የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ፍትሕ ወልደሰንበት (ዶ/ር) የምሥራቅ አፍሪካ ዞን አምስት የእጅ ኳስ ተቋምን በፕሬዚዳንትነት እንዲመሩ ተመርጠዋል፡፡ የዞኑን እጅ ኳስ በፕሬዚዳንትነት እንዲመሩ በበይነ መረብ በተደረገው ምርጫ የኡጋዳዋን ዕጩ ተወዳዳሪ ስድስት ለሦስት በሆነ ድምፅ አሸንፈው ስለመሆኑም የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፈዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡
ባለፈው ሐሙስ መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም. በተደረገው የዞን አምስት ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ላይ የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን በዚህ ደረጃ ኃላፊነት ሲረከብ የመጀመርያ ስለመሆኑ ጭምር ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡ ዞኑን ላለፉት ሦስት ዓመታት ሲመሩ የቆዩት ኡጋንዳዊቷ ቪላ ሪቻርድ እንደነበሩም ተመልክቷል፡፡
ምርጫውን አስመልክቶ አስተያየታቸውን ለሪፖርተር የሰጡት የዞን አምስት አገሮችና የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ፍትሕ ወልደሰንበት (ዶ/ር)፣ ‹‹ይህ እንደ አገር ከፍተኛ ስኬት ነው፣ ከዚህም ባሻገር እንደ እነዚህ ዓይነት ዕድሎች ለስፖርቱ የሚፈጥረው ዕድል ይኖራል፡፡ በዞኑ በሚኖረኝ የኃላፊነት ጊዜ ከማሳካቸው ዓበይት ጉዳዮች ስፖርቱን ከማሳደግ በተጨማሪ፣ ጽሕፈት ቤቱን ወደ አዲስ አበባ ማምጣት የዕቅዴ አንዱ አካል እንዲሆን ነው፡፡ ግን ደግሞ ይህን ለማድረግ መንግሥት የኢትዮጵያን እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ከቢሮ ጋር የተያያዙ መሠረተ ልማቶች እንዲሟሉለት ድጋፍ ማድረግ ሲችል ብቻ ነው፤›› ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ እጅ ኳስ ከውድድርና ሥልጠና ጋር ተያይዞ ከፍተኛ እጥረት እንዳለ የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ ‹‹ከዚህ በኋላ ብሔራዊ ተቋሙ ከአፍሪካና ከሌሎችም ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ግንኙነት በመፍጠር ችግሮቹን ለመቅረፍ ይሠራል፤›› ብለዋል፡፡
በዞን አምስት ግብፅ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ጅቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ቡሩንዲና ኢትዮጵያ በኮንግረሱ መሳተፋቸውን ጭምር ፕሬዚዳንቱ ፍትሕ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡