የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ የተመደቡ ሰባት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሥራ ኃላፊዎች ላይ ‹‹Persona Non Grata›› ትዕዛዝ መስጠቱን ይፋ አድርጓል።
መሠረተ ቃሉ ላቲን የሆነው ‹‹Persona Non Grata›› የእንግሊዝኛ አቻው ‹‹Unwelcomed Person›› በተቀራራቢ የአማርኛ ትርጓሜው ደግሞ የማይፈለግ ወይም ተቀባይነት የሌለው ሰው እንደ ማለት ነው።
ነገር ግን የዓለም የውጭ ግንኙነት መርሆችን የሚደነግገውና አገሮች የሚገዙበት የቬና ኮንቬንሽን ውስጥ ከተቀመጡ የሕግ ተቀባይነት ካላቸው ሥነ ሥርዓቶች አንዱ ነው።
የኢትዮጵያ መንግሥት ሰባቱ የተመድ የሥራ ኃላፊዎች ከኢትዮጵያ ግዛት ለቀው እንዲወጡ ያስታወቀው ሐሙስ መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም. ሲሆን፣ ውሳኔው የሚመለከታቸው ሰባት የሥራ ኃላፊዎችም በ72 ሰዓታት ውስጥ ከኢትዮጵያ ግዛት ለቀው እንዲወጡ የሚያዝ ደብዳቤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለእያንዳንዳቸው በተናጠል እንዲደርሳቸው ማድረጉን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ሰባቱ የተመድ የሥራ ኃላፊዎች በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባታቸው ከኢትዮጵያ ግዛት ለቀው እንዲወጡ መወሰኑንም በይፋ አስታውቋል።
ከኢትዮጵያ ግዛት ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ከወጣባቸው የተመድ የሥራ ኃላፊዎች መካከል አንዷ በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ተወካይ የሆኑት ሚስ አዴሌ ኮድር ሲሆኑ፣ በኢትዮጵያ የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ተጠባባቂ ምክትል አስተባባሪ የሆኑት ሚስ ጋዳ አል ጣሂር ሙዳዊ፣ በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ አገልግሎት አስተባባሪና ቋሚ ተጠሪ ጽሕፈት ቤት የሰላምና ልማት አስተባባሪ የሆኑት ሚስተር ኪዌሲ ሳንስክሎቴም ትዕዛዝ ወጥቶባቸዋል።
ከተገለጹት በተጨማሪም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ኃላፊ ሚስተር ሳኢድ መሐሙድ ሔርሲ፣ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ አገልግሎት ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት የሰብዓዊ ድጋፍ ምክትል አስተባባሪ የሆኑት ሚስተር ግራንት ሊቴ፣ የዚሁ ተቋም ከፍተኛ ኮሚሽነር ቢሮ ባልደረባ የሆኑት ሶኒ ኦኒግ ቡላና የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚስ ማርሲ ቪጎዳ ትዕዛዝ ወጥቶባቸዋል።
ከኢትዮጵያ ግዛት ለቀው እንዲወጡ የተወሰነባቸው የሥራ ኃላፊዎች ውሳኔውን ለመፈጸም የተሰጣቸው የ72 ሰዓት የጊዜ ገደብ በአሁኑ ወቅት ተጠናቋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ውሳኔን ተከትሎ የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬስን ጨምሮ፣ የተለያዩ የአውሮፓ አገሮችና የአሜሪካ መንግሥት ባወጡት መግለጫ የኢትዮጵያን ውሳኔ አውግዘዋል።
‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት ሰባት የተመድ የሥራ ኃላፊዎች ከኢትዮጵያ ግዛት ለቀው እንዲወጡ መወሰኑን መስማቴ በእጅጉ አስደንግጦኛል፤›› ሲሉ ጉተሬስ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
በመግለጫው አክለው እንደተናገሩት፣ የተመድ የሰብዓዊነት አገልግሎት የሚመራው መሠረታዊ በሆኑት የገለልተኝነት፣ የሰብዓዊነትና ነፃነት መርሆችን ጠብቆ ነው፡፡
‹‹በኢትዮጵያ የተመደቡ የተመድ ሠራተኞች እነዚህን መርሆች ጠብቀው የሰብዓዊነት ድጋፎችን እያከናወኑ ስለመሆኑ ሙሉ እምነት አለኝ፤›› ያሉት ዋና ጸሐፊው፣ ‹‹ትዕዛዝ የወጣባቸው የተመድ ሠራተኞች በኢትዮጵያ የሰብዓዊነት ድጋፍ ተግባራቸውን እንዲቀጥሉ ይደረጋል በሚል እምነት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር እየተነጋገርን እንገኛለን፤›› ብለዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት ሰባት የተመድ የሥራ ኃላፊዎችን ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ማዘዙን አሜሪካ አጥብቃ ትቃወማለች፤›› ብሏል። በማከልም ከአገር እንዲወጡ የታዘዙት የተመድ የሥራ ኃላፊዎች በኢትዮጵያ እየተካሄደ ላለው የሰብዓዊ ዕርዳታ ወሳኝ ሚና እየተወጡ መሆኑን በመጥቀስ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ውሳኔውን እንዲሰርዝ ጥሪ አቅርቧል።
የአውሮፓ ኅብረት ሊቀመንበር በበኩላቸው የተመድ ዋና ጸሐፊ ያወጡትን መግለጫ እንደሚጋሩ በመግለጽ፣ በኢትዮጵያ ሚሊዮኖች ከፍተኛ የሰብዓዊነት ዕርዳታ በሚያስፈልጋቸው ወቅት የተመድ የዕርዳታ ሠራተኞችን ከአገር ማባረር ተቀባይነት የለውም ብለዋል። ‹‹የኢትዮጵያውያንን ሕይወት መታደግና ድጋፍ ለሚሹትም ድጋፍ ማድረግ የኢትዮጵያ መንግሥት ቀዳሚ ኃላፊነት ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በተመሳሳይ የእንግሊዝ መንግሥት በአዲስ አበባ በሚገኘው ኤምባሲው ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት ውሳኔውን በአፋጣኝ እንዲቀለብስ እንጠይቃለን፤››› ብሏል።
በአዲስ አበባ የሚገኘው የጀርመን ኤምባሲ በበኩሉ የተመድ ዋና ጸሐፊ ያወጡትን መግለጫ እንደሚጋራ በመግለጽ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ውሳኔውን እንዲቀለብስ ጥሪ አቅረቧል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ውሳኔ ሕጋዊነትና ፖለቲካዊ አንድምታ
ከትግራይ ክልል ግጭት ጋር በተያያዘ በክልሉ ለተፈጠረው ሰብዓዊ ቀውስ ድጋፍ እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ መንግሥት ለዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅቶች ፈቃድ የሰጠ ቢሆንም፣ መንግሥት የሰጠው ፈቃድ በርካታ ቢሮክራሲያዊ ሒደቶችን ማለፍ የሚጠይቅ በመሆኑ ፈጣን ድጋፍ ለተረጂዎች እንዳያቀርቡ እንደገደባቸው የተመድ የሰብዓዊነት ድጋፍ ሰጪ ኤጀንሲዎችን ጨምሮ ሌሎች ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅቶች በተደጋጋሚ ሲገልጹና ይህንን መሠረት አድርገውም በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ወቀሳ ሲሰነዝሩ ይደመጣሉ።
የኢትዮጵያ መንግሥት በተቃራኒው እነዚህ ድርጅቶች ከተቋቋሙበት ዓላማ ውጭ በትግራይ ክልል የሚገኙ ተዋጊ ኃይሎችን ይደግፋሉ የሚል ክስ ያቀርባል።
የፌዴራል መንግሥት ጦር ከትግራይ ክልል ከመውጣቱ አስቀድሞ አንድ ዓለም የዕርዳታ ድርጅት ሠራተኞች ከተፈቀደላቸው ቀጣና ውጪ ጥሰው በመሄዳቸውና በአካባቢው የነበሩ የፀጥታ ኃይሎች እንዲመለሱ የሰጧቸውን ትዕዛዝ ባለማክበራቸው፣ ለማስደንገጥ ያክል ተኩስ እንደከፈቱባቸው መታዘዙንና ተኩስ ሲከፈትም መቆማቸውን አንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለሥልጣን አስታውቀው ነበር።
ወደ ትግራይ ክልል ዕርዳታ ለማድረስ የገቡ ከ400 በላይ የጭነት ተሽከርካሪዎች ዕርዳታውን አቅርበው ለቀጣይ ጭነት መመለሳቸውን ማረጋገጥ የእነዚሁ ተቋማት ኃላፊነት ቢሆንም፣ ከገቡት ተሽከርካሪዎች ውስጥ ከክልሉ የወጡት በጣት የሚቆጠሩ መሆናቸውን በመግለጽ መንግሥት ዕርዳታ የማቅረቡን ኃላፊነት በወሰዱት ዓለም አቀፍ ተቋማት ላይ ወቀሳ እያቀረበ ነው።
ወደ ትግራይ ክልል ዕርዳታ ለማድረስ ገብተው ሳይመለሱ የቀሩት ተሽከርካሪዎችን በክልሉ ያለው ተዋጊ ኃይል ለግጭት ተግባር እየተጠቀመባቸው እንደሆነ መንግሥት ጥርጣሬውን ከገለጸ በኋላ፣ በአዲስ አበባ የሚገኘው የተመድ ቢሮ ተሽከርካሪዎቹ አለመመለሳቸው ሥጋት እንደፈጠረበት አስታውቋል። ይሁንና ተሽከርካሪዎቹ ለምን እንዳልተመለሱ ከመናገር ተቆጥቧል።
በአዲስ አበባ የሚገኘው የተመድ ቢሮ ሥጋቱን መግለጹን ተከትሎ ሕወሓት መግለጫ ያወጣ ሲሆን፣ በመግለጫውም በአዲስ አበባ የሚገኘው የተመድ ጽሕፈት ቤት ምክንያቱን ሳያጣራ ሥጋቱን መግለጹ ትክክል አይደለም በማለት አውግዟል።
በማከለም ተሽከርካሪዎቹ ዕርዳታውን ካደረሱ በኋላ መመለስ የሚገባቸው ቢሆንም፣ መንግሥት ለተሽከርካሪዎቹ የፈቀደው ነዳጅ ለአንድ ጉዞ ብቻ የሚበቃ በመሆኑ ለመመለስ እንደተቸገሩ ገልጿል። በተጨማሪም ዕርዳታውን የጫኑ ተሽከርካሪዎችን የሚዘውሩ አሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ ክልል ለመድረስ በርካታ የይለፍ ውጣ ውረዶች ያጋጠማቸው በመሆኑ፣ ከትግራይ ክልል ለመመለስ ፈቃደኛ አለመሆናቸውን በመግለጫው አስታወቋል።
ይህንን ተከትሎ የተመድ የሥራ ኃላፊዎች ተሽከርካሪዎቹ ከትግራይ መመለስ ያልቻሉት መመለሻ ነዳጅ ስላላገኙ እንደሆነ፣ ባለፈው ሳምንት ለተለያዩ የውጭ የመገናኛ ብዙኃን ገልጸዋል።
ለዚህም መንግሥትን በዋነኛነት ተጠያቂ አድርገዋል። ይህንን በይፋ ከተናገሩት መካከልም ባለፈው ሳምንት በጉዳይ ላይ ለአንድ የውጭ የመገናኛ ብዙኃን ቃለ መጠይቅ የሰጡት የተመድ የሰብዓዊ ገዳዮች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር የሆኑት ማርቲን ግሪፍዝ ይገኙበታል፡፡
ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት በሰባት የተመድ የሥራ ኃላፊዎች ላይ ‹‹Persona Non Granta›› በመባል የሚታወቀውን ትዕዛዝ በማሳለፍ፣ ከኢትዮጵያ ግዛት ለቀው እንዲወጡ ወስኗል።
ይህንን የኢትዮጵያ መንግሥት ትዕዛዝ አስከመልክቶ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ የውጭ ግንኙነት ባለሙያ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ትዕዛዝ በዓለም አቀፍ የውጭ ግንኙነትን በሚገዛው የቬና ኮንቬንሽን ማዕቀፍና መርሆች የሚፈቀድ እንደሆነ ይገልጻሉ።
የቬና ኮንቬንሽን አንቀጽ ዘጠኝ ላይ ‹‹Persona Non Granta›› በተመለከቱ የተቀመጡ ድንጋጌዎች፣ ማንኛውም አገር በግዛቱ ውስጥ የተፈቀደለትን የዲፕሎማሲ ተግባር በመጣስ ሲንቀሳቀስ የተገኘን የውጭ ዲፕሎማት የማባረር መብት እንደሚሰጡ ያስረዳሉ።
በዚህ ኮንቬንሽን አንቀጽ ሥር የተቀመጡ ሌሎች ድንጋጌዎች አንድን የውጭ ዲፕሎማት ከአገር ከማስወጣት ባለፈ፣ ለዲፕሎማሲ ሥራ ወደ ተመደበበት አገር ከመግባቱ አስቀድሞ የተመደበበት አገር ይህንኑ ድንጋጌ መጠቀም በሚያስችሉ ምክንያቶች ወደ አገር እንዳይገባ መከልከል እንደሚችልም ገልጸዋል።
በዚሁ የቬና ኮንቬንሽን አንቀጽ ሥር የተቀመጠው ሌላው ድንጋጌ ከተመደበበት የዲፕሎማሲ ተግባር ውጭ ተንቀሳቅሷል የተባለ ማንኛውም ዲፕሎማት፣ ወይም በዚሁ ማዕቀፍ ውስጥ የሚወድቅ የተመድ ባልደረባን ከአገር እንዲወጣ ያዘዘ መንግሥት ምንም ዓይነት ማብራሪያም ሆነ ምክንያት የመስጠት ግዴታ እንደሌለበት የሚደነግግ መሆኑን አስረድተዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግሥት ያሳለፈው ውሳኔ የሕግ ድጋፍ እንዳለውና ለዚህ ውሳኔ ያደረሰውን ምክንያትም መግለጽ እንደማይጠበቅበት፣ ይህ ቢሆንም የኢትዮጵያ መንግሥት ግዴታ ሳይኖርበት በቂ የሆነ አጭር ምክንያት መስጠቱን ገልጸዋል።
ይህ የኢትዮጵያ መንግሥት ውሳኔ ከሕግ አንፃር የቅቡልነት ጥያቄ ባይነሳበትም፣ ፖለቲካዊ ሥሌቱ የተጠና ካልሆነ ግን ፖለቲካዊ መዘዝ ሊያመጣ እንደሚችል አጠያያቂ አይደለም ይላሉ።
በተለይ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከትግራይ ክልል ቀውስ ጋር በተገናኘ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ማዘዛቸው፣ ማዕቀቡ ይመለከታቸዋል ከተባሉት መካከል በትግራይ ክልል ሰብዓዊ ዕርዳታ እንዳይደርስ ያስተጓጎሉ እንደሚሆኑ መጠቀሱ ሥጋቱ እንዲያይል ያደርገዋል ሲሉም ያክላሉ።
የኢትዮጵያ መንግሥት ሰባት የተመድ የዕርዳታ ሠራተኞች ከአገር እንዲወጡ ማዘዙ የአሜሪካ ማዕቀብን ማፋጠን ብቻ ሳይሆን፣ ማዕቀቡን ለመጣል የተቀመጠውን ዕርዳታን የማስተጓጎል ምክንያት ማሟላት እንደሆነ የሚገልጹ አሉ።
የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን ሲወስን ፖለቲካዊ ሥሌቱን ሠርቶና መዝኖ እንደሚሆን የተናገሩት የውጭ ግንኙነት ባለሙያው ግን በዚህ አይስማሙም። እንደ እሳቸው ገለጻ መንግሥት እዚህ ውሳኔ ላይ ከመድረሱ አስቀድሞ ሊመጣበት የሚችለው የውጭ ጫና ከሞላ ጎደል እንደተከሰተ ይገልጻሉ።
መንግሥት የተጠና በሚመስል ሁኔታ የተመድ የሥራ ኃላፊዎችን ብቻ ለይቶ ከአገር እንዲወጡ መወሰኑ፣ የውጭ ጫናውን እያደረሱበት የሚገኙ ምዕራባውያን መንግሥታት ቆም ብለው እንዲመዝኑ ሊያደርጋቸው እንደሚችል ያምናሉ።
በተለይ በአሁኑ ወቅት በሱዳን የተፈጠረው የሥልጣን ሽኩቻ የሱዳንን የሽግግር መንግሥት የሚደግፉት ምዕራባውያን ላይ ድንጋጤ እንደፈጠረ፣ ይህ ሥጋት ባለበት በኢትዮጵያ ላይ ጫናውን ማጠንከር በአፍሪካ ቀንድ ቀውስ ላይ ቤንዚን እንደ መጨመርና ጥቅማቸውን አሳልፎ እንደ መስጠት አድርገው ሊቆጥሩት እንደሚችሉ ገልጸዋል።
የአሜሪካ መንግሥት ባወጣው መግለጫ ግን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ውሳኔ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ያዘዙትን ማዕቀብ ከመጣል እንደማያዘናጋው አስታውቋል።
ሌላው ጉዳይ የኢትዮጵያ መንግሥት ውሳኔን አክብረው ሰባቱ የተመድ የሥራ ኃላፊዎች ከኢትዮጵያ ግዛት ባይወጡስ የሚለው ነው። ይህንን በተለመለከተ ሪፖርተር ያነጋገሯቸው የውጭ ግንኙነት ባለሙያው፣ ከአገር እንዲወጡ የታዘዙት የተመድ የሥራ ኃላፊዎች በተሰጣቸው ጊዜ ከአገር አለመውጣት እንደሚችሉ ገልጸዋል።
ነገር ግን ከተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ከተጠናቀቀ በኋላ በአገር ውስጥ የተገኙ እንደሆነ የኢትዮጵያ መንግሥት ግለሰቦቹን እንደ ዲፕሎማት ያለ መቁጠር መብት እንደሚኖረው፣ ለዲፕሎማት የሚሰጠው ያለ መከስስ መብትን እንደሚያጡ ጠቁመዋል። ይህም ማለት የኢትዮጵያ መንግሥት ሕግ ተላልፈዋል ብሎ ካመነ የማሰርና የመመርመር መብት፣ እንዲሁም ክስ የመመሥረት መብት እንደሚሰጠው አስረድተዋል።