Friday, July 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊለተፈናቀሉ ወገኖች የሚደርሰው ድጋፍ በአግባቡ እየተሠራጨ አለመሆኑ ተገለጸ

ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚደርሰው ድጋፍ በአግባቡ እየተሠራጨ አለመሆኑ ተገለጸ

ቀን:

በኢትዮጵያ ከተለያዩ ቦታዎች ተፈናቅለው ለሚገኙ ወገኖች የሚደርሰው የሰብዓዊ ዕርዳታ ድጋፍ በአግባቡ እየተሠራጨ ባለመሆኑ ቅሬታ እየፈጠረ መሆኑን ተገለጸ፡፡

ይህም የተገለጸው የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ የበላይ ጠባቂ አባቶች ሐሙስ መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም. በካፒታል ሆቴል ‹‹በጎነት ለሰብዓዊነትና ለአገር ሰላም›› በሚል መሪ ቃል የድጋፍ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብርን አስመልከቶ በሰጡት መግለጫ ነው፡፡

የኢትዮጵያ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር እድሪስ እንደገለጹት፣ በተለያዩ ተቋማት ላይ ለተጎዱ ወገኖች የሚደረገው የድጋፍ ማሰባሰብ መርሐ ግብር የሚበረታታ ቢሆንም፣ ድጋፉን የሚሹ ወገኖች ሆኑ ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተደጋጋሚ ቅሬታ ሲያስነሱ እየተሰማ ነው፡፡

2013 ተፈጥሯዊም ሆነ ሰው ሠራሽ ችግሮች ያስተናገደ ዓመት መሆኑን ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ፣ ‹‹ይህንን ተረድቶ ያሉትን ክፍተቶች በመገንዘብና በማሳለፍ በተለያየ ምክንያት የተጎዱ ወገኖችን በመደገፍ ፈጣሪ የሚወደውን ሥራ መሥራት ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡

የድጋፍ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብሩም የሁሉም ሃይማኖት ተቋማት ድርሻ እንደሆነ፣ ከዚህም በተጨማሪ ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር ለተቸገሩ ወገኖች መድረስ እንደሚገባ አክለዋል፡፡ በተለይም በውጭ አገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን (ዳያስፖራዎች) የወገኖቻቸውን ችግር በመረዳት በገንዘብም ሆነ በቁሳቁስ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አብራርተዋል፡፡

ከዚህ በፊትም ከመከላከያ፣ ከየሠራተኛው ከሃይማኖት ተቋማት እንዲሁም ከማኅበረሰቡ ለተፈናቀሉ ወገኖች የገንዘብም ሆነ የዓይነት ድጋፍ መደረጉን ገልጸው፣ በአሁኑ ወቅትም ይህንንም ድጋፍ ለተጎዱ ወገኖች በተገቢው መንገድ ለማድረስ የተዋቀሩት ኮሚቴዎች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡  

በኢትዮጵያም ችግሩ በተከሰተበት ቦታዎች ላይ ሕፃናት፣ አረጋውያንና እናቶች በአጣብቂኝ ውስጥ እንደሚገኙ፣ እነዚህንም ወገኖች ለመታደግ የሁሉም ኃላፊነት መሆን እንዳለበት የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አረጋዊ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

ለተጎዱ ወገኖች በትክክለኛው መንገድ ድጋፍ በማድረስና በሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ በተከፈተው የንግድ ባንክ አካውንት የገንዘብ ዕርዳታ በማድረግ ሁሉም የበኩሉን ተሳትፎ እንዲያደርግ ብፁዕ አቡነ አረጋዊ በአጽንኦት አሳስበዋል፡፡

በተለያዩ ቦታዎች ላይ የተጎዱ ወገኖችን ለመርዳት የሃይማኖት ተቋማት ትልቁን ድርሻ እንደተወጡ፣ ከዚያም አልፎ የተፈናቀሉትን ወገኖች ታሳቢ በማድረግ ካለፈው ጳጉሜን 1 እስከ ጳጉሜን 5 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ የጸሎት መርሐ ግብር መከናወኑን ያስታወሱት የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ወርቅነሽ ብሩ ናቸው፡፡  

በአሁኑ ወቅትም የተዋቀረው ኮሚቴ ‹‹በጎነት ለሰብዓዊነትና ለአገር ሰላም›› የሚል መሪ ቃልን በመከተል የሚሠራ መሆኑን፣ ይህንንም ለማሳካት የገንዘብ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጋር በመነጋገር ፈቃድ እንዲያገኙና የሒሳብ አካውንት እንዲኖራቸው መደረጉን ሚኒስትር ዴኤታዋ አስረድተዋል፡፡

በዓይነትም ሆነ በገንዘብ የሚመጣውን ግብዓት የተዋቀረው ኮሚቴ በራሱ መንገድ ለተጎዱ ወገኖች የሚያደርስበት ሁኔታ ማመቻቸቱን ያስታወሱት ወ/ሮ ወርቅነሽ፣ ይህንን በጎ ተግባር ለማድረግ በየክልሉ ከሚገኙ የሰላም ሚኒስቴር ተቋማት ጋር በቅንጅት የሚሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ለተጀመረው ዘመቻ ስኬት በኢትዮጵያ ንግድ  ባንክ የባንክ አካውንት 1000430591251 እና የዶላር አካውንት 0100051300080  መከፈቱ ተገልጿል፡፡ 

ኅብረተሰቡ ለተፈናቀሉት ወገኖች የበኩሉን አስተዋጽዖ እንዲደርግ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔው ጥሪ አቅርቧል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...