Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርአፈራራሽ የፖለቲካ ድንክነት በሽታ በኢትዮጵያ!

አፈራራሽ የፖለቲካ ድንክነት በሽታ በኢትዮጵያ!

ቀን:

ሁሴን አዳል መሐመድ (ዶ/ር)

አወይ የዘመን ነገር! ቁጭ ብለው የሰቀሉትን ቆሞ ማውረድ ይቸግራል፡፡ 1960ዎቹ የቀድሞ ተማሪዎች የኅብረት ትግል ሲጀመር ዋለልኝ መኮንን በድፍረት ለመድረክ እስካበቃው ድረስ የሕዝብ ድጋፍ ስላልነበረው በቋንቋ ተጋሪነትውድ፣ብሔርየሚለውን ቃል ለማንነት መግለጫ ደፍሮ የሚናገር ተማሪ አልነበረም፡፡ ቀደም ሲል በብሔር መጠራት የሕዝብ ድጋፍ ያልነበረው በዘመነ መሳፍንት ወቅት ተፈጥሮ የነበረው የሕዝብ በጎጥ መሰነጣጠቅ ካስከተለው መጥፎ የታሪክ ጠባሳ በመነሳት፣ እንዲሁም ተማሪዎቹ የብሔር  ጽንሰ ሐሳብ ትርጉምን ከአገር በቀል ዕውቀት ዓውድ አፈንግጠው በባዕዳን የፖለቲካ ኢኮኖሚ ትርጉም ዕይታ ስለተመለከቱ፣ ይህም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ፣ መስተጋብርና አብሮነት የማይመጥን ትርጉም ሆኖ ስለተገኘ ነበር፡፡ ትግሉ የመምህራንን ተሳትፎ በውል ስላላካተተ ተማሪዎቹ የሚያነሱት የሚጥሉት ነገር ሁሉ የገባቸውን ያህል እንጂ መሆን የነበረበትን  ስላልነበር ስሜት መር እንጂ ዕውቀት መር አልነበረም፡፡

በአሁኑ ወቅት ደግሞ ባለፉት 30 ዓመታት የተሞከረው ቋንቋን መሠረት ያደረገው ፌዴራላዊ አስተዳደር አወቃቀር በአገርና በሕዝብ ላይ ያስከተለውን ጦስ በመጥላት፣ የጋራ ባህልና ታሪክ ተጋሪነት የፈጠረውን የጋራ ማንነትና ሥነ ልቦና ከተቀበረበት ጉድጓድ አውጥቶ የቅርብ ማንነቱን በመልክዓ ምድር ዓውድ ለመመልከት፣ ብሎም በዚህ ዓውድ ዙሪያ ለመሰባሰብ ፍላጎቱን የሚያሳየው፣ ነገር ግን በራሱ መተማመን የጎደለው ዜጋና በዜጎች ውስጥ ፍርኃትን የሚያሰርፁ ቡድኖች እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ ፍርኃት አንጋሾቹ በአንድ በኩልየብሔር ፖለቲካአንግሧቸውየብሔር ፖለቲካማዕድ ላይ ተቀምጠው ማዕዱ እንዳይደርቅ አጥብቀው የሚታገሉ፣ በሌላ በኩል  እንወክለዋለን ብለው በሚያስቡት የብሔረሰብ ሕዝብ ላይየብሔር ፖለቲካውየፈጠረውን የህልውና አደጋ ተቋቁሞ ለመቀልበስ ወቅታዊ የግዴታ ጥሪ ያለባቸው፣ ሁሉም ሰው ለእነሱ የአስተሳሰብ ቅኝት እንዲገዛ ፍላጎትና ምኞት ያላቸው  የፖለቲካ ልሂቃን ናቸው፡፡

ስለሸዋ፣ ወሎ፣ ጎጃምና ጎንደር ማንሳት አማራን ማዳከም ነው፣ እንዲሁም በትይዩ ወለጋ፣ ባሌ፣ ሐረርጌ፣ አርሲ ብሎ ማንሳት ኦሮሞነትን ማዳከም ነው፣ ወዘተ የሚሉ አንዳንድ አገር አፈራራሽ የፖለቲካ ድንክዬዎች (Saprophytic Political Dwarfs) አሉ፡፡የብሔር ፖለቲከኞችየኑሮ ክህሎት ሕይወት አልባ ዘአካልን በማፈራረስ (Decay) ላይ የተመሠረተው የፈንገስ የሕይወት ስትራቴጂ ጋር በምሥለት (Analogy) መታየት ስለሚችል፣ ጽሑፉን በዚህ መልኩ ለማቅረብ ተገደድኩ፡፡የብሔር ፖለቲከኞችምለዘመናት የፀና አገርንና በውስጧ ረግቶ በአብሮነት የኖረውን ሕዝብ ኖሮ ለመረበሽ አገር እየሰባበሩና ሕዝብ እየበታተኑ ስለሚኖሩ ምሥለቱ በሚገባ በገኃድ ይንፀባረቃል፡፡ እያልኩ ያለሁት፣እኔም ስለኢትዮጵያ ያገባኛልበሚል አቋም በመሆኑ፣የብሔር ፖለቲከኞችንፖለቲካ፣ አፈራራሽ የድንክዬዎች ፖለቲካ (Saprophytic Political Dwarfism Syndrome) ብለው ገላጭነት አይጎድለውም ብዬ አስባለሁ፡፡ ጥራዝ ነጠቅየብሔር ፖለቲካዕውቀት እንዲናኝቁን እያወቀ፣ በፍርኃትም ይሁን፣ በይሉኝታ በቸልታ ወይም የቤተ መንግሥት ግብር ለመቋደስ፣ ይህን ሁሉ ክፋት ከዳር ሆኖ የሚታዘብ ወይም ለኑሮው ሲል በግብረ በላነት ገብቶ የሚፈተፍት ኢትዮጵያዊ ነኝ ባይ ዜጋ ቅር ይለዋል ብዬ አልገምትም፡፡

እነዚህ አፈራራሾች (Saprophytes or Saprotrophs) እነማን ናቸው ቢባል፣ በግልጽ ያልተረዱትንየብሔር ፖለቲካፍልስፍና ጠንሳሾችና በቅብብሎሽ ወደ ሌላ ዘመን አሻጋሪዎች ናቸው፡፡ አማራንና ኦሮሞን፣ የሌላውንም ብሔረሰብ ሕዝብ ስፋት ጥበት ወርድና ቁመና ሳያዩ ሁሉንም በአንድ ጠባብ ጃኬት ውስጥ እያስገቡ የሚለኩ፣ የፖለቲካ ሴራውን ለጠነሰሰ ቡድን ቃል ኪዳን አድረው፣ የተነገራቸውን የውሸት ፖለቲካ ጽንሰ ሐሳብ ሁሉ ሳያቅማሙ ቡና ይመስል እንደ ወረደ የሚጋቱ፣ ራሳቸውን ለዘለዓለም የአዕምሮ ባርነት አሳልፈው የሰጡ ኪራይ ሰብሳቢ ቅንጭር የፖለቲካ ቡድኖችና የቡድኑ ርዕዮተ ዓለም ማዕድ ተጋሪዎች (ግብረ በላዎች) ናቸው፡፡

እዚህ ላይ የአማራ ሕዝብን ጉዳይ ስናነሳ በጋራ ሥነ ልቦና፣ የጋራ ባህልና ታሪክ ተጋሪነት ጎልብቶ ለዘመናት የፀናውን ሸዌነት፣ ወሎዬነት፣ ጎጃሜነትና ጎንደሬነት አስተዳደራዊ አወቃቀር ተከትሎ የአገርን የውስጥ አስተዳደር ማዋቀር ለአማራ ሕዝብ ውስጣዊ ብዝኃነት መጎልበት ይበልጥ ይጠቅማል፣ የሕዝብ ፍላጎት ይስተናገዳል፡፡ የወጣበትን ብሔረሰብ ለማያውቅም ሆነ የሁለት፣ ሦስትና አራት ብሔረሰብ ደም አለኝ በማለት በብሔረሰብ ምደባ ዕጦት ለሚንገዋለለው፣ እንዲሁም ጭራሽ ብሔረተሰቡ ለጠፋበት ዜጋ ዕፎይታ ይሰጣል፡፡ ያሉትንም ብሔረሰቦች በየደረጃው በሚፈጠር የውስጥ አስተዳደር እርከን ከፍታ ላይ በማስተሳሰር የኢትዮጵያን ሕዝብ አብሮነት በጠበቀ መሠረት ላይ ለማዋቀር ይረዳል፡፡ 

በፌዴሬሽን ምክር ቤት በሚደረግ የውክልና መቀመጫ ወንበርና በየዓመቱዳር 29 ቀን በሚደረግ የብሔረሰቦች በዓል የባህል ትርዒት ለአንድነታችንና አብሮነታችን ከመተማመን ይልቅ፣ ብሔረሰቦችን እንደ ሲሚንቶ በሚያያይዘው በየደረጃው እየገነባ በሚሄደው በነባሩ የሕዝብ አስተዳደር አወቃቀር ላይ ብናተኩር ይሻላል፡፡ የአገር እንጂ የብሔረሰብ ድንበር የለም፡፡ የአንድ ብሔረሰብ የአስተዳደር ወሰን አልፎ ከሌላው ብሔረሰብ መንደር ውስጥ የሚገኝ ዜጋ ወሰንተኛነት ወይም ባዕድነት እንዲሰማው አያደርገውም፡፡ የየብሔረሰቡ ሕዝብ የሚፈልገው እኩልነትና ፍትሕ በተከበረበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የዜግነት መብቱ ተከብሮ በመረጣቸው ተወካዮቹ እያተስተዳደረ፣ በአፍ መፍቻ ቋንቋው መንግሥታዊ አገልግሎት እያገኘ በነፃነት አብሮ እንዲኖር እንጂ፣ በድንበር ተካልሎ በጉርብትናና በጠላትነት እየተያየ በመኖር ወደ መለያየት ማዝገም አይደለም፡፡ ያም ሆነ ይህ የአገር ውስጥ አስተዳደር አወቃቀር የጉዳዩ ባለቤት ሕዝበ ውሳኔ የሚሻ ትልቅ አጀንዳ እንጂ፣ በፓርቲ ሕፈት ቤት ውስጥ በድብቅ ተወስኖ በሕዝብ ላይ የሚጫን የአምባገነኖች ውሳኔ ሊሆን አይገባውም፡፡ በኢትዮጵያችን የሆነው ግን ይህ ነው፡፡

የነባሩን የአስተዳደር አወቃቀርንድምታ አዋጪነት እያወቁ በመካድ፣ ብሔረሰቦችን በቋንቋ ማዕቀፍ ውስጥ አጥብበው የሚያጥሩ የጨለመባቸው ዘገምተኛ የውሸት ትርክት ጸሐፊዎችና ተራኪዎች የነባሩ የአገር ውስጥ አስተዳደር አወቃቀር አማራጭ ፀሮች ናቸው፡፡ ለምሳሌ የአማራ ሕዝብ እንጂ አማራ የተባለ ነገድ በታሪክ የለም ሲባሉልጅ ለአናቷ ምጥ አስተማረችእንዲሉ በታሪክ ጠልነት ተነሳስተው በመረጃ ላይ ተመሥርቶ በጥቁርና ነጭ ቀለም የተጻፈውን የታሪክ አስረጂ ሁሉ በጭፍንነት ሲያጣጥሉ አላዋቂነታቸውን አይጠራጠሩም፣ ኃፍረትም አይሰማቸውም፡፡
የአማራ ሥርወ መንግሥት ብሎ በተንኮል መነገር ከመጀመሩ በፊት የሰለሞናዊ ሥርወ መንግሥት በሚባሉት የአክሱምና የዛጉዌ ዘመነ መንግሥታት፣ ከተለያየ ነገድ የተውጣጣ ሠራዊት ከተራው ሕዝብ ውጪ ለሆነ ሚስጥራዊ መግባቢያ ሲባል የየነገዱን ቋንቋ አሳጥሮና አስረዝሞ እያዳቀለ በመናገር የፈጠረው የቤተ መንግሥት ቋንቋ የመሆን ዕድል ያገኘው አማርኛ ቋንቋ ቀስ በቀስ እየጎለበተ ሄዶ የሕዝብ ቋንቋ መሆን ስለመቻሉ፣ በጥንት ጊዜ የተጻፉ ድርሳናት ያስገነዝባሉ፡፡ በአለቃ ታዬ ተጽፎ በወንጌላዊት ማኅበር ማተሚያ ታተመ፣ አሥመራ 1920 .ም. የታተመ የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ፣ በአጭር የወጣ ቃል መጽሐፍ ይህን መረጃ ቁልጭ አድርጎ ያቀርባል፡፡
ይህን ድቅል ቋንቋ የተናገረ የአገሩ ሰው ሁሉ የአማራነት ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ወይም ሰውነት  መጠሪያ አገኘ፡፡ ቀስ በቀስ  በሒደት በልፅጎ የሕዝብ መግባቢያ፣ የጋራ ቋንቋና ላለፉት 600 ዓመታት የመንግሥት የሥራ ቋንቋ ለመሆን በቃ፡፡ አማራነት ውስጥ ኢትዮጵያ አለች፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ አማራነት አለ፡፡ በአማርኛ ቋንቋ ውስጥ የበርካታ ነገዶች ቋንቋ ተዋጽኦ አለ፡፡ እያደር ቋንቋው በመስፋፋትና አድማሱን እያሰፋ በመሄድ በየደረሰበት ሁሉ የየነገዱ ቋንቋ ሥርገት እያጎለበተው፣ የሁሉም ነገድ ሕዝብ የሚግባባበትና የሚገበያይበት የጋርዮሽ ቋንቋ ሆነ፡፡ ገና ከአነሳሱ ጀምሮ የብዙ ነገዶች ቋንቋ ተዋጽኦ የነበረው አማርኛ ቋንቋ ከተጨማሪ ነገዶች ቋንቋ ቃላትንና ድምፅን በየጊዜው እየተዋሰና በዚያው እየዳበረ፣የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር” (ኢሕአዴግ) መላ አገሪቱን እስከተቆጣጠረበት ግንቦት 1983 .ም. ማግሥት ድረስ፣ በኢትዮጵያ በሁሉም አካባቢዎች ከአፍ መፍቻ ቋንቋ በተጨማሪ የትምህርትና የመንግሥት ሥራ ቋንቋ ሆኖ  አገልግሏል፡፡

ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ገና ከጠዋቱ አቅዶ የተነሳየብሔር ፖለቲካቡድን አማርኛ ቋንቋን የነፍጠኛ ቋንቋ፣ የገዥ መደብ ቋንቋ፣ የመጨቆኛ መሣሪያ፣  ወዘተ በማለት በውሸት ፈርጆ፣ በሌሎች ብሔረሰብ ሕዝብ ለማስጠላት፣ በዚሁ ቋንቋ እየተጠቀመ አገርን ለማፈራረስ፣ ሕዝብን ከሕዝብ ለመለያየት ተቀመበት፣ ብሎም የፖለቲካ ኪራይ መሰብሰቢያ አድርጎ ተጠቀመበት፡፡  ማኅበረሰባዊ የቋንቋ ዕድገት ታሪክ ሒደትን ተከትሎ የተፈጠረውን አማርኛ ቋንቋ ለሁሉም ብሔረሰብ ሕዝብ የጋራ መጠቀሚያ ለማድረግ እንዴት በጋራ እናዳብረው ብሎ ከማሰብ ይልቅ፣ ቋንቋው እንዴት ይጥፋ የሚለው ገዥየብሔር ፖለቲካየምርምር ሐሳብ ሆነ፡፡ የአማርኛ ቋንቋ በሌሎች የብሔረሰብ ቋንቋዎች ላይ ተፅዕኖ እንዳሳደረ አድርገው ይቀሰቅሳሉ፡፡ ዳሩ ግን  አማርኛ ቋንቋ የሕዝብ የጋራ መግባቢያና የመንግሥት የሥራ ቋንቋ ሆኖ ከማገልገሉ በስተቀር፣ ሌሎች ቋንቋዎችን ለማጥፋት በመሣሪያነት ጥቅም ላይ አልዋለም፡፡ እስከ ደርግ ዘመን መጨረሻ ድረስ በነበረው ጊዜ የወቅቱ የአገራችን አቅም በፈቀደው መጠን 15 የተለያዩ የብሔረሰብ ቋንቋዎች መሠረተ ትምህርት  ይሰጥ እንደነበር መጥቀሱ በቂ ማስረጃ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት እንኳ ብዙ ከመወራት አልፎ ደረጃ የተጠበቀ ወይም ከዚህ በላይ የተጨመረ ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡

ዛሬ ሸዋ፣ ወሎ፣ ጎጃም፣ ጎንደር በሚባሉ የመልክዓ ምድር አካባቢዎች አማርኛ ቋንቋ ቀዳሚ ታሪካዊ መሠረት በማግኘቱ ሌላውን የጋራ ማንነት መገለጫ አማራጭ ትታችሁአማራ ነንማለትን ለምን አትለማመዱም፡፡ እንዲሁም በትይዩ ወለጋ፣ ባሌ፣ ሐረርጌ፣ አርሲ መባል  የፈጠረውን የጋራ ሥነ ልቦና ምንነት ረስታችሁ በጅምላኦሮሞ ነንለምን አትሉም በማለት ሥውር የፖለቲካ ፍላጎታቸውን ደብቀው ሕዝብን የሚያስገድዱየብሔረሰብ ቋንቋ አምላኪ ቡድኖችኢዴሞክራሲያዊ አቀራረብ፣ የፖለቲካ ዳቦ ጋጋሪዎችና ቋንቋ ተናጋሪነት ላይ የተመሠረተየብሔር ፖለቲካዘመን አሻጋሪዎች ደራሽ (መጤ) ትርክት ነው፡፡ ስለሌሎች ቋንቋ ተናጋሪዎችም እንዲሁ ነው፡፡  አንድ አፍታ ቆም ብሎ ታሪክን መመርመር የሚሳናቸው የብሔር ፖለቲካልሂቃንከእኛ ወዲያ ያወቀ ላሳርበማለት ግግም ብለው ባሉበት ተገትረው ይቀራሉ፡፡ ከእነዚህ ግትሮች ጋር አገር የምንጋራ ሌሎቻችን በጣም በጣም አድርገን ተቸገርን!!!
እኛ በኅብረ ብሔራዊነትና ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት አብረን እንኑር ስንል፣ እነርሱ ግንበብሔረሰብኛነትተለያይተን ለየብቻችን እንኑር ይሉናል፡፡ ነገር ግን አገራችንም ሆነ ሕዝቧ በምንም መመዘኛ ሊለያይ የሚችል ስላለመሆኑ በአመክንዮት ለማስረዳትም፣ ለመረዳትም የሚያስቸግሩ/የሚቸገሩ ናቸው፡፡

እንደ ጣዖት የሚያመልኩት የዘር ፌዴራሊዝም በኢትዮጵያ ላይ ተግባራዊ ለመደረግ የሚያስቸግርበትን ምክንያት ጭራሽ መስማት አይፈልጉም፡፡ የዘር ፌዴራሊዝም አዋጪ ሆኖ አገር ያስቀጠለ የትኛው አገር እንደሆነ አጣቃሽ ማስረጃ  አያቀርቡም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለረዥም ዘመን በመስተጋብርና በአብሮነት በመኖሩ ምክንያት በደም፣ በባህልና በታሪክ ስለተሰናሰለ ከዘር ቅልቅል የፀዱ ብሔራዊ ክልሎችን ለመፍጠር ያለውን አዳጋችነት አይረዱም፡፡ በኦሮሞ የፖለቲካ ልሂቃን በኩል ኦሮሞነትን በኦሮሚኛ ቋንቋ ተናጋሪነት ብቻ አጥበበው፣ የባህል፣ የታሪክና የጋራ ሥነ ልቦና ውስጣዊ ብልኃትነቱን ደምስሰውና ጨፍልቀው፣ በአንድ ግድግዳ አጥር ውስጥ ቀርቅረውየብሔር ፖለቲካንለቡድን መጠቀሚያ ለማድረግ ደፋ ቀና የሚሉ ሰዎች በዝተዋል፡፡ በዚህ አማካይነትየብሔር ፖለቲካውርስን ከአባታቸው ትሕነግ በመረከብ ዘመን በማሻገር በድቡሽት ላይ በቆመ የፖለቲካ ወንበር ላይ ተተክተው፣ በየዙሩ ጎሌ (Dominant) የብሔረሰብ ስብስብ ወኪል በመሆን የኢትዮጵያን ሕዝብ ሰላም በየተራ በዘላቂነት ለመንሳት የሚፍጨረጨሩ፣ ለቡድን ዓላማ የተጉ ሰዎች እየታዩ ነው፡፡ ዕድሜ ለሰጠው ሰው፣ ወር ተራ ነውና፣ ጊዜ ጠብቀው የሚነሱ የሌላ ብሔረሰብ ተረኞችም ወደፊት መምጣታቸው አይቀርም፡፡

የብሔር ፖለቲካውጤት የሆነው በቋንቋ ላይ የሚመሠረት የክልል አወቃቀር ማዕከላዊነትን ከአዲስ አበባ አውጥቶ ወደ ክልል ከተሞች በማዛወር ክልላዊ አሀዳዊነትን ከመፍጠር በስተቀር፣ ከቀበሌ እስከ ክልል ድረስ ባለው መዋቅር የትየለሌ የሥራ መደቦችን በመክፈት ለተግተለተለየብሔር ፖለቲካቡድን ግብረ በላ ዕድልና ምቾት ከማስገኘቱ ሌላ፣ ፍትሕና ርትዕ ለሚፈልገው የየብሔረሰቡ ሕዝብም ሆነ በአጠቃላይ ለአገራችን ሕዝብ ያስገኘው የዕድልም ሆነ የድል ጭማሪ የለም፡፡  ከዚህ አንፃር  በውስጥና የውጭ ኃይሎች የጋራ ትብብር በኢትዮጵያ ላይ የተጋረጠውን የህልውና አደጋ በአንድነት በመሆን ከቀለበስን በኋላ በጋራ ምክክር ማስተካከል የሚገባን መለስተኛ የፖለቲካ አጀንዳ እንዳለ ግልጽ  ነው፡፡

የብሔር ፖለቲካልሂቃን በፈጠሩት አውቆ አጥፊነት አገራችን አሁን ለደረሰችበት ውድቀት ተዳርጋለች፡፡ ይህን አደገኛ ጥፋት ለማረም ከዚህ በኋላ የምናጠፋው ጊዜ ሊኖር አይገባም፡፡ የአዲሱ የተወካዮች ምክር ቤት ጉባዔ አባላት ይህን ችግር በውል ተገንዝበው በሕዝብ ውስጣዊ ብዝኃነት ላይ የተመሠረተውን የውስጥ አስተዳደር አወቃቀር በጥናት ላይ ተመሥርቶ ወደ ነበረበት ከፍታ እንዲመለስ ጥረት ቢደረግ፣ መጪው ዘመን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ብሩህ ጊዜ፣ ለአዲሱ የተወካዮች ምክር ቤትም መልካም የሥራ ዘመን ይሆንላቸዋል ተብሎ ይታመናል፡፡

ኢትዮጵያ በክብር ለዘለዓለም ትኑር!

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በወሎ ዩኒቨርሲቲ በተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የሥነ ሕይወት ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...