በቅድሚያ በአጠቃላይ ሲታይ በአሁኑ ጊዜ በአገራችን ያለውን ችግርና ፈተና በአንክሮ እየተመለከቱ ፈጣሪ ቀና ቀናውን አመላክቷቸው ሰላምን ለማውረድ ለሚጥሩ ሁሉ፣ በግሌ ያለኝን ልባዊ አክብሮትና አድናቆት ልገልጽ እወዳለሁ፡፡ ጥረታቸውም እንዲሳካላቸው ከሚፀልዩትና ከሚመኙት ሰዎች አንዱ ነኝ፡፡
ከተዓማኒ ምንጭ በተጨባጭ ሁኔታው ላይ ያተኮረ ጥርት ያለ ዜና በተገቢው መንገድ የማግኘት ችግር በአንድ በኩል፣ በሌላ በኩል ደግሞ በርካታ የተወሳሰቡና ዝብርቅርቅ ያሉ የዜና ዘገባዎች ባሉበት ሁኔታ ላይ የምንገኝ መሆናችን ግልጽ ነው፡፡ ስለሆነም እውነተኛውን ነባራዊ ሁኔታ ተረድቶ በወቅታዊ ሒደቶች ላይ ከግል ድምዳሜ ላይ መድረስ አዳጋች የመሆኑ ጉዳይ እኔን እንደሚያስቸግረኝ ሁሉ፣ ሌሎችንም እንዲሁ ያስቸግራቸዋል ብዬ አምናለሁ፡፡
ከላይ እንደጠቀስኩት በአጠቃላይ የሚሰማውና የሚታየው የመረጃ መወሳሰብ፣ እያንዳንዱ ሰው በቅርብ ከኖረበት፣ በይበልጥ ከሚያውቀውና የቅርብ ቤተሰቡ ከሚገኝበት አካባቢ ተገኙ ተብለው የሚሰሙትን የሞት፣ የረሃብ፣ የሰላም ማጣትና የመፈናቀል ችግሮች አስመልክቶ የሚነገረው ሁሉ፣ ከቦታው ርቆ ላለ ከፍተኛ የአዕምሮ ጭንቀት የሚያሳድርበት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በመሆኑም ጭንቀቱን የሚገልጽበትን መንገድ በአዕምሮው ማሰላሰሉ አይቀርም፡፡
ስለሆነም ‹‹ውሻ በበላበት ይጮሃል›› እንደሚባለው እኔ የዚህ የግል ግልጽ ደብዳቤ ማሳሰቢያ አቅራቢ፣ በሚገባ ተንከባክባ፣ አሳድጋ፣ አስተምራ፣ ድራ ኩላ ለአሁን ማንነቴ ምክንያት በሆነችው ወልድያ ከተማና በአካባቢዋ የሚገኙትን ከተሞችና ሠፈሮች አስመልክቶ የሚነገሩት ለትክክለኛነታቸው እርግጠኛ መሆን ያልተቻለባቸው ዜናዎች ከፍተኛ ጭንቀትና የመንፈስ አለመረጋጋት ስላሳደሩብኝ፣ ስሜቴን በሥራ ጠባያቸውና ኃላፊነታቸው ለውጥ ሊያመጡ ለሚችሉ ሁሉ ለመግለጽ ግዴታ ከሆነብኝ ሰንብቷል፡፡
በዚያ አካባቢ ላደግንና እኔን ጨምሮ ከረድኤቱ ለተቋደስን ሁሉ የአካባቢውን ሰው ሰላማዊነት፣ ደግነት፣ እንግዳ ተቀባይነት፣ ቸርነት፣ አፍቃሪነት፣ የዋህነት፣ በአጠቃላይም «የደጋጎቹ» አካባቢ በመባል ሲጠራ የኖረው ኅብረተሰብ በማያፈናፍን ታላቅ ችግር ላይ ሆኖ ማየት እጅግ ከባድ ነው፡፡
ይህ ደግ ኅብረተሰብ በተለይ አሁን ያለበትን ወቅታዊ ሁኔታ ስንመለከት በቀጣይነት ሊገጥመው የሚችለው ዕጣ ፈንታ ምን ይሆን? በውስጡ የሚገኙት አረጋውያን፣ ሴቶች፣ ሕፃናት፣ የጤና እንከን ያለባቸው ሁሉ አሁን ያሉበትና በቀጣይነትም ሊገጥማቸው የሚችለው መከራና ፈተና ምን ይሆን? ከሚሉት ጥያቄዎች ላይ እውነተኛ መረጃ አለማግኘት ተጨምሮበት የስሜት መረጋጋት ሊኖር አይችልም፡፡ ስለሆነም እጅግ የከፋ ጥፋት፣ ችግርና መከራ ይደርስ ይሆን? የሚለው ጥያቄ በአካባቢው ላደግን ወገኖች የዕለት ተዕለት የሥጋትና ጭንቀት ምንጭ ሆኗል፡፡
ልዩ ልዩ ችግሮች ከደረሱ በኋላ ለወገን መልሶ መቋቋም መድረስ ላይ አስደማሚ ከፍተኛ ጥረት እንደሚደረግ ሁሉ፣ ከመነሻው ጥፋቱ እንዳይደርስ ከፍተኛ ጥንቃቄና ጥረት ማድረግ ቀደምት አማራጭ መሆኑ ለሁሉም ግልጽ ነው፡፡ በዚህም ረገድ ጥረት እየተደረገ ይሆናል የሚል ግምት አለኝ፡፡
የተጨናነቀ ስሜትን ለማረጋጋትና የአካባቢው ችግር ያላንዳች ተጨማሪ ጥፋት መፍትሔ እንዲያገኝ ለማድረግ የሁሉም ጥረት ወሳኝነት እንዳለው አምናለሁ፡፡ በተለይ ግን በግል ተሰሚነት፣ በወሳኝነት፣ በአስተዳደር፣ በመንፈሳዊ አባትነት፣ ወዘተ እንዲሁም በታሪክ አጋጣሚ በወቅቱ በኃላፊነት ላይ ያላችሁ ኢትዮጵያውያን ወገኖች ሁሉ የምንወዳትን ወልድያንና አካባቢዋን በሆደ ሰፊነት፣ በጥበብና በፈሪኃ እግዚአብሔር ተመርታችሁ ውድመት፣ ጥፋትና የባሰ ቀጣይ ረሃብ እንዳይደርስ የሚያስችል መልካም ሥራ በመሥራት አካባቢውን ትታደጉት ዘንድ በታላቅ ትህትና አሳስባለሁ፣ እማፀናለሁም፡፡ የፈራነው ቀርቶ ፈጣሪ በኪነ ጥበቡ የመፍትሔውን መንገድ አመቻችቶ እንዲታደገን ከልብ እለምናለሁ፡፡
(አረጋ ይርዳው (ዶ/ር)፣ ከአዲስ አበባ)