Thursday, April 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ኤቴኤም ማሽኖች በብዛትና በጥራት ያልተቋረጠ አገልግሎት ሊሰጡ ይገባል!

በሚፈለገው ደረጃ ዕድገት አሳይተዋል ባይባልም፣ ዘመናዊ የባንክ አገልግሎቶች በተለያየ መንገድ እየተተገበሩ ነው፡፡ ዘመናዊ የባንክ አገልግሎት መገለጫ በመሆን ከሚገለጹት መካከል ደግሞ ኤቲኤም ተጠቃሽ ነው፡፡

የኤቲኤም ማሽኖች በፋይናንስ እንቅስቃሴ ውስጥ ያላቸው ጠቀሜታ እየጎላ መጥቷል፡፡ እንደ ሞባይልና ኢንተርኔት ያሉ የዲጂታል የባንክ አገልግሎቶች በኢትዮጵያ ገና ያልሰፋና አሁንም ብዙ መንገድ የሚቀረን በመሆኑ፣ እንዲሁም አሁን ባለን ግንዛቤና የአጠቃቀም ቅለት የኤቲኤም ማሽኖችን አገልግሎት በተለየ እንድናየው ያደርገናል፡፡

መረጃዎች እንደሚያሳን በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የኤቲኤም ማሽኖች ቁጥር አሥር ሺሕ እንኳን አልሞላም፡፡ ነገር ግን ባሉት የኤቲኤም ማሽኖች በመጠቀም በዓመት ውስጥ የሚንቀሳቀሰው የገንዘብ መጠን ከፍተኛ እንደሆነ ይገመታል፡፡ ይህ ከየትኛውም ዘመናዊ የክፍያ ዘዴዎች ሁሉ የተሻለ የተጠቃሚዎች ቁጥር ያለውና ወደፊትም እንደሚኖረው የሚሳይ ነው፡፡

ከኢትዮጵያ የሕዝብ ቁጥር አንፃር ሲመዘን የኤቲኤም ማሽኖች ቁጥር እጅግ በጣም አነስተኛ መሆኑ ግን አይካድም፡፡ ባሉትም በአግባቡ እየተጠቀምን ነው ወይ? ወይም ማሽኖቹ በተገቢው መንገድ አገልግሎት እየሰጡ ነው ወይ? የሚሉት ጥያቄዎች ሲነሱ ግን አጥጋቢ ምላሽ ላናገኝ እንችላለን፡፡

ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር በየባንኩ ቅርጫፎች በመሄድ ገንዘብ ለማውጣት አሰልቺ ስለሚሆን፣ የእነዚህ ማሽኖች በአማራጭነት መቅረብ የፋይናንስ ዘርፉን የአገልግሎት አሰጣጥ በአንፃራዊነት አቃልሏል፡፡ ደንበኞችም ቢያንስ ገንዘብ ለማውጣት አማራጭ ሆነው እየተገለገሉበት ነው፡፡

በተለይ የባንክ ቅርንጫፎች በአገልግሎት ሰዓት በተገደበበትና ከስምንት ሰዓት ያልበለጠ ሰዓት የሚሠሩ መሆኑ፣ 24 ሰዓት ገንዘብ ለማውጣት የሚያስችሉት እነዚሁ የኤቲኤም ማሽኖች ናቸው፡፡ የቱንም ያህል መጠናቸው አነስተኛ ቢሆንም የሁሉንም ባንኮች የኤቲኤም ማሽኖች በማስተሳሰር በአገር አቀፍ ደረጃ የአንዱ ባንክ ካርድ ለሌላውም እንዲያገለግል ማድረግ መቻሉ ደግሞ ለተገልጋዮች እንደ መልካም ዕድል የሚታይ ነው፡፡ የአገሪቱ ባንኮች በአብዛኛው ቅዳሜና እሑድን፣ እንዲሁም የበዓላት ቀናት ቅርንጫፎቸውን አገልግሎት የማይሰጡ በመሆኑ፣ ቢያንስ አስፈላጊ ለሚባል ፍላጎት ገንዘብ አውጥቶ ለመጠቀም እነዚህ የኤቲኤም ማሽኖች ብቸኛ አማራጭ ናቸው ተብሎ ይወሰዳል፡፡

በመሆኑም በኤቲኤም ማሽኖች በሌሎች አገሮች እንደሚታየው ገንዘብ ማስገባትና ሌሎች የባንክ አገልግሎቶችን ማግኘት የማይቻልባቸው ቢሆንም፣ አንድ የባንክ ደንበኛ ለአስቸኳይ ፍላጎቱ ገንዘብ ማውጣት የሚቻልበት ዕድል የሚፈጥሩ ናቸው፡፡ በተለይ እንደ አዲስ አበባ ያሉ ከተሞች የኤቲኤም ተጠቃሚዎች በርከት ስለሚሉ ወደ ባንኮች ቅርንጫፍ ገንዘብ ለማስገባት ካልሆነ በስተቀር ገንዘብ ለማውጣት ኤቲኤምን ተመራጭ በማድረግ የመገልገል ልምድን በማዳበራቸው በኤቲኤም የሚደረግ የገንዘብ እንቅስቃሴ እየጨመረ መጥቷል፡፡

ከየትኛውም የኤቲኤም ማሽን በየትኛውም ባንክ ካርድ ገንዘብ ማውጣት የሚቻልበት ዕድል መፈጠሩ ደግሞ በከተሞች አካባቢ የኤቲኤም ተጠቃሚዎች ቁጥራቸው በየጊዜው እየጨመረ እንዲመጣ አድርጓል፡፡ ይህ ባንኮችን አበረታቶ እጅግ ብዙ ወጪ የሚጠይቀውን በከተሞች አካባቢ የሚያደርጉትን ቅርንጫፍ የመክፈት ልምድ በተወሰነ ደረጃ ገታ በማድረግና ቅርንጫፍ ወዳልተስፋፋባቸው አካባቢዎች በማተኮር የኤቲኤም ማሽኖችን ማብዛት ይጠበቅባቸዋል ማለት ነው፡፡ ይህ ዕርምጃ ለእነሱም ጥቅም እንደሚሆንም ይታመናል፡፡  

የኤቲኤም ግልጋሎትን በተወሰነ ደረጃ የምንገልጸው ከሆነና እየሰጡ ያለው አገልግሎትና እየተለመደ ከመምጣቱ አንፃር የአገልግሎት አሰጣጡም ጥርት ማለት አለበት፡፡ የእነዚህ ማሽኖች ግልጋሎት በይበልጥ ከሥራ ሰዓት ውጪ በእረፍትና በባዓላት ቀናት በእጅጉ አስፈላጊ ከመሆናቸው አንፃር በእነዚህ ቀናት አገልግሎታቸው እንዳይታጎል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

በተለይ የባንክ ቅርንጫፎች አገልግሎት በማይሰጡባቸው ቀናት ባንኮቹ ደንበኞቻቸውን በአግባቡ ለማስተናገድ የኤቲኤም ማሽኖቻቸውን ከሌላው ጊዜ በተለየ ሁኔታ ለአገልግሎት ዝግጁ ማድረግ፣ በቂ ገንዘብ እንዲኖራቸው ማድረግና ብልሽት ቢገጥማቸው ወዲያው በማስተካከል አገልግሎታቸውን እንዲቀጥሉ ካልተደረገ፣  ተገልጋዩን ማማረራቸው አይቀርም፡፡ በተደጋጋሚ መታዘብ እንደቻልነውም ጥቂት የማይባሉ ማሽኖች ከአገልግሎት ውጪ የሚሆኑበት አጋጣሚዎች ይፈጠራሉ፡፡ በቂ ገንዘብ የሌላቸው ሆነው የሚገኙ ማሽኖችም ያጋጥማሉ፡፡

ሌላው በአንዳንድ ቦታዎች የአራትና የአምስት ባንኮች የኤቲኤም ማሽኖች ተደርድረው፣ አንድ ተገልጋይ ከአራቱ ወይም ከአምስቱ ማሽኖች አንደኛው ይሠራል በሚል ሙከራዎች ሲያደርጉ ሁሉም የማይሠሩበት ጊዜ አለ፡፡

ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ፣ እሑድና ሰኞ መታዘብ እንደቻልኩትም በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች ከሚገኙ የኤቲኤም ማሽኖች ገንዘብ ለማውጣት ብዙዎቹ ሲቸገሩ ነበር፡፡ እኔም በግሌ ገንዘብ ከኤቲኤም ለማውጣት በተለያዩ የኤቲኤም ማሽኖች ላይ ያደረኩት ሙከራ ሳይሳካኝ ቀርቷል፡፡

ትራንስፖርት ይዤ በየመንገዱ በሚገኙ ኤቲኤም ማሽኖች ላይ ያደረኩት ሙከራ አለመሳካቱ ደግሞ በይበልጥ አስገርሞኛል፡፡ ገንዘብ እናገኛለን ብለው በየኤቲኤሙ ሙከራ ሲያደርጉ የነበሩ ተገልጋዮች፣ አገልግሎት ባለማግኘታቸው ሲበሰጫጩ ማየታችን ‹‹ለምን እንዲህ ይሆናል?›› የሚል ጥያቄ እንድናነሳ ያደርገናል፡፡ ስለዚህ ባንኮች ከሥራ ሰዓት ውጪና በበዓላት ቀናት በተለያየ በአጋጣሚ ሥራ ላይኖር በሚችሉባቸው ቀናትና ኤቲኤም ማሽኖች ተፈላጊውን አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ካልቻሉ ግልጋሎታቸው ጎዶሎ መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት