ጋሻው አበዛ (ዶ/ር) በሜሪላንድ ቶውሰን ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር ሲሆኑ የታላቅ አፍሪካ ሩጫ ዳይሬክተር ናቸው። ጋሻው በዓለም ዙሪያ ካሉ ድርጅቶች ጋር በስፖርት ቢዝነስ ጋር በተያያዘ በማማከር ሥራ ይታወቃሉ፡፡ ከስፖርት ቢዝነስ፣ ከስፖንሰርሺፕና ከማኀበራዊ ሚዲያ ጋር በተያያዘ በርካታ መጻሕፍትን በጋራ አዘጋጅተዋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ በስፖርት አስተዳደርና ግብይት ጉዳዮች ስኬታማ ጊዜን አሳልፈዋል፡፡ በቅርቡም በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ላይ ከሚሳተፉ ክለቦች ጋር መዋቅራዊ፣ የገቢ መጠን ማሳደግና በሒደት ክለብን እንዴት ሕዝባዊ ማድረግ የሚቻልበትን መንገድ ጋር በተያያዘ እያማከሩ ይገኛሉ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በጋራ እየሠሩ እንደሚገኙና በቅርቡም ይፋዊ ውል እንደሚያስሩ ይጠበቃል፡፡ በሌላ በኩል በመጪው ጥቅምት ወር በአሜሪካ በሚከናወነው ዓመታዊው የታላቁ አፍሪካ ሩጫ ውድድር ላይ በርካታ ተሳታፊዎች እንደሚካፈሉ ይጠበቃል፡፡ ዳዊት ቶሎሳ ከጋሻው አበዛ (ዶ/ር) ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
ሪፖርተር፡ – በአሜሪካ በየዓመቱ በሚሰናዳው የታላቅ አፍሪካ ሩጫ በርካታ ኢትጵያውያን ይሳተፋሉ፡፡ ስለ ታላቅ አፍሪካ ሩጫ አጀማመር ቢያብራሩልን?
ዶ/ር ጋሻው፡- የታላቅ አፍሪካ ሩጫ መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ነው፡፡ የዓመታዊ ውድድሩ መጀመር ምክንያት የሆነው በአፍሪካ ስኬታማ የሆኑ አትሌቶች የተጓዙበትን መንገድ መነቃቃትን ስለፈጠረ ነው፡፡ በዋሽንግተን ዲሲ በሚዘጋጀው የ5 ኪሎ ሜትር ዓመታዊ ሩጫ ላይ በርካታ ተሳታፊዎች ይካፈላሉ፡፡ የዚህ ዓመት ውድድርም ጥቅምት 6 ቀን በዋሽንግተን ዲሲ በሄንስ ፖይንት ኢስት ፖቶማክ ፓርክ ለሦስተኛ ጊዜ ይካሄዳል፡፡ በውድድሩ ማኅበረሰብን ማቀራረብ፣ የአዲስ ትውልድ ልጆችን የአገር ቤት ባህላቸውን እንዲያወቁ ማድረግ ግብ ያደረገ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ውድድሩና አጠቃላይ ጉዞው ምን ይመስላል?
ዶ/ር ጋሻው፡- አጀማመሩና እስካሁን ያለው ሒደት አበረታች ነው፡፡ የታላቅ አፍሪካ ሩጫ ለቤተሰብ ተስማሚና አስደሳች ክስተት ነው። ተሳታፊዎች በደስታ እየተካፈሉበትና ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣ ውድድር ነው፡፡ ተሳታፊዎች በኩነቱ ለመካፈል ሁለት ዓይነት አማራጭ አላቸው፡፡ አንደኛው በክሬዲት ካርድ አማካይነት መመዝገብ የሚቻል ሲሆን ሌላኛው ለተመዝጋቢዎች ተደራሽ እንዲሆን በተለያዩ መደብሮችና ሱቆች እንዲገኝ አመቻችተናል፡፡ የምዝገባ ቋቱም ቲሸርት፣ የውድድር ቁጥሮችና የውድድር መረጃን የያዙ ፓኬጆችን ከመደብሮቹ ማግኘት ይችላል፡፡ በቀደሙት ዝግጅቶቻችን ደራርቱ ቱሉ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ የዲባባ ቤተሰብ፣ ብርሃኔ አደሬ፣ ሚሊዮን ወልዴ፣ ፋጡማ ሮባና ሌሎችን በክብር እንግድነት ማስተናገድ ችለናል። ኃይሌ ገብረሥላሴ በአገር ቤት የጀመረው የታላቁ ሩጫ ሕዝባዊ ውድድር ለእኛ ትልቅ አርዓያ ሆኗል፡፡ ለዚህም ትልቅ ክብር አለን፡፡
ሪፖርተር፡- በሩጫው ከኢትዮጵያውያን ባሻገር ማን ይሳተፋል? እንዲሁም ተሳታፊዎች በውድድሩ ምን ዓይነት ተሳትፎ ማድረግ ይችላሉ?
ዶ/ር ጋሻው፡- በአፍሪካ ታላቅ ሩጫ ለመሳተፍ ዕድሜ፣ ዘርና የትውልድ አገር ሳይለይ ሁሉም በደስታ መሳተፍ ይችላል፡፡ ተሳታፊዎች በዓለም ታዋቂ ከሆኑ አትሌቶች ጋር ተሠልፈው በ5 ኪሎ ሜትር ርዝመት ባለው የስፖርት ፌስቲቫሎች ላይ የመሳተፍ ዕድል ይኖራቸዋል። ልጆች በ1 ኪሎ ሜትር ሩጫ ውስጥ መመዝገብና መሮጥ/መራመድ ይችላሉ። ዝግጅቱ በአገራችን ሩጫ በሚሊዮኖች ከሚቆጠረው እሴት የመነጨ በመሆኑ ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን አንድ ላይ ሆነው በድምቀት አብረው ለማክበር ሲመለከቱ ማየት እጅግ አስደናቂ ነው። የሩጫው መፈክርም ‹‹የተሻለ አብሮነት›› ይሰኛል፡፡
ውድድሩ ከሦስት ዓመት በፊት እ.ኤ.አ. 2019 የመጀመሪያው ታላቁ አፍሪካ ሩጫ በስኬት አልፏል፡፡ ሁለተኛው በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ማከናወን ስላልተቻል በበይነ መረብ አማካይነት ታዋቂ አትሌቶች በተገኙበት ተከናውኗል፡፡ ተሳታፊዎችም ካሉበት ቦታ ሆነው በኮቪድ-19 አስፈሪ ጊዜያት ሲያሳልፉ መቆየታቸውን ተከትሎ መንፈሳቸው እንዲነቃቃ ለመርዳት በዓለም ዙሪያ ካሉ ኢትዮጵያውያንና ታዋቂ አትሌቶች ጋር ተቀላቅሎ የመሳተፍ ዕድል አግኝተዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ከውድድሩ ጎን ለጎን የበጎ አድራጎት መርሐ ግብር በማሰናዳት በኢትዮጵያ የልብ ማዕከልን ለመገንባት እየተንቀሳቀሳችሁ ትገኛላችሁ፡፡ ስለ በጎ ሥራዎ ቢያብራሩልን?
ዶ/ር ጋሻው፡- ከዚህ ቀደም ድርጅታችን በየዓመቱ ከሕፃናትና ትምህርታዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዝ በበጎ አድራጎት ላይ ለተሰማሩ ተቋማት ድጋፍ ያደርጋል፡፡ ድጋፉም ከውድድሩ ዝግጅት ከሚገኝ ገቢ ተቀንሶ የሚደረግ ነው፡፡ በዚህ ዓመት ገቢው በኢትዮጵያ ለሚገነባው የልብ ማዕከል ለማሰባሰብ ታቅዷል፡፡ በዚህ ረገድ፣ በየዓመቱ የትኛውን የሰብዓዊ ድጋፍ ላይ የተሰማራ ድርጅት መደገፍ እንዳለበት የሚወስነው ቦርዱ ነው።
ሪፖርተር፡- የታላቅ አፍሪካ ሩጫ ሕዝባዊ ውድድር ከማድረግ ባሻገር ታዋቂ አትሌቶችን የማሳተፍ ዕቅድ አለው?
ዶ/ር ጋሻው፡- ለጊዜው የዚህ ውድድር ዋና ዓላማ ኢትዮጵያውያንን አንድ ላይ ማሰባሰብና አዲሱን ትውልድ ከባህላቸው ጋር ማስተዋወቅ ነው። በውድድሩ ውስጥ መሳተፍ ብቻ አይደለም፡፡ ተሳታፊው እርስ በርስ ተቀራርቦ የቤተሰብ ስሜትን መፍጠር ግቡ ያደረገ ነው፡፡ በአሜሪካ የሚኖሩ በርካታ የዓለም ሻምፒዮናና የኦሊምፒክ ተወዳዳሪዎች አሉ። በዚህ ዓመት ለእነሱ የተዘጋጀ ልዩ ዝግጅት ተሰናድቷል። ወደፊትም በውድድሩ ውስጥ ታዋቂዎችን ጋብዞ ለማወዳደር አቅደናል።
ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከሚሳተፉ ክለቦች ጋር በተለያዩ ጉዳዮች እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ክለቦቹን በምን መንገድ ነው የሚረዷቸው?
ደ/ር ጋሻው፡- በቅርቡ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከሚሳተፉት ፋሲል ከነማ፣ ባህር ዳርና ከሌሎች ክለቦች ጋር መሥራት ጀምረናል። በተጨማሪም በቅርቡ ከሌሎች ክለቦች ጋር ለመሥራት እየተነጋገርን ነው። ዋናው ሥራችን የክለቡን አወቃቀሩ፣ የገቢ ምንጩ ማሳደግ፣ የሰው ኃይልን ማጠናከርና ክለቦቹን ሕዝባዊ መሠረት የማስያዝ ላይ ትኩረት አድርገን እየሠራን እንገኛለን፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ እየሠራን ነው። በቅርቡም ተመሳሳይ ሥራዎች ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር ለመሥራት በይፋ የውል ስምምነት እንፈራረማለን፡፡
ሪፖርተር፡- በኢ–ስፖርት ንግድና ግብይት ላይ ያተኮሩ የሁለት መጻሕፍት ተባባሪ ጸሐፊና የአንድ መጽሐፍ ተባባሪ አርታኢ ነዎት። ስለ መጽሐፎቹ ቢገልጹልን?
ዶ/ር ጋሻው፡- መጽሐፎቹ በኢ–ስፖርቶች ላይ ትኩረታቸውን ያደረጉ ሲሆን አንደኛው ‹‹ኢ–ስፖርት በንግድና ኅብረተሰብ ላይ የሚያሳድሩት ተፅዕኖዎች›› እንዲሁም ሁለተኛው ‹‹የስፖርት ስፖንሰርሺፕ ግንዛቤዎች›› በሚል ርዕስ ስለስፖንሰርሺፕ የተዘጋጁ ናቸው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚያተኩር ሲሆን፣ ‹‹ማኅበራዊ ሚዲያ በስፖርት ላይ፣ ንድፈ ሐሳብና ተግባሩ›› የተሰኘ ነው፡፡ የስፖርት ስፖንሰርሺፕ ብዙውን ጊዜ እንደ ስጦታ ሆኖ ይታያል፡፡ ነገር ግን በተቃራኒው ስፖንሰርሺፕ ንግድ ነው። ተማሪዎቼን ከአንደኛ ዲግሪ፣ ከድኅረ ምረቃ እስከ ዶክትሬት ትምህርት ደረጃ ለመርዳት እነዚህን መጻሕፍትን እጠቀም ነበር። በቅርቡ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ተወያይተን ለኢትዮጵያ የሚስማማውን የስፖርት ግብይት የሚመለከት መጽሐፍ ለማዘጋጀት እየተንቀሳቀስን እንገኛለን፡፡
ሪፖርተር፡- የታላቅ አፍሪካ ሩጫ ቀጣዩ ዕቅድ ምንድነው?
ዶ/ር ጋሻው፡ ቀጣዩ ዕቅዳችን ታላቁን የአፍሪካ ሩጫ በአሜሪካ ውስጥ ባሉ የተለያዩ ግዛቶች መውሰድና ሕዝባችንን አንድ ላይ ለማሰባሰብ እንደ መድረክ መጠቀም ነው።