Thursday, May 30, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉለፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ክፍለ ኢኮኖሚ ሚና

ለፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ክፍለ ኢኮኖሚ ሚና

ቀን:

(ክፍል አንድ)

በበቀለ ፀጋዬ

ለፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ክፍለ ኢኮኖሚ ሚናን በማሳየት፣ ይህንኑ ዘርፍ ለማሳደግ ሊወሰዱ የሚገቡ የፖሊሲና አስተዳደራዊ ዕርምጃዎችን በመጠቆም የመወያያ አጀንዳም እንዲሆን አቅርቤአለሁ፡፡

- Advertisement -

የማኑፋክቸሪንግ  ወይም የአምራች ኢንዱስትሪ ክፍለ ለኢኮኖሚ ትኩረት መስጠት ያለበት ምክንያት ክፍለ ኢኮኖሚው ከሌሎች ከበለፀጉ አገሮች ታሪክም እንደምንረዳው የአገር ዋንኛ የኢኮኖሚው መሠረት በመሆኑ ነው፡፡ የአምራች ኢንዱስትሪው ሁሉንም የኢኮኖሚ አውታሮች ማንቀሳቀስ የሚችል ትልቅ ሞተር ነው ማለት ይቻላል፡፡ አገራችን ለዚህ ኢንዱስትሪ የሚያገለግሉ በቂ የተፈጥሮና ታዳሽ ጥሬ ዕቃዎች እንዳሏት ብዙ ማስረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ፕራይመር ሀብቶች የተባሉትን የተፈጥሮና ታዳሽ ሀብቶችን ለአገር ትልቅ ጥቅም ወደ የሚሰጡ ሀብቶች መለወጫ መሣሪያ (Tool) ነው፡፡ እነዚህ ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው የሚያገለግሉ ቀጥተኛ ግብዓቶች ወይም ጥሬ ዕቃዎች የእርሻ ውጤቶች፣ የማዕድን ሀብቶች፣  የኤሌክትሪክ ኃይል፣ አየርና ውኃ ናቸው፡፡ አየርና ውኃ እንዴት የኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃ ይሆናሉ የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ ውኃን በተመለከተ ለማጠቢያነት የሚኖረው አገልግሎት እንደተጠበቀ ሆኖ በጥሬ ዕቃነት ለፈሳሽ ሳሙናዎች ምርት፣ ለቢራና ለስላሳ መጠጦች፣ ግሉኮስና በፈሳሽ መልክ ለሚሰጡ የተለያዩ መድኃኒቶች ጨምሮ ለበርካታ ምርቶች ለጥሬ ዕቃነት ያገለግላል፡፡ አየር በቀጥተኛ በማጣራትና በመለየት ለምሳሌ ኦክስጅን ለመተንፈሻ ከሚሰጠው የጤና አገልግሎት ውጪ ለላብሳ (የዲተርጀንት ዋና ጥሬ ዕቃ) የመሳሰሉት የኬሚካል ኢንዱስትሪ ምርቶች ለማምረትም ያገለግላል፡፡ ናይትሮጂንና ኦክስጂን ለዩሪያ ማዳበሪያ ምርትም  ከጥሬ ዕቃዎቹ ዋነኛዎቹ ናቸው፡፡ ናይትሮጂን ሌሎች በርካታ እንደ አሞኒያ አምኒይም ናይትሬት ማዳበሪያን ናይትሪክ አሲድ የመሳሰሉትንም በርካታ ምርቶች ለማምረት ያገለግላል፡፡

ሌላው የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ጠቀሜታ ከፍተኛ የኋልዮሽና የወደፊት የኢኮኖሚ ትስስር የሚፈጥር የቴክኖሎጂ የኢኮኖሚ ዘርፍ መሆኑ ነው፡፡ እነዚህ እርስ በርስ የሚደጋገፉ የኢኮኖሚ ዘርፎች ናቸው፡፡ አምራች ኢንዱስትሪው የግብርና ማሽነሪዎችን ማዳበሪያና ፀረ ተባዮችና ፀረ አረም በማቅረብ የእርሻውን ክፍለ ኢኮኖሚ ሲያሳድግ የእርሻው ክፍለ ኢኮኖሚ ደግሞ ሲያድግ በቂ ጥሬ ዕቃዎች ለአብነት ለምግብ ዘይቶች ዕድገት ማነቆ  የሆኑትን  የቅባት እህሎች፣ ለዳቦ ምርት ስንዴ ለእንስሳት መኖ  በቆሎ ለቢራ ፋብሪካዎች የብቅል ገብስ የመሳሰሉትን ያቀርባል፡፡ ይህ የሚያሳየው ግብርናና ኢንዱስትሪው እንዴት እንደሚደጋገፉ ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ አምራች ኢንዱስትሪው ሲያድግ ግብርናውን ያሳድጋል፡፡ ግብርናው ሲያድግ ተመልሶ ኢንዱስትሪውን ያሳድጋል ማለት ነው፡፡

የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው በራሱ የሚፈጥራቸው የውስጥ ትስስሮች የአንዱ ኢንዱስትሪ ለሌላው ጥሬ ዕቃ መሆን የብረታ ብረትና የኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪው ለሌሎች ኢንዱስትሪዎች በማምረቻ መሣሪያነት የሚኖረው መመጋገብ የመሳሰሉት ግንኙነቶች ሌሎች ማሳያዎች ናቸው፡፡ በሌላ በኩል የኋልዮሽና የወደፊት ግንኙነቶችን በተመለከተም ብዙ የሥራ ዕድል እየፈጠረ ለሚገኘው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ከሲሚንቶ፣ ብረት፣ ሴራሚክ፣ የእንጨትና የኤሌክትሪክ ዕቃዎችንና ሌሎች ግብዓቶች ምንጭ መሆኑም ዕውቅ ነው፡፡ የአምራች ኢንዱስትሪው ለንግድና ሌሎች የአገልግሎት ሰጪ ክፍለ ኢኮኖሚ ዕድገት ሊያበረክተው የሚችለውን አስተዋጽኦም ዘርዝሮ መጨረስ አይቻልም፡፡  እነዚህ ሁኔታዎች የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ምን ያህል የኢኮኖሚው አንቀሳቃሽ ሞተር እንደሆነ የበለጠ ያረጋግጣሉ፡፡ ስለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ጠቀሜታና አስፈላጊነት ይህን ያህል ካልን ይህን ክፍለ ኢኮኖሚ ለማሳደግ የትኞቹ በውስንነት የሚታዩ ፖሊሲዎችና የአሠራር ሒደቶች ሊሻሻሉ ይገባል የሚሉትን ሐሳቦችን እንያቸው፡፡

የሚታዩ  ውስንነቶች

ውስንነቶቹ ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና የፕሮጀክት ማኔጅመንት ብቃት ማነስ በሚል ሊገለጹ ይችላሉ፡፡ ይሁን እንጂ ይበልጡኑ በአንዳንድ ፖሊሲ ነክ በሆኑ ጉዳዮች ያጋጠሙ ክፍተቶችና የመፍትሔ ሐሳቦች እንደሚከተለው ይቀርባሉ፡፡ የኢንዱስትሪ ፖሊሲን በተመለከተ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አዲስ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ እያስጠና እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ በሚዘጋጀው ፖሊሲ ትኩረት የሚያገኙ ከሆነ እሰየው ነው፡፡ ካልሆነ ግን በዚህ የጽሑፍ አዘጋጅ የተወሰኑ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚያስፈልጉ ጉዳዮች እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡

በቀላል ኢንዱስትሪ (Light Indsustry) ላይ የተመሠረተው በሚገባ ፖሊሲ ሊፈተሽ ይገባል የሚለው ነው፡፡ ቀላል ኢንዱስትሪ የሚለው በዋናነት በጨርቃ ጨርቅ በቆዳ፣ በምግብና መጠጥ በአግሮ ኢንዱስትሪ ወዘተ. ላይ የተመሠረቱ ኢንዱስትሪዎች ሆነው ፖሊሲያችን በእነዚህ ዓይነት ፋብሪካዎች ግንባታ ላይ ብቻ የተመሠረተ መሆኑ ነው፡፡ ብዙ የጉልበት ሠራተኛ እንዲሁም በቀላሉ ሊሠለጥን የሚችል የተማረ የሰው ኃይል ስላለ በተለይ ብዙ የሰው ኃይል የሚቀጥረው የጨርቃ ጨርቅና የቆዳ ኢንዱስትሪዎች ያስፈልጋሉ፡፡ እንዲሁም ሌሎች አገሮች ለዕድገታቸው የተጠቀሙት የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪን በሚል በአገሪቱ በሙሉ በአብዛኛው ለዚሁ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲገነቡ ተደርጓል፡፡

ቀደም ሲል የነበረው ፖሊሲ ከባድ ኢንዱስትሪ (Heavy Industry) የሚባሉ እንደ ብረታ ብረት፣ ኢንጂነሪንግና የመሠረታዊ ኬሚካል ኢንዱስትሪዎች ትልቅ ካፒታልና ቴክኖሎጂ ስለሚጠይቁ ከጊዜ በኋላ የምንገባበት ይሆናል ተብሎ ታስቦ እንደሆነም ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ የአገሪቱ ዕድል በጠበበ መንገድ ከመወሰን ይልቅ በፖለቲካው ረገድ እንደተደረገው የርዕዮተ ዓለም ጉዳይ በተጨባጭ ሁኔታዎች ላይ ተመርኩዞ ሁሉንም ማለትም፣ ቀላል ኢንዱስትሪውንም ሆነ ከባድ ኢንዱስትሪውን ያዋሃደ የኢንዱስትሪ ልማት ፖሊሲን መከተሉ የበለጠ አዋጭ መሆን አለበት የሚል ሐሳብ ነው ለማንሸራሸር የተፈለገው፡፡ በዚህ ዋናዎቹ መመዘኛዎች የአገራችን አንፃራዊ ጠቀሜታ ጎልቶ የሚወጣበት መሆን ይኖርበታል፡፡ አንፃራዊ ጠቀሜታዎችን የሚወሰኑት ደግሞ የሥራ ዕድል መፍጠርና ድህነትን መታደግ ዋነኛው ሆኖ የአገራችንን ሌላው ተግዳሮት የሆነውን የውጭ ምንዛሪ የማፍራት ወይም የማዳን ተልዕኮ ኖሮት፣ ለዚሁ መሳካት በአገር ውስጥ በሚገኙ ጥሬ ዕቃዎች ላይ የተመሠረቱ ኢንዱስትሪዎች ቅድሚያ ሊያገኙ ይገባል የሚል ነው፡፡ ስለሆነም ጥሬ ዕቃዎቹ በዋነኛነት በእርሻ ውጤቶችና በማዕድን ሀብቶች ላይ የተመሠረቱ ከሆኑና የሠራተኛው ኃይል ተጨምሮበት አንፃራዊ ጠቀሜታው ከፍ ያለ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ የሥራ ዕድል ፈጠራው ጉዳይ መታሰብ ያለበት ኢንዱስትሪው በቀጥታ የፈጠረውን የሰው ኃይል ብቻ ሳይሆን፣ በታሰበው ኢንዱስትሪ ምክንያቶች በኋልዮሽና በወደፊት ትስስሮች ሊፈጠሩ የሚችሉት የሥራ ዕድሎች ጭምር መሆን ይኖርበታል፡፡ ስለሆነም ለቀላል ኢንዱስትሪ ነው ቅድሚያ የምንሰጠው በሚል በጨርቃ ጨርቅና በቆዳ በምግብ ኢንዱስትሪዎች በመሳሰሉት ላይ ብቻ በመጠመድ፣ የተፈጥሮ ጋዝን በመጠቀም ማዳበሪያዎችንና የፕላስቲክ ግብዓቶችን ከማምረት መገደብ፣ ወይም ብረትን ከአፈር በማውጣት ማምረት አለመቻል ተገቢ አይሆንም፡፡ ስለሆነም ፖሊሲው ሁሉንም ለአገራችን አንፃራዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ምርቶች ማምረት በሚያስችል መልኩ ማስተካከያ ያሻዋል፡፡

የኤክስፖርት  ተኮር  ኢንዱስትሪያላይዜሽን  ፖሊሲን  እንደገና  ስለመፈተሽ

ኤክስፖርት ተኮር ኢንደስትሪያላይዜሽን የሚለው ፖሊሲን አስፈላጊነት በተመለከተ ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ታይዋን፣ ሲንጋፖርና ቻይና የመሳሰሉት የደቡብ እስያና  የሩቅ  ምሥራቅ አገሮች በኤክስፖርት ተኮር ኢንዱስትሪያላይዜሽን ሒደት ስላደጉ፣ ኢትዮጵያም ይህን ፈለግ በመከተል ማደግ ትችላለች በሚል ላለፉት ዓመታት ይህ ፖሊሲ በዋናነት ሲራመድ ቆይቷል፡፡ በእርግጥ በቅርቡ በሐሳብ ደረጃ ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን የሚተኩ ኢንዱስትሪዎችንም እናበረታታለን የሚል  አቅጣጫም ተይዟል፡፡ በተግባር ግን ለውጡ ለወደፊት በተስፋ ይጠበቃል፡፡ እነዚህ የተጠቀሱት አገሮች ያደጉበት ጊዜና አሁን ዓለም የምትገኝበት ጊዜ አንድ አይደለም፡፡ ሌላው የሥራ ባህልየሥነ ልቦና ዝግጅትየኅብረተሰቡ አስተሳሰብየአመራር ጥበብ የትምህርትና የሙያ ዝግጅት የመሳሰሉት ጉዳዮች ከእኛ አገር ጋር ተመሳሳይ ላያደርጋቸው ይችላል፡፡ በዚያን ጊዜ ያልነበሩ በአሁኑ ጊዜ ግን ዓለምን በኢንዱስትሪ ምርት ያጥለቀለቁ አገሮች በርካታ ናችው፡፡ በመሆኑም ከእነዚህ ጋር መወዳደሩ ቀላል አይደለም፡፡ ስለዚህ እነዚህንና አስቻይ ሌሎች ሁኔታዎችን ስናመዛዝንና ስናጠና በስሜትና በምኞት ብቻ ኢትዮጵያን የተጠቀሱት አገሮች ባደጉበት መንገድ ብቻ ነው ማሳደግ አለብን የሚለው ግፊት የሠራ አይመስልም፡፡ አንድ ሰው መጉረስ ካለበት በላይ እንዲጎርስ ቢፈለግ ታንቆ ይሞታል፡፡ መጉረስ ባለበት ልክ ነው መጉረስ ያለበት፡፡ ይህ በመሆኑ የኤክስፖርት መሪ ኢንዱስትሪያላይዜሽኑ እየተሞከረ ያለ ቢሆንም፣ በተለይ በኢትዮጵያውያን በሚመሩ ኩባንያዎች የተፈለገውን ያህል ውጤት አስገኝተዋል ማለት አይቻልም፡፡

በገቢና በወጪ ንግድ መካከል 13 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ ጉድለት ባለበት አገር፣ የጎደለውን ይህን መጠን በከፊል አገር ውስጥ ሊተኩ በሚችሉ ምርቶች ለመተካት የሚደረገውን ጥረት ችላ በማለት፣ ይህን ያህል ለኤክስፖርት የምናለቅስበት ምክንያት ለዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ አይታየውም፡፡ ኤክስፖርት ማድረግ ቢቻል ጥሩ ነበር፡፡ ግን ለብዙ ዓመታት ተሞክሮ እስካሁን ብዙም የሚያመረቃ  ውጤት ባለመታየቱ ተቃራኒውንም ማሰቡ ተገቢ ይሆናል፡፡ ለወደፊቱ በሒደት ውስጣዊ አቅም ሲዳብር፣ የአገራችን ገጽታ ሲያድግ፣ የማሸጊያ ዕቃዎችም እንደ ልብ መገኘት ሲችሉ፣ የሎጂስቲክስ አገልግሎቱና የቢሮክራሲ ውጣ ውረድ ሲቃለል፣ እንዲሁም አንፃራዊ ጠቀሜታ ያላቸው በትልቅ አቅም መሠረታዊ የኢንዱስትሪ ምርቶች ሲመረቱ የዕድገት ሒደቱን ጠብቆ በርካታ የኢንዱስትሪ ምርቶችን ወደ ውጭ መላክ የሚቻልበት ጊዜ ይመጣል፡፡ እስከዚያ የተጀመረው ሙከራም እንደተጠበቀ ሆኖ ግን ከውጭ የሚገቡትን ምርቶች በመተካት የውጭ ምንዛሪ ማዳን ላይ ቢተኮር ለአገራችን የበለጠ ይጠቅማል፡፡ ይህም ከሁለቱም እንዳናጣ ያደርገናል፡፡ ኢትዮጵያውያንም ከኢንዱስትሪው አስወጥቶ አቅም ላዳበሩ የውጪ ኩባንያዎች ብቻ ሁኔታዎችን ከማመቻቸትም ይታደጋል፡፡ በእርግጥ የቴክኖሎጂ አቅማቸው የዳበረና የገበያ ትስስር ከውጭ ጋር የፈጠሩ፣ በተለይ የውጭ ኩባንያዎች በኤክስፖርት ላይ እንዲያተኩሩ ግፊት መፍጠሩ ተግባር ግን ይቀጥል፡፡ አንዳንድ የመንግሥት ኃላፊዎች ኤክስፖርት ማድረግ ሲጀመር ነው ከውጭ የሚገባውን ውድድር መቋቋም የሚቻለው ይሉናል፡፡ ይህም ቢሆን አይከፋም ነበር፡፡ ግን የግድ ሊሆን አይገባም፡፡ የውስጥ የእርስ በርስ ውድድሩ ራሱም ለዚህ ሊያዘጋጅ ይችላል፡፡ ስለሆነም ተኪ ምርቶችን በተለይ የአገር ውስጥ ጥሬ ዕቃዎችን ተጠቅመው ለሚያመርቱት ኤክስፖርት ከሚያደርጉት ባልተናነሰ ድጋፍ ቢደረግላቸው መልካም ይሆናል፡፡

በቀጥታ  የውጭ  ኢንቨስትመንት  ላይ  ያለውን  ፖሊሲና  አመለካከት  የመፈተሽ አስፈላጊነት 

የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት (FDI) ለአንድ አገር ዕድገት የሚኖረው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ለብዙ አገሮችም ዕድገት ጠቅሟል፡፡ በእርግጥ መስኩ በቂ ክትትልና አመራር ካላገኘ በአገር ላይ ጉዳትም ሊያስከትል የሚችል ነው፡፡ በአገራችን ከዚህ ቀደም አንዳንዶች አሮጌ ማሽነሪዎችን እንደ አዲስ በማስቆጠር በማስመጣትና ከሚገባቸው በላይ የባንክ ብድር በመውሰድ ለዕዳ በመዳረጋቸው፣ ባንኮችን ብሎም አገራችንን መጉዳታቸው የሚታወስ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ‹‹ህልም ተፈርቶ ሳይተኛ አይታደርም›› እንደሚባለው አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ጉዳቱን በመቀነስ፣ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንቱን በተጠናና ኢትዮጵያውያን ሊሰማሩበት በማይችሉት መስኮች እንዲገቡ ማድረጉ አያጠያይቅም፡፡ በዚህ ማስተላለፍ የተፈለገው ዋነኛ መልዕክት የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንቱን እንደ ዋነኛ የአገር ውስጥ ዕድገት ምንጭ መወሰድ የለበትም የሚለው ነው፡፡ በአንዳንድ የመንግሥት ኃላፊዎች ሁሉንም የኢንዱስትሪ ግንባታ ፍላጎት ለውጭ ባለሀብቶች ለመስጠት የሚደረገውን ሩጫ ቆም ብለን እናጢነው ለማለትም ነው፡፡ ኢትዮጵያውያንን በውጭ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያኖችን ጨምሮ በአገሪቷ የኢኮኖሚ ግንባታ ለማሳተፍ ዕድሎቹን በማሟጠጥ መጠቀም ላይ የበለጠ  እንዲተኮር ግፊት ለመፍጠርም ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ማሳመኛ ዋነኞቹ ምክንያቶች ኢትዮጵያውያኑ ትርፋቸውን ወደ ውጭ የማይወስዱና በዚህ ሰበብ ከአገር የሚወጣውን ዶላር ማስቀረቱ ብቻ ሳይሆን፣ በአገራዊ ስሜት ለአገራቸው ዕድገት የሚሠሩ በመሆናቸው ለሥራዎች መስፋፋትና ዕድገት የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ስለሚሆን ነው፡፡ በዚህ ረገድ ራሳችንንም ለማሳመን እንዲረዳ በአሁኑ ወቅት በውጪው ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት የሚታዩ ውስንነቶችን እስኪ እንይ፡፡

የውጭ ቀጥተኛ  ኢንቨስትመንቱ  የውጭ  ምንዛሪ ያስገኛል፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር ይካሄዳል፣  የሥራ ዕድል ይፈጥራል፣ ወዘተ. ጥቅም ያስገኛል በሚል መሠረተ ሐሳብ ላይ ተመርኩዞ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ጥቅሞች ለአገር እንደታሰበው ተገኝተዋል ወይ? የሚሉት ግን ጥናት ይሻሉ፡፡ የውጭ ምንዛሪን ማፍራትን በተመለከተ ግን የሚወጡት መረጃዎች የሚጠቁሙት የሚገኘው የወጭ ምንዛሪ ከውጭ ለመግዛት የሚጠቀሙበት ስለሆነ እንዲያውም ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ እንዳስፈለጋቸው ነው፡፡ በእርግጥ ይህም በጥናት ሊረጋገጥ የሚገባ ቢሆንም፣ በዚህ ረገድ የታሰበውን ያህል ውጤት  አለመገኘቱ ግን ይነገራል፡፡ እንዲያውም በዚህ ሳቢያ የአገሪቱ ሀብት በውጭ እየተመዘበረ ነው የሚባልም አለ፡፡ እንዲህ ዓይነት ኢንዱስትሪዎች የመምራትና የማስተዳደር ብቃት ባለማዳበራችን በሚፈለገው ሁኔታ የምንቆጣጠርና የምንከታተልም አይመስልም፡፡ የውጭ ምንዛሪን በተመለከተ መታየት ያለበት የውጭ ምንዛሪ ግኝት መመዘኛ ይህን ያህል የሚያወጣና  የውጭ ምንዛሪ በሽያጭ ተገኘ ብሎ ማውራት ብቻ ሳይሆን ዋና መለኪያ መሆን የሚኖርበት፣ በሽያጭ የተገኘው ከውጭ ለሚገዙ ግብዓቶች ከወጣው የውጭ ምንዛሪ ጋር ሲቀናነስ ምን ያህል ትርፍ ዶላር አገሪቱ አገኘች የሚለው ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ኩባንያ አሥር ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ አስገኝቶ 11 ሚሊዮን ዶላር የወጭ ምንዛሪ ለግብዓቶች ግዥ ቢያውልና ምርቱን በሙሉ ኤክስፖርት ቢያደርግ፣ አገሪቱ አንድ ሚሊዮን ዶላር  የውጭ ምንዛሪ ኪሳራ አጋጠማት ማለት ነው፡፡ በእርግጥ በአገር ውስጥ የፈጠረው የሥራ ዕድልና ተያያዥ ጥቅሞች ሚዛን ውስጥ የሚገቡበት ሁኔታ ሊኖር ቢችልም፣ ኤክስፖርት የሚያደርጉ ፋብሪካዎች በዚህ መንገድ እየተመዘኑ ነው ወይ የሚሉት ጥያቄዎች ምላሽ ሊያገኙ ይገባል፡፡ በእርግጥ እነዚህም ቢሆኑ ከውጭ የሚገቡ አንዳንድ ተመሳሳይ ምርቶችን ሊተኩ የሚችሉ ከሆነ፣ ለአገር ውስጥ ገበያም በከፊል ቢያቀርቡ ተወዳዳሪነታቸውና ትርፋማነታቸው ይጨምራል፡፡ ምክንያቱም ከእነዚህ ምርቶች ተመሳሳይ ምርቶችን ከውጭ የምናስገባ ከሆነ አገር ውስጥ የሚመረተውን በደካማ ዋጋ ሸጠን ይህንኑ የሚተካ ያለቀለት ምርት ከውጭ ካስገባን፣ የኤክስፖርት ቁጥርን ብቻ ማሳየት ትርጉም የለውም፡፡ ለአብነት ሸሚዝ፣ የተሰፉ ሱሪዎች፣ ጃኬቶች፣ ወዘተ. ያለቀላቸውና ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ቀላል አይደሉም፡፡

በቴክኖሎጂ ሽግግሩም ረገድ ምንም የለም ባይባልም ይህን ያህል ጎላ ያሉ ውጤቶች እስካሁን ስለመታየታቸው የሚቀርቡ መረጃዎች አያሳዩም፡፡ ሌላው በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ስም ኢትዮጵያውያን ከተሰማሩባቸው ኢንዱስትሪዎች እንዳይወጡ የመጠበቅ አስፈላጊነት ነው፡፡ ለምሳሌ በሳሙናና በዲተርጀንት ምርቶች በኢትዮጵያ አብዛኞቹ አገር በቀል ፋብሪካዎች የአገሪቱ ፍላጎት ተሟልቷል፡፡ እንዲያውም  በጥሬ ዕቃዎች እጥረት ከአቅም በታች ነው የሚመረተው፡፡ ስለዚህ ከውጭ በተለይ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት የሚባለው አያስፈልግም፡፡ ያሉት ፋብሪካዎች የውጪ ምንዛሪ በበቂ አግኝተው በሙሉ ቢሠሩ በአገሪቱ ከሚያስፈልገው በላይ  ነው መመረት የሚችለው፡፡ አስፈላጊ ሲሆን ኢትዮጵያውያን ያላቸውን ፋብሪካ በማስፋፋት የምርቱን መጠን መጨመር ይችላሉ፡፡ ይህ በዚህ እያለ በቅርቡ በትልቅ መጠን እነዚህን ምርቶች የሚያመርት የውጭ ኩባንያ እንዲገባ ተደርጓል፡፡ ይህ እንግዲህ አሁን የሚገኙትን ብዙዎቹን የሳሙናና የዲተርጀንት ፋብሪካዎችን ከመሻማት ውጭ ምንም ለአገር የማይፈይደው የለም፡፡ አንዳንድ ኃላፊዎች ትርፍ ምርት የሚመረት ከሆነ ኤክስፖርት ይደረጋል ይሉናል፡፡ ይህ ከተቻለ የውጭ ኢንቨስተሮቹ ለኤክስፖርት ብቻ እንዲያመርቱ ያድርጉ፡፡ በጎረቤት ያሉት አገሮች ከደቡብ ሱዳን የመንገድ ትራንስፖርት ግንኙነት ከሌላት አገር በስተቀር፣ ሁሉም የሳሙናና የዲተርጀንቶች ምርቶች ስለሚያመርቱ ወደ ጎረቤት አገሮች በእነዚህ ምርቶች ወደ ኤክስፖርት ገበያ መግባት ከባድ ነው፡፡ ሌሎች አገሮችን በተመለከተ እነዚህ ምርቶች በትልልቅ ‹መልቲ ናሽናል› ኩባንያዎች በየአገሩ ስለሚመረቱ ኤክስፖርት በማድረግ መወዳደር የሚቻል አይደለም፡፡

እነዚህ የውጭ ኩባንያዎች ይህ ድርጊት በተለያዩ የማጭበርበሪያ ጥበቦች ጭምር፣ የኢትዮጵያን አምራቾች ቀስ በቀስ ከዚህ ኢንዱስትሪ ማስወጣት ይከተላል የሚል ሥጋት አለ፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያውያን የተካኑባቸውን የሳሙናና የዲተርጀንት ምርቶች በውሳኔ ሰጪዎች ዕውቀት ማነስ ምክንያት ለሌሎች አሳልፈን በመስጠት፣ ኢትዮጵያውያን ከዚህ ኢንዱስትሪ እንዳይወጡ ጥንቃቄ ማድረግና የዕርምት ዕርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ጠንካራ በሆኑባቸው የኢንዱስትሪ  መስኮች የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንቶችን በማስገባት የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን  ማዳከም፣ የአገራችንን ኢንዱስትሪ እንደ አንዳንድ የጎረቤት አገሮች የአገሬውን ዜጎች  የበይ ተመልካች ወይም ተላላኪዎች እንዳይሆኑም ጥንቃቄ ማድረግ ያሻል፡፡ ስለዚህ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት የመሳቡ ክንውን  እንደተጠበቀ ሆኖ ከዚህ ቀደም ያሉት ሁኔታዎች ተጠንተው፣ የአገራችንን ጥቅም የበለጠ በሚጠብቅ መንገድ ስትራቴጂካዊ በሆኑ በተመረጡ ኢንዱስትሪዎች ላይ በመመሥረት በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆኑ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎች ላይ የሚያተኩር፣ ለዜጎች በቂ ክፍያና የሥራ ደኅንነትን የሚጠብቅ፣ በጥናትና በዕቅድ ላይ ተመሥርቶ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፖሊሲና ስትራቴጂ ተከልሶና የቅርብ ክትትልም ተደርጎ የሚሠራበት ሁኔታ ሊመቻች ይገባል፡፡

የጥቃቅንና  አነስተኛ  አደረጃጀቶችን  በአግባቡ  መጠቀም

ጥቃቅንና አነስተኛ ድርጅቶች ለአንድ አገር ዕድገት አስፈላጊና ጠቃሚ መሆናቸውና ለብዙ አገሮች ዕድገት መነሻ እንደሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ በመሆኑም እነዚህን በአግባቡ በመምራት ተጠቃሚ መሆን ያሻል፡፡ በዚህ ረገድ በአደረጃጀትና በማበረታቻ አቅርቦት  ክፍተቶች  ይታያሉ፡፡

በአደረጃጀት  ላይ  ማስተካከያ  ስለማድረግ

የሥራ አጥ ቁጥርን በመቀነስና የሥራ ዕድል ፈጠራን በማሳደግ ለኢኮኖሚው ዕድገት አስተዋጽኦ ለማድረግ ይቻል ዘንድ፣ ሥራ የሌላቸውን ወጣቶች በማኅበር በማደራጀትና ሥልጠናም በመስጠት መንግሥት ወደ ሥራ ሲያሰማራ ቆይቷል፡፡ የዚህ ዓይነት አካሄድ ምን ያህል ለውጥ አመጣ ወይም ጥቅም አስገኘ የሚባለው የተጠና ጭብጥ ማስረጃ ማቅረብ ባይቻልም፣ ከሚሰሙት አንዳንድ መረጃዎችና በተጨባጭም የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ካጋጠመው ክስተት በመነሳት ይህ አካሄድ አገሪቱን በሚፈለገው መጠን እየጠቀማት ባለመሆኑ ፖሊሲው ቢፈተሽ መልካም ይሆናል፡፡ ወጣቶቹ የገንዘብ ብድር የምታገኙት ተደራጅታችሁ ስትቀርቡ ነው ስለሚባሉ፣ አብዛኛውን ጊዜ የባህሪ ተመሳሳይነትና የዓላማ አንድነት የሌላቸው ገንዘቡን ለማግኘት ብቻ ተደራጀን ብለው ይቀርባሉ፡፡ ሁሉም እኩል መብት ያላቸው አባላት በመሆናቸውና የሐሳብ ጋብቻ ስለማይፈጠር አመራር ሰጪና ተመሪው ሊለይ በማይችልበት ወደ ሥራው ይገባል፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነው መስማማትና ተመሳሳይ ራዕይ ለመያዝ ይቸገራሉ፡፡  በውጤቱም ስምምነት ላይ ለመድረስ ያዳግታቸዋል፡፡ ራስ ወዳድነትና የእርስ በርስ ጥርጣሬ በሚበዛበት ባህላችን የዚህ ዓይነት ስብስብ ስኬታማ የመሆን ዕድሉ ጠባብ ነው፡፡ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ተሳትፎ የነበረበት በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል በአርሲ ዞን ሌሙና ቢልበሎ ወረዳ መንግሥታዊ ባልሆነ የልማት ሥራ ደጋፊነት፣ ሥራ ለሌላቸው ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር የተደራጁት ስድስት የሆኑ የጥቃቅንና አነስተኛ ማኅበራት አንድ ዓመት በላይ ሳይዘልቁ ነው ንብረቱን ሸጠው የተከፋፈሉትና ማኅበራቱ ፈርሰው የተበታተኑት፡፡  በዚሁ ወረዳ አንድ በአፕል ልማት በመንግሥት የተደራጁት  ሁሉም ፈርሰው ተበታትነው ነው የታዩት፡፡ በእርግጥ ሌሎች በመንግሥት ተሸካሚነት የሚወዛወዙ ወይም በአግባቡ የሐሳብ ጋብቻ ሊፈጥሩ የሚችሉ የተሳካላቸውም ጥቂቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ግን ከፈሰሰባቸው የአገር ሀብት፣ አደረጃጀት፣ የሰው ጉልበትና ዕውቀት ከጠየቀው ውጪ ጋር የሚመጣጠኑ ውጤቶች የተመዘገቡ አይመስልም፡፡

የዚህ ዓይነት የተለያየ አመለካከት፣ ውስጣዊ ጥንካሬና ድክመት የያዘ ስብስብን ኢንተርፕሬናዊ ማድረግ ከባድ ነው፡፡ በዚህ ንቃተ ህሊና ሁሉንም ባለሀብት በማድረግ በእኩልነት አብሮ መሥራትና ተገቢውን አሠራር የሚሰጥ ከእነዚህ ዓይነት ስብስቦች ማውጣት ቀላል አይሆንም፡፡ ይልቅ የኢንተርፕሬነር መመዘኛ የሚያሟሉትን ከውስጥ መርጦ፣ እነዚህ ሌሎችን ቀጥረው እንዲያሠሩ በማበረታታትና በመደገፍ ኢንተርፕሬነሮችን በማውጣት መሥራቱ ነው የሚመረጠው፡፡ የህንዶችና የቻይኖች ኢንተርፕሬነሮች ዕድገት ታሪክ የሚያረጋግጠው ይህንኑ ነው፡፡ ተያይዘው ሁሉም ከሚወድቁ የተወሰኑት ቢወጡ ነው ተመራጭ የሚሆነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሁኔታዎች ተፈትሸው በማኅበሩ ተደራጅተው የተሳካላቸው በዚያው መቀጠላቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በሌሎቹ ላይ ማስተካከያ ቢደረግና በአብዛኛው የኢንተርፕሬነር ተሰጥኦ ያላቸውን ወጣቶች በመመልመል የተለየ ድጋፍ በማድረግ፣ በርካታ የግል ኢንተርፕሬነሮችን ለማፍራት የሚያግዝ ፖሊሲና ስትራቴጂ ተቀርፆ፣ እነዚህ ሌሎቹን ቀጥረው በማሠራት የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ ቢተገበር የበለጠ ተመራጭ ነው፡፡ የሙያ ብቃትና ክህሎት ላላቸው የተማሩ የኢንተርፕሬነር ዝንባሌ ላላቸው ወጣቶች በግልም ሆነ በቡድን በሚያቀርቡት የፕሮጀክት ሐሳቦች አዋጪነት እየታየ የመሬት አቅርቦትና የባንክ ብድር እንዲሰጣቸውእነዚሁ ኢንዱስትሪዎች ከትልልቅናመካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ተመጋጋቢ እንዲሆኑ፣ ወይም የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው መንግሥታዊ ድጋፍና ክትትል ማድረግ የመንግሥት ዋነኛ የትኩረት መስክ መሆን ይኖርበታል፡፡

የግብር  ዕፎይታ  ማበረታቻ  አስፈላጊነት

ከጥቃቅንና አነስተኛ ደረጃ ሥራቸውን የሚጀምሩት ዜጎች ሊበረታቱና የበለጠ ተጠናክረው በሁለት እግራቸው እንዲቆሙ በተለያየ መንገድ መደገፍ አስፈላጊ ነው፡፡ ከጥቃቅንና  አነስተኛ ሥራ የሚጀምሩ ወገኖች የመጀመርያ ተግባር ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረጉ ነው ዋና ግብ መሆን የሚገባው፡፡ በዚህ ደረጃ የእነዚህ ዜጎች ስኬት በራሳቸው መኖር የሚጀምሩበትና ለሌሎች ሸክም የማይሆኑበት ሁኔታ ውስጥ መግባት ነው፡፡ ለዚህ ዕውቅና ሰጥቶ ለወደፊቱ ዳግም ለሌሎች መኖር እንዲጀምሩ ማስቻል ነው ከመንግሥት የሚጠበቀው፡፡ እውነታው ይህ ሆኖ እያለ እነዚህ ኃይሎች ከግብር ጋር በተገናኘ የሚደርስባቸው በደል ተስፋ አስቆራጭ ሆኖ ይታያል፡፡ በግብር አስገቢውና ተያያዥነት ያላቸው የቁጥጥር አካላት የአመለካከት ልዩነት በሚያደርሱባቸው ተፅዕኖዎች፣ በርካታ ሥራ ጀማሪዎች ሥራቸውን ዘግተው እጅና እግራቸውን አጣጥፈው እንዲቀመጡ ተደርገዋል፣ እየተደረጉም ነው፡፡ ስለሆነም አነስተኛና ጀማሪ ድርጅቶች ቢያንስ ለሦስት ዓመታት ከትርፍ ግብር ነፃ ሆነው በግብር ስም ከሚፈጠርባቸው ችግር ከሚፈጥሩ  አካላት ተገላግለው በነፃነት እንዲሠሩ፣ የፖሊሲ ማሻሻያ ቢደረግ በርካታ ዜጎች ሥራ እንዲፈጥሩና ከድህነት ተላቀው ሌሎችን እንዲያግዙ ያደርጋል፡፡ እነዚህ ወገኖች በተለያዩ ሥልጠናዎች እንዲታገዙና በገበያ ትስስር በመሳሰሉት ዕገዛ በማድረግ ውጤታማ እንዲሆኑ ቢበረታቱ፣ በርካታ ሥራ ፈጣሪ ዜጎችን ለማፍራት ይረዳል፡፡ በዚህ አጋጣሚ በችርቻሮ የንግድ ዘርፍ የሚገኙት አብዛኞቹ ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ የሚጋፉ በመሆኑ ጥናት ተካሂዶ ገቢውን ለመሰብሰብ የሚወጣው ወጪና የሚያስገቡት ገቢ ተነፃፅሮ፣ እንዲሁም የሚከሰተው የመልካም አስተዳደር ጉድለት ወይም ምግባረ ብልሹ አሠራር የሚፈጥረው ጉዳይ ግምት ውስጥ ገብቶና ጥናት ተካሂዶ አነስተኛ ቸርቻሪ ነጋዴዎች ከንግድ ትርፍም ሆነ የተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ የሚደረጉበት ሁኔታም ቢፈጠር የተሻለ ይሆናል የሚል እምነት አለው የጽሑፉ አዘጋጅ፡፡ በቻይናና በህንድ የሚታዩ ሁኔታዎች ይህንን ያረጋግጣሉ፡፡

በዕቅድና  በጥናት  ላይ  የተመሠረተ  የፕሮጀክት  አመራር  አስፈላጊነት

የኢንዱስትሪም ሆነ የሌሎች ፕሮጀክቶች ዕቅዶች ሲዘጋጁ ቆይተዋል፡፡ በቅርቡም በመንግሥት የአሥር ዓመት መርህ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ከዚሁ የተወሰደ በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የ2014 በጀት ዓመት ዕቅድም መዘጋጀቱ ይታወቃል፡፡ የሚዘጋጁት ዕቅዶችን ግን በበቂ ጥናት ላይ ተመሥርተው ዘርዘር ያሉ፣ የገበያ ትስስርን መሠረት ያደረጉና ክፍተቶችን በሚሸፍን መንገድ የሚዘጋጁ አይመስልም፡፡ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪን በተመለከተ የትኞቹን ጉድለቶች ማሟላት ይሻላል? የትኞቹ ዘርፎች ለጊዜው የተሟላ ኢንዱስትሪዎችን ይዘዋል? ስለዚህ ኢንቨስተሮችን የገበያ ውድድሩ የሚበዛበት፣ በቂ ፋብሪካዎች ካሉባቸው ዘርፎች ወደ ተጓደለውና የምርት እጥረት የሚታይባቸው እንዲገቡ አቅጣጫ የማስያዝና የመግፋት ሁኔታ እምብዛም አይታይም፡፡ የዕቅዱ ዝግጅት የግል ክፍለ ኢኮኖሚውን አቅጣጫ የሚያሲዝና የሚመራው ስላልሆነ፣ ይህ ክፍል በዘፈቀደ የሚጓዝ በመሆኑ የአገሪቱ ውድና ቁጥብ ሀብት ሲባክን ይታያል፡፡ ይህን በሚመለከት የምግብ ዘይቶችን፣ የሳሙናና የዲተርጀንት ምርቶችን ፕሮጀክቶችን ማየት ይቻላል፡፡

በቅርቡ ነሐሴ 24 ቀን 2013 ዓ.ም. በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ‹‹የዘይት ኢንዱስትሪውን የግብዓት እጥረት ለማቃለል›› በሚል ርዕስ ሥር የቀረበው ጽሑፍ፣ ‹‹በአሁኑ ወቅት 232 የምግብ ዘይት ፋብሪካዎች ይገኛሉ፡፡ 26 የሚሆኑት ግዙፍ ፋብሪካዎች ሲሆኑ፣ 206 የሚሆኑት ደግሞ መካከለኛና አነስተኛ ናቸው፡፡ ፋብሪካዎቹ በዓመት ከ1.2 ቢሊዮን ሊትር በላይ የምግብ ዘይት ማምረት አቅም አላቸው፡፡ አገር አቀፍ የምግብ ዘይት ፍላጎት በአንፃሩ 906 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ነው፡፡ ይሁንና አብዛኞቹ ፋብሪካዎቹ በግብዓት እጥረት ምክንያት በሙሉ አቅማቸው እያመረቱ አይደለም፡፡ ይህ በመሆኑም የአገሪቱን ፍላጎት እንኳን ማርካት አልተቻላቸውም፡፡ የፍላጎቱ 40 በመቶ ብቻ አገር ውስጥ እየተሸፈነ ይገኛል፡፡ በሙሉ አቅም ወደ ሥራ በሚገቡበት ወቅት አገሪቱ ከውጭ የምታስገባው የምግብ ዘይት ምርት ቀስ በቀስ ቢቀነስ  በሙሉ በአገር ውስጥ መተካት ትችላለች፤›› ይላል፡፡ በሌላ በኩል ሰኔ 9 ቀን 2013 ዓ.ም. በአዲስ ዘመን ጋዜጣ በዚህ ጉዳይ ላይ የቀረበው ጽሑፍ በቡሬ ከተማ በጥር ወር መጀመርያ የተመረቀው አምስት ቢሊዮን ብር ኢንቨስት የተደረገበት ፊቤላ የአቶ በላይነህ ክንዴ የዘይት ፋብሪካ፣ የአገራችንን 60 በመቶ የምግብ ዘይት ፍላጎት እንደሚሸፍንና  በደብረ ማርቆስ ከተማ በአቶ ወርቁ አይተነው በ5.2 ቢሊዮን ብር የተቋቋመው ደብሊውኤ በሙሉ አቅም ሲያመርት፣ የአገራችንን የምግብ ዘይት ፍጆታ 60 በመቶ እንደሚሸፍን ነው የተገለጸው፡፡ ይህ በዚህ እንዳለ ሰኔ 23 ቀን 2013 ዓ.ም. በወጣው በዚሁ አዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ ‹‹የግብዓት አቅርቦት ችግር በመቅረፍ በሚል›› በተዘጋጀ የውይይት መድረክ፣ ኢትዮጵያ ለድፍድፍ የምግብ ዘይት ግዥ በዓመት ሁለት ቢሊዮን  ዶላር እንደሚያስፈልጋት፣ የቅባት እህሎችን ፍላጎት በአገር ውስጥ ለማሟላት አሥር ዓመታት እንደሚፈጅ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መግለጻቸው ተወስቷል፡፡

 ከእነዚህ መረዳት የሚቻለው የዛሬ አሥር ዓመት ለሚሟላ ጥሬ ዕቃ፣ ዛሬ ፋብሪካዎቹን መቋቋም አስፈላጊ አለመሆኑን ነው፡፡ በቂ ዕቅድና ክትትል ቢኖር ኢንቨስትመንቱን በከፊል ወደ ሌሎች በማዞር፣ የአገር ሀብትን ከማባከን ማዳን ያቻል ነበር፡፡ የግብዓት ችግር ባለበትና ባለፈው በአንድ ዓመት በድምሩ ሁለቱ ከአገሪቷ ፍጆታ በላይ አቅም ያላቸው ፋብሪካዎች፣ በዚህ ዓይነት ካፒታል መቋቋማቸው ጥያቄ መጫሩም አይቀርም፡፡ ምናልባት አንዳቸው ፓልም ዘይትን በቀጥታ ከውጭ ከማስገባት፣ የፓልም ዘይት ድፍድፉን በማምጣት እሴት ጨምሮ ለማቅረብ የተሻለ ይሆናል በሚል ሲሆን፣ ሌላኛው ፋብሪካ የሰሊጥ ዘይትን በመጭመቅ ዘይቱ ለውጭ ገበያ ይቀርባል የሚባልም አለ፡፡ ግን በዚህ አቅም ለሚመረተውስ ምርት የውጭ ገበያውስ አለ? የሰሊጥ ዘይት ለማብሰያ ማለት ለማቁላሊያና ለመጥበሻ ዓይነት አያገለግልም፡፡ እሳት ሲነካው ጣዕሙ ስለሚበላሽ፡፡ ስለዚህ ለአትክልት ዘይትነት ብቻ ስለሚውል ለኢትዮጵያ ገበያ አገልግሎቱ የተመጠነ ነው፡፡ ስለሆነም ይህ ፋብሪካ በሰሊጥ ላይ ብቻ የሚመሠረት ሳይሆን፣ ሌሎቹንም የቅባት እህሎች መጠቀሙ አይቀርም፡፡ በእርግጥ ኢንተርፕሬነሩ አቶ ወርቁ በቅባት እህሎች እርሻም ላይ የሚሳተፉ በመሆናቸውና አቅሙ ስላላቸው የሚቻላቸውን እንደሚሠሩ ይጠበቃል፡፡

ከላይ ከተገለጹት መረጃዎች ለመገንዘብ የሚቻለው በአገር ውስጥ እስካሁን የተቋቋሙት ፋብሪካዎች የማምረት አቅም 1.2 ቢሊዮን  ሊትር ወይም 1.2 ሚሊዮን ቶን ሲሆን፣ የአገራችን ፍጆታ 906 ሚሊዮን ቶን ከሆነ ፋብሪካዎቹ ከአገሪቱ ፍጆታ በላይ የማምረት አቅም አላቸው ማለት ነው፡፡ ይህ ሆኖ ግን አንድ አዲስ የምግብ ዘይት ፋብሪካ ለማቋቋም ጥያቄ ቢቀርብ አያስፈልገንም፡፡ በዚህ ረገድ በቂ ፋብሪካዎች አሉ ብሎ የፕሮጀክት ሐሳቡን ወደ ሌላ እንዲቀይር የሚያደርግ መንግሥታዊ አካል አለ ወይ? የሚለው ነው፡፡ ብድር አቅራቢ ባንኮችም በቂ መረጃ ስለሌላቸው የምግብ ዘይት ፋብሪካን ለማቋቋም ለሚጠየቅ ብድርን ከመፍቀድ የሚታቀቡ አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ በጥናት ላይ የተመሠረተ አገራዊ ዕቅድ ኖሮ በሚታሰበው ኢቨስትመንት ለመቀጠልና ላለመቀጠል አቅጣጫ የሚያስይዝ መንግሥታዊ አካል አስፈላጊ ይሆናል፡፡

ከእነዚህ በቅርቡ ከተቋቋሙት ትልልቅ ፋብሪካዎች ጋር የተያያዘ ሌላ ጉዳይም ላንሳ፡፡ እነዚህ የምግብ ዘይት አምራቾች ከምግብ ዘይቱ በተጨማሪ በተረፈ ምርቱ ሳሙናን እስከ ማጠናቀቂያ ድረስ የሚያመርት ፋብሪካ በጎን አቋቁመዋል፣ ወይም ለማቋቋም ዕቅድ ይዘዋል፡፡ በሌላ በኩል የሳሙና ኑድልስ የሚያመርቱም ሆነ እስከ ማጠናቀቂያው ድረስ ማምረት የሚችሉ በሙያውም የተካኑና ከበቂ በላይ የሆኑ፣ በጥሬ ዕቃ እጥረትና በገበያ እጥረት ጭምር በሙሉ አቅማቸው የማያመርቱ የሳሙና ፋብሪካዎች በአገራችን አሉ፡፡ ይህ ሁኔታ እያለ እነዚህ የምግብ ዘይት ፋብሪካዎች በሳሙና ምርት ውስጥ መግባት አልነበረባቸውም፡፡ እነሱ ተረፈ ምርቱን አጣርተው የማጠናቀቂያ ሥራ ለሚሠሩ አነስተኞችንና መካከለኞችን ጨምሮ ከ400 ያላነሱ የዚህ ተጠቃሚ ለሆኑ የሳሙና ፋብሪካዎች ምርታቸውን ቢያቀርቡ ጥሩ የገበያ ትስስር ይፈጥራሉ፡፡ ሌሎችም በተለይ ትንንሽ ፋብሪካዎችም እንዲያድጉ ዕድል ይሰጡዋቸዋል፡፡ በአገሪቱ በቂ የሳሙና ፋብሪካዎች ስላሉ ተጨማሪ የሳሙና ፋብሪካ ማቋቋም፣ ተጨማሪ የአገር ሀብት ወጪ ሊደረግም አይገባም ነበር፡፡

እነዚህ ሁለት ብርቅዬ ኢንተርፕሬነሮች ላደረጉት ተግባር ሊመሠገኑ እንጂ ሊወቀሱ አይገባም፡፡ ግን እነሱ መረጃ ሊኖራቸው ስለማይችል በጉዳዩ ላይ የሚያማክር፣ አማራጮችን የሚሰጥና እንዲስተካከል የሚያደርግ መንግሥታዊ ተቋም መኖር ነበረበት፡፡ ነገር ግን አለመኖሩን ለመጠቆምና ይህ ባለመሟላቱ የደረሰውን ጉዳት በማሳየት፣ ለወደፊት ለሌሎች በመማሪያነት እንዲያገለግል ለምሳሌነት የቀረበ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ የጥናትና የዕቅድ ጉዳይ የአግሮ ኢንዱስትሪውንም ኢንዱስትሪያል ፓርክ ይመለከታል፡፡ ፓርኮቹ ሲመሠረቱ ለሚቋቋቁሙት ኢንዱስትሪዎች በቂ ግብዓት አለ ወይ? የሚሉት ጥናቶች ስለመጠናታቸው ግልጽ አይደለም፡፡ በዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ እምነት ከአግሮ ኢንዱስትሪው ፓርክ ቀድመው መሠራት የነበረባቸው የእርሻ ግብዓቶችን ዓመቱን ሙሉ ለማምረት የሚያስችሉ የመስኖ ግድቦችን መገንባቱና በቂ  የግብርና ምርት ማምረቱ ነበር፡፡ የሥጋና የወተት ፋብሪካዎችን ከማስፋፋት በፊት ቀድመው ለተገነቡት የሥጋ ፋብሪካዎችና የወተት ፋብሪካዎች በቂ እንስሳትን ለማቅረብ እንዲቻል፣ የመኖ ማምረቻ ፋብሪካዎችን ማስፋፋትና የእንስሳት ምርቶችን በጥራትና  በመጠን የማሳደግ ሥራዎች መቅደም ነበረባቸው፡፡

የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለመገንባት ፋብሪካዎቹን የሚያሠራ በቂ ግብዓት ሳይኖር፣ ወይም እነዚህ ሁኔታዎች በዕቅድ ውስጥ ሳይገቡ ወይም ቀደም ሲል የተቋቋሙት የዱቄት ፋብሪካዎች በጥሬ ዕቃ እጥረት እየቆሙ ነበር፡፡ የሥጋ ፋብሪካዎች ለዕርድ የሚሆኑ በቂ እንስሳት ባለማግኘታቸው በሙሉ አቅማቸው በማይሠሩበት፣ የወተት ፋብሪካዎች በወተት እጥረት እየቆሙ፣ እንዲሁም ለፍራፍሬ ጭማቂ ፍራፍሬዎች  ሳይኖሩ በየአካባቢው እንደ ዩኒቨርሲቲዎቹ በፉክክር የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለማቋቋም መቻኮል ስሜታዊ  ውሳኔ እንጂ፣ በአዋጭነት ጥናት ላይ የተመሠረተ የባለሙያዎች የጥናት ውጤት አይመስልም፡፡ መሆን የነበረበት ግን በበቂ ጥናቶች ላይ ተመርኩዞ ፍላጎቱ ገፍቶ ሲመጣና የአግሮ ኢንዲስትሪው ፓርክ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የሚኬድበት ቢሆን ይመረጥ ነበር፡፡

ይህ የመስኖ ግድቡ ቀድሞ ቢስፋፋና ስንዴም ሆነ በቆሎና አኩሪ አተር፣ እንዲሁም የፍራፍሬዎችና የአትክልቶች ምርቶች በበቂ ተመርተው ነባሮቹ ፋብሪካዎች በሙሉ ኃይላቸው እየሠሩ ትርፍ ምርት ቢመረት እንኳን፣ በጥሬነታቸው ወደ ውጭ እየላኩ ፍላጎቱ ጎልቶ ሲመጣ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ቢቋቋሙ የአገር ሀብትን በአግባቡ ለመጠቀም ያስችል ነበር፡፡ ለወደፊቱ እንዲህ ዓይነት ኢንቨስትመንቶች ሲወሰኑ በቂ ጥናቶች ሊደረጉና ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ፕሮጀክቶች በፖለቲከኞች ውሳኔ ብቻ ሳይሆን፣ በባለሙያዎች የጥናት ውጤት መሠረት የሚወሰኑ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ሌላው ትኩረት የሚሻው ጉዳይ ከዘመቻና ከጥድፊያ ሥራ ተላቀን ተቋማትን በመገንባት በሰከነና በጥናትና ዕቅድ ላይ ወደ ተመሠረተ የልማት ሥራ የመግባት አስፈላጊነት ነው፡፡ ይህ ሲባል በዘመቻ እየተሠሩ ያሉ እንደ የደን ልማት፣ የዛፍ ተከላና በስንዴ ምርት ራስን መቻል የመሳሰሉትን ጥረቶችን ለማንኳሰስ ሳይሆን፣ ጅምሩ የሚደገፍና የሚበረታታ ሆኖ የደን ልማቱን ሥራ በዘላቂነት ለማስቀጠል ግን ተቋማዊ ይዘት ኖሮት በተጠያቂነት ኃላፊነትን መውሰድ በሚያስችል በፕሮግራምና በዕቅድ፣ በተለያዩ ማበረታቻዎች ማዕቀፍ አማካይነት መምራት ቢቻል መልካም ይሆናል፡፡ ሌላው የኢንዱስትሪዎችን ትስስር መሠረት ያደረጉ ክፍተቶች የሚታይባቸውን የኢንዱስትሪ ዓይነቶች በመለየት ኢንቨስተሮች እንዲያተኩሩባቸው የተጠናከረ  የዕቅድ ሥራ የመሥራት አስፈላጊነት ነው፡፡ ይህ ቀደም ሲል እንደ ተጠቀሰው ውስን የአገሪቱን ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም፣ አላስፈላጊ ተመሳሳይ ምርቶችን ብቻ በሚያመርቱና እርስ በርስ ገበያን በማሻማት ጉዳት ከማስከተልም ያድናል፡፡ ኢንዱስትሪዎቹንም ተወዳዳሪና ምርታማ ያደርጋል፡፡

የትስስርና  ኮንትራት  መሰጣጠት  አሠራርን  መተግበር  

የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ከራሱ ኢንዱስትሪም ሆነ ከሌሎች የኢኮኖሚ አውታሮች እንደ አገልግሎት ካሉት ጋር የሚኖረው ቁርኝት ወይም ትስስር ጠንካራ መሆኑ በዚህ ጽሑፍ ታይቷል፡፡ ይህንኑ ትስስር የበለጠ ለማጠናከር እንደ አንድ የፖሊሲ ማዕቀፍ ተይዞና ስትራቴጂ ተነድፎ መንግሥታዊ ዕውቅና ተሰጥቶት፣ በተጠናና በታቀደ መንገድ ቢሠራ የበለጠ ለአገር ይጠቅማል፡፡ የትስስርና የኮንትራት መሰጣጠትን ጠቃሚነት በመረዳት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እ.ኤ.አ. የካቲት 19 ቀን 2004 ዓ.ም. ኮንሰልታንት ቀጥሮ ማስጠናቱ ይታወሳል፡፡ በጥናቱ በርካታ አገሮች በዚህ መሠረት የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ከአገር ውስጥ አምራቾች ጋር እንዴት በማጣመር የቴክኖሎጂ ሽግግር እንደሚካሄድ፣ በገበያው ትስስር የአገሬው ዜጎች ኢንዱስትሪዎች እንዴት እንደሚያሳድጉ ተሞክሮዎችን ሁሉ ያዘለ ነበር በአማካሪው የተዘጋጀው የጥናቱ ሰነድ፡፡ የዚህ ጥናት ኮፒ በዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ እጅ ይገኛል፡፡ ጥናቱ ተካሄደ እንጂ በወቅቱ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በዚህ ላይ የተሠራ ምንም አልነበረም፡፡ ስለዚህ ይህን የትስስርና የኮንትራት መሰጣጠትን በተመለከተ ተቋማዊ አሠራር እንዲኖረው በማድረግ የኩባንያዎች አንዱ የማኅበራዊ ኃላፊነት መወጫ  ቢሆን መልካም ይሆናል፡፡ ከምን ያህሉ ጋር ትስስር እንደፈጠሩ እንዲያሳይ ኩባንያዎቹ ሽልማትና ዕውቅና እንዲያገኙ ማድረግም ጠቀሜታው ከፍተኛ ይሆናል፡፡ ትስስሩ ፋብሪካዎችን ብቻ ሳይሆን አገልግሎት ሰጪ የሆኑትን እንደ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የመከላከያ ተቋም፣ ወዘተ. የመሳሰሉትንም በመጨመር ሁሉም ቅድሚያ ለአገር ውስጥ ምርት ግዥ እንዲሰጡ በፖሊሲ በተደገፈ አካሄድ የአገር ውስጥ አምራቾች የሚያድጉበት ሁኔታ ማመቻቸት  ተገቢ ይሆናል፡፡

ሌላው የትስስሩ ሒደት ትኩረት ማግኘት ያለበት የአምራች ኢንዱስትሪዎች ሲቋቋሙ ተመጋጋቢ ሊሆኑ በሚችሉበት ሁኔታ የገበያ ትስስሩን የሚያጠናክሩ ኢንዱስትሪዎችን  አቅዶ የተለየ ድጋፍ ማድረግ ነው፡፡ በዚህ ረገድ እንደ ምሳሌ የጨርቃ ጨርቅ እንዱስትሪን ብንወስድ የኋልዮሽና የወደፊት ትስስሮችን መሠረት ያደረጉ ከግብርናው የጥጥ ምርት ጀምሮ ለእነዚህ ኢንዱስትሪዎች የሚያስፈልጉ የተለያዩ ግብዓቶች ምንድናቸው? እነዚህንስ በተለይ ኢትዮጵያውያን እንዴት አምርተው ለእነዚህ ኩባንያዎች ማቅረብ ይችላሉ? የሚሉት በቂ ትኩረት አግኝተው ከዋናዎቹ ባላነሰ የፖሊሲ ድጋፍ ማግኘትና መተግበር ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ባለማሟላታቸው የሚታዩ ውስንነቶች ከጥጥ ጀምሮ በከፊል ያላለቀላቸው ብትን ጨርቆች፣ ማቅለሚያ ማጠቢያን ጨምሮ እስከ ቁልፍ ድረስ ከውጭ በውድ የውጭ ምንዛሪ ይገባሉ፡፡ ይህ ሒደት የውጪ ምንዛሪን ማባከኑ ብቻ ሳይሆን ከሎጂስቲክስ  ከቢሮክራሲ ውጣ ውረድና ከታክስ ጋር  በሚያያዙ ጉዳዮች በሚጨምረው የግብይት ዋጋ የመጨረሻ የምርቱን ዋጋ ከፍ ስለሚያደርግ፣ ተወዳዳሪነትን በመቀነስ በኩል አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡

በዚህ በቀረበው ሁኔታ ለጨርቃ ጨርቅም ሆነ እንዲሁም የቆዳ ፋብሪካዎች ወደ ጫማ ማምረት እንዲሸጋገሩ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በአብዛኛው በአገር ውስጥ፣ በተለይ በኢትዮጵያውያን እንዲመረቱ የሚያስፈልጉ ኢንዱስትሪዎች ተለይተው አስፈላጊው ድጋፍ ቢደረግና ትልልቅ ፋብሪካዎች በተለይ የውጭ ኩባንያዎች ለአገር ውስጥ አምራቾች የቴክኖሎጂ ድጋፍ ጭምር እያደረጉላቸው እንዲያመርቱና ምርቶቻቸውን  እንዲጠቀሙ፣ በተለያዩ የማበረታቻ ሒደቶችና የማስገደጃ ዘዴዎች የታጀበ የአሠራር ሥርዓት ቢዘረጋ አገራችን የበለጠ ትጠቀማለች፡፡ የቴክኖሎጂ ሽግግርም ሊከሄድ ይችላል፡፡

የቴክኖሎጂ  ሽግግርና  ቴክኖሎጂን  የመቀበል  ብቃት 

የቴክኖሎጂ ሽግግር (Technology Transfer) እና ቴክኖሎጂን የመቀበል ብቃት (Technology Absorption Capacity) በተመለከተ በተለይ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የሚተገበር  ፖሊሲና ስትራቴጂ አገራችን ያስፈልጋታል፡፡ ቴክኖሎጂን የመቀበል ብቃት ማሳደግ ማለት በሌላ በኩል የሠለጠነ የሰው ኃይል የማፍራትና ቴክኖሎጂዎችን በቀላል ማሸጋገር ብቻ ሳይሆን፣ አሻሽሎ ወደ መሥራት ጭምር የሚወስድ ለአንድ አገር እንደ ካፒታል የሚወሰድ ሀብት ነው፡፡ የደቡብ እስያና የሩቅ ምሥራቅ አገሮች ያደጉት እንዲህ ዓይነት አቅሞችን መንግሥታቸው ሆን ብሎ በመገንባቱ ነው፡፡ ለዚህ የአቅም ግንባታ የሚረዱ የምርምርና ሥርፀት ሥራዎች በምርምር ተቋማትና በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች እንዲስፋፉ የሚያበረታታ ይዘት ኖሮት የተፈተኑ ቴክኖሎጂዎችን ተግባራዊ ለማድረግ በሚያመቻች ሁኔታ ፖሊሲውና ስትራቴጂው ሊያግዝ ይገባል፡፡ አንዳንድ ኢንዱስትሪዎች ሌሎችን ደግፈውና አብቅተው የግብዓቶቻቸው አቅራቢ በማድረግ በሚሠሩት ሥራዎች ማግኘት ስለሚገባቸው ማበረታቻዎች ዕውቅና ማትረፍ ሊሆን ይችላል፡፡ የሚበረታቱበት ሁኔታዎች ቢፈጠሩ መልካም ይሆናል፡፡

ቴክኖሎጂ የመቀበል ብቃት ማሳደግን በተመለከተ ብቃት ኖሯቸው፣ ተሰጥኦና ተነሳሽነት ያላቸውን የተማሩ ወጣቶች በመመልመል አቅምን የበለጠ እንዴት ማሳደግ እንደሚቻል ማቀድና መተግበርንም ያሻል፡፡ ይህ እንደ ጃፓን፣ ቻይና የመሳሰሉ አገሮች እንዳደረጉት በቴክኖሎጂ ወደ አደጉ አገሮች በመላክ ቴክኖሎጂዎችን እንዲቀስሙ፣ እንዲሁም በምርምርና ሥርፀት ሥራዎች በማሳተፍ ልምድ እንዲያገኙ ማድረግና በተለይ በኢንጂነሪንግ መስክ ከውጭ የሚመጡ ማሽኖችን ፈታቶ በማጥናት ተመሳሳይ ማሽኖችን ኮርጆና አስመስሎ በመሥራት (Reverse Engineering) በመሳሰሉት በማሳተፍ የአቅም ግንባታውን ማካሄድ ያሻል፡፡ በሌላ በኩል በውጭ የሚኖሩና የቴክኖሎጂ ዕውቀት ያላቸው ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በውጭ በየቴክኖሎጂ መስኩ ተደራጅተው በተወሰነ ጊዜ ወደ አገር ቤት እየመጡ ዕውቀታቸውንና ልምዳቸውን ሊያካፍሉ በሚያስችሉ የሥልጠና፣ የምክርና የክትትል  (Mentorship)  ጉዳዮች ላይ እንዲሠራ በዘርፉ ፖሊሲና ስትራቴጂው መኖሩ ጠቀሜታ አለው፡፡

የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎችንና የቴክኖሎጂ ተቋማትን ምን ዓይነት ሙያ ያላቸው ኃላፊዎች መምራት እንዳለባቸውም በግልጽ ሊቀመጥ ይገባል፡፡ ስለአንድ ድርጅት ራዕይ ኖሮት ለመምራት የመሪነት ክህሎት ሊኖረው የሚችል የዚያ ባለሙያ መሆን የግድ አስፈላጊ ነው፡፡ የአካውንታንት፣ የኢኮኖሚክስ፣ ወዘተ. የማኅበራዊ ሳይንስ ባለሙያዎች የቴክኖሎጂ ተግባራት በሚከናወኑበት ድርጅቶች እንዲመሩ ማድረግ አሁን በአገራችን አልፎ አልፎ የሚታየው የአሠራር ሁኔታ ሊፈተሽና ሊስተካከል ይገባል፡፡ ሥልጠናዎችንም በተመለከተ የመንግሥት ወጪን በማጋራት ጭምር የግል ድርጅቶችንም ጨምሮ የሥልጠና ዓይነቶችም ተለይተው፣ በተለያዩ ዘርፎች ሥልጠና በሚሰጥበት ላይም ፖሊሲና ስትራቴጂው ሊያግዝ ይገባል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የቤካስ ኬሚካልስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ማኔጂንግ ዳይሬክተር፣ የኢትዮጵያ ኬሚካል ውጤት አምራቾች የዘርፍ ማኅበር ሰብሳቢና የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[የክቡር ሚኒስትሩ ባለቤት የኬንያው ፕሬዚዳንት ያስተላለፉትን መልዕክት ተመልክተው ባለቤታቸውን በነገር ይዘዋቸዋል]

የኬንያው ፕሬዚዳንት ከሕዝባቸው ለቀረበባቸው ቅሬታ የሰጡትን ምላሽ ሰማህ? እንኳን ምላሻቸውን...

የኢትዮ ኤርትራ ሰሞነኛ ሁኔታና ቀጣናዊ ሥጋቱ

“ግንቡን እናፍርስ ድልድዩን እንገንባ” የሚል ፖለቲካዊ መፈክር ጎልቶ በሚሰማበት፣...

ኦሮሚያ ባንክ ከተበዳሪ ደንበኞቼ ውስጥ 92 በመቶ የሚሆኑት አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ናቸው አለ

ኦሮሚያ ባንክ ለደንበኞቹ ከሰጠው ብድር ውስጥ ለአነስተኛና ለመካከለኛ ኢንተርፕራይዞች...

ሽቅብና ቁልቁል!

ጉዞ ከመገናኛ ወደ ሲኤምሲ ጀምረናል። ተሳፋሪዎች የዕለት ጉርሳቸውን መሸፈን...