Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉኢትዮጵያውያን  አዲስ  ከሚደራጀው  የብልፅግና  ፓርቲ መንግሥት ምን ይጠብቃሉ?

ኢትዮጵያውያን  አዲስ  ከሚደራጀው  የብልፅግና  ፓርቲ መንግሥት ምን ይጠብቃሉ?

ቀን:

በጉ ጆርጊ  ታ

ሰሞኑን ጀርመናውያን ባደረጉት ምርጫ ከ15 ዓመታት በላይ አገሪቱን ሲመሩ የነበሩትንና የጀርመን ብቻ ሳይሆን፣ የአውሮፓም መሪ ተደርገው ሲቆጠሩ የነበሩትንና በዓለም እጅግ ኃያሏ ሴት የአንጌላ ሜርክል ፓርቲ መሸነፉን ከመገናኛ አውታሮች ሰምተናል፡፡ ሴትዮዋ የሥልጣን ጊዜያቸው ስላበቃ ለውድድር ባይቀርቡም፣ እንዴት የእሳቸው ፓርቲ ለድል እንዳልበቃ ለመረዳት የጀርመንን ሕዝብ ፖለቲካዊ ባህልና ታሪክ፣ ሕዝቡ በእሳቸው አስተዳደር የተደሰተበትንና የተከፋበትን ሥረ ነገር በቅርበት ማወቅ ወይም መመርመር ይጠይቃል፡፡

በእኛም አገር በኢትዮጵያ በአፄ ምኒልክ ዘመን ተነገረ የተባለና ዛሬም ድረስ ቢያንስ በእኔ አስተያየት እውነት የሆነ አንድ ባህል አለን፡፡ ታሪኩ ንጉሠ ነገሥቱ የግብር ክፍያ ላይ ጭማሪ ለማድረግ ከማሰባቸው ጋር የተያያዘ ነው፡፡ እናም የግብር ጭማሪ አዋጅ ያስነግሩና ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት እስኪ ሰው ምን እንደሚል አዳምጡ ብለው አገልጋዮቻቸውን ያዛሉ፡፡ የተሰበሰበው ወይም የተሰለለው የሕዝብ ድምፅ ‹‹እንዲህማ ተሆነ ንጉሥ ቢቸግራቸው ነው›› የሚል መሆኑን በሰሙ ጊዜ በሉ እንግዲህ በአዋጁ መሠረት ይፈጸም አሉ ተባለ፡፡ ይኸው ታሪክ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ሲደገም እንደተለመደው ሕዝቡ ምን ይላል ተብሎ ጥናት ሲደረግ ብትፈልጉ መረጃ ቢሰበሰብ ልትሉት ትችላላችሁ የተገኘው ምላሽ ‹‹ዝም አለ ወይም ምንም አላለም›› ሆኖ ሲገኝ፣ ንጉሡ ‹‹እህህ! ነገር አለ ማለት ነው፣ በሉ ተውት›› የሚል ትዕዛዝ ይሰጣሉ፡፡  ይህን ታሪክ ምን ላይ እንዳነበብኩት ወይም የት እንደሰማሁት አሁን ትዝ አይለኝም፣ እኔ የፈበረክኩት ግን አይደለም፡፡ እንደ ታሪኩ ሁሉ ባለፈው ሰኔ ኢትዮጵያውያን ምርጫ ጣቢያ የሄዱት የሆዳቸውን በሆዳቸው ይዘው ይመስለኛል፡፡

ከፖለቲካው ማዕከል ብዙ የራቅኩ ስለሆነ ከወዳጆቼና ከቤተሰብ ጋር ከማደርገው ውይይት ባሻገር የዘንድሮን ምርጫ ማን ያሸንፋል የሚለውን ለመተንበይ የሚያስችል መረጃ አልነበረኝም፡፡ እንደ አብዛኛው የእኔ ቢጤ አንደኛው ፓርቲ እዚህና እዚያ አካባቢ፣ ሌላኛው ደግሞ እንዲሁ በተወሰኑ አካባቢዎች፣ ሌሎችም እንዲሁ ያሸንፉና የሚመሠረተው መንግሥት ጥምር ሊሆን ይችላል ብዬ ነበር የገመትኩት፡፡ በእኔ የፖለቲካ ድንቁርና ግምቴ ሚዛን የሚደፋ እንደማይሆን ቢገባኝም፣ ብልፅግና በዚህ ዓይነት የሰፋ ልዩነት ያሸንፋል ብሎ የጠበቀ ብዙ ዜጋ ነበረ ብዬ አላሰብም፡፡ ፖለቲከኞቹ የነበራቸውን ትንበያ ሳናካትት፡፡ ታዲያ ለብዙዎቻችን በተባራሪ ወሬ እንደ ሰማሁት የምርጫ ቦርድ ሰዎች ሳይቀሩ ይህ የሰፋ የድምፅ ልዩነት ያልተጠበቀ ነበር፡፡ ጥያቄው እኛ በተለይም ቀለም ቆጥረናል የአገራችንን የፖለቲካ ትኩሳት በደንብ ተረድተናል ብለን የምናስብ ሰዎች እንዴት የሕዝቡን ስሜት ሳናነበው ሳንረዳው ቀረን? በሚል ሊቀርብ ይችላል፡፡

ግን ከዚያም የቀጠለው ጥያቄ ከሞላ ጎደል በሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ከምርጫው ውድድር ራሳቸውን ያገለሉ ሳይቀሩ ዘርፈ ብዙ መከራከሪያ እያቀረቡ፣ የረገሙትና ለዚህች አገር አይመጥንም ወይም ለዚህ ብሔር አይበጅም ብለው ያወገዙት ፓርቲ እንዴት በዚህ ዓይነት የሰፋ ልዩነት የሕዝቡን ድምፅ ሊያገኝ ቻለ? የሚለው ይመስለኛል፡፡ የምኒልክ ዘመንን ታሪክ ያስታወሰኝም ይህ አስገራሚ ኩነት ነው፡፡ በባህላችን አለመስማማታችንን ከምንገልጽባቸው ብልኃቶች አንደኛው ዝምታ ነው፡፡ ብትፈልጉት በጓደኛሞች መካከል ወይም በቤተሰብ ውስጥ አለዚያም በሥራ ባልደረቦችና በጎረቤታሞች መካከል ታገኙታላችሁ፡፡ ሙያ በልብ ነው፡፡ ከምርጫው ጋር ለምን ይህንን ፓርቲ ከሌሎች አብልጠህ/ሽ መረጥሽ/ክ የሚል መጠይቅ በሌለበት ይህን ሚስጥር በምን ማወቅ ይቻላል? መካድ የማይቻለው ግን እያንዳንዱ መራጭ ብልፅግናን ይሁን ሌላ ፓርቲ ያለ ምክንያት አለመምረጡን ነው፡፡ የዘርፉ ባለሙያዎች የተጠኝዎችን ማንነት በማይለይ ወይም በሚስጥር በሚይዝ (Anonymous) መላ መለስተኛ ጥናት አድርጋችሁ ጀባ ብትሉን ለተመረጡትም፣ ላልተመረጡትና ለእኛም አወቅን ባዮች ብዙ ትምህርት ይሆነናል፡፡

የመረጠውን ፓርቲ ተጠያቂ ከማድረግ ባለፈ የሚመሠረተው መንግሥት በሥልጣን ዘመኑ እንዲያከናውን ሕዝቡ የሚጠብቀውን ለውጥ ከ‹‹ወትሯዊ›› ምርጫዎች  የተለየ የሚያደርጉት ወቅት ላይ መሆናችንን መገንዘብ፣ ይህንንም የሕዝብ ስሜት በከፍተኛ ጥንቃቄ ማዳመጥና ተገቢውን የአጭርና የረዥም ጊዜ ዕቅድ ነድፎ ምላሽ መስጠትና ይህም ሲደረግ ሕዝቡን በደረጃው ማሳተፍ እጅግ አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡ የዚህ ውጤትም ሕዝብ በመንግሥት ላይ አመኔታ እንዲያሳድርና ‹‹አገሬ ነው››  የሚለው ስሜቱ እንዲጎለብት ማስቻል ነው፡፡ በእኔ አስተያየት በሕዝብ ዘንድ ‹‹ይህ መንግሥት የቆመው ለእኔ ነው፡፡ አገሪቱም የእኔ ናት!›› የሚል ስሜት ማስፈን ተቻለ ማለት፣ ከድህነት ማጥ ለመውጣትና ሰላማዊ አገር ለመመሥረት መሠረቱ ተቀመጠ፣ የማይናወጥ መሠረት ተጣለ ማለት ነው፡፡

ከአዲሱ መንግሥት ሕዝቡ ብዙ እንዲጠብቅና ይህም ባይሟላለት እንዲቆጣና ለአመፅ እንዲነሳሳ የሚያደርጉት አንዳንድ ቁልፍ ጉዳዮች የምላቸውን ላንሳ፡፡

መንግሥት በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የገባበትን ጦርነት እንደ ራሱ ጦርነት በመውሰድ ገደብ የለሽ ተሳትፎ አድርጓል፣ ተዋግቷል፡፡ ልጆቹን ወደ ግንባር መርቆ ልኳል፣ ደም ሰጥቷል፣ ገንዘብ፣ ምግብና ቁሳቁስ አቅርቧል፡፡ ከባለሀብቱ፣ ከክልል መንግሥታት፣ ከመንግሥት ሠራተኞችና ከሌሎች ተርታ ዜጎች ባሻገር አንዲት ገጽታቸው የተጎሳቆለ እናት 1,000  እንጀራ ጋግረው ለሠራዊቱ ማቅረባቸውና በአማራ ክልል ባለ አንድ የጦር ግንባር የሆነ ከተማ ነዋሪ የሆኑ ወጣቶች የመስቀልን በዓል የወታደሮችን ጫማ በመወልወል ለሠራዊቱ ያላቸውን ክብር የገለጹበት መንገድ ብቻ፣ እንኳን የሚናገሩት ታሪክና ጮክ ብሎ የሚጣራ  የዕዳ ቁልል ነው፡፡

በብዙ አገሮች እንደታየው ሕዝብን ለቁጣና ለአመፅ አነሳስቶ መንግሥት በነውጥ አንዲነሳ የሚያደርገው የኑሮ ውድነት ነው፡፡ መራጩ ሕዝብ ግን ዝም ያለው ያለምክንያት አይደለም፡፡ የገባውን ያህል ተረድቶ ደግሞም ይህንኑ ችግርና ሰቆቃ ችሎ ነው ብልፅግና ያስተዳድረኝ ብሎ የወሰነው፡፡ ምናልባትም እስኪ መጀመርያ የገባበትን የጠብመንጃ ጦርነት ይወጣ ብሎ ይሆናል ፋታ እንስጠው ያለው፡፡ በመንግሥት በኩል  ‹‹ዋጋ ለማረጋጋት›› የሚደረገውን ጥረት እንሰማለን፡፡ የሺሕ ማይል ጉዞ በአንድ ዕርምጃ ነው የሚጀመረው እንዲሉ ድርጊቱ ጥሩ ጅማሮ ቢሆንም፣ ከኑሮ ወይም ዋጋ ውድነቱ ስፋትና ጥልቀት አንፃር ዓባይን በጭልፋ ነው፡፡ ረዥም መንገድና ብዙ ፈተና ማለፍ አለብን፡፡ በዚህም ሕዝብ ከመንግሥት ያልዘገየ ምላሽ ይጠብቃል፡፡

በየአካባቢው ሕዝብ በሰላም እንዳይኖር ፀጥታ በማደፍረስ፣ ዜጎችን በመግደልና አካለ ጎደሎ በማድረግ፣ በዛቻና ማስፈራሪያ የመኖሪያ ቀዬአቸውን ትተው እንዲፈናቀሉና እንዲሰደዱ፣ ቤታቸውና ንብረታቸው እንዲፈርስ፣ ወዘተ. የተደረጉ ኅብረተሰቦችንና ዜጎችን ብዛት በተመለከተ መንግሥት በቂ መረጃ እንዳለው የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጭምር እንደምንሰማውም ይህ ውስብስብ የአፈናና የወንጀል መረብ ራሳቸው የመንግሥት ባለሥልጣናትን ያካተተ መሆኑን ነው፡፡ ወንጀለኞቹ ለሕግ እንዲቀርቡ፣ ተፈናቃዮች ወደ መንደራቸው ተመለሰው የቀደመ ኑሯቸውን በሰላም አንዲቀጥሉ መንግሥትን አሁኑኑ መፍትሔ ካልሰጠኸን ብለው ያልጠየቁት፣ አሁንም በምክንያት ነው፡፡ ግን ጥበቃው ገደብ አለው፡፡ ገደቡን ሲያልፍ…?

ሙስናና የጎደፈ አስተዳደር

ይህ ጉዳይ መልከ ብዙ ነው፡፡ የቀበሌና የወረዳ አስተዳደሮች አብዛኛው ሕዝብ ለትንሹም ለትልቁም ጉዳይ በየዕለቱ ደጅ የሚጠናቸው ናቸው፡፡ የነዋሪነት መታወቂያ ለማውጣት፣ ያገባ/ያላገባ ማስረጃ፣ ለጥቃቅን የቤት ወይም የአጥር ዕድሳት ወይም ጥገና ፈቃድ ፍለጋ፣ እዚህ ግባ ለማይባሉ ጥቃቅን ግጭቶች ፍትሕ ፈላጊዎች፣ ለአነስተኛና ጥቃቅን ንግድ ፍቃድ፣ ግብር ለመክፈል፣ ፈቃድ ለማሳደስ፣ የሁከት ይወገድልኝ አቤቱታዎች፣… ወዘተ. ሕዝቡ ተስፋ የቆረጠባቸው ግን ደግሞ ምርጫ ስለሌለው ‹‹ቀን እስኪያልፍ…›› እንዲሉ ‹‹ድንጋዩን በኪሱ…›› ቀን እየጠበቀላቸው መሆኑን የተመራጩ መንግሥት አካላት የማያውቁት ሚስጥር አይደለም፡፡ የመንግሥትና የግል ጤና ተቋማት፣ የውኃ፣ የስልክና የመብራት አገልግሎት፣ የመሬት ይዞታ አስተዳደር፣ ግብር ተቀባይ መሥሪያ ቤቶች፣ ፍርድ ቤቶችን ጨምሮ ከሞላ ጎደል በሁሉም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዛሬም ተገልጋዩ ሕዝብ እንደ ደጅ  ጠኚ ተለማምጦ፣ አንገቱን ደፍቶ፣ እጅ መንሻ ሰጥቶ ለዚያውም ጥራቱ የተጓደለ ግልጋሎት የሚሰጥን መንግሥት የሚታገሰው ለዝንታለም አይመስለኝም፡፡

በነገራችን ላይ ሰው ታሞብኛል ብላችሁ አምቡላንሰ ብትደውሉ፣ ከላኪና ተቀባይ ሐኪምና ተቋም ስምና ስልክ ለታመመባችሁ ሰው የአምቡላንስ አገልግሎት እንደማታገኙ ስንቶቻችሁ ናችሁ የምታውቁት? የግል የሕክምና ተቋማት የሚጠይቁት የአገልግሎት ክፍያም በሕዝቡ ዘንድ መነጋገሪያ ከሆነ ውሎ አደረ፡፡ ከፋም ለማም እንደ ብዙዎች አስተያየት እነዚህ ግልጋሎቶች ከአዲስ አበባ እየራቃችሁ ስትሄዱ ‹‹ከዝንጀሮ ቆንጆ…›› እንዲሉ የባሰ ብልሹ ሆነው ነው የምታገኟቸው፡፡ ስለዚህ ጉዳይ እኔም በግሌ ካጋጠሙኝ ልምዶች የምመሰክረው አለኝ፡፡ በአስተዳደር፣ በአገልግሎትና በፍትሕ ዕጦት ሕዝብ ብዙ ያልተመለሱ ጥያቄዎች አሉት፡፡ እነዚህም ጥያቄዎች ደግሞ ሕዝብ ያልዘገየ ምላሽ የሚጠይቅባቸው ናቸው፡፡

ምን ይደረግ?

አገልግሎቶች ይቀላጠፉ፣ ሐኪም ሁሉንም በሽተኛ ሊያድን አይችልም፡፡ በድህነታችን ምክንያት ደግሞ የሕክምና ጥበብ የደረሰባቸውን ቴክኖሎጂዎች በሁሉም ቦታ ማዳረስ ለጊዜው አንችልም፡፡ በከፍተኛ  ደረጃ የሠለጠኑ ባለሙያዎችን በሁሉም ቦታ ማዳረስ አይቻለን ይሆናል፡፡ ግን ቢያንስ አንድ ታማሚ ሰብዓዊ ክብሩ ሳይዋረድ ወይም ዘመድና ጓደኛ ሳያሻው ምንህን ነው ያመመህ? ምን ልርዳሽ? ተብሎ/ላ የምትስተናገድበት የጤና አጠባበቅ ሥርዓት ማደራጀት ሳንችል ቀረን? አዎን ሁሉም የጤና ባለሙያዎች በቂ የክህሎትና የባህሪ ወይም የሥነ ምግባር ሥልጠና ሳይሰጣቸው ቀርቶ ይሆናል፡፡ አዎን ለጤና ባለሙያዎች ከሥራቸው ክብደትና ኃላፊነት አኳያ የሚያገኙት  ጥቅማ  ጥቅም በቂ አይሆን ይሆናል፡፡ ይህ ግን እንደ አገሪቱ የኢኮኖሚ አቅም  ዕድገት  የጤና ባለሙያውን ጥቅማ ጥቅሞች አብሮ እንደሚያድግ፣ አሁን ካለንበት የኢኮኖሚ ድቀት አስክንወጣ ግን የሙያ ግዴታን ላለመወጣት እንዴት ምክንያት ይሆናል? የጤና ሚኒስቴርና  የክልል ጤና ቢሮዎች ይህንን ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥተው ይሥሩበት፡፡ የሕክምና አገልግሎት እንደ ምሳሌ ይቅረብ እንጂ፣ የአገልግሎት ማሻሻያዎች ሁሉንም የሚመለከታቸው የዘርፍ ሚኒስቴሮችና መሥሪያ ቤቶችን የሚያካትት እንደሆነ ተደርጎ ይታሰብልኝ፡፡ ዝርዝርና በርካታ ድካም የሚጠይቅ ሥራ መሆኑ ሳይዘነጋ በእኔ አስተያየት ከሁሉ የሚቀድመው የፖለቲካ አመራሩ ቁርጠኝነት ነው፡፡ ሌላ ሌላው ሁሉ ከዚያ ይከተላል፡፡

ሕዝባዊ ተሳትፎ

ሕዝብ በአገሬ ጉዳይ ያገባኛል ሊል የሚችለው መንግሥት የሕዝብን ድምፅ የሚሰማባቸው መድረኮች ሲፈጠሩለትና የሰጠው ሐሳብና አስተያየት በመንግሥት ውሳኔዎች ዓይነተኛ ግምት እንደሚሰጣቸው ሲገነዘብ ነው፡፡ አንደሚመስለኝ በብዙ የገጠር አካባቢዎች የተዳከሙ ግን ያልፈረሱ የኅብረተሰብ ሥርዓቶችና መዋቅሮች አሉ፡፡ እነዚህን እንደ ሁኔታው ማጥበቅ፣ ማጠናከርና  ማሻሻል ጠቀሜታው እጅግ የላቀ ነው፡፡ ሰሞኑን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ያቀረበው የሶዶ ጉራጌዎች የዳኝነትና የዕርቅ ጉባዔ አንድ ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ የጋሞ አባቶችና እናቶች ያን ሰሞን የተፈጸመው የቡራዩ ሰቆቃና ግፍ እንዳይስፋፋና በአጭሩ አንዲቋጭ የወሰዱት አርዓያነት ያለው ተግባር፣ በየአካባቢው ያለንን ባህላዊ ዕውቀትና ጥበብ አንዴት ለአገር ጥቅም ማዋል እንደሚቻል አስተምሮን ያለፈ የታሪካችን አንድ አካል ሆኗል፡፡ እነዚህ በምሳሌነት ተጠቀሱ እንጂ በሁሉም ብሔሮች ዘንድ ያሉ ዕድሜ ጠገብ የትየለሌ የማኅበረሰብ አስተዳደር ሥርዓቶች እንዳሉን የታወቀ ነው፡፡

ከተሞች የተለየ አሠራር ያስፈልጋቸው ይሆናል፡፡ ነገር ግን ከመኖሪያ ሠፈሮችና ጎረቤቶች ጀምሮ በየአካባቢው በሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች፣ በአካባቢ ጥበቃና ፅዳት፣ በግጭት አፈታት፣ በደስታና በሐዘን ጊዜ ስለሚኖሩ ትብብሮች፣ ወዘተ. ብዙ ሥራ ይቀረናል፡፡ አዲስ አበባና ምናልባትም አንዳንድ ትልልቅ ከተሞች የመኖሪያና የንግድ ወይም የሥራ ቦታዎች መቀላቀልና በሥርዓት አለመደራጀት፣ በነዋሪዎች ላይ ከሚያስከትለው የጤና ጉዳትና በልጆች አስተዳደግ ላይ ሊፈጠር ከሚችለው በጎ ያልሆነ ተፅዕኖ ማላቀቅ ታላቅ ትኩረት የሚያሻው  ጉዳይ  ነው፡፡ የከተማ ዕቅድ አውጪዎችና የጤና ተመራማሪዎች በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ የናሙና ጥናት አድርገው ከውሳኔ ሐሳብ ጋር ለመንግሥት ቢያቀርቡ፣ በመረጃ ላይ የተመሠረተ የፖሊሲና የተግባር አቅጣጫ ለመንደፍ ያስችላሉ፡፡ አንድ ጊዜ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የማሳጅና የጭፈራ ቤቶችን፣ እንዲሁም በየትምህርት ቤቱ ጥጋ ጥግ ጠላ መጠጫ፣ ጫት መቃሚያና ሺሻና ሀሺሽ ቤቶችና አልጋ የማከራየት ንግዶችን ብዛትና በአካባቢው ነዋሪዎችና ሕፃናት ላይ የሚያስከትላቸውን ተፅዕኖዎች በተመለከተ ያስጠናው ጥናት እንደነበረ አንድ የማምናት ወዳጄ አጫውታኛለች፡፡

ሰላም ዕርቅ

ልዩነቶቻችንን በአጉሊ መነጽር እየፈለግን ተቋስለናል፡፡ ይህን ቁስል ለመሻር መትጋት አለብን፡፡ በየአካባቢው የተጀመሩ የዕርቅና የሰላም ጥረቶች ተጠናክረው ይቀጥሉ፣ በዕውቀት ልምድና አገራዊ ጥበብ ላይ ተመርኩዘው ይበልፅጉ፡፡ በየከተማውና የገጠር መንደሮች ሰላም ይሰበክ ዕርቅ ይውረድ፡፡ በትግራይ ሕዝብና በተቀሩት ኢትዮጵያውያን መካከል የተፈጠረው መከፋፈል ከሁሉም የላቀ ትኩረት የሚሻ ይመስለኛል፡፡ የትግራይ ልጆች  በማንኛውም የኢትዮጵያ ክፍል እንዳሻቸው ተዘዋውረው ይማሩ፣ ይነግዱ፣ ይሥሩ፡፡ ሌላውም ኢትዮጵያዊ እንዲሁ ባሻው ክልል ሌላ ስያሜም ይሰጠው እንደሆነ፣ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ያለገደብ እየተዘዋወረ አገሩን ይወቅ፣ ይማር፣ ይነግድ፣ ይሥራ፡፡ ምናልባትም በ‹‹Demographic Engineering››ነት እንዳልከሰስ እንጂ፣ ወጣቶች የትዳር ጓደኞቻቸውን ከራሳቸው ብሔር ወይም ጎሳ ውጪ እንዲሹ ቢበረታቱስ? ይህ ሐሳብ ተቀባይነት የሚያገኝ ከሆነ የየብሔሩን ባህልና ቋንቋ ከመጠበቅና ከማበልፀግ ተግባር ጋር ተባባሪ እንጂ ተፃራሪ መሆን እንደሌለበት ልብ ይሏል፡፡ እንዲያውም ከተለያዩ ብሔሮች ከተጋቡ ወላጆች የሚወለዱ ልጆች የሁለቱንም ወላጆቻቸውን ባህልና ቋንቋ እንዲያጠኑ፣ የወላጆቻቸው ወይም የአያቶቻቸውን የትውልድ መንደር እንዲያውቁ ዕድል መፍጠር አገራቸውን የበለጠ ለማወቅ ይጠቅማል ብዬ የማስበው ወይም አስተያየት የምሰጠው፣ በጎ ስለመሰለኝ ብቻ እንጂ ሐሳቡ አከራካሪ መሆኑን አጥቼው አይደለም፡፡

ከላይ የተሰነዘሩት አስተያየቶች እጅግ የገዘፉ የአገር አስተዳደር ብልኃቶችን ወይም ፖሊሲዎችን (የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ ሕይወትና አገልግሎቶችን፣ የአገር ደኅንነትና ፀጥታን ወይም የውጪ ፖሊሲን፣ ወዘተ.) የሚተኩ ወይም እነዚህ ፖሊሲዎች ላይ አስተያየትና ትችት ማቀረብ ላይ ያተኮሩ አይደሉም፡፡ በእያንዳንዱ ትልልቅ አገራዊ ፖሊሲ ላይ መተቸት ምናልባትም የዘርፉ ባለሙያዎችንና የሚመለከታቸውን አካላት ያካተተ ውይይትና ምክክር የሚጠይቅ ሰፊ ሥራ ይመስለኛል፡፡ ይልቁንም የጸሐፊው መልዕክት ሕዝቡ መንግሥትን አንዲያምንና አገሬ ነው የሚል የባለቤትነት ስሜቱ በበለጠ እንዲዳብር ዛሬ ነገ ሳይባል በቅድሚያ ሊሠራ የሚገባው፣ መሠረታዊ የአገልግሎትና የአስተዳደር ማሻሻያ ላይ የግሉን አስተያየት ለማጋራት ከሚል መነሳሳት ያቀረበው፡፡ ለእነዚህ ጉዳዮች ዕልባት መስጠት ከተቻለ በጋራ ወገባችንን አስረን ከድህነት ለመውጣት የሚያስችል ሥርዓት ገነባን ማለት ነው፡፡ ይህ አጭር ጽሑፍ ውይይትና ትችት ካስከተለ ጥረቱ ተሳካ ማለት ነው፡፡ ባለሥልጣናቱ በሚዲያ ፍተሻቸው ዓይናቸው ካረፈበት ደግሞ ተጨማሪ ስኬት ነው ካላሰቡበት እንዲያስቡበት፣ ካሰቡበት እንደ ተጨማሪ ድምፅ ያገለግላቸው ይሆናል፡፡

ደህና ክረሙ!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኩባንያ አስተዳደር ለኢትዮጵያ ባንኮች ውጤታማነት

የጠቅላላ ጉባኤ፣ የጥቆማና ምርጫ ኮሚቴ፣ የተቆጣጣሪ ቦርድ፣ የዳይሬክተሮች ቦርድና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...