Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትየአዲስ ሥራ መጀመርያ አዲስ ዘመን

የአዲስ ሥራ መጀመርያ አዲስ ዘመን

ቀን:

በገነት ዓለሙ

‹‹… ይህ ቀን ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የአዲስ ታሪክ ዘመን መክፈቻ ነው፣ በዚህም በአዲስ ዘመን ሁላችን መፈጸም ያለብን አዲስ ሥራ ይጀመራል፤›› ይህ ለዛሬው ጽሑፌ መነሻ ያደረግሁት ጥቅስ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንግግር የተወሰደ ነው፡፡ የጣሊያን የቅኝ አገዛዝ ምኞትና ሙከራ በተቀጨበት ወቅት፣ ይህንን ንግግር ከሌሎች መካከል በኦፌሴል ከመዘገቡት ውስጥ አንዱ የሆነው የ‹‹ፍሬ ከናፍር ዘ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ›› መጽሐፍ በርዕሱ እንደሚለው፣ ‹‹ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት አፄ ኃይለ ሥላሴ በድል አድራጊነት ከመናገሻ ከተማቸው አዲስ አበባ በገቡ ጊዜ ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም. የተናገሩት ቃል ነው››፡፡ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ የትኛውም ዕትም ብትመለከቱ በመጀመርያውና በማስትሄድ ገጹ ግንቦት 30 ቀን 1933 ዓ.ም. መቋቋሙን፣ (ለምሳሌ በ2014 ዓ.ም. ደግሞ) 81ኛው ዓመቱ ላይ መሆኑን ይነግረናል፡፡ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ስሙን ያገኘው የቅኝ ገዥነትን ድጋሚ አዲስ ምኞት ድል ባደረግንበት በዚያ ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ አዲስ የታሪክ ዘመን መክፈቻ ይሁን ባልነው በዚያ አዲስ ዘመን ነው፡፡

ዕውን ያንን፣ ያኔ የጀመርነውን፣ በድል የጀመርነውን ዘመን አዲስ አደረግነው ወይ? ‹‹ሁላችንም መፈጸም ያለብን አዲስ ሥራ›› ጀመርን ወይ? አዲስ ዘመን ጋዜጣስ ራሱ በይዘቱም፣ በሕይወቱም የዚህ የአዲስ ዘመን ምልክትና ጌጥ ሆኖ ኖረ ወይ? ብለን ብንጠይቅ መልሱ አዎንታዊ አለመሆኑ የታወቀ ነው፡፡ በአዲስ ዘመን የጋዜጣ ታሪክ ውስጥ በራሱ ብንወስን እንኳን ጥሩም የሚያኮራም መልስ አናገኝም፡፡ የጋዜጣ ታሪክ የአንድ አገር የዴሞክራሲ ታሪክ፣ የጤንነት የደም ምርመራ ውጤት መግለጫ ነውና፡፡

አንዳንድ ምልክቶችንና ማሳያዎችን ላቅርብ፡፡ ለምሳሌ በንጉሠ ነገሥቱ የመጨረሻዎቹ ዘመናት ውስጥ፣ በ1960ዎቹ አብዛኞቹ ዓመታት ውስጥ፣ አዲስ ዘመን በፊት ለፊት ገጹ አንደኛው የላይኛው ጫፍ/ጠርዝ ላይ ‹‹የጠዋት ጋዜጣ›› የሚል የገዛ ራስ መግለጫ ይዞ ሲወጣ በደንብ አውቃለሁ፡፡ አዲስ ዘመን ይህን የሚለው፣ የጠዋት ጋዜጣ መሆኑን የሚገልጸው በእርግጥም በሳምንት ስድስት ቀን (ወይም ከሰኞ በስተቀር በየዕለቱ) የሚታተም ጋዜጣ ሆኖ እያለ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ የፕሬስ ነፃነት ግን እንኳንስ የጠዋትም፣ የምሽትም ጋዜጣ መመስከር ይቅርና ሌላ ዕለታዊ ጋዜጣ መታደል ሳይችል የቀረ ከስንትና ስንት ዓመት በኋላ በ1980ዎቹ መጨረሻ ላይ ‹‹ዕለታዊ አዲስ›› የተባለ ጋዜጣ የሞከረውን ጅምር ያጨናገፈ ነው፡፡ ከ1950ዎቹ መጀመርያ ላይ አንድ ብሎ የጀመረው የአዲስ ዘመን ዕለታዊነትም ቢሆን ለስም ያህል ከተሰፋ ቁና በላይ ትርጉምም ሥፍራና ቦታ ያለው አይደለም፡፡

ኢትዮጵያ ‹‹አዲስ ዘመን›› ስትጀምር ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም. የመጀመርያውና የመጨረሻው አልሆነም፡፡ ደርግም አብዮቱ ‹‹የፈነዳበትን›› ዓመት ኢትዮጵያ የተፈጠረችበት፣ ዘመን መቆጠር የጀመረበት አድርጎ ለማቅረብ መከራውን አይቷል፡፡ ኢሕአዴግም ‹‹ኢትዮጵያን ለአሥራ ሰባት ዓመታት ሲገዛ የቆየው የወታደራዊ አምባገነን መንግሥት መገርሰስ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ አገሩንና መንግሥቱን በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንደ አዲስ ለመገንባት የሚችልበትን ዕድል የከፈተ ታሪካዊ ወቅት በመሆኑ…›› ብሎ ግንቦት 20 አዲስ ዘመን ተብሎ ነበር፣ ያም ሳይሆን ቀረ፡፡

የሩቁን፣ ነባራዊው ሁኔታ ሲበዛ የራቀውን የንጉሠ ነገሥቱን ዘመን ነገር ለጊዜው እንተወውና ደርግም ኢሕአዴግም ዴሞክራሲ አቋቋምን፣ ሪፐብሊክ መሠረትን ብለው አውጀዋል፡፡ የአገሪቱን መንግሥት እንደ ቅደም ተከተላቸው የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ፣ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲዊ ሪፐብሊክ ብለው በሕግ ሰይመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን ነፃና ትክክለኛ ምርጫ አካሄዶ የፈቃዱ ውጤት የሆነ መንግሥት ዓይቶ አያውቅም፡፡ በአገርና በመንግሥት የአደረጃጀት ፍጥርጥር ምክንያት በኢትዮጵያ ውስጥ የሕዝብን ልዕልና መወከል የሰመረለት ሪፐብሊክ ማቋቋምና ማደራጀት አንችልም፡፡ የዚህ ምክንያት ለዴሞክራሲ የሚስማማ የመንግሥት መሠረት በኢትዮጵያ ውስጥ ኖሮ ስለማያውቅ ነው፡፡ ከአንድ ፓርቲ፣ ከአንድ ወገን፣ ወይም ከአንድ ኃይል ግልጽም ሆነ ሥውር ተፅዕኖ የተላቀቀ ዓምደ መንግሥት በኢትዮጵያ ውስጥ ስላልነበረ ነው፡፡ ኖሮ ስለማያውቅ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት የኢትዮጵያ፣ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የአዲስ ታሪክ መክፈቻ፣ አዲስ ሥራ የአገር የሥልጣን መዋቅራትን ከፓርቲም ሆነ ከየትኛውም ኃይል ወገናዊነት ነፃ አድርገን ማነፅ ነው፡፡ ከቡድን ይዞታነት፣ ባለቤትነት ወይም ተቀጽላነት የፀዳ አገዛዝ የመገንባት ተቀዳሚ ሥራ አለብን፡፡ ሥርዓተ መንግሥትና ፓርቲ መቀላቀላቸው የተወገዘበት፣ ነውር የሆነበት አገር መገንባት አለብን፡፡ የመንግሥት አውታራት የፓርቲ ጋሻ ጃግሬ መከማቻ የሆኑበትን አሠራር ማስወገድ አለብን፡፡

ከምርጫ 2007 በኋላ ያለውን፣ የተሞካከረውን፣ የተካሄደውን፣ ይቅር፣ ይራዘም፣ ወዘተ የተባለውን ምርጫ ልዩ የሚያደርገው ይኼው ምክንያት ነው፡፡ ይኼ ጉዳይ በጣም አስፈላጊና መሠረታዊ በመሆኑ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ዴሞክራሲ! ዴሞክራሲ! የሚሉ ሁሉ የጥበብ መጀመርያ ብቻ ሳይሆን የጋራ መገናኛና የወል አደራ መሆን ያለበት ጉዳይ ስለሆነ በሰፈው መብራራት፣ ተደደጋግሞ መገለጽ አለበት፡፡ ኢትዮጵያ በተለይም ከመጋቢት 2010 ዓ.ም. በኋላ፣ ድኅረ ግጭት ምርጫ የምታደርገው የሆነ የጊዜ ቀጠሮ ስላለ፣ በሕግ የተወሰነ ‹‹በየጊዜው›› የሚል ድንጋጌ ስላለ፣ ከምርጫ 2007 ዓ.ም ጀምሮ የተቆጠረ የአምስት ዓመት ጊዜ ‹‹ስለደረሰብን›› አይደለም፡፡ እንደህ ያለ ምርጫማ ያለ መጋቢት 2010 ዓ.ም. ከኅዳር 2008 እስከ 2010 ዓ.ም. ድረስ የተካሄደው ጉዳትም፣ ውድመትም ጥፋትም ያደረሰው ትግል ሳይኖር ማካሄድ የአገር ችግር አልነበረም፡፡ የበጀትም ችግር አለብን አላለም፡፡ ሁሉም፣ የተለያየ ፍላጎት፣ የሥልጣን ፍላጎት ጭምር ያላቸው ሁሉ፣ ነገር ግን ለዴሞክራሲ እንታገላለን የሚሉ በሙሉ፣ በጋራና በአንድነት ሊስማሙበት የሚገባ ጉዳይ መጀመርያ የተለያዩ ፓርቲዎችን የሚያንተረክክ፣ እነዚህን ፓርቲዎች ያለ አድልኦ በእኩልነት የሚያይና የሚያስተናግድ፣ የየፓርቲዎችን አባላትና ተከታዮች ‹‹ከልጅ ልጅ›› ሳለይ በእኩልነት የሚያይ ሜዳ፣ ውድድር፣ ዳኛ፣ ወዘተ ነው፡፡

ዋናው የለውጥና የሽግግር የፖለቲካ ጥያቄ ዴሞክራሲን ማደላደል፣ ሕግ የማስከበርን፣ ፀጥታን፣ የአገር ደኅንነትንና ሰላምን የመጠበቅና የማስከበር ግዳጅን የጋራ ሥራ ማድረግ ሆኖ ሳለ፣ በዋናው ጥያቄ ውስጥ ገብተው መፈታት የሚገባቸው ግን ዋናውን ጥያቄ የሚያሰናክሉ ጉዳዮች በትግል ኃይሎች ውስጥ ንፋስ አስገባ፡፡ ይህም የለውጡን ተጠናዋቾች የሚያግዝና የበላይነት የሚያቀዳጅ አደጋ ፈጠረ፡፡ የጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ያልተለመደ፣ ያልተጠበቀና ታይቶ የማይታወቅ ወረራ፣ ክህደትና ጥቃት የደረሰውም በዚሁ ከባቢ አየር ውስጥ ነው፡፡

በብዙ ውጣ ውረድና አደገኛ ሁኔታዎች በገነኑበትና በገነተሩበት ሁኔታ ውስጥ የተካሄደውም ምርጫም፣ ከእነ ችግሮቹና ገና ካልተጠናቀቁ ቀሪ ተግባሮቹ ጋርም ቢሆን አብዛኛውን የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ ላይ አሠለፈ፡፡ ለውጡንና ሽግግሩን ከክሽፈት የማዳን ተግባር፣ አገርን ከማዳን የእናት አገር ጥሪ ጋር ብቻ ሳይሆን ፌዴራላዊ ዴሞክራሲን እውነተኛ መሠረት ከማስያዝ ተልዕኮና ግዳጅ ጋር አጣመረ፡፡

በዚህ ምክንያት፣ በዚህ የ2013 ምርጫ አማካይነት በየደረጃው የተመረጡ የምክር ቤት አባላትና በእነሱም አማካይነት የሚደራጁት ምክር ቤቶች ራሳቸው፣ በተራቸው (በፈንታቸው)፣ በየሥልጣን አድማሳቸው ውስጥ የሚያደራጃቸው የሥራ አስፈጻሚዎች (ይህ ሁሉ ሥራና አደራ መታየት ያለበት) ለውጡንና ሽግግሩን ብሎም አገርን ከማዳን፣ ዴሞክራሲን ከማደላደል፣ እስከ ዛሬ ድረስ ተጭኖንና ተጭኖብን የነበረውን የመንግሥት አውታር ከፓርቲ ታማኝነትና ተቀጽላነት ከማፅዳት የአዲሲቱ ኢትዮጵያ የአዲስ ታሪክ ዘመን መክፈቻ ሥራና ገድል አንፃር ነው፡፡ ‹‹በዚህ በአዲስ ዘመን ሁላችን መፈጸም ያለብን አዲስ ሥራ›› የሚጀምረው በዚህ አማካይነት ነው፡፡

በ2013 ዓ.ም. የተደረገው ጠቅላላ ምርጫ (የሕዝብ ተወካዮችና የክልል ምክር ቤቶች አባላት ምርጫ) ሁሉም በመላ አገሪቱ በተመሳሳይ ጊዜ ባለመካሄዱ ገና የሚካሄዱ ምርጫዎችና የምንጠብቃቸው ውጤቶች ቢኖሩም፣ የተካሄደው ምርጫና የታወቀው ውጤት በራሱ ለሌሎች ቀሪ ሥራዎቻችን ግፊትና ስንቅ የሚሆኑ ድሎች ናቸው፡፡ ሲጀመር መንግሥት የለም፣ ከመስከረም 25 በኋላ ኢትዮጵያ መንግሥት አልባ ነች፣ ከመስከረም 25 በኋላ የሚወጣ ሕግ፣ ወዘተ ሁሉ ፉርሽ ነው የተባለው 2012 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ነው፡፡ የዚህ ምክንያት አሁን ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት እንደ 2007 ዓ.ም. ባለው (እንደ 2002 ዓ.ም.፣ እንደ 1997 ዓ.ም.፣ ወዘተ) ምርጫዎች አልተደራጀም ተብሎ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትና የ2013 ዓ.ም. ምርጫ ትርጉም የሰጠውና አምሳያ የሌለሽ አዲስ ጀብድ (Feat) ያደረገው ግን፣ ምርጫው ከምንጊዜውም የበለጠ የሕዝቦች ልብ የተላወሰበት፣ ወዘተ በመሆኑ ብቻ አይደለም፡፡ ምርጫው ከ2012 ዓ.ም.፣ ከእነ ጭራሹም ከግንቦት ወር ነቅነቅ፣ ፈቀቅ አይልም የሚል ከሕግ ይልቅ የ‹‹ፖለቲካ›› ተቃውሞ በገጠመ ጊዜ አነሰም በዛም ጉዳዩ መፍትሔ ያገኘው ሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት መሠረት ነው፡፡ ዝርዝሩና ታሪኩ ቦታ ይወስዳል፡፡ በአጭሩ ግን በባለመብቱ ሕገ መንግሥታዊ የሥልጣን አካል የተወሰነው፣

  1. የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሕዝብ ጤና ጥበቃ ሥጋት ሆኖ ባለበትና የበሽታውን ሥርጭት ለመቆጣጠር የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ፀንቶ በቆየባቸው ጊዜያት ከተነሳም በኋላ፣ አዲስ ምርጫ ተካሄዶ፣ የሥልጣን ርክክብ እስከሚፈጸምበት ጊዜ ድረስ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ የክልል ምክር ቤቶችና የፌዴራልና የክልል አስፈጻሚ አካላት የሥራ ዘመን እንዲቀጥል፣
  2. የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር፣ እንዲሁም የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና የሳይንሱ ማኅበረሰብ አባላት ወረርሽኙ የሕዝብ ጤና ሥጋት አለመሆኑን ካረጋገጡበትና ይህም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከፀደቀበት ጊዜ ጀምሮ ከዘጠኝ ወራት እስከ አንድ ዓመትም ባለው ጊዜ ውስጥ ምርጫው እንዲካሄድ ተብሎ ነው፡፡

ይህንን ሁሉ አስተናግዶ ነው ምርጫው የተካሄደው፣ በመካሄድም ላይ ያለው፡፡ ገና ግን ብዙ ይቀረናል፡፡ ገና ብዙ ይቀረናል የምንለው የመስከረም 20 ቀን 2013 ምርጫ ሒደትና ውጤት፣ ከዚያም ሊያድር የሚችል፣ ወይም በ‹‹አረም›› የምንመለስበት ነገር ስለሚኖር ብቻ አይደለም፡፡ የትግራይ ክልልም ምርጫ ገና ብዙ ይቀረዋል፡፡ አገር እዚህ ክልል ውስጥ፣ ከዚያም ወደ ሌላ ክልሎች የተስፋፋ ባለብዙ ግንባር ጦርነት ውስጥ ነች ማለት ብቻ የጉዳዩን ሙሉ ምሥል አይገልጸውም፡፡ በረሃብ አደጋና በጅምላ ግድያ ወንጀል የሚከሱን፣ ለዴሞክራሲና ለሰብዓዊ መብት አሳቢና መድኃኒት ነን የሚሉን ኃያላን በማዕቀብ፣ በሥውር ሴራ አንቀው ሌላ ‹‹ለውጥ›› እየፈለጉልን መሆኑንም ማወቅ አለብን፡፡ አዲሱ ዘመን አዲሱ ‹‹የመንግሥት ምሥረታ›› በዚህ በአዲስ ዘመን ሁላችንም መፈጸም ያለብን፣ የአዲስ ሥራ ጅምር ይህንን ሁሉ ከቁጥር ማስገባትና ማካተት አለበት፡፡

በዚህ ረገድ እስካሁን ከምርጫው በኋላ ማለትም የሰኔ 14ቱ ምርጫ በተካሄደባቸውና ውጤቱ በታወቀባቸው ሁሉ፣ በዚህ ምርጫ መሠረት እየተካሄደ ያለውና ያየነው ምክር ቤቶችን በምርጫው ውጤት መሠረት የማደራጀት፣ በተደራጁት፣ ማለትም መመረጣቸው በተረጋገጠላቸው፣ የመሃላ ቃል በፈጸሙት፣ አፈ ጉባዔያዎቻቸውንና ምክትላቸውን መርጠው የሕዝብ ተወካይነት ሥራቸውን በጀመሩ ምክር ቤቶች አማካይነት በሚደራጀው መስተዳድር አማካይነት ሥልጣን የመረከቡ ተግባር ገና ግርታና ብዥታ ያለው መሆኑን ከመመስከር አልተረፍንም፡፡ ወይም አልዳንንም፡፡ ያ ሁሉ የአምስት ፓርላማ፣ የአምስት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ልምድ፣ ወይም የሃያ አምስት (ከዚያ በላይ) ልምድ ያስመዘገበልን ዋስትና የለም፡፡ ያለፉት ሦስት ዓመታት ልዩ ልዩ ዓይነት መራራነትም ሆነ መራርነት ይህ ነው የሚባል ትምህርት አላስጨበጡንም፡፡ አሸናፊ ፓርቲ በሚያደራጀው የከተማ መስተዳደር ውስጥ፣ ለምሳሌ የዚያው የአሸናፊው ፓርቲ አባል ሆኖ የተመረጠ የምክር ቤት አባል ከፓርቲው መድረክ ውጪ የእኛ ብሔረሰብ በካቢኔው አመራር ውስጥ አልተወከለም ብሎ በአደባባይና በይፋ በቀጥታ የቴሌቪዥን ሥርጭት ቅሬታ ሲያሰማ ማየት ቀላል፣ የመውደቅ የመነሳት፣ ትንሽ የመጋጋጥ ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡

ከዚሁ ከገዥው ፓርቲ ራስ፣ ከራሱ ሳልወርድ ብልፅግና ፓርቲ በፌስቡክ ገጹ ቅዳሜ መስከረም 15 ቀን 2013 ዓ.ም. ለጥፎ ያስነበበንን ጽሑፍ ከሌሎች መካከል ለምሳሌ ያህል እንመልከት፡፡ እንደሚከተለው ይነበባል፡፡

ምርጫ በተካሄደ በአንድ ወር ውስጥ መንግሥት እንዲመሠረት ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ ነው፣ ሊታለፍ ወይም ሊሸጋገር የሚችል አይደለም፣ ምክንያቱም በፀሐይና በብርድ ቆሞ ድምፅ የሰጠው ሕዝብ ድምፁ ዋጋ መኖሩን የሚያረጋግጠው መንግሥት ሲመሠረት ነው፡፡ የሚመሠረተው ጠንካራ መንግሥት አገሪቱ ውስጥ እየታዩ ያሉ መሠረታዊ ችግሮችን የመፍታት አቅምም ሆነ ኃላፊነት አለበት፡፡

ባለፈው ሰኔ ወር የተካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ መቋጫ የሚሆነው ተፎካካሪ ፓርቲዎች በፓርላማ ገብተው እንዳገኙት አብላጫ መቀመጫ መሠረት በማድረግ መንግሥት ይመሠርታሉ፡፡ ምርጫው ከተካሄደ በኋላ የመንግሥት ምሥረታው የማይቀር ሒደት ነው፡፡

መንግሥት ከመመሥረት ይልቅ ከባዱ ነገር የነበረው ምርጫ ማካሄድ ነበር፡፡ ነገር ግን ምርጫው እንደታሰበው ሰላማዊ ሆኖ ሕዝቡ ድምፁን ለሚፈልገው ፓርቲ ሰጥቶ ተጠናቋል፡፡ ስለሆነም የሕዝቡን ድምፅ ማክበር የሚቻለው ደግሞ መንግሥት ሲመሠረት ነው፡፡ እንደ አገር እያየናቸው ያሉ ማንኛውንም ችግሮች ደረጃ በደረጃ መፍታት የሚቻለው ሕጋዊ መንግሥት ሲመሠረት ብቻ ነው፡፡ መንግሥት መኖሩ ለሁሉም ነገር መልስ ይሰጣል፡፡

አንዳንዶች አሁን አገሪቱ ያለችበት ሁኔታ መንግሥት መመሥረት ያስችላል ወይ? ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ እዚህ ላይ ማጤን የሚያስፈልገው ጉዳይ ቢኖር ኢትዮጵያ ያለችበት ቀጣናዊ፣ አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታውን መረዳት ላይ ነው፡፡ እንደ አገር እየደረሰብን ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ጫና፣ ኢኮኖሚያዊ አሻጥር፣ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንን ሚዛናዊ ያልሆነ ዕይታ ወይም ወደ አንድ ወገን ያደላ ዘገባና ሌሎችንም ጉዳዮች መፍታት የምንችለው ጠንካራ መንግሥት መመሥረት ስንችል ብቻ ነው፡፡

መንግሥት እንዲመሠረት ከሚገፋፉ ምክንያቶች አንዱ አገሪቱ ያለችበት ወቅታዊ ሁኔታ ነው፡፡ ይህ በመሆኑ መንግሥት መመሥረት የሚያስችለውን ድምፅ ማግኘት የቻለው አሸናፊ ፓርቲ ለሚፈጸሙ ማንኛውም ዓይነት ውሳኔዎች ሕጋዊ መሠረት እንዲኖረው የሚያስችለው በመሆኑ፣ መንግሥት መመሥረቱ ከምንጊዜውም በላይ አስፈላጊነቱ የጎላ ነው፡፡

ሲመስለኝ ይህን የብልፅግና ፓርቲ የፌስቡክ ገጽ ይህን የመሰለ የዕውር ድንብር፣ የአልዳኝም ባይ ዝም ብሎ ጀብዱና ክርክር ውስጥ የከተተው፣ ‹‹አገሪቱ ያለችበት ሁኔታ መንግሥት መመሥረት አያስችልም›› የሚሉ ወገኖች መኖራቸው፣ ወይም ይህንን ጥያቄ አድርገው የሚያነሱ መኖራቸው ነው፡፡ የፌስቡክ ገጽ ባለቤት መከራከሪያ ደግሞ ‹‹መንግሥት እንዲመሠረት ከሚገፋፉ ምክንያቶች አንዱ አገሪቱ ያለችበት ወቅታዊ ሁኔታ ነው›› ነው፡፡ ይህንን አቋም ለመርታት ግን የብልፅግና ፌስቡክ ገጽ ‹‹ምርጫ በተካሄደ በአንድ ወር ውስጥ መንግሥት እንዲመሠረት ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ ነው፤›› ሊተላለፍና ሊሸጋገርም አይችልም ይላል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ግን እንዲህ ያለ ድንጋጌ የለውም፡፡ ‹‹አንድ ወር›› የሚባል ነገር ሕገ መንግሥቱ ውስጥ ይፈለግ ቢባል ምርጫን በሚመለከት የምናገኘው በአንቀጽ 58 (3) እና 60 (4) ብቻ ነው፡፡ አንደኛው ድንጋጌ እንደ አቀማመጣቸው፣ ‹‹የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚመርጠው ለአምስት ዓመታት ነው፣ የሥራ ዘመኑ ከማብቃቱ ከአንድ ወር በፊት አዲስ ምርጫ ተካሄዶ ይጠናቀቃል፤›› ይላል፡፡ ሌላኛው ድንጋጌ ደግሞ ስለምክር ቤቱ መበተን በሚደነግገው አንቀጽ ውስጥ ያለው፣ ምክር ቤቱ የተበተነ እንደሆነ ከስድስት ወራት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ መደረግ ያለበት አዲስ ምርጫ በተጠናቀቀ በ30 ቀናት ውስጥ፣ ‹‹አዲሱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሥራውን ይጀምራል፤›› የሚለው ነው፡፡

‹‹ምርጫ በተካሄደ በአንድ ወር ውስጥ መንግሥት እንዲመሠረት ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ ነው፤›› የሚለው የብልፅግና ጽሑፍ ትንሽ ‹‹ቀረብ›› የሚለው እንዲያው ይሁን ብንል፣ ‹‹ምርጫው በተጠናቀቀ በ30 ቀናት ውስጥ አዲሱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሥራውን ይጀምራል፤›› የሚለው ነው፡፡ ያም ቢሆን የምርጫው ውጤት የሆነው የተወካዮች ምክር ቤት ሥራውን ይጀምራል ማለት መንግሥት ይመሠረታል፣ መንግሥት ይመሠርታል፣ ወይም ያደራጃል ማለት አይደለም፡፡ መንግሥት የማደራጀት ወይም የመመሥረት ሥራ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 56 እንደተወሰነው በምክር ቤቱ ውስጥ አብላጫውን መቀመጫ ባገኘው የፖለቲካ ድርጅት/ድርጅቶች በመሆኑ ምክር ቤቱ ሥራ ከጀመረ በኋላ በምን ያህል ጊዜ መንግሥት ይመሠረታል ማለት በሕግ ‹‹የተወሰነ›› የጊዜ ጉዳይ ሳይሆን፣ የተለያየ መጠን ያለው የወንበር ክምችት ያገኙ ፓርቲዎች ስምምነት ለመድረስ የሚወስዱት ጊዜ ነው፡፡

እንዲህ ያለ የዕውር ድንበር፣ የግብር ይውጣና ከሁሉም በላይ ደግሞ የ‹‹ፖለቲካዬን ይጠቅመኛል›› እና ኃላፊነት የጎደለው ክርክር/መከራከሪያ ቀርቦ አገር ሲፈታ በታየበት፣ የብቻ ግንጥል ምርጫ ተካሄዶ፣ ለዚህ ሁሉ ቀውስ በበቃንበት አገር ውስጥ ዝም ብሎ፣ ይጠቅመኛል ብሎ (ደግሞም አይጠቅምም) ‹‹ምርጫ በተካሄደ በአንድ ወር ውስጥ መንግሥት እንዲመሠረት ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ ነው፤›› ማለት ሕገ መንግሥታዊም፣ ዴሞክራሲያዊ ፖለቲካም አይደለም፡፡ በተለይም በገዥው ፓርቲ በጭራሽ አያምርበትም፡፡

ከብልፅግና ፓርቲ፣ ከገዥው ፓርቲ፣ በተለይም ለውጡንና እንደ ጉድ የተሰባሰበውንና አንድ የሆነውን ሕዝብ ድጋፍ ካገኘው የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ መንግሥት የምንፈልገውና የምንጠብቀው ይህንን የመሰለ የፌስቡክ ገመና እና ተራ ወሬ ማራገፍ፣ መፀየፍና ማውገዝ፣ ተጠያቂም ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ በአዲሱ መንግሥት (የአስፈጻሚው የመንግሥት የሥልጣን አካል) ማደራጀት ወቅትም ሆነ ከዚያ በኋላ በሚሠራውና በሚከተለው አመራር አማካይነት ‹‹ተዓምር›› አከል ነገር ሲፈጥር ማየት ነው፡፡ በዚህ አገርን ማዳንና የተጀመረውን ለውጥ ማዳን አንድ ላይ በገጠሙበት ወቅት መላ ኅብረተሰብ ሆ ብሎ ሲነሳ ዓይተናል፡፡ ከሞላ ጎደል መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲንም ሰላምንም በመናፈቅና አንዳችም ማወላወል እንደሌላቸው በምርጫው ጊዜም፣ ከምርጫው በፊትና በኋላ በነበራቸው ርብርብ ቁልጭ አድርገው አሳይተዋል፡፡ ምርጫው የተካሄደው አገር ለጦርነት በተዳረገችበት ወቅት ምርጫውም የሰላማዊ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሕጋዊና ዴሞክራሲያዊ ውድድር መሆኑ ቀርቶ፣ ወደ እርስ በርስ መባላት እንዲለወጥ አስፈላጊው ሁሉ በተደገሰበት ወቅት ነው፡፡ የኢትዮጵያ መራጭ ግን፣ ከሞላ ጎደል ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ጨምሮ ምርጫው ማኒፌስቶን ከማኒፌስቶ የምናማርጥበትና የምናበላልጥበት ሳይሆን ለአገር ህልውና የምንዋደቅበት፣ ሕግና ሥርዓትን፣ ሰላምና ፀጥታን የማስከበር የመንግሥት አቅምን አግዘን የምንፋለምበት፣ ይህም የሞት ሽረት ትግል መንበረ መንግሥቱን ከፓርቲ ተቀጽላነትና ጋሻ ጃግሬነት ነፃ የምናወጣበት፣ በአጠቃላይ ይህን ሁሉ ትግል በግንባር ቀደምትነት የሚመራውን የለውጥ ኃይል በርታ፣ ግፋ፣ ገና ነው ብለን መርቀን መሪነቱን የምናፀድቅበት ውሳኔ ሕዝብ ነው ብሎ የምርጫ ፍላጎቱን ገለጸ፡፡ ምርጫው ሪፈረንደም ነበር የሚባለውም በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ይህን በመሰለ በምርጫም፣ በዘመቻም፣ በአገር መከላከልም ሆ ብሎ የተነሳውን ሕዝብ ያየ ሁሉ፣ ይህንንም ዓይቶ በዚህ ዓይነት የሕዝብ ታላቅነት ውስጥ መብቀልና መኖር፣ በዚህም ሕዝብ አይዞህ፣ በርታ፣ ግፋ፣ ገና ነው መባሉ መታደል ነው ያለ ሁሉ የተመረጠውን ፓርቲና መንግሥት ጨምሮ አፀፋዊ ምላሹ አዲስ የሚቋቋመውን መንግሥት የተቻለውን ያህል፣ የሕዝቡን ያህል ዥንጉርጉር ማድረግ ትንሹ የጨዋነት ምልክት ነው፡፡ ብዙ ሰዎች አዲስ አበባ መስተዳድር ውስጥ በታየው ‹‹አካታችነት›› ተገርመዋል፡፡ የፌዴራሉ መንግሥት የካቢኔ ሠራዊት ጥንቅር ይህንን በበጎ ይዘቱ ‹‹መሳቂያ›› ሊያደርገው፣ ‹‹ዓባይን ያላየ ምንጭ ያመሠግናል›› አሰኝቶ መተረቻ ሊያደርገው ይገባል፡፡

ዋናው ጉዳይ ግን ይህ አይደለም፡፡ ወይም ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ከረዥም ጊዜ አንስቶ እየተጀመረ፣ እየከሸፈ እንደገና ሲጀመር የቆየና ተገትሮ የኖረ የዲሞክራሲ ጥያቄ አለ፡፡ ከአምባገነንነት ወደ ዲሞክራሲ የመሸጋገር፣ በመጋቢት 2010 ዓ.ም. ከምር የጀመረ የመላ ኢትዮጵያውያንን ድጋፍና ተከታይነት መጎናፀፍ ብቻ ሳይሆን የዓለምን ውድና ብርቅ ሽልማት ማሸነፍ የቻለ ለውጥና ሽግግር ነበር፡፡ ጥቃትም የደረሰበት ይኸው ጅምርና ጉዞ  ነው፡፡

ኅብረ ብሔራዊ ማንነትን ከኢትዮጵያዊ ማንነት ጋር ማስማማትና ማልማት ይቻላል ብሎ፣ ከዲሞክራሲ አልባነት ወደ ዲሞክራሲ የመሸጋገር ትልም መርጦ፣ የአገሪቱን የሥልጣን አምዶች ከፓርቲ ታማኝነትና መዳፍ የማላቀቅ የማሻሻያ ሒደት ውስጥ ገብቶ፣ ከዚህ በፊት በአገሪቷ ታሪክ ያልነበረ አዲስ ውጤት ማለትም ሕዝቦች በድምፃቸው ሿሚና ሻሪ የሚሆኑበት ሥርዓት መንግሥት የሚያመጣ የተጀመረ ሥራና አደራ አለብን፡፡

መላውን ሳምንት ስለምርጫ፣ ስለከተማ፣ የክልል፣ የፌዴራል ምክር ቤቶችና ስለመንግሥት ምሥረታ ሲወራ ሰምተናል፡፡ ምርጫ ትርጉም የሚኖረው፣ የምክር ቤቶችን በምርጫ መደራጀት የሚወስነው፣ ሿሚነትና ተቆጣጣሪነታቸውን ከመልክ ያለፈ እውነት የሚያደርገው የመንግሥታዊ አውታራት፣ ሁሉም የመንግሥት የሥልጣን አውታራት፣ በተለይም ደግሞ የፀጥታ፣ የመከላከያና የደኅንነት አውታራት ከፖለቲካ ቡድን መዳፍ ነፃ ሆነው መደራጀታቸው ነው፡፡ የአዲስ ዘመን የአዲስ ዓመትና የአዲስ መንግሥት ዋናው ሥራችን በዚህ ላይ ማተኮርና በእሱም ላይ የደረሰውን ጥቃት ቀልብሶ ለውጡንና ሽግግሩን ዘላቂ ማድረግ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...