Saturday, June 15, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ኢሬቻ ፍልስፍናዊ፣ ሃይማኖታዊና ባህላዊ አንድምታው

በዮሴፍ ሙሉጌታ ባባ (ዶ/ር)

የሰው ልጅ በተፈጥሮው ሃይማኖታዊ ፍጡር (religious being) ነው። ይህ ተፈጥሯዊ ባህሪው የሰው ልጅህልውና የተለየ ያደርገዋል። ሰው ያለማቋረጥ ፈጣሪውን የመሻቱ ዋነኛ ምክንያት ተፈጥሯዊ ማንነቱ ነው። ፈጣሪን ለማግኘት የሚደረግ ፍለጋ በመሠረቱ ነባራዊ (universal) አሊያም ተፈጥሯዊ (innate) ነው። ማንኛውም ሰው ከዚህ ነባራዊ እውነታ ውጪ የሚሆንበት መንገድ የለም።

ስለዚህ የሰው ልጅ ፈጣሪውን ያለማቋረጥ የመሻቱ ምስጢር መለኮታዊ (divine) እንጂነ ልቦናዊ (psychological) አሊያም ማኅበራዊ (sociological) አይደለም። ሰው ከአዕምሮ (intellect) እና ነፃ ፈቃድ (free-will) ጋር የተፈጠረ በመሆኑ፣ የፈጣሪውን ህልውና ማረጋገጥ ይችላል። በተለይ የዓለምን እንቅስቃሴና የራሱን ድንቅ ተፈጥሯዊ ባህሪውን መነሻ በማድረግ፣ ስለፈጣሪ ህልውና ይጠይቃል፣ ይመረምራል፣ ማረጋገጫዎችን ያቀርባል። ፍጥረትን መንደርደሪያ አድርጎ የፍጥረት ሁሉ ጀማሪ የሆነውን ዓለምን የሚቆጣጠር አንድኃይልእንዳለ ይደርስበታል። በመጨረሻምማጋኖወይምዋቃ› ወይምእግዚአብሔር› ወይምዬሪወይም ‹God›…፣ ወዘተ እያለ የሚጠራውን አንድ ፈጣሪ እንዳለ በውስን አዕምሮው አንደኛ በተለያዩ መንገዶች ይገነዘባል (understanding)፣ ሁለተኛ የተለያዩ ትርጓሜዎችን (interpretation) ይሰጥበታል።

ይህ እውነታ አንድ ነገር ያስገነዝበናል፣ የሰው ልጅ አዕምሮ የፈጣሪን ህልውና የማወቅና የማረጋገጥ ተፈጥሯዊ አቅም አለው። የሰው ዘር ሁሉ ፈጣሪውን የማወቅ ብቃት/ችሎታ አለው። ይህ የዕውቀት ብርሃን በመላውለም የምናስተውለውና የሰው ልጅ በተፈጥሮው የተጎናፀፈው የፈጣሪን ህልውና የሚያውቅበት መንገድ ነው።

በአገር በቀል ሃይማኖቶች ላይ የሚሰነዘሩ መሠረተ ቢስ ትችቶች

‹‹የቄስ ልጅ እግዚአብሔር አጎቱ ይመስለዋል!›› እንደሚባለው ሁሉ፣ ስለሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባህርይና ስለሃይማኖት ምንነት ጥልቅ ግንዛቤ የሌላቸው አንዳንድ ሰዎች በአገር በቀል ሃይማኖቶች (indigenous religions) ላይ ያልተገባ ትችቶች ሲሰነዝሩ ይስተዋላል። በተለይ ያለምንም ጥልቅ የምርምርራ፣ገር በቀል ሃይማኖታዊ ድርጊቶችን (ጸሎት፣ የአምልኮ ሥርዓቶች፣ የስጦታ ምፅዋት፣ ሙዚቃ፣ ዘፈን…፣ ወዘተ) “ሰይጣናዊአድርጎ ለመሣል ይደፍራሉ።

እዚህ ላይ አንድ መሠረታዊ ስህተት ነቅሰን እናውጣ፡፡ ሰው ፈጣሪ በሰጠው አዕምሮ የሁሉ ነገር ምክንያትና ፍፃሜ ስለሆነው ስለፈጣሪው ህልውና ራሱ ማረጋገጥ የሚችል ሆኖ ሳለ፣ አንድን ሕዝብሃይማኖት አልቦአድርጎ መውሰድም ሆነ ሃይማኖታዊ መገለጫዎቻቸውንሰይጣናዊአድርጎ መውሰድ ትልቅ ስህተት ብቻ ሳይሆን፣ ፈጣሪ ራሱን መቃወም ነው። ዛሬም አንዳንድ ሰዎች አገር በቀል ሃይማኖታዊ ድርጊቶችን ያላግባብ እንዲተቹ ምክንያት የሆኑት ቅድመ ፍረጃ (prejudice) እና አድልኦ (bias) ናቸው። በመላ አፍሪካ የሚስተዋለውና ለአገር በቀል ሃይማኖቶች የሚሰጠው የተሳሳተ ትርጉም ምንጩ ይኼው ነው።

ግና አንድ ነባራዊ እውነታ አለ፡፡ ይኼውም የሰው ልጅ ታሪካዊ ፍጡር (historical being) ነው። ስለዚህ ከራሱ ባህል ተነጥሎ (detached) የሌላውን ሃይማኖት መገንዘብ የሚችልበት መንገድ ከቶ የለም፣ኖርም አይችልም። ሌሎችም የግለሰቡንገር በቀል ሃይማኖቱን መንገዘብ የሚችሉት በገዛ ራሳቸው ባህልና ሃይማኖትውድ (context) ውስጥ ሆነው ነው። የትኛውም ባህል መረዳት የምንችለው ደግሞ የማኅበረቡን ንጽረተ ዓለም (worldview) በጥንቃቄ የተገነዘብን እንደሆነ ብቻ ነው። አንድ ማኅበረሰብ ዓለምን፣ ሌሎችንና ራሱን የሚገነዘብበትና ለሌላው የሚያስረዳበት መንገድ/ዘዴ ንጽረተ ዓለም/ሥነ ኑባሬ ተብሎ ይጠራል። ንጽረተ ዓለም የአንድን ሕዝብ ባህል፣ እምነትወግ፣ ቋንቋሥርዓትማንነት…፣ ወዘተ አንድ ላይ ያቀፈ እጅግ ሰፊና ጥልቅ ጽንሰ ሐሳብ ነው።

ለምሳሌ የማኅበረሰቡን ንጽረተ ዓለም አለማክበርና አለመጠበቅ (በአጠቃላይ አለመገንዘብ) በክርስትናና በእስልምና ሃይማኖቶች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል። ምሳሌውን የበለጠ ግልጽ ለማድረግ፣ አንድ የወንጌል ሰባኪ የክርስትና ሃይማኖት በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ እንዲኖረው ከፈለገ አስቀድሞ ሁለት ነገሮችን ማድረግ ይኖርበታል፡፡

አንደኛው የሌላውን ሕዝብ ንጽረተ ዓለም በጥልቀት ተረድቶ ማገናዘብ ሲሆን፣ ሁለተኛው የራሱን ባህል ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮነጥሎ መለየትናቸው። ለሁለቱም ግልጽ ምሳሌዎችን ሰጥቼበት ወደ ሌላ ጉዳይ ልለፍ፡፡

1. ኢትዮጵያውያን ንጽረተ ዓለም ገና በትክክልና በግልጽ ማገናዘብ ያልቻለ አንድ ሚሽነሪ፣እንጀራከሕዝቡ የዕለት አኗኗር ዘይቤ ጋር ያለውን ጥብቅ ግንኙነት መረዳቱ አለው ብለን አንገምተውም። በዚህ የተነሳ “I am the bread of life!” የሚለውን የወንጌል ክፍል በስህተትእኔ የሕይወት ዳቦ ነኝ!” የሚል አቻ ያልሆነ ትርጉም ይሰጠዋል፡፡

2. በተመሳሳይ መልኩ ሕይወቱን ሙሉ የጤፍ እንጀራ ሲመገብ የኖረው አንድ ከአገረ ሸዋ የሆነ ክርስቲያን የቦረና ኦሮሞን ባህል/ንጽረተ ዓለም ጠንቅቆ ያላወቀ እንደሆነየዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን!” የሚለውን የጌታ ጸሎት በሰማ ጊዜ ፈጽሞ ግራ ሊገባው ይችላል። ምክያቱም በቦረና ማኅበረሰብ ዘንድየዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን!” የሚለው የጸሎት ክፍል ምንም ትርጉም አይሰጥምና።

እዚህ ላይ ሁለት ጥያቄዎችን እናንሳ፣ ጥያቄ 1. ለመሆኑ ከዚህ ቀደም ስለክርስትና ሃይማኖት ምንም ሰምቶ የማያውቅ አንድ ግለሰብእጣንእናሻማበክርስትና አስተምህሮ ውስጥ በቀጥታ ምን ትርጉም እንዳላቸው ማወቅ ይችል ይሆን?

ጥያቄ 2. በሌላ በኩል ከዚህ በፊት ስለኦሮሞገር በቀል ሃይማኖት ምንም ዓይነት መረዳት ያልነበረው አንድ ሰውእርጥብ ሳርእናኦዳ ዛፍበኦሮሞ ማኅበረሰብ ዘንድ ያለውን ትርጓሜ መገንዘብ ይቻለው ይሆን?

ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ እጅግ በሚያሳዝን መልኩ የሥራ ሙያ ክፍፍል (professionalism) የሚባል ነገር ጠፍቷል። ማንም ሰው በስሜት ብቻ እየተነዳ በፈለገው ርዕሰ ጉዳይ ላይ ትንተና ይሰጣል። አንድ ግለሰብ ሁሉንም የዕውቀት ዘርፎች እንዲሁ በቀላሉ የመረዳት ብቃት አለው ከተባለ፣ በትምህርት ዓለም ውስጥ የሥራ ሙያ ክፍፍል ለምን አስፈለገ? ያም ሆነ ይህ ማንም ሰው በቂ መረጃና ጥልቅ ግንዛቤ ሳይኖረው በአንድ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ያልተገባና መሠረተ ቢስ ትንተና ቢሰጥ ይህውቀት ሳይሆን ፕሮፓጋንዳ አሊያም ምሁራዊ ውስልትና ይሰኛል።

ይህ የሥራ ሙያ ክፍፍልም እኔንም ይመለከተኛል። በተለይ የአፍሪካ ፍልስፍና ሆነ ነገረ መለኮት በቀጥታ ይመለከተኛል። አገር በቀሉ የኦሮሞ ሃይማኖት በአፍሪካ ፍልስፍና ሥር የሚጠቃለል ሲሆን፣ ኢሬቻ ደግሞ የዚህገር በቀል ሃይማኖት አንዱ አካል ነው። ከላይ እንደተገለጸው የትኛውንም አገር በቀል ሃይማኖት ለመረዳት፣ አስቀድመን ስለሕዝቡ ንጽረተ ዓለም ወይም ዲበ አካል ግልጽ የሆነ ጽንሰ ሐሳብ ሊኖረን ይገባል። እንግዲያውስ በምርምር ሥራ የተደገፈው የኦሮሞ ሕዝብ ንጽረተ ዓለም ፍልስፍናዊ ትንተና እንደሚከተለው ይቀርባል።

የኦሮሞ ሥነ ኑባሬ (Ontology)

የኦሮሞ ሥነ ኑባሬ (Ontology) በሦስት አንኳር አንኳር ጽንሰ ሐሳቦች ይከፈላል። እነርሱም፣ () ሁማ (Uumaa—cosmology)፣ () ዋቃ (Waaqa—Undiffrentiated-Being) እና () ሳፉ (Safuu—Human – Ontology) ናቸው።

() ሁማ (Uumaa—cosmology)ሁማ (Uumaa) የሚለው ቃል ሁሙ (Uumuu) ከሚለው ግስ የተገኘ ሲሆን፣ ቀጥተኛ ትርጉሙም መፍጠር ማለት ነው። ሁማ የኦሮሞ ትዕይንተ ‹‹ዓለም›› (cosmos) ፍልስፍናዊ ጽንሰ ሐሳብ ነው። ‹‹ዓለም›› ውስጥ ያለው ነገር በሙሉ በዚህ ሁማ ውስጥ የሚታቀፍ ሲሆን፣ ህልውና ያለው ማንኛውንም ነገር ያጠቃልላል። ስለዚህ ቃሉ ሕይወት የሌላቸውን ነገሮች፣ ህያው አካላትንና መንፈሳዊ ኅላዌዎችን ሁሉ ያመላክታል። ግና በኦሮሞ ንጽረተ ‹‹ዓለም›› ፍጥረት (creation) ተሠርቶ ያለቀና ቋሚ ነገር (static) ሳይሆን ቀጣይነት ያለው ነገር (a continous process) ተደርጐ ይወሰዳል። ለምን? ይህንን ጥያቄ በትክክል ለመመለስ በመጀመርያ ደረጃ በኦሮሞ አገር በቀልውቀታዊ አረዳድ ውስጥ ያለውን የዋቃ ጽንሰ ሐሳብ ቀጣይነት ካለው ሁማ ጋር ለምንና እንዴት ፈጽሞ መለያየት በማይቻል ሁኔታ እንደተቆራኘ በጥንቃቄ እንመረምራለን።

() ዋቃ (Waaqa)፡ የኦሮሞ ሕዝብ ስለዋቃ ያለው ጽንሰ ሐሳብ በጣም ግልጽ ነው። የሁሉም ነገር አስገኚ ዋቃ ነው። ዋቃ ምሉዕ በኩለሄ (omniscient) ሁሉን ቻይ (ominipresent) ዘላለማዊ (eternal) ፍፁም (absoulute) እና ገደብ የሌለው (infinite) ነው። ዋቃ ፍፁም አንድ ነው። ዋቃ ፍፁም አንድ ቢሆንም ቅሉ፣ ራሱን የሚገልጸው ግን በተለያየ መንገድ ነው። በተለይ ዋቃ ማንነቱን ለሁማ (Uumaa) የሚገልጸው በአያና (Ayyaana) አማካይነት ነው።

አያና የሁሉም ነገሮች ምንነት ወይም ንጥረ ነገር (essence) የሚወስን፣ በአካል የማይታይ አሚነ መሠረት (immaterial principle) ነው። በኦሮሞ ፍልስፍናሳቦት (thought) ሁሉም ነገር ከዋቃ የሚመነጨው በአያና መልክ ነው። የእያንዳንዱን ነገር ምንነት (essence) ሆነ የጋራ ባህርዮቻቸው (common properties) የሚወስነው አያና ነው። Gudrun Dahl አያና የእያንዳንዱን ነገር ባህርይና ዕጣ ፈንታ የሚወስን በአካል የማይታይ አሚነ መሠረት መሆኑን በትክክል ሞግተዋል። Lambert Bartles የጥናቱ ግኝትም ‹‹ተራራዎች፣ ዛፎች፣ ቀናት፣ ወራትና ወቅቶች፣ እያንዳንዱ ሰውና የዘር ሐረጉ›› የራሳቸው አያና እንዳላቸው ያረጋገጠ ሲሆን፣ ‹‹እነዚህ አያናዎች ሕይወታችንን የሚገዙ፣ ህልውናችንን የሚወስኑ፣ እንዲሁም የራሳቸው ህልውና አላቸው ተብሎ ይታሰባል›› ሲል Oromo Religion በተሰኘ የምርምር ሥራው ውስጥ አስረድቷል። Joseph van de Loo በበኩሉ አያና ‹‹የማይታይ አካል፣ መንፈስ›› እንደሆነ The Religious Practices of the Guji Oromo በተሰኘ ጥናታዊ ሥራው ውስጥ አስገንዝቧል።

የአያና ጽንሰ ሐሳብ በዋናነት የሚያመለክተውልውና ያለው ማንኛውም ነገር የራሱ ‹‹አያና›› እንዳለው ነው። አያናአልቦ ፍጡር የለም። ያለ አያና የአንድን ነገር ምንነት ማወቅ አይቻልም፡፡ ጽንሰ ሐሳቡም ሊኖረን አይችልም። አንድን ነገር ከሌላኛው ለይተን እንድናውቅ ወይም እንድንረዳ የሚያስችለን አያና ነው። ይህንን በተመለከተ Gudrun Dahl እንዲህ ሲል ያብራራል፡፡

‹‹አገር በቀል የኦሮሞ ትዕይንተ ዓለም የተመሠረተው ከፊል አፍላጦናዊ (a quasi-platonic) በሆነው በዕውኑ ዓለም (the real world) እና በሐሳባዊ ዓለም (the ideal-world) መካከል ነው። በቁሳዊው ዓለም ውስጥ የሚኖርና በረቂቁ መልክ ያለው ማንኛውም ነገር ከዚህ ከማይታየው አሚነ መሠረት (Ayyaana) ጋር የተቆራኘ ሲሆን ለአንድ ነገር ባህርይና ጣ ፈንታ ወሳኝነት አለው።

አያና የእያንዳንዱን ነገር ምንነትና ዕጣ ፈንታ የሚወስን ከሆነ የሰው ልጅ ህልውና በአያና ኾኖ ከተገኘው ውጪ ሌላ የመሆን አማራጭ አለው ወይ? ለዚህ ፍልስፍናዊ ጥያቄ ምክንያታዊና አሳማኝ መልስ መስጠት የሚቻለው አንድ ሰው የዋቃ (Waaqa) እና የሳፉ (Safuu) ጽንሰ ሐሳቦችን በትክክል የተገነዘበ እንደሆነ ብቻ ነው። ለምሳሌ ዋቃ የሚለው የኦሮምኛ ቃል Creator ወይም God አሊያም Supreme Being ወደሚለው የእንግሊዝኛ ቃል መተርጎም ትክክል እንዳልሆነ Lambert Bartles በትክክል ያሳስባል። ምክንያቱም በኦሮሞ ፍልስፍና ምንም እንኳ ዋቃ ከሰው ልጅ ዕውቀትና ልምድ በላይ የሆነ (transcendental) እና ከሁሉ የላቀ ነፃልውና ያለው አምላክ ቢሆንም ቅሉ፣ ከሁማ ጋር አብሮ የነበረና ያለ (immanent) እንጂ ራሱን ሙሉ በሙሉ ከተጨባጩ ዓለም ነጥሎ የሚኖር ስላልሆነ ነው። በዚህ ዓለም ውስጥ ዋቃ በብዙ መንገድ ራሱን የሚገልጽ ሲሆን፣ እንደ ህልውና (being) የምንረዳቸው ወይም የምናስባቸው የተለያዩ ነገሮች ሁሉ የእርሱ የፈጠራ ውጤቶች ናቸው። ስለዚህ Divinity (“መለኮታዊ”?) የሚለው ቃል የዋቃን ጽንሰ ሐሳብ የተሻለ እንደሚገልጽ Lambert Bartles ያሳስባል። ይህ የሆነበት ዋነኛ ምክንያት ቃሉ በአንድ ጊዜ የአንድን ነገርልውናና የህልውናውን ተፈጥሯዊ ባህርይ (ዓይነት) በአዕምሮው እንዲገነዘብ ያስችለዋል ተብሎ ስለሚታመን ነው።

በተመሳሳይ መልኩ Karl Eric Knutsson ዋቃ የሚለው ቃል በምዕራቡ ‹‹ዓለም›› ነገረ መለኮት አስተምህሮ ውስጥ የምናውቀውን የእግዚአብሔርን አንድነትና ነፃነት ጽንሰ ሐሳብ የማይወክል መሆኑን ያስገነዝባል። እርሱም እንደ Lambert Bartles ሁሉ Divinity የሚለውን ቃል የዋቃን ጽንሰ ሐሳብተሻለ እንደሚገልጸው Authority and Change በተሰኘ የምርምር ሥራው ውስጥ ተከራክሯል።

Lambert Bartles Karl እና Eric Knutsson ነገረ ሰብዓዊ አረዳድና ትንተና (anthropological understanding and interpretation) እንዳለ ሆኖ Undeffrenciated Being የሚለው የእንግሊዝኛ ቃልገር በቀሉን የዋቃን ጽንሰ ሐሳብ የተሻለ ለምን እንደሚገልጸው ፍልስፍናዊ ማብራሪያ መስጠት ያስፈልጋል። ይህንን ፍልስፍናዊሳቤ ከሁለት ወገን ማየት ይቻላል፡፡

አንድም አገር በቀሉ የኦሮሞ ሥነ ዕውቀት ዋቃን የሚገልጽበት መንገድ ጥንቃቄ የተሞላበት ነው። በማንኛውም ጊዜና ቦታ ዋቃ የሚለው ቃል ሲጻፍም ሆነ ሲነገር ‹‹ጉራቻ›› የሚለውን ቅጽል አስከትሎ ነው። ቀጥተኛ ትርጉሙም ‹‹ጥቁር›› ማለት ሲሆን በኦሮሞ ንጽረተ ዓለም ጥቁርነት የልዕልና ምልክት ብቻ ሳይሆን፣ የዋቃን ቀዳማዊነት (Originality) የሚገልጽ ነው። ጥቁርነት የዋቃ ምንነት በሰው አዕምሮ ሊደረስበት የማይቻል እጅግ ፍፁምስጢር መሆኑን የሚገልጽ ጽንሰ ሐሳብ ነው። Dahl እና Gemechu እንደሚያስረዱት ማንኛውም ነገር በአያና መልክ የሚመነጨው ከዚውልውናው ሙሉ በሙሉ ‹‹ከማይታወቅ›› ዋቃ ጉራቻ መሆኑን ይሞግታሉ። ስለዚህ Undeffrenciated Being የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል የዋቃን ጽንሰ ሐሳብ የተሻለ የመግለጽ ብቃት አለው።

ሁለቱም በኦሮሞገር በቀል ፍልስፍና አያናን ከዋቃ ጽንሰ ሐሳብ ነጥሎ መገንዘብ ስለማይቻል ሁለቱም ፈጽሞተቆራኙ ናቸው። ይህ ቁርኝት ከኦሮሞ የፍጥረት ግንዛቤ የሚመነጭ ነው። Dahl እንደሚሞግተው የኦሮሞ ምልዓተ ዓለም፣ ሥነ ምኅዳርና የሰው ልጅልውና ከዋቃ የሚመነጭ ፍሰት ነው። ይህ የሚያመለክተው ፍጥረት ቋሚና ተሠርቶ ያለቀ ነገር ሳይሆን ቀጣይነት ያለው መሆኑን ነው። በኦሮሞ ንጽረተ ዓለም ፍጥረት በሆነ ወቅት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ብቻ ተከናውኖ ያበቃ ጉዳይ አድርጎ መውሰድ ስህተት ነው። የፍጥረት ድርጊት አሁንም ቢሆን አለና።

በዚህ መሠረት ምንም እንኳ የማንኛውም ነገር ተፈጥሯዊ ባህርይና ዕጣ ፈንታ በአያና የሚወሰን ቢሆንም ቅሉ፣ የሁማ ወይም የአያና ህልውና በራሱ የተመሠረተው በዋቃ ላይ ነው። ስለዚህ የአያና እና የዋቃ ጽንሰ ሐሳቦች ፈፅሞ የተቆራኙ ናቸው ሲባል፣ ሁለቱም አንድ ናቸው ማለት እንዳልሆነ በአጽንኦት ሊሰመረበት ይገባል። አያና የዋቃ ‹‹ንዑስ አካል›› ነው። Lambert Bartles ‹‹አያና ዋቃ ነው፣ ዋቃ ግን አያና አይደለም›› ሲል የሚሞግተው ይህንን ታሳቢ በማድረግ መሆኑን አሁንም ልብ ማለት ያሻል። ዋቃ ከሁሉም ሰዎች ጋር ግንኙነት ያለው ሲሆን፣ እያንዳንዱ ግለሰብ የእርሱንርዳታ ይጠይቃል።

በተቃራኒው አያና የዋቃ ነፀብራቅ ነው።ርዳታውን የሚጠይቁ ግለሰቦች በምርጫ አሊያም በተፈጥሮ ከእርሱ ጋራ ግንኙነት ያላቸው ናቸው። አያና ከዋቃ የሚፈስና ሁሉንም ፍጥረት የሚሞላ ነው። የእያንዳንዱን ፍጡር ውስጣዊና ውጫዊ ውቅረትም ይወስናል። ሆኖም አያና ለሰዎች ሳይታይ ይኖራል። ለምሳሌ የምናየው ግለሰቡን እንጂ አያና(ውን) አይደለምና። ይህ የማይታየው አያና ነው የሚታየውን የሰው ገጽታ የሚሠራውና የሚወስነው። በሌላ አገላለጽ በዚህ ዓለም ውስጥ ነገሮች ማንነታቸውን ወይም ተፈጥሯቸውን ጠብቀው መኖር እንዲችሉ የሚያደርጋቸው አያና ነው፡፡ የራሳቸውልውና እንዲኖራቸውም ያደርጋል። እንደ Lambert Bartles ሁሉ ዋቃ የሚለው ቃል በጣም አጠቃላይ ጽንሰ ሐሳብ የሚወክልና አያናን እንደሚያካትት Karl Eric Knutsson ይሞግታል።

እዚህ ላይ አንድ ነገር ልብ ማለት ያሻል። አያና እንደ ሁማ በጊዜና በቦታ ሕግ አይገዛም። የሁሉም ነገሮች ምንነት አስገኝ አያና ነው። ማንኛውም ህልውና ወደ መኖር ከመምጣቱ በፊት አያና() ነበር። የነገሮች መኖር ወይም የህልውናቸው ምክንያት አያና ሲሆን የአያና የመጨረሻ አስገኝ (ultimate-cause) ደግሞ ዋቃ ነው። ዋቃ የሁሉ ነገር አስገኝ የማይጠፋ፣ማይለወጥ፣ ቋሚና ዘለዓለማዊ ነው። ስለዚህ አያና ነገሮች ማንነታቸውን ጠብቀው እንዲኖሩ የሚያደርጋቸው በዋቃ በኩል ብቻ ነው። በኦሮሞ ንጽረተ ‹‹ዓለም›› ጽንሰ ሐሳብ አያና የነገሮች ሁሉ አስገኝ ተደርጎ ይወሰዳል። በዚህ አኳኋን አያና ሁማን እንደሚያካትት ሁሉ ሁማም አያናን ያቅፋል። በአገር በቀሉ የኦሮሞ ሃይማኖት አስተምህሮ መሠረት እያንዳንዱ ሰው በአያና በኩል በተቀበለው ፀጋ አማካይነት ፈጣሪውን ያመሠግናል። ሁሉን ቻይ ለሆነው ዋቃዮ የሚቀርበው ይህ ምስጋና የተለያዩ ሃይማኖታዊ መገለጫዎች አሉት። የኢሬቻ ክብረ በዓል ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ነው።

ኢሬቻ የምስጋና ቀን!

ኢሬቻ በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ እንደ ቅዱስ በዓል ይከበራል።ኢሬቻ በዓል ለዋቃ ጉራቻ ምስጋና የሚሰጥበት ቀን ነው። የመልካም ነገሮች ሁሉ ምንጭ ዋቃዮ ነው። ሕዝቡ ለዚህ መልካም ስጦታ ከልብ የመነጨ ምስጋና ለአምላኩ የሚያቀርብበትናየዋቃዮ ስጦታ ተመልሶ ለዋቃዮ የሚሰጥበት ቅዱስ በዓል ነውብለው ከልብ ያምንበታል። ስለዚህ ኢሬቻ ማለትስጦታማለት ነው።

በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ለምለም ሳር የሰላምና የብልፅግና ምልክት በመሆኑ፣ በኢሬቻ በዓል ላይ የሚሳተፈው እያንዳንዱ ግለሰብ፣ ይህንን ለምለም በሁለት እጆቹ በመያዝ አምላኩን ያመሰግናል። ከሁሉም በላይ ክረምቱን ከበረዶ፣ ከከባድ ነፋስ፣ ከጎርፍና ከውርጭ የታደጋቸውን ታላቅና ቅዱስ አምላካቸውን አንድ ላይ ሆነው ያመሠግናሉ። መኸሩንና አዝመራውን ደግሞ እንዲባርክላቸው ወደ ፈጣሪ ይጸልያሉ። ስለዚህ የኢሬቻ በዓል ከጨለማ ወደ ብርሃን ላሻገረ አምላክ የሚሰጥ የክብር ዋጋ ነው።

አገር በቀል የሆኑ የእምነት በዓላትን የመገንዘብና የማብራራት ችግር ያለባቸው ኢትዮሮፒያንስ (Westernized Ethiopians) ግን፣ የኢሬቻ በዓልን በተሳሳተ መንገድ ሲረዱና ሲተረጉሙ ይታያሉ። ለምሳሌ በበዓሉ ላይ የሚደረገውን የአምልኮ ሥነ ሥርዓት በመመልከት፣ ሕዝቡ ዋቃዮን ሳይሆን ውኃውን አሊያም ሰይጣንንእንደሚያመልክአድርገው ይረዳሉ። ኦድላይ ሶቴቪንስንበአቶሚክ ቦንብ ውስጥ ሰይጣን የለም፣ በሰዎች ልቦና እንጂእንዳለ ሁሉ፣ ሰይጣን በእነዚህ ሰዎች አዕምሮ ውስጥ እንጂ በውኃ ውስጥ አይኖርም። ሰይጣን ዳክዬ ወይም ጉማሬ አይደለም፡፡ ካልጠፋ ቦታ ውኃ ውስጥ አሁን ምን ይሠራል! ባይሆን የሰይጣን ትክክለኛ አድራሻና ማደሪያ የሰው ልቦና ነው፡፡ ስለዚህ ኢትዮሮፒያንስ ሰይጣንን ልቦናቸው ውስጥ ይፈልጉት!

በተቃራኒው ውኃ የሕይወት ምልክት ነው። ለዚህም ነው ውኃና ልምላሜ እንደ ዋቃዮ ስጦታ የሚታዩት። ያለ ውኃ ሕይወት ቀጣይነት የለውም። ውኃ ዋቃዮ ለፈጠራቸው ልጆቹ የሰጠው ፀጋ ነው። ድሪቢ ደምሴ ቦኩ እንዳለው፣ኦሮሞ ወንዝ፣ ጫካና ተራራ ይወዳል፣ የተፈጠረበትና ፍቅር ያገኘበት ስለሆነ በየዓመቱ ለምለም ሳርና የአደይ አበባ ይዞ ለኢሬቻ ወንዝ ውኃ ዳርቻ በመሄድ፣ ተራራ ላይ በመውጣት፣ ለፈጣሪው ምስጋና  ያቀርባል። በጤና፣ በሰላም፣ ለሰውና ለከብትርባታ እንዲሰጠውም ይጸልያል።

ኢሬቻ ሃይማኖታዊ ክብረ በዓል ነው። ለምሳሌ ፋሲካ፣ አረፋ፣ ጥምቀት፣ ገና…፣ ወዘተ ሃይማኖታዊ በዓሎች ናቸው እንጂ፣ በራሳቸው ሃይማኖት አይደሉም፡፡ የኦሮሞገር በቀል ሃይማኖት ዋቄፋና ተብሎ ይጠራል። Waaqa ማለት እግዚአብሔር ማለት ሲሆን፣ Faana ማለት ደግሞ መከተል ማለት ነው። ትርጉሙም ፈጣሪን/እግዚአብሔርን መከተል ማለት ነው። ለኦሮሞ ሕዝብ ዋቃ የሁሉ ነገር አስገኝ፣ የማይጠፋ፣ የማይለወጥ፣ ቋሚና ዘለዓለማዊ ነው። የሁሉም ነገር ምንጭ ዋቃ ነው። ዋቃ ምሉዕ በኩለሄ (omniscient) ሁሉን ቻይ (ominipresent) ዘላለማዊ (eternal) ፍፁም (absoulute) እና ገደብ የሌለው (infinite) ነው።

የኢሬቻ ቅዱስ በዓል ጸሎት

ሀዬ! ሀዬ! ሀዬ! (አሜን አሜን አሜን)

ሀዬ! የእውነትና የሰላም አምላክ!

ሀዬ! ጥቁሩና ሆደ ሰፊው ቻይ አምላክ!

በሰላም ያሳደርከን በሰላም አውለን!

ከስህተትና ከክፉ ነገሮች ጠብቀን!

ለምድራችን ሰላም ስጥ!

ለወንዞቻችን ሰላም ስጥ!

ከጎረቤቶቻችን ጋር ሰላም ስጠን!

ለሰውም ለእንስሳቱም ሰላም ስጥ!

ከገዳ ባህላችን ከዋቄፋና እምነታችን ጋር አኑርልን!

አንድነታችንን አጠንክርልን!

ትናንሾቻችንን አኑርልን!

ጤነኛና ብልህ ልጆች ስጠን!

ወላድ በጤና ትገላገል!

የወለደችውን አሳድግላት!

ሕፃን በእናቱ እቅፍ ይደግ!

ለወላድ ጤናና ዕድሜ ስጣት!

ላልተማረው ዕውቀት ስጥልን!

አምላክ አደራጀን!

አደራጅተህ አታፍርሰን!

ተክለህ አትንቀልን!

ፈጥረህ አትዘንጋን!

ክፉውን ያዝልን!

ከወንጀልና ከወንጀለኛ አርቀን!

ምቀኛና ቀናተኛውን ያዝልን!

ከመጥፎ አየር ጠብቀን!

ንፁሕ ዝናብ አዘንብልን!

ያለአንተ ዝናብ የእናት ጡት ወተት አይሰጥምና!

ያለአንተ ዝናብ የላም ጡት ወተት አይሰጥምና!

ያለአንተ ዝናብ መልካው ውኃ አይሰጥምና!

ያለአንተ ዝናብ ምድሩ ቡቃያ አይሰጥምና!

ከእርግማን ሁሉ አርቀን!

በአባቱ ከተረገመ አርቀን!

በእናቷ ከተረገመች አርቀን!

እውነትን ትቶ ከሚዋሽ አርቀን!

ከረሃብ ሰውረን!

ከበሽታ ሰውረን!

ከጦርነት ሰውረን!

ልጄ እያሉ አልቅሶ ከመቅበር ሰውረን!

በጥቁር ፀጉር ከመሞት ሰውረን!

በነጭ ፀጉር ከመደህየት ሰውረን!

አርሶ ምርት ከማጣት ሰውረን!

ከሌላ ሰው ጦስ ሰውረን!

ከከፉ ነገር ሁሉ ሰውረን!

ገዳው የሰላም፣ የልምላሜና የድል ነው!

ሀዬ! ሀዬ! ሀዬ!

የኦሮሞ ባህልን ከወንጌል እሴቶች (Gospel Values) ጋር እንዲስማሙ አድርጎ ማስተማር

ኢሬቻ የባዕድ አምልኮ ነው!” ለሚሉት ሰዎች መልስ ለመስጠት ውድ ጊዜያቹን በከንቱ ባታጠፉ መልካም ይመስለኛል! በኦሮሞ (አፍሪካ) ፍልስፍና ዙሪያ ምርምር እያደረግን ያለን ግለሰቦች፣ ከዚህ በፊት በቂ መልስ ሰጥተንበታል፣ ማድረግ ያለብህን ነገር የኦሮሞ ባህልን ከወንጌል እሴቶች (Gospel Values) ጋር እንዲስማሙ አድርጎ ማስተማር ነው። ኦሮሙማ – OROMUMMAA (Oromo identity) የፈጣሪ ስጦታ ነውና እንንከባከበው! የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ፣ ቋንቋና ማንነት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳንል እናስተምር፡፡ ከመማር አንቦዝን! ክርስቶስ ወደዚች ምድር ይዞ የመጣው ‹‹ወንጌል›› ፍቅር፣ ሰላምና አንድነትን እንጂለ… ነፍስ ዲያቆን መች አነሰው!” የሚለው ወንጀል አይደለም! ስለዚህ ራሳችንን ከህሊና ባርነት ነፃ እናውጣ! አንተ የፈጣሪ ውድ ልጅ ነህ! በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ያለን እንደሆነ፣ እንደ አነ አባ Lambert Bartles አባ Joseph Loo፣ አባ Claude Sumner፣ Fr. Ton Leus…etc በኦሮሞ ሕዝብ ባህልና ፍልስፍና ላይ ጥልቅ ምርምር እናድርግ! በስፋት ተመራመሩበት! የሌሎችን ባህል፣ ቋንቋና ሃይማኖት አክብሩ! በፍፁም አታንቋሽሿቸው! ስለማንነትህ የገዛ ነፍስህን እንኳ ሳትሳሳ አሳልፈህ ለመስጠት ሁሌም ዝግጁ ሁን!፡፡ ቸር እንሰንብት፡፡

 

ከአዘጋጁ፡-

ጸሐፊው የቢኤ፣ የማስተርስና የፒኤችዲ ዲግሪዎችን በፍልስፍና፣  በሳከርድ  ቴኦሎጂ ቢዲ ሲኖራቸው፣ በካፑቺን ፍራንቸስካና የፍልስፍናና የነገረ መለኮት ኢንስቲትዩት (CFIPT) የአፍሪካ ፍልስፍና መምህር ናቸው፡፡  የምርምር ትኩረታቸውም በMetaphilosophy, Oromo Philosophy, Continental Philosophy, Post-colonial African Philosophy, Sage Philosophy, and Post-modernism ላይ  ነው፡፡ በኅትመት ደረጃ ‹‹Metaphilosophy or Methodological Imperialism? The Rationale for Contemporary African Philosophy with Reference to Oromo Philosophy›› እና ‹‹የኢትዮሮፒያንስ አስተሳሰብ፤አበበ በሶ በላ› vs ‹ጫላ ጩቤ ጨበጠ›..››ን ጨምሮ ከኦሮሞ ፍልስፍና ጋር የተያያዙ በርካታ መጻሕፍትንና የጥናት ውጤቶችን አሳትመዋል፡፡ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles