ከአበባ ተረፈ ምርት የሚዘጋጅ ማዳበሪያ፣ የአበባ አምራቾችን የሰው ሠራሽ የማዳበሪያ ወጪያቸውን እስከ 33 በመቶ እንደሚቀንስላቸው ተገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ አበባ አትክልትና ፍራፍሬ አምራቾችና ላኪዎች ማኅበር ባለፈው ሐሙስ መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም. ባሰናዳው የውይይት መድረክ ላይ እንደተገለጸው፣ በርካታ የአበባ አምራቾች ከአበባ ምርት የሚገኝን ተረፈ ምርት በመጠቀም በሁለት ዓይነት መንገድ ማዳበሪያ በማዘጋጀት የማዳበሪያ ወጪያቸውን እየቀነሱ ነው፡፡
የማኅበሩ የቆሻሻ አወጋገድ መምርያ ኃላፊ አቶ ቶማስ ተክለሥላሴ እንዳመለከቱት፣ እንዲህ ዓይነቱ የማዳበሪያ ዝግጅት የአበባ እርሻዎቹ ለሰው ሠራሽ ማዳበሪያ የሚያወጡትን ወጪ በአማካይ እስከ 33 በመቶ እንዲቀንስላቸው አስችሏቸዋል፡፡ ይህም ማለት አንድ መቶ ኩንታል የሰው ሠራሽ ማዳበሪያ የሚጠቀሙ ከሆነ አንድ ሦስተኛ የሚሆነውን የማዳበሪያ ወጪያቸውን ከሚያዘጋጁት ማዳበሪያ መሸፈን መቻላቸውን አመልክተዋል፡፡ አንዳንድ እርሻዎችም ይህንን ማዳበሪያ ለራሳቸው ከመጠቀም ባሻገር፣ በአካባቢያቸው ላሉ ገበሬዎች እየሰጡ ስለመሆኑ ይኸው የአቶ ቶማስ ማብራሪያ ያመለክታል፡፡
እነዚህ የአበባ ተረፈ ምርቶች በምርት ሒደት ወቅት የሚወዳድቁ የአካባቢው ቅጠሎች፣ ምርቱን ለገበያ ለማቅረብ በማሸግ ሥራ በሚሠራበት ጊዜ የሚወዳድቁና የሚተራርፉ ምርቶች ናቸው፡፡ ይህም የአበባው ግንድንና ቅጠልን ሁሉ ያጠቃለለ መሆኑን የገለጹት አቶ ቶማስ በየቀኑ ከእርሻው ከፍተኛ መጠን ያለውን ተረፈ ምርት ያስወግዳሉ፡፡ አሁን ግን እነዚህን ተፈረ ምርቶች አበስብሶ ተፈጥሮአዊ ማዳበሪያ እንዲዘጋጅበት በማድረግ እንዲጠቀሙባቸው እየተደረገ ነው፡፡
ይህ ተፈጥሮአዊ ማዳበሪያ በሁለት መልክ የሚሠራ መሆኑን የገለጹት አቶ ቶማስ፣ አንደኛው ተረፈ ምርቱን ፈጭቶ በማበስበስ በመደብ በማከቸትና ባክቴሪያ በመጠቀም በቶሎ እንዲበሰብስ በማድረግ የሚዘጋጅ ነው፡፡
ሁለተኛው ደግሞ የመሬት ትልን ተጠቅሞ የከብት እዳሪን በማከል ጭምር የሚዘጋጅ ፈሳሽ ማዳበሪያ ነው፡፡ ይህንን በሰፊው በተገበሩ እርሻዎች ላይ ለማዳበሪያ የሚያወጡትን መቀነስ የቻሉ በመሆኑ ሌሎች እርሻዎችም በተመሳሳይ መንገድ እንዲጠቀሙ የሚያስችል አሠራር ተዘርግቶ እየተሠራበት ይገኛል፡፡
ባለፈው ሐሙስም እንዲህ ባለው ማዳበሪያ በመጠቀም ውጤት ያገኙ የአበባ እርሻዎች ተጎብኝተዋል፡፡ ከመስክ ጉብኝቱ መረዳት እንደተቻለውም አንዳንድ የአበባ እርሻዎች ይህንን ማዳበሪያ ለአካባቢው ገበሬዎች እያቀረቡ ስለመሆኑ ነው፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በሰው ሠራሽ ማዳበሪያና ሌሎች ለእርሻው ጥቅም የሚውሉ ምርቶች ምክንያት የተበከለ ውኃን በማከም መልሶ የሚጠቀሙ እርሻዎች ቁጥር እያደገ መምጣቱም ተገልጿል፡፡ እስካሁን ባለው መረጃም 31 የሚሆኑ የአበባ እርሻዎች የተበከለ ውኃን በማከም ዳግም ጥቅም ላይ እንዲውል የሚያስችል ቴክኖሎጂ በመትከል እየሠሩበት እንደሆነና አስሩ ደግሞ ቴክኖሎጂውን እየተከሉ መሆኑን ከተሰጠው ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በአበባና አትክልትና ፍራፍሬ ምርት ላይ ከተሰማሩ እርሻዎች ውስጥ ወደ 86 የሚሆኑት በማኅበሩ ሥር የሚገኙ ናቸው፡፡ የአትክልት፣ የአበባና የፍራፍሬ ምርት በ2013 በጀት ዓመት ከቡናና ማዕድን ምርት ቀጥሎ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ያስገኘ ዘርፍ ሲሆን፣ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ500 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ አስገኝቷል፡፡