በአትሌቲከሱ ዘርፍ የሜዳ ተግባራትን ጨምሮ ከመካከለኛ ርቀት እስከ ማራቶን ታላላቅና ስመ ገናና አትሌቶችን በማፍራት የምትታወቀው ኬንያ፣ ወርልድ አትሌቲክስ በ2025 የሚያካሂደውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለማዘጋጀት ጥያቄ አቀረበች፡፡
ቢቢሲ ስፖርት የኬንያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ጃክሰን ቱዊን ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ፣ ኬንያ ወርልድ አትሌቲክስ በ2025 የሚዘጋጀውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ማዘጋጀት የሚስችላትን ሰነድ አቅርባለች፡፡
ኬንያ ከዚህ ቀደም የዓለም አገር አቋራጭን ጨምሮ ዕድሜቸው ከ20 ዓመት በታች የዓለም ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮናን አዘጋጅታ በስኬት ያስተናገደች አገር ስለመሆኗ ጭምር ቢቢሲ ሰፖርት በዘገባው ጠቅሷል፡፡
ኬንያ ሻምፒዮናውን ለማዘጋጀት ብቃቱም ሆነ አቅሙ እንዳላት፣ ወርልድ አትሌቲክስም ይህን ከግምት አስገብቶ በአፍሪካ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ ሻምፒዮናውን ለማዘጋጀት ጊዜው አሁን ስለመሆኑ ጭምር ቢቢሲ ፕሬዚዳንት ቱዊን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ የአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን (ሲኤኤ) ፕሬዚዳንት ሐማድ ካልካባ በበኩላቸው፣ ሻምፒዮናውን አፍሪካ ማዘጋጀት እንደሚገባት መናገራቸው ዘገባው አመልክቷል፡፡
አትሌቲክሱን በበላይነት የሚያስተዳድረው ወርልድ አትሌቲክስ ኬንያ ያቀረበችውን ሰነዱን ተመልክቶ ውሳኔውን ከ2022 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በኋላ እንደሚያሳውቅ ተነግሯል፡፡
አሜሪካዊ የቀድሞ ኦሊምፒክ አሸናፊ ጀስቲን ጋትሊን፣ በኬንያ ናይሮቢ የሚገኘው ካሳራኒ ስታዲየም የዓለም አቀፉን አትሌቲክስ ሻምፒዮና የማስተናገድ አቅም እንዳለው መናገሩ በዘገባው ተጠቅሷል፡፡