Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርየአዲስ አበባ ጉዳይ ከመቼውም በላይ ይመለከተናል!

የአዲስ አበባ ጉዳይ ከመቼውም በላይ ይመለከተናል!

ቀን:

በንጉሥ ወዳጅነው

አዲስ አባባ በታሪኳ ለመጀመርያ ጊዜ እንስት ከንቲባ አግኝታለች፣ ወ/ሮ አዳነች አቤቤን፡፡ በእርግጥ ባለፉት ወራት ምንም እንኳን በመዲናዋ ምክር ቤት ተመርጠው ባይሆንም፣ በምክትል ከንቲባነት ውስንነቶቹ እንደተጠበቁ ሆነው አዲስ አባባን በሚያስመሠግን ደረጃ መምራታቸው በተለያዩ አስተያየት ሰጪዎች ሲነገር ሰንብቷል፡፡

አገሪቱ የቆየችበት የለውጥ ማግሥት ነውጥና የፖለቲካ ምስቅልቅል፣ መዲናዋ ቀስ በቀስ አሳድጋው የነበረው ከፍተኛ የማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ፍላጎት መናርና መዋቅሩን ለዓመታት እግር ከወርች አስሮት የቆየው የመልካም አስተዳደር ዕጦትና ሌብነት በሚፈለገው ደረጃ ለመምራት አስችሏቸዋል ማለት ግን አይቻልም፡፡ የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት ፈተናውም ቀላል አልነበረም፡፡

- Advertisement -

ከመሬትና ከመንግሥት ቤቶች፣ ከገቢዎችና ጉምሩክ፣ ከመንግሥት ገዥ፣ ሽያጭና የአገልግሎት ኪራይ፣ እንዲሁም ከማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት አንፃር የሚታዩ የሕዝብ ቅሬታዎችና የዘረፋ በሮች በሚገባ ተዘግተው ነበር ማለትም ራስን እንደማታለል ይቆጠራል፡፡ እናም ስለትናንት ሳይሆን ስለነገ ለማሰብ አዲስ አባባን ወደ ላቀ ምዕራፍ የሚያሸጋግር አመራርና መንግሥታዊ መዋቅር እንዲገነባ መመኘት ብቻ ሳይሆን፣ ከወዲሁ ለማስታወስ ነው ይኼንን ጉዳይ የማነሳው፡፡

ዛሬ ከአገራችን አልፋ ለአፍሪካ ኅብረት መቀመጫና ለዓለም የዲፕሎማቲክ ከተማነት የበቃችው አዲስ አበባ ከ138 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረች ነች፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን እንደ እነ ኒውዮርክና ብራሰልስ ካሉ ዓለም አቀፍ ከተሞች ጋር የምትስተካከልበት የዲፕሎማቲክ ማዕከልነቷ ሲነገር የቆየ ነው፡፡ ምንም እንኳን ከለውጡ ወዲህ ደብዘዝ ያለ ደረጃ ላይ ያለ ጉዳይ ቢሆንም፣ ዞሮ ዞሮ አዲስ አባባ የአፍሪካ እንብርት መዲና ነች፡፡

አዲስ አበባ ከተማ ተመሠረተች የሚባለው በ1886 ዓ.ም. አፄ ምኒልክ ከእንጦጦ ወርደው ከሠፈሩበት ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ ለዛሬዎቹ አሮጌ መንደሮች መነሻ የሆኑትም የምኒልክ ሹመኞችና የጦር መሪዎች፣ ወታደሮችና ተከታዮቻቸውን ይዘው ድንኳኖቻቸውን የተከሉባቸው ሥፍራዎች ናቸው፡፡ ከዚያ ወዲህ የተስፋፉት አብዛኞቹ አዳዲስ ሠፈሮችም ትንሽ የማይባሉት በደርግ 17 ዓመታት፣ ባለፉት ሰላሰ ዓመታት ደግሞ በስፋት ከከተማዋ ማስተር ፕላንም አልፈው ከአጎራባች ወረዳዎች መሬት እያካተቱ የተለጠጡ ናቸው፡፡ ለዚህም ነው ዛሬ መዲናዋ 11 ክፍላተ ከተሞችንና 121 ወረዳዎችን ይዛ ተንጣላ የተገኘችው፡፡

ከኢትዮጵያ ፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ እውነታ አንፃር አዲስ አባባ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ማዕከል ብቻ ሳትሆን የጋራ ቤታቸው ነች፡፡ መላው የአገሪቱ የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች መቀመጫና የፖለቲካ ኢኮኖሚው ውሳኔ ምንጭ መሆኗ ብቻ ሳይሆን፣ በምጣኔ ሀብትና ፋይናንስ ረገድም እስከ 65 በመቶ የሚሆነው የአገሪቱ የገንዘብ ዝውውር የሚንቀሳቀሰው በዚህችው ታሪካዊ ከተማችን ነው፡፡ የምድርና የአየር ትራንስፖርት ማዕከልነቷም የታወቀ ነው፡፡

ከእነዚህና ሌሎች በርካታ እውነታዎች አንፃር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች ብቻ ሳይሆኑ፣ አሁን የሕዝብ ኃላፊነት የተሸከመው መላው ተሿሚና መንግሥታዊ መዋቅር የወደቀበት ኃላፊነት ግዙፍና ከፍተኛ ነው፡፡ አዲስ አባባ ወደ ሜትሮፖሊቲያን ከተማነት እያደገች የምትሄድ እንደ መሆኑ ከሰላምና ደኅንነት አንስቶ፣ በአጠቃላይ የማኅበራዊና የመሠረተ ልማት፣ እንዲሁም ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚውንና ዲፕሎማሲውን አቀላጥፎ የሚከወንባት መሆንና አዲስ ምዕራፍ የሚጀመርባት መሆን አለባት፡፡

እነዚህን ወሳኝ ተግባራት በአመርቂ ሁኔታ ለመፈጸም የፌዴራሉ መንግሥትም ሆነ ሁሉም ክልሎች፣ እንዲሁም ሕዝቡ አጋር መሆን አለባቸው፡፡ ከልማትና ከማኅበራዊ ደኅንነት አኳያ ደግሞ በተለይ ኦሮሚያ ክልልና ፊኒፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን የተሳለጠና የተቀናጀ አሠራር ውስጥ ሊገባ ግድ ይለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ እስከ 5.5 ሚሊዮን ሕዝብ የሚደርስ ነዋሪ እንደያዘች ሲገመት፣ ከሞላ ጎደል ከመላው የአገሪቱ አካባቢዎች በታሪክ አጋጣሚ የተሰባሰቡ ዜጎችን እንዳቀፈች ይታመናል፡፡ በዚህም ምክንያት ባለፉት 30 ዓመታት በአገር ደረጃ ከተዘረጋው የዘውግ ፌዴራሊዝም አንፃር እንኳን፣ ከየትኛውም የአገሪቱ አካባቢ በተለየ ኅብረ ብሔራዊነትን ተላብሳ፣ ዜጎች ተሳስበውና ተረዳድተው በጋራ ቤትነት የሚኖሩባት መሆኗን ማጠናከር የተግባራቱ ሁሉ ቀዳሚ መሆን አለበት፡፡

ለዚህ ደግሞ በተጨባጭ አመራሩ ከመንደርና የማንነት ትርክት እየወጣ፣ በጠንካራ አገራዊነትና ሕዝባዊነት መንፈስ መረባረብ ነው የሚጠበቅበት፡፡ በወሳኝ ቦታዎች ላይ የሚመደቡ አመራሮችም ሆኑ ሙያተኞች፣ ሊመራቸው የሚገባው ብቃትና ችሎታ ወይም ተነሳሽነት እንጂ የማንነት መቧደን መሆንም የለበትም፡፡ ያ እምብዛም ያልጠቀመ ሽርክና በሕወሓት/ኢሕአዴጉ የሁለት አሠርት ተኩል የሥራ ዘመኖች እንዴት ያለ ጥገኛ አመራር፣ ኪራይ ሰብሳቢ፣ ንፋስ አመጣሽ ባለሀብት፣ ጉዳይ ገዳይና ደላላ፣ ነውረኛ ሕገወጥ የመሬት ወራሪና መሰል ኃይል ሰማይ ምድሩን ሞልቶት እንደነበር አንዘነጋውም፡፡ 

ከዚህ አንፃር በቀደሙት የመዲናዋ አስተዳደር ካለ በቂ ምትክ የተነሱና የተፈናቀሉ የአጎራባች አርሶ አደሮችን ለማገዝና ለማካካስ የተደረገው ሙከራ መልካም ሆኖ፣ እስካሁን ተጠረቃቅመው ከታዩ ችግሮች ወጥቶ የአንድ አገር፣ የጋራ ከተማና ዋና መዲና በሚመራበትና በሚተዳደርበት መንፈስ ዜጎች በፍትሐዊነትና በእኩልነት መርህ እንዲጠቀሙባትና ግዴታቸውንም እንዲወጡ የማድረጉ ሥራ ለነገ ሊባል የሚችል አይደለም፡፡ ይኼ ደግሞ የአዲሱ አመራር የፖለቲካ አስኳል ትኩረት ሊሆን ግድ ነው፡፡

በሕገ መንግሥትና በቻርተሩ መሠረት የነዋሪዎቿን የጋራና የተናጠል ጥቅም የምታስከብር፣ ለአጎራባች አርሶ አደሮችም ሸክም ሳትሆን አጋር የምትሆን፣ ሕጋዊነት፣ እኩልነትና ፍትሐዊነት የሚንፀባረቁባት መዲና የማድረጉ ጉዳይ የአሁኑና የመጪው ትውልድ ከፍተኛ ኃላፊነት ነው፡፡ ይኼ ደግሞ በጠንካራ መሠረት ላይ እንዲጀመር ጥረት መደረግ ያለበት ባለፈው ሳምንት በተመሠረተው አዲሱ ምክር ቤት መሆን አለበት፡፡

አዲስ አባባ ለረዥም ዘመናት የአገሪቱ ማዕከላዊ መንግሥት ሀብት፣ ዕውቀትና ቴክኖሎጂ የፈሰሰባት ምድር መሆኗን ከላይ ጠቅሻለሁ፡፡ በውስጧ ያሉ ሕዝቦች ከራሷ አልፈው በየትኛውም ዓለም ለዘመናት ሠርተው ለልጅ ልጅ እያስተላለፉ ያቆዩትን ያሳደጉት ከፍተኛ ሀብትም የያዘች መዲና ነች፡፡ እናም አሁን የሚያስፈልገው የዜጎችን የሀብት ዋስትና በማጠናከር እንደ አገርም ሆነ በመዲናዋ በግለሰቦች የተከማቸን ሀብት ወደ ላቀ ጥቅም፣ ወደ ሰፊ ሥራ ዕድልና አገራዊ ቱሩፋትነት ማሳደግ እንጂ እንዲቀመጥና እንዲሸሽ ማድረግ አይደለም፡፡

ወደ አዲስ ምዕራፍ ለመሻገር የሚቻለውም ያለፈውን ብልሽት አርሞ ወሳኝ የፖለቲካ ኢኮኖሚ አስተዳደር፣ ለተጠያቂነትና ለግልጽነት አርዓያ የሆነ መዋቅር፣ ብሎም የሰላም ዋስትና የመሆን የፀጥታና ፍትሕ አካል በማቆም ነው፡፡ ይኼ ደግሞ በአገር ደረጃ ላይ መረጋገጡም ግድ ቢሆንም፣ ለአዲስ አባባ ልዩ ትርጉም የሚሰጠው እንደሆነ ሊዘነጋ አይገባም፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን በወንጀልም ሆነ በግፍ ከሕዝብ የተዘረፈ ሀብትና ንብረት ካለም ሕግና ሥርዓትን ተከትሎ ለሕዝብ ጥቅም እንዲውል መደረጉ ቸል መባል የለበትም፡፡

አዲስ አበባ ወደ ላይ የመመዘዝ (ፎቅ የመሆን) ዕድገቷ ከዛሬ አሥራ አምስት ዓመታት ወዲህ ጀምሮ ጥሩ ዕርምጃ አሳይቷል ቢባልም፣ በዚያው ልክ ባለቤት አልባ ፎቆች ሳይቀር እንደ እንጉዳይ የበቀሉባት የሕገወጥነት መፈንጫ ሆና ነበር የቆየችው፡፡ ይህ እውነታ ከዚህ ቀደምም ትግል ሊደረግበት ተሞክሮ ያለ ውጤት የቀረው ደግሞ፣ በመንግሥታዊ መዋቅሩ ብልሽትና በአሻጥር እንደነበር ሁሉም የሚፈርደው ነው፡፡ ይኼ አሁን ላይ ይበልጥ ሊስተካከል ግድ ይለዋል፡፡

ምናልባት ለመዲናዋ ዕድገት መጓተትም ሆነ የኑሮ ውድነት መባባስ ቁልፍ የችግር ምንጭ የሆነው የመሬትና የቤት ባለቤትነት ጉዳይ፣ ከለውጡ ወዲህም ቢሆን እዚህ ግባ የሚባል ውጤት እንዳልነካው ይታወቃል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ የቀደመው ብልሽትና መጥራት ያለባቸው ጉዳዮች መብዛት ነው ቢባል እንኳን አንድ ቦታ ላይ መቋጫ ሊያገኝ ግድ ነው፡፡

ዜጎች ተደራጅተውም ሆነ በተናጠል ከመንግሥት በሊዝም ሆነ በሌላ መንገድ ቦታ ገዝተው ቤት መሥራት ካልቻሉ፣ ጥገኞች የሚያሾሩት የመሬት ንግድ በከፍተኛ ጣራ መንገሡ አይቀሬ ነው፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት እንደታየው ያለ የግብይቱ ያዝ ለቀቅም ሆነ የጥቂቶች መሬት ሻጭነትና የብዙኃኑ ግራ መጋባትም የሚያዛልቅ አይደለም፡፡ መሬት ላይ ያለውን አንዳንድ አመራርና ባለሙያ ከገባበት ዘረፋና ውንብድና እንዳላወጣውም ሕዝቡ በአደባባይ እስከ መናገር ደርሷል፡፡

መሬቱ በዚያም በዚህም ቢገኝም ግንባታን ለማከናወን እንደ ሲሚንቶ፣ ብረት፣ ቆርቆሮና መሰል ግብዓቶች እጥረትና የገበያ ብልሽት ከነገሠ ችግሩን መቅረፍ አይቻልም፡፡ ስለዚህ እንደ ዘይትና ስኳር ብቻ ሳይሆን ከዚያም በላይ የኮንስትራክሽን ዘርፉን እንከኖች ማከም፣ ለአጠቃላይ የመዲናዋ ዕድገት ወሳኝ ዕርምጃ ነው፡፡ ስለዚህ አዲሱ አስተዳደር ቀውስ ለማስቀረት የወቅታዊ ሕዝብ ንቅናቄ ሥራዎች ወጥቶ በተጠናና ዘላቂ ብልፅግናን ዕውን በሚያደርግ ዘርፉን መምራት ይጠበቅበታል፡፡

እዚሁ ላይ መነሳት ያለበት ጭብጥ መዲናዋ የኑሮ ውድነት፣ የቤት እጥረት፣ የሥራ ዕጦት፣ መሠረታዊ የፍጆታ ግብዓቶች እጥረት፣ የመሠረተ ልማት፣ የውኃ፣ የመብራት፣ የስልክ፣ የትራንስፖርት፣ የጤና፣ የአነስተኛና ጥቃቅን፣ የሴት የሕፃናት፣ የበሽታው፣ የመድኃኒቱ፣ የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛው፣ ወዘተ ዓይነት ችግሮች የተከማቹባት መሆኗንም ያለ መዘንጋቱ ጉዳይ ነው፡፡

እነዚህ የታዳጊ ከተማ ጫናዎች በጊዜ ሒደት ሊቃለሉ የሚችሉት አብዛኛው ነዋሪ በተቀበለውና በሚያምነው መዋቅር ስትመራ እንደ መሆኑ መጠን፣ እሱን ዕውን ማድረግ ተችሏል፡፡ ስለሆነም በየፊናው ሕዝቡም በእኔነት ስሜትና በንቃት መሳተፍ እንዲችል መደረግ አለበት፡፡ ይህን ማድረግ ወቅቱ የሚጠይቀው ትልቅ ተግባር እንደመሆኑ የወ/ሮ አዳነች ካቢኔና መላው አመራር ለተሻለ ውጤት ሊረባረቡ ግድ ይላቸዋል ለማለት እፈልጋለሁ፡፡

ቀደም ሲልም ቢሆን አዲስ አበባ በሁሉም ዘርፎቿ ከፍተኛ ለውጥ ያስመዝገበች መሆኗ አይታበልም፡፡ ባለፉት መቶ ዓመታት ያልተከናወኑ ሥራዎችና ልማቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ ተሠርተዋል ቢባል ግነት የለውም፡፡ ግን ዋናው ፈተና የፍትሐዊነት መጓደል፣ የጥገኝነትና ብልሽት መበራከት፣ ብሎም ሕገወጥነትና ሙስና መጎልበት እንደነበር ለውጡ ራሱ ያጠናው ጥናት ደጋግሞ አረጋግጦታል፡፡ ይህን መቅረፍና መቀነስ ነው አዲስ ምዕራፍ ከፋችነት፡፡

ከላይ የተጠቃቀሱትንና ሌሎች የሕገወጥነት ችግሮችን ቀርፎ፣ ከሁሉ በላይ መዲናዋን ከየዘውግ ፖለቲካ አሻጥር በማውጣት የኢትዮጵያና የአፍሪካ መዲናነቷን የሚያበስሩ ዕርምጃዎችን መውሰድም የአዲሱ አመራር የቤት ሥራ ነው፡፡ ዛሬ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያለው ጥገኛ አዲስ አበባን ሊሻማ የሚፈልገው በጎጥ መሥፈርት እየለካ ነው፡፡ ይህ የተዛባ አስተሳሰብ ተቀባይ ላይኖረው የሚችለው ደግሞ ከታችኛው መዋቅር አንስቶ የፖለቲካና የፐብሊክ ሰርቪስ ሥራን እየለዩ፣ መዋቅርን በብቃትና በሙያተኛ ማደራጀት፣ የፖለቲካ አመራሩም ከአቅጣጫ ሰጪነት ያለፈ ሚና እንዳይኖረው ማድረግ ሲቻል ነው፡፡

ይህም ያለፈውን የዛገ አስተሳሰብ ከማረም በላይ፣ ከዚህ በኋላ የተፈጠረውን አደገኛ ልሂቅ ለማስቆምና እየተቧደነ የሕዝብ ሀብት ላይ እንዳሻው የሚወስነውን ጥገኛ ይገታዋል፡፡ የሕዝብ ሀብትን ለመቆጣጠር ብቸኛ አማራጭ የሆኑትን እንደ ግልጽነትና ተጠያቂነት፣ የሕዝብ አገልጋይነትና ተቆርቋሪነት ብሎም ፍትሐዊነትና እኩልነትን ለማስፈንም የሚበጅ ነው፡፡

በእርግጥ እንኳንስ አዲስ አበባን የመሰለ የተውሰበሰበ ከተማ ሌሎች መለስተኛ ከተሞችንም ቢሆን ማስተዳደር እንዲህ ቀላል አይሆንም፡፡ ትናንትም ሆነ ዛሬ በመዲናዋ ለሚነሳው የፍትሐዊ ሀብት ክፍፍል ጥያቄ፣ የሙስናና የመልካም አስተዳደር ብልሽት፣ መዋቅሩንና የመንግሥትን ሥልጣን ተጠቅሞ የሕዝብ ሀብትን መበዝበዝ (በተለይ መሬት) ዓይነቶቹ ችግሮች በጥብቅ እየተፈተሹ መስተካከል ያለባቸውም ከዚህ አንፃር ነው፡፡ አዲስ ምዕራፍ ሊከፈት የሚችለውም በዚህ ዓይነቱ ትግል ብቻ ነው፡፡

ባለፉት ሦስት የለውጥ ዓመታት እንደታየው አዲስ አባባ ሁሉን ያቀፈች መሆኗ ብቻ ሳይሆን፣ በአንፃራዊነትም ቢሆን ሰላማዊ ከተማ ሆና ነው የቆየችው፡፡ አገራችን በሕዝባዊ እንቢተኝነት በምትናወጥበት የቀደመው ወቅትም ሆነ እስካሁን በብሔር ፖለቲካ በየቦታው ሕዝብ ሲተራመስ መዲናዋ አንፃራዊ ደኅንነቷ ተጠብቆ ለመቆየቷ የአስተዳደሩ ብቻ ሳይሆን፣ የሕዝቡም ሰላም ፈላጊነት ታክሎበት ነው፡፡ ይህን በጎ ገጽታ አጠናክሮ ችግሮቿን ቀርፎ ለመቀጠል ልዩ ትኩረት መስጠት ተገቢ ነው፡፡

እነዚህንና መሰል ችግሮች በአንድ ጊዜና በጥቂት ዓመታት እንኳንስ ማስወገድና ሥርዓት ማስያዝ በራሱ አስቸጋሪ መሆኑ እርግጥ ነው፡፡ ግን አዲሱ አመራር ከማይበጅ የእኛ/የእናንተ ፖለቲካ ውዝግብ ወጥቶ በታሪክ አጋጣሚ እጁ የገባውን የማልማት ዕድልና አገር የመቀየር ኃላፊነት በላቀ ውጤት ለማጀብ ሙሉ ቁርጠኝነት ካሳየ፣ ጀምሩን በጠንካራ መሠረት ላይ ማቆም አይከብደውም፡፡ ደግሞም ዕውን ሊያደርገው የሚችልበት ዕድል አለው፡፡

የወ/ሮ አዳነች የቀደመው ካቢኔም ሆነ የለውጡ አመራር ከመጣ ወዲህ ከእነ ጉድለቱም ቢሆን፣ ከቀደሙት ዓመታትም የተሻሉ የመልካም አስተዳደርና የሕግ የበላይነት ማስፈን ጅምሮች ታይተዋል፡፡ በድፍረት ሕገወጡን የመሬት ወረራ አጋልጦ የማረም እንቅስቃሴ መጀመር፣ መስቀል አደባባይና ጃንሜዳን የመሰሉ አወዛጋቢና ታሪካዊ ቦታዎችን በፍጥነት ገንብቶ (በተለይ አፋቸውን ከፍተው የኖሩ የወል ቦታዎችን ታሪካዊ ቅርስና ፓርክ በማድረግ) ማጠናቀቁ በታሪክም ያስመሠግነዋል፡፡ የትምህርት ቤቶች ምገባና የዝቅተኛ ነዋሪዎች ድጋፍም እንዲሁ፡፡

መሀል ከተማ ውስጥ ተወትፎ የፅዳትና የጤና ጠንቅ የነበረውን አትክልት ተራ አንስቶ፣ በምትኩ ሰፊና ደረጃውን የጠበቀ የአትክልት ተራ በአጭር ጊዜ ገንብቶ የማስለቀቁ ጥረት፣ በትራንስፖርት ዘርፍ ያለውን የከተማዋ ጫና ለመቀነስ ጥረት መጀመሩም… ይበል የሚያሰኙ ናቸው፡፡ እነዚህ ተግባራት ሲከናወኑ ደግሞ ጥቅሙ የተነካበት መንጫጫቱ ባይቀርም፣ የብዙኃኑን ጥቅም እያሰሉ መረባረብ የአሁኑ አመራር ትምህርት ሰጪ ሥራዎች ናቸው፡፡ ተስፋፍተው መግፋት ይኖርባቸዋል፡፡

ወደፊትም ቢሆን እንዲህ ያሉ የለውጥ ዕርምጃዎች ላይ ካለ ሥራ ተቀምጦ፣ ወሬ የሚጠርቀውም ሆነ በማኅበራዊ ድረ ገጽ አሉባልታ ላይ የተጠመደውን ሸፍጠኛ ማዳመጥና መልስ ለመስጠት መታከት አያስፈልግም፡፡ ‹‹ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡ…›› እንዲሉ ሁሉም በየፊናው ይተቻል፡፡ እኛም ያሻንን እንናገራለን እንጂ ውስብስብና የፍላጎት ድብልቅልቅ ከተማን ማስተዳደር እንዲህ ቀላል እንደማይሆን የታወቀ ነው፡፡ ግን አሁንም ሕዝብ መረጦ አደራ ሰጥቷችኋልና የበለጠ የምንጫነው አስተዳደሩን ነው፡፡

እንደ ከተማ ከዚህ ቀደም የነበረው ሌላው መሠረታዊ ችግር ከግብር አሰባሰብ፣ ግመታና ትግበራ ጋር በተያያዘ የሚስተዋለው ኢፍትሐዊነትና ሌብነትም ነበር፡፡ ይህ በሁሉም ነዋሪ ኑሮ ላይ ተፅዕኖ የሚያደርስ ተግባር እንደ ፖለቲካ መሣሪያ ተደርጎ አንዱ እየተማረረ ከአገር ሲሳደድበት፣ ሌላው እየፏነነ እንዲፈነጭበት ሲደረግ መቆየቱ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነበር፡፡ በቀጣይም የግብር መረቡን ማስፋት እንጂ ሕጋዊ ሆኖ ግዴታውን እየተወጣ ያለውን ማሳደድ ሊታረም የሚገባው ነው፡፡

በመዋቅሩ ውስጥ በተሰገሰጉ አንዳንድ ሌቦች አማካይነት ስንቶች ለብዝበዛና ለምሬት ተጋልጠው እንደነበርም አይዘነጋም፡፡ አሁንም ይህ ትልቅ ዘርፍ በጥገኞች መሞዳሞድ ለአደጋ እንዳይጋለጥ መደረግ አለበት፡፡ ይህን ወሳኝ የመንግሥት ገቢ ምንጭ ማስተካከልና እንዲጠናከር የማድረግ ጉዳይ ራሱ የሕዝቡ ታማኝነትና ተቆርቋሪነት ሊታከልበት ቢገባም፣ የአዲሱ አስተዳደር ሙሉ ትኩረትም ሊነፈገው አይገባም፡፡

የትኛውም መንግሥት ወይም የትኛውም ከተማ የማያልቅና የተትረፈረፈ ሀብት እንደሌለው የሚታወቅ ነው፡፡ የሀብት ግብዓት ከግለሰብ ጀምሮ እስከ መንግሥት ድረስ እጅግ በጣም ውስን ነው፡፡ ሁሉንም ችግሮቹን በአንዴ ለመፍታት የሚያስችል ሀብት የትም የለም፡፡ ስለዚህ ከተሞች በተለይ እንደ አዲስ አበባ ያሉ ደሃ ከተሞች ያላቸውን ውሱን ሀብት በትጋትና በፍትሐዊነት መሰብሰብ ብቻ ሳይሆን፣ በአግባቡ የመጠቀም ብቃት እንዲኖራቸው አዲሱ አመራር ካለፈው ጊዜ ትምህርት ወስዶ መረባረብ ነው ያለበት፡፡ ሕዝቡንም ማሳተፍ ግድ ይለዋል፡፡

በአጠቃላይ አዲስ አባበ እንደ ስሟ ይበልጥ ደምቃ የሁላችንም የጋራ ቤት መሆን ትችል ዘንድ፣ በሕዝብ ምርጫ የተመሠረተው አዲሱ አስተዳደር የተጣለበት ኃላፊነት ከፍተኛ ነው፡፡ በተለይም መልካም ጅምሮቹን በማጠናከር፣ ድክመቶቹንም ቀርፎ አዳዲስ ድሎችን በማስመዝገብ፣ የሕዝቡም ሚና ቢሆን ከመቼውም ጊዜ በላይ ተጠናክሮ መውጣት ያለበት ነው፡፡

የጋራ ቤታችን ሌብነት፣ ዘረፋም ይባል ሙስናን ልትሸከም አይገባትም፡፡ በተበላሸ ቢሮክራሲና አድሏዊ በሆነ የፖለቲካ አመራር/አሠራር ነዋሪዎቿ የሚታመሱበት የታሪክ ምዕራፍም ማብቃት ይኖርበታል፡፡ እነዚህና ሌሎች ከፍተኛና መለስተኛ ችግሮች ሊቀረፉ የሚችሉት ደግሞ ያለፈውን ብልሽት በጥብቅ እያረሙና ሳይደግሙ ለውጥን በመምራት ብቻ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...