Thursday, February 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናመንግሥት የተመድ ሠራተኞች ከአገር እንዲወጡ ትዕዛዝ ያስተላለፈበትን ምክንያት አስታወቀ

መንግሥት የተመድ ሠራተኞች ከአገር እንዲወጡ ትዕዛዝ ያስተላለፈበትን ምክንያት አስታወቀ

ቀን:

መንግሥት በአትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ሕገወጥ ሥራ ሲሠሩ ተደርሶባቸዋል በማለት በ72 ሰዓታት ውስጥ አገር ለቀው እንዲወጡ ውሳኔ ያስተላለፈባቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ሠራተኞች ምክንያት ይፋ አደረገ፡፡ በመሆኑም የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦትንና የኮሙዩኒኬሽን መሣሪያዎችን ለሕወሓት ታጣቂዎች ማቀበል፣ የተደረጉ የፀጥታ ስምምቶችን መጣስና ሌሎችም ሕገወጥ ድርጊቶችን ሲፈጽሙ በመገኘታቸው መሆኑን ጠቁሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዓርብ መስከረም 21 ቀን 2013 ዓ.ም. አመሻሹን ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ከሐምሌ 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ትግራይ ክልል ዕርዳታ ለማድረስ ተልከው ያልተመለሱና በሕወሓት ታጣቂዎች ለወታደራዊ እንቅስቃሴ እያገለገሉ ያሉ ተሽከርካሪዎች እንዲመለሱ ለማድረግ ግለሰቦቹ ያሳዩት ለዘብተኝነት፣ እንዲሁም የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦትን የፖለቲካ ይዘት እንዲኖረው በማድረግ ሐሰተኛ መረጃ ማሠራጨት እንደሆነ አብራርቷል፡፡

 

በ72 ሰዓት ከአገር እንዲወጡ ትዕዛዝ የወጣባቸው የተመድ ሠራተኞች  የዓለም ሕፃናት አድን ድርጅት ጽሕፈት ቤት (ዩኒሴፍ) እና በተመድ የሰብዓዊ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቶች  ሥራ ሲሠሩ የነበሩ ሰባት የውጭ አገር ዜጎች መሆናቸው መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም. መገለጹ ይታወሳል፡፡

ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው እንደጠቆመው፣ ኢትዮጵያ እንደ አንድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መሥራች አገር የድርጅቱን ቻርተር በሙሉ ቁርጠኝነት ስትፈጽም መቆየቷንና የተመድ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች በተለይም በኢትዮጵያ በነበራቸው ረዥም ቆይታ፣ የሕይወት አድን ዕርዳታ ለሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ሲያደርሱ እንደነበር አስታውቋል፡፡

ይሁን እንጂ እ.ኤ.አ በኅዳር 29 ቀን 2020 የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል የተስተካከለና የተቀናጀ የሰብዓዊ አቅርቦት እንዲኖር ለማድረግ ከተመድ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች ጋር የመግባቢያ ስምምነት ቢያደርግም፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ባለው ሁኔታ አንዳንድ የድርጅቱ ሠራተኞች ሥራቸውን ገለልተኛና ነፃ ሆነው ተልዕኳቸውን በስምምነቱ መሠረት ማከናወን አለመቻላቸውን ‹‹ባልጠበቅነው መልኩ ሲንቀሳቀሱ ተመልክተናል›› ሲል በመግለጫው አስታውቋል፡፡

በተለያዩ ጊዜያት የታዩትን ከፍተኛ የሆኑ የሕግ ጥሰቶች ለተመድ የበላይ ኃላፊዎችና ሌሎች ዓለም አቀፍ ወዳጆች በተለያዩ አጋጣሚዎች እንዲያውቁት ቢደረግም ችግሩ በሚያሳዝን መልኩ በመቀጠሉና በተፈጠሩ የግንኙነት ችግሮች ምክንያት የኢትዮጵያ መንግሥት የተወሰኑ የተመድ ኃላፊዎች አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ መጠየቁን አስታውቋል፡፡

ይሁን እንጂ አንዳንድ አገሮች የተመድ ፀጥታው ምክር ቤት ጉዳዩን እንዲያጤነው የጠየቁበት መንገድ ኢትዮጵያን ከፍተኛ ሁኔታ እንዳሳዘናትና ሁኔታው የኢትዮጵያን ሉዓላዊ መብት በመግፋት በውስጥ ጉዳይና አገራዊ ደኅንነት ላይ ግልፅ የሆነ ጣልቃ ገብነት እንደሆነ አስታውቋል፡፡

ስለሆነም የኢትዮጵያ መንግሥት የፀጥታ ምክር ቤት ጉዳዩን አስመልክቶ የሚያደርገውን ጥሪ ውድቅ ያደርገዋል ብሎ እንደሚያስብና የሰብዓዊ አቅርቦቱም በዚህ ምክንያት ይስተጓጎላል ብሎ እንደማያስብ በመግለጫው አመልክቷል፡፡

ሐሙስ መስከረም 20 ቀን 2013 ዓ.ም. የወጣው ትዕዛዝ በርካታ ኢትዮጵያውንን እያነጋገረ ሲሆን የተመድ ኃላፊዎችን ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ አበሳጭቷል፡፡

ለአብነትም ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ዕርዳታ ሕጎችን በሚጥሱ የውጭ ኃይሎች ላይ በምታደርገው ዕርምጃ ወደኋላ ልትል አይገባም ሲሉ የገለጹት የሰላም ሚኒስቴር አማካሪና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ሳሙኤል ተፈራ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

በተመሳሳይ በአሜሪካ የሚገኘው የሲቢኤሲ ጋዜጠኛዋ ሄርሜላ አረጋዊ 400 በላይ ዕርዳታ ጭነው ወደ ትግራይ የተላኩ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መኪኖች ትግራይ ቀርተውጦርነቱን ይበልጥ ለማቀጣጠል ጥቅም ላይ ሲውሉ እንደነበር በመጥቀስ፣ ለሁለት ወራት ያህል የትግራይ ታጣቂዎች ወደ አማራና አፋር ክልሎች በመግባት ሺዎችን ሲገድሉ ‹‹ለምን ዝም አላችሁ›› በማለት በቲውተር ገጿ አስታውቃለች፡፡ አክላም ‹‹በአፍሪካውያን ሕይወት መጫወት ይብቃ›› ብላለች፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ያወጣውን ትዕዛዝ ተከትሎ የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በሁኔታው መደንገጣቸውን ገልጸው፣ ሠራተኞቹ ወደ ሥራ እንዲመለሱ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በሌላ በኩል የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አንቶኒዮ ቢሊንከን፣ ለሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ወሳኝ ሚና ያላቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰባት የውጭ አገር ዜግነት ያላቸውን ሠራተኞች የኢትዮጵያ መንግሥት በአገር ውስጥ ጉዳይ ‹‹ጣልቃ ገብተዋል›› በሚል በ72 ሰዓታት ከአገር እንዲወጡ ተብሎ ትዕዛዝ መሰጠቱን አጥብቀው እንደሚያወግዙ በመግለጽ፣ መንግሥት ውሳኔውን እንዲቀይር በፅኑ እንጠይቃለን ብሏል፡፡

የኢትዮጵያን መንግሥት ውሳኔ ተከትሎ ዋይት ሐውስን ጠቅሶ አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካን ኤምባሲ በትዊተር ገጹ ባወጣው መግለጫ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ያሳለፈው ያልተጠበቀ ውሳኔ በከፍተኛ ሁኔታ የሚወገዝ መሆኑን አስታውቋል፡፡ በዚህም የፀጥታው ምክር ቤትና ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ የኢትዮጵያ መንግሥት በሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ሠራተኞች ላይ በሚያደርገው ክልከላ አፋጣኝ ዕርምጃ እንዲወሰድ ሲል ጠይቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ማስተካከያ

በሪፖርተር ጋዜጣ ረቡዕ ጥር 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ዕትም...

[ክቡር ሚኒስትሩ በወቅታዊ ፀጥታና ደህንነት ጉዳዮች ላይ የቀረበላቸውን ምክረ ሐሳብ እያደመጡ ነው]

ችግሩ ምን እንደሆነ በትክልል ለይተነዋል ግን ግን ምን? በይፋ መናገር አልነበረብንም። ለምን? ችግሩን...

የ12ኛ ክፍል የብሔራዊ ፈተና ውጤትና እንደምታው

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) የትምህርትን...

ንግድ ባንክ ከቪዛና ማስተር ካርድ ጋር ተደራድሮ ያስጀመረው የገንዘብ ማስተላለፊያ ቴክኖሎጂና ፋይዳው

ከውጭ ወደ አገር በሕጋዊ መንገድ የሚላክ ገንዘብ (ሬሚታንስ) መጠን...