Thursday, February 29, 2024

ኢትዮጵያ በ76ኛው የተመድ መድረክ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ከመስከረም 15 ቀን 2014 .ም. ጀምሮ ለሁለት ሳምንታት በአሜሪካ ኒውዮርክ ከተማ  በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ጽሕፈት ቤት ሲካሄድ የነበረው የድርጅቱ 76ኛው ጠቅላላ ጉባዔ፣ ሰኞ መስከረም 17 ቀን 2013 ዓ.ም. ተጠናቋል፡፡

በመቶዎች የሚቆጠሩ የአገር መሪዎችና ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች በተገኙበት  በዚሁ ዓመታዊ ጉባዔ  ኢትዮጵያን ወክለው በስብሰባው የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒሰትር አቶ ደመቀ መኮንን ስለኮቪድ-19፣ ስለአየር ሙቀት መጨመር፣ ስለአገራዊ ወቅታዊ ሁኔታ፣ ስለሱዳን የድንበር ወረራ፣ ስለ ታላቁ የህዳሴ ግድብና ሌሎች ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ሰፋ ያለ ንግግር አድርገዋል፡፡

አቶ ደመቀ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሰው ልጆችን ሕይወት ማመሰቃቀሉን በመጥቀስ ለወረርሽኙ ክትባት ለማግኘት የተከናወኑ ሳይንሳዊ ምርምሮችና የፈጠራ ሥራዎች የሰው ልጅን ለመታደግ ያላቸውን ግዙፍ አቅም፣ የክትባትናምርምር  ግኝት፣ እንዲሁም ሥርጭት ላይ ለተሳተፉ ሳይንቲስቶች፣ መሐንዲሶችና ሌሎች ባለሙያዎች  አድናቆታቸውን በመግለጽ ንግግራቸውን ጀምረዋል፡፡

ይሁን እንጂ ሳይንስ ለሰብዓዊ አገልግሎት በተገቢው መንገድ ሊውል የሚችለው ፖለቲካ በቀና ልቦናና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ሲመራ ቢሆንም፣ ርትዕ ባልሆነ መንገድ በሚከናወን የክትባት ክፍፍል ምክንያት አፍሪካ እጅግ ዝቅተኛ በሆነ የክትባት ተደራሽነት ምጣኔ፣ ከሌሎች የሚተርፉ አነስተኛ የክትባት አቅርቦቶችን ለመጠበቅ መገደዷን ተናግረዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በየትም ቦታ የፀረ ኮቪድ-19 ክትባት መርሐ ግብር ተደራሽ መሆን እንደሚገባ በየጊዜው ቢናገርም፣ ሀብታም በሚባሉ ምዕራባውያንና ደሃ በሚባሉ የምሥራቅና የአፍሪካ አገሮች መካከል ሥርጭቱ ኢፍትሐዊ በሆነ መንገድ እየተከናወነ ስለመሆኑ አገሮች እየተናገሩ መሆናቸውን አውስተዋል፡፡

tender

በዚህም በታዳጊ አገሮች ላይ ወረርሽኙ እያሳደረ ያለውን አስከፊ ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖን ለመመከት በሚያስችል ደረጃ በቂ የኢኮኖሚና የፋይናንስ ዕርምጃ አለመወሰዱን በመጥቀስ፣ አቅም ያላቸው አገሮች የችግሩን ዓለም አቀፋዊ ባህሪና ይዘት ከግምት ያስገባ ትብብርን የጠየቁት አቶ ደመቀ፣ ‹‹በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የተናጠል ደኅንነት ሊኖር እንደማይችል፣ የሁላችንም ደኅንነት በጋራ ሳይረጋገጥ ማንኛችንም ደህና እንደማንሆን መታወቅ ይኖርበታል፤›› ብለዋል፡፡

የዓለም ሙቀት መጨመር ለድህነት መባባስ እጅግ አሳሳቢና ገፊ ምክንያት መሆኑንና እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ኢኮኖሚያቸው በግብርናናአርብቶ አደር የተመሠረተ አገሮች ላይ የህልውና አደጋ እንደተደቀነባቸው፣ በአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ምክንያት የምግብ ሥርዓትን የሚያዛባ የግብርና መሬት መንጠፍና የብዝኃ ሕይወት መመናመን እንደገጠማቸው አስታውቀዋል፡፡

ኢትዮጵያ በትብብር መንፈስ ተቋማት ያላሳለሰ ድጋፍ ስትሰጥ መቆየቷን በመጥቀስ፣ ‹‹ይህ ፅኑ አቋማችን የሚመነጨው ለይስሙላ ሳይሆን፣ ታሪክ እንደሚመሰክረው ሕግን መሠረት ያደረገ ሥርዓት ችግር ውስጥ በወደቀበት ወቅት ከደረሰብን በደል በመነሳት ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹በዚህም አገሮች ወደ ትብብር ግንኙነት መድረኮች ለመመለስ የሰጧቸውን የቁርጠኝነት ቃላትን እናደንቃለን፤›› ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ በዚህ ረገድ የአገሮች ሉዓላዊነትንና እኩልነትን፣ በውስጥ ጉዳዮች ጣልቃ አለመግባትን፣ እንዲሁም በጋራ ጥቅምናመከባበር ላይ የተመሠረተትብብር መርሆዎች አስፈላጊነትን እንደሚደገፉ አስታውቀዋል፡፡

አቶ ደመቀ የኃያላን አገሮች በደሃ አገሮች ላይ እያሳደሩት ያለውን ጫና ሲገልጹ፣ የትብብር ወገን ግንኙነት ሉዓላዊነትን፣ ውስጣዊ አንድነትንና የፖለቲካ ነፃነትን ለማስጠበቅ በቆሙ መንግሥታት ትከሻ ላይ የወደቀ መሆኑንበዚህ ረገድ የትብብር ግንኙነት ዓላማ ተፈጻሚ የሚሆነው አገሮች የውስጥና የውጭ ጉዳዮቻቸውን በነፃነትና በብቃት ለማስተዳደር ሲችሉ ብቻ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

‹‹በእርግጥ የሰው ልጅ የጋራ ፍላጎቶች በመሠረታዊነት ተመሳሳይ እንደሆኑ የሚታወቅ ቢሆንም፣ ነገር ግን በአመለካከትና በምንከተላቸው ዘዴዎች፣ በባህል፣ በታሪክ፣ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እውነታዎች ውስጥ ባለው ብዝኃነታችን ምክንያት ልዩነት መፈጠሩ የማይቀር መሆኑንና ብዝኃነትን እንደ ፀጋ በመውሰድ፣ የውስጥና የውጭ ጉዳዮቻችንን በምናስተዳድርባቸው ፖሊሲዎችና አሠራሮች ላይ ማናችንም በሌላው ላይ የበላይ ሆኖ የመታየት ፍላጎት ሊኖር አይገባም፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከሦስት ዓመታት በፊት ተስፋ ሰጪ የለውጥ ጉዞ መጀመሯን፣ በዚህም የተካሄዱት የለውጥ ሥራዎች  ለዴሞክራሲ፣ ለሰብዓዊ መብቶች፣ ለሰብዓዊ ልማትናቀጣናዊ መረጋጋት አዲስ የተስፋ ጎህ የቀደዱ ናቸው ብለዋል፡፡

በአገር ውስጥ በብሔራዊ ጥቅምና አካባቢ ሰላም ላይ ጉዳት በማድረስ የተተከለውን  ውስብስብ የሙስና መረብ፣ ሕገወጥሥልጣን አጠቃቀምና ሕገወጥ የገንዘብ ፍሰቶችን በማስወገድ ረገድ አበረታች ውጤቶች እንደተመዘገቡ ለጉባዔው ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ የተካሄደው ለውጥ ከፈተናዎች የፀዳ አለመሆኑን፣ ‹‹እንደ ማንኛውም  ዴሞክራሲ፣ የዴሞክራሲ ሥርዓታችን ግንባታ በመረጋጋትና በሁከት መካከል ሚዛን ለማስጠበቅ የሚደረግ ሒደት በመሆኑ፣ በእኛ የለውጥ ጥረቶች ውስጥ እኩልነትን እንደ መገፋት የሚቆጥሩ ቡድኖች ሚዛኑን ለማደናቀፍና ሁከት ለመፍጠር፣ እንዲሁም የሥርዓተ አልበኝነትን ዕድሜ ለማራዘም የተቻላቸውን ሁሉ ጥረት ማድረጋቸውን ቀጥለዋል፤›› ብለዋል፡፡

በእነዚህ የጥፋት መሪዎች ተዋናይነት በንፁኃን ዜጎች ላይ ሊገመት የማይቻል ኢሰብዓዊ ጥቃት፣ ሁከት ማነሳሳትና ንብረት ውድመት መድረሱ ሳይበቃ በኢትዮጵያአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን አቶ ደመቀ ተናግረዋል፡፡

ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ምሽት ምንም ዓይነት ጥርጣሬ ያልገባቸው የኢትዮጵያ የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ከውስጥ ጥቃት እንደተፈጸመባቸው  በማስታወስ፣ ‹‹ይህን እንደ አገር የገጠመንን አደጋ ለመከላከል የኢትዮጵያ መንግሥት አስፈላጊውን ዕርምጃ ለመውሰድ ተገዷል፤›› ብለዋል፡፡

ነገር ግን አገሪቱ የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎት ለማሟላት እየተንቀሳቀሰች ባለችበት ወቅት፣ የጥፋት ቡድኑ የተዘጋጀበትን ሰብዓዊ ቀውስ የመፍጠር ዕቅድ ተግባራዊ ከማድረጉም በላይ ክፋት የተሞላበት የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ከፍቷል ሲሉ አቶ ደመቀ ገልጸዋል፡፡

‹‹በዚህም በግል ፍላጎቶችና ጥቅሞች የሚዘወር ፖለቲካና የውጭ ፖሊሲ፣ እውነታውን በመሸፈን የተዛባ የፖሊሲ ውሳኔ ሊያሰጥ እንደሚችልም ተገንዝበናል፤›› ብለዋል፡፡

የሰብዓዊ አገልግሎት ድጋፍ የፖለቲካ ዓላማ ማስፈጸሚያ መሣሪያ እየሆነ መምጣቱንና ወንጀል ጠንሳሾቹናና ደጋፊዎቻቸው የሐሰት መረጃዎችን በማቀነባበር፣ እንዲሁም ሐሰተኛና ዘግናኝ ምሥሎችን በመፈብረክ የተዛባ ግንዛቤ እንዲፈጠር መንቀሳቀሳቸውንም አቶ ደመቀ አብራርተዋል

‹‹የሕዝባችን እውነተኛ ሰቆቃ በቂ እንዳልሆነ፣ የተወሰነውን የሕዝብ ክፍል እንደ አረመኔ ከሚፈርጅ አስተሳሰብ ጋር ለማዛመድ ጥረት የተደረገባቸው ሐሰተኛ ውንጀላዎች አሉ፤›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ሰብዓዊ ዕርዳታ የመስጠት ግዴታውን ስለመወጣቱ፣ የተናጠል ሰብዓዊ የተኩስ አቁም ስለማወጁ፣ የምርመራ ሥራዎችንና ተጠያቂነት የማስፈን ዕርምጃዎችን ስለ መውሰዱ የተናገሩት አቶ ደመቀ የሐሰት ውንጀላዎችን ግን መቀልበስ እንዳልተቻለ አስረድተዋል፡፡

‹‹በዚህ ውንጀላ የተነሳ በዚህ ጊዜ አጀንዳ በሚቀረፅላቸውና ቀለብ በሚሰፈርላቸው ሚዲያዎች ተከሰን፣ መርህ አልባ በሆነ ፖለቲካ ተፈርዶብን፣ እንዲሁም በተናጠል የተጣለ ማዕቀብ ተደቅኖብን እንገኛለን፤›› ብለዋል፡፡

በቀደሙት ጊዜያት  በሌሎች አካላት ላይ ማዕቀቦች ሲጣሉ መቃወማችን የሚታወስ ሲሆን፣ በተመሳሳይ በኢትዮጵያም ላይ የሚደረግ ፍትሕና ርትዕ የሚጎድለው አካሄድ ተግባራዊ እንዳይሆን እንመክራለን በማለት የገለጹት አቶ ደመቀ፣ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ጫና የሚያሳድሩ ማንኛቸውም ዕርምጃዎች ግንኙነቶችን አሻሽለው ሰለማያወቁ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

‹‹እኛ የምንወስዳቸው ጥንቃቄ የተሞላባቸው ዕርምጃዎች አገሪቱ ከገጠማት የህልውና ፈተና ጋር ተመጣጣኝ ስለመሆናቸው፣ ምንም እንኳን አላስፈላጊ ጫናዎች ቢኖሩም  የኢትዮጵያን  ሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነትና የፖለቲካ ነፃነት የማስጠበቅ ከባድ ግዴታን እንወጣለን፤›› በማለት አስታውቀዋል።

ከወዳጅ አገሮች ለኢትዮጵያ የሚቀርበው ትብብርና ቅን አሳቢነት ተቀባይነት ቢኖረውም፣ ገንቢ አቀራረብን የመጠቀም፣ መተማመንን የማዳበርና መረዳትን የመፍጠርን አስፈላጊነት አመላክተዋል፡፡

በአንድ ግዛት ውስጣዊ ጉዳይ ላይ ድጋፍ ወይም አልፎ ተርፎም አስተያየት ለመስጠት  የሚደረግ ሙከራ ስለችግሩ ውስብስብነት ሙሉ ግንዛቤን የሚጠይቅ መሆኑ ሊታወቅ እንደሚገባ በመጥቀስ፣ አገሪቱ እያጋጠማት ያለው ፈተና በኢትዮጵያ ድንበሮች ላይ ብቻ የተወሰነ አለመሆኑንና ይባሱንም መላው የአፍሪካ ቀንድ በዚህ ቡድን  የተነደፈለትን  አጥፊ መንገድ እየተጋፈጠ በመሆኑ፣ ከዚህ ወንጀለኛ ቡድን ጋር የሚደረገውን ግብግብ ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ መደገፍ አካባቢያዊ ሰላምን ለማስቀጠል እንደሚረዳ አቶ ደመቀ በንግግራቸው አውስተዋል፡፡

ውይይት ሁልጊዜ የመንግሥት ተመራጭ አካሄድ በመሆኑ በዚህ መሠረት ኢትዮጵያ ለሰላም እልህ አስጨራሽ እንቅስቃሴዎች ክፍት እንደሆች፣ ‹‹ከዚህ ጋር በተያያዘ ከአፍሪካ  ኅብረትና ከአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ጋር ኢትዮጵያ መር ብሔራዊ ውይይት ለመምራት እንሠራለን፤›› ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹የአፍሪካ ኅብረት የራሱን ጥበብ ተግባራዊ ለማድረግ ቦታ ይሰጠዋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፤›› ብለዋል፡፡

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን መስከረም 7 ቀን 2014 ዓ.ም. በፈረሙት ፕሬዚዳንታዊ ትዕዛዝ፣ የትግራይ ክልል ግጭት በተኩስ አቁም ስምምነት መፍትሔ እንዳያገኝ ያደረጉና በግጭቱ ምክንያት በንፁኃን ላይ ለተፈጸሙ አሰቃቂ ሰብዓዊ ጥሰቶች ተጠያቂ ባሏቸው ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ማዘዛቸው ይታወሳል፡፡

 

በሌላ በኩል ደግሞ የሕወሓት ቡድን የአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነትን እንደማይቀበል በይፋ  ገልጿል፡፡

‹‹የሰብዓዊ ዕርዳታ  አቅርቦትን  ለማረጋገጥና የአጋሮቻችንን በገለልተኛ፣ በነፃነትና በሰብዓዊነት መርሆች ላይ የተመሠረተ የሥራ እንቅስቃሴ ለማሳለጥ መንግሥት ያላሳለሰ  ቁርጠኝነት  አለው ያሉት አቶ ደመቀ፣ ‹‹ከዚህ ውጪ በውስጣዊ ጉዳዮቻችን ጣልቃ ለመግባት የሚቀርብ ማንኛውም ሰበብ ምክንያት ሊሆን አይችልም፤›› ብለዋል፡፡

‹‹አስቀድሞ እንደተደገሰልን የጥፋት ድግስ ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያ ተበጣጥሳ በከሰመች ነበር፤›› ያሉት አቶ ደመቀ፣ ይህ የስግብግቦች አካሄድ ኢትዮጵያን ብቻ በማፍረስ የሚያበቃ አለመሆኑንና የአፍሪካ ቀንድን ፖለቲካዊ ምኅዳር የሚለውጥ፣ ስትራቴጂካዊ ቀጣናውን ወደ የማያባራ ብጥብጥና ትርምስ ሊቀይረው ይችል እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለማንም የደኅንነት ሥጋት ሆና እንደማታውቅና በሕዝቦቿ ፅኑ አቋም ሁሌም ሰላም ወዳድ አገር ሆና የምትኖር፣ ቀጣናዊውና  ዓለም አቀፋዊ ሰላም ወደ ነበረበት  እንዲመለስ  የበኩሏን  አስተዋጽኦ  የምታበረክት ትሆናለች  ብለዋል፡፡

በመሆኑም ኢትዮጵያ ሀቀኛና ግልጽ ለሆኑ የሰላም ዕርምጃዎች ምንጊዜም ዝግጁ እንደሆነች፣ አፍራሽ ያልሆነ መንገድ ለመከተል ከአፍሪካ ኅብረትና ከአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ጋር  ለመሥራት ዝግጁ ስለመሆኗ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ሌሎች አገሮች በተቋሞቻቸው ላይ የደረሱባቸውን ጥቃቶች ለመታደግ ላበረከተችው ድጋፍና ትብብር፣ ተመሳሳይ ድጋፍ እንደምትፈልግ አስታውቀዋል፡፡

በሌላ በኩል በአፍሪካ የፖለቲካና የፀጥታ ምኅዳር መንግሥታትን በኃይል መገልበጥ፣ የጋራ ወታደራዊ ልምምዶች፣ ጠበኝነት፣ በሉዓላዊ አገር ውስጥ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት፣ ማፈናቀልና ቅጥረኝነት፣ የተፈጥሮ ሀብቶችን መቀራመት፣ ሚስጥራዊ ወታደራዊ ስምምነቶች፣ የጂኦ ፖለቲካዊ ውድድሮችና ሌሎችም እየተስፋፉ ስለመምጣታቸው አመላክተዋል፡፡

በመሆኑም በዚህ ፈታኝ ጉዞ ላይ ያለውን አካሄድ በፍጥነት መቀየር ካልተቻለ፣ አፍሪካን  ለማተራመስና በራሳቸው ሀብት ባይተዋር ለማድረግ እየተካሄዱ ላሉ ጥረቶች አዲስ በር መክፈት ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ ‹‹በዚህም ከአንድ ወገን ተው ባይ ከሌለው  የበላይነት ይልቅ፣ የአፍሪካዊ ወንድማማችነት ዓርማ ከፍ የሚያደርጉ ብዙ አገሮች ይኖራሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

‹‹በኅዳር 2014 ዓ.ም. ኢትዮጵያ አይታ በማታውቀው የደኅንነት ቀውስ ውስጥ በነበረችበት ወቅት፣ ስናምነው የነበረ ጎረቤት አገር (ሱዳን) የዓለም አቀፍ ሕግን በመጣስ ግዛታችንን የወረረ ሲሆን፣ ይህ ወረራ እስከ ዛሬ ድረስ ቀጥሏል፤›› በማለት አስታውቀዋል፡፡

ኢትዮጵያ ይህንን ችግር ለመፍታት ዲፕሎማሲያዊ የመፍትሔ ሐሳቦችን ለመቀበል ዝግጁ መሆኗን በመግለጽ አካሄዱ በፍጥነት እስካልተቀየረ ድረስ፣ ይህም ሌላው አፍሪካን የማተራመስና የአፍሪካውያንን ዕጣ ፈንታ ወደ ከፋ የመብት ጥሰት የሚያሸጋግር ምዕራፍ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

የተጠናቀቀው 2013 ዓ.ም ለኢትዮጵያ ሕዝብ አዲስ ምዕራፍ የተበሰረበትም ጊዜ ነበር ያሉት አቶ ደመቀ፣ ‹‹የዴሞክራሲ ልምምዳችን ወደ አንድ ደረጃ ከፍ ያለበትና ነፃ፣ ፍትሐዊ፣ ሰላማዊና ታዓማኒነት ያለው፣ ከፍተኛ የመራጭ ቁጥር የተመዘገበበት አገራዊ ምርጫ ተካሂዶበታል፤›› ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ በዚሁ ዓመት ሙሉ ለሙሉ በአገር ሀብት የገነባነው የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ የውኃ ኃይል ማመንጫ የሁለተኛ ዓመት የውኃ ሙሌት በስኬት በመጠናቀቁ፣ ሌሎችም አገሮች በራስ አቅም የተነደፈ፣ በራስ ገንዘብ የሚገነባና የሚጠናቀቅ የታዳሽ ኃይል ማመንጫዎችን እንዲያለሙ መነቃቃት እንደፈጠረ ይታመናል ብለዋል፡፡

‹‹ነገር ግን የምኞታችን ተፃራሪ በመሆን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ቤቶቻቸው ብርሃን እንዲያገኙና ቁጥራቸው እያሻቀበ ለመጣው ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ተስፋ ለመፈንጠቅ የምናደርገው ጥረት፣ በዓለም አቀፍ አካላት የፖለቲካ ትርጉም  እየተሰጠው በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት እየተካሄደ ያለውን የድርድር ሒደት ሲያስተጓጉል ቆይቷል፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

‹‹ከሁሉም በላይ የሚገርመውና የሚያሳዝነው ነገር ከራሳችን ውኃ እንዳንጠጣ መከልከላችን ነው፤›› ያሉት አቶ ደመቀ፣ ‹‹ዓባይንና የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ የእኛ መተማመኛ እውነት፣ ፍትሕና ጥበብን መሠረት ያደረገው የመተባበር መንገዳችን ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ስለሆነም የተፈጥሮ ሀብትን የመጠቀም የትውልድ ጉጉት በቅኝ አገዛዝ ውርስ፣ ኢፍትሐዊ በሆነ፣ ሀብትን በብቸኝነት የመቆጣጠር አጉል የተንጠራራ ምኞት እንደማይስተጓጎል፣ የድርድር አጋሮች ይህን በውል ተገንዝበው በአፍሪካ ኅብረት መሪነት በሚካሄደው የድርድር ሒደት ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ውጤት ላይ ለመድረስ እንደሚዘጋጁ ተስፋ እናደርጋለን፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡

በንግግራቸው ማጠናቀቂያ ላይ፣ ‹‹በሰላም ማስከበር ዘመቻ ተሰማርተው የሚገኙ ወታደሮቻችን በዳርፉርና በአብዬ የተሰጣቸውን ግዳጅ በብቃት ተወጥተዋል፡፡ በተመድና በአፍሪካ ኅብረት በሰማያዊ መለዮ ተሰማርተው ግዳጃቸውን በብቃት ለፈጸሙ የሰላም ማስከበር አባላት አክብሮቴንና የኢትዮጵያን ኩራት ለጉባዔው እገልጻለሁ፤›› ብለዋል፡፡

የሰላም አስከባሪ ሠራዊት አባላት ለኑሮ ፈታኝ በሆኑ፣ የማኅበረሰብ ግጭቶች የእርስ በርስ ባሉባቸው፣ መደበኛ ያልሆኑ የጦርነት ዘዴዎች በሚጠቀሙና የግዛት ባለቤትነት አለመግባባቶች ባሉባቸው ሥፍራዎች ተመድበው እንዲሁም ያልተፈቱ አስተዳደራዊ ችግሮችን ተቋቁመው መስዋዕትነት መክፈላቸውን አውስተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -