እና የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በተገኙበት ውል ያሰሩት ሰኔ 1 ቀን 2013 .ም. እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ በቻይና የሲልክ ሮድ ፈንድ ድጋፍ ተደርጎለት 600 ሚሊዮን ዶላር ያቀረበው ሁለተኛው ተጫራች ኤምቲኤን ባቀረበው የገንዘብ መጠን ማነስ ሳቢያ ፈቃድ ሳያገኝ ቀርቷል፡፡

መንግሥት ለሁለተኛው የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ኩባንያ ፈቃድ ለመስጠት የፖሊሲ ማሻሻያ ማዕቀፎች የተካተቱበት፣ ማለትም የሞባይል ገንዘብና ሌሎች መሰል ጉዳዮችን በማስተካከልና የበለጠ አበረታች በማድረግ ጨረታ ለማውጣት ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ ማስታወቁ የሚታወስ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች