– የፖለቲካ ልዩነቶችን ለማጥበብ አካታች ብሔራዊ የውይይት መድረክ እንደሚካሄድ አስታወቁ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በአዲሱ መንግሥት ምሥረታና በበዓለ ሲመታቸው ላይ ለተገኙ፣ የአፍሪካ አገሮች መሪዎችና የተያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት ሥነ ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ኢትዮጵያ በፍቅር የሚቀርቧትን ወዳጅ አገሮችን በበጎ እንደምትቀበል አስታወቁ።
በኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች የፓርላማ ፖለቲካ ሥነ ሥርዓትን በሚከተሉ አገሮች ባልተለመደ መንገድ በተካሄደው የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በዓለ ሲመት ላይ፣ የምዕራብ አፍሪካና የምሥራቅ አፍሪካ አገሮችን የሚወክሉ የአገር መሪዎች ታድመዋል።
ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. በተካሄደው አጠቃላይ ምርጫ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን አብላጫ ወንበር ያሸነፈው ብልፅግና ፓርቲ፣ የፓርቲውን ሊቀመንበር በጠቅላይ ሚኒስትርነት እንዲያገለግሉ በመምረጡ፣ ይህንኑም ሰኞ መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ማለዳ ለተሰበሰበው ምክር ቤት ማሳወቁን ተከትሎ፣ ምክር ቤቱ የፓርቲውን ውሳኔ ተቀብሎ ሊቀመንበሩን ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በጠቅላይ ሚኒስትርነት ሰይሟል።
የምክር ቤቱ ሥነ ሥርዓት ተጠናቆ ካበቃ ከቀትር በኋላ የጠቅላይ ሚኒስትሩ በዓለ ሲመት በመስቀል አደባባይ የተከበረ ሲሆን፣ በዚህም ወቅት በእንግድነት የተጋበዙት የአፍሪካ አገሮች መሪዎች ንግግር በማድረግ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) መንግሥትና የአፍሪካ ተምሳሌት ከሆነች ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ጋር አብረው እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል።
መሪዎቹ በተከታታይ ንግግር አድርገው ካጠናቀቁ በኋላ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) በመድረኩ ለተገኙ እንግዶችና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ንግግር አድርገዋል።
ንግግራቸውን ባደረጉበት ወቅትም ኢትዮጵያ የገጠማትን የውስጥ ቀውስ ተከትሎ የበረታባትን የውጭ ጫና በመቃረን፣ ከኢትዮጵያ ጎን ለቆሙ አገሮች ምሥጋና አቅርበዋል።
አክለውም ኢትዮጵያን ለመጫን የሞከሩና የሚሞክሩ አገሮችን በተመለከተ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
‹‹ኢትዮጵያ ወደ ብልፅግና ለምታደርገው ጉዞ የወዳጆቿን ድጋፍ ትሻለች። ነገር ግን ማንኛውም ወዳጅነት የኢትዮጵያን ክብርና ሉዓላዊነት በሚሰዋ መልኩ መሆን የለበትም፣ ሊሆንም አይችልም፤›› ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ጉዳይ ላይ አክለው ሲናገሩም፣ ‹‹በፍቅር መንፈስ ለሚቀርቡን አገሮች ልባችንና በራችን ለድጋፋቸውና ለምክራቸው ሁሌም ክፍት ነው፤›› ብለዋል።
ኢትዮጵያ የገጠማትን የውስጥ ችግር እንደምትፈታ ያረጋገጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ችግሮቹን ለመፍታትም በአጭር ጊዜ ውስጥ ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ውይይት መድረክ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።
‹‹የፖለቲካ ልዩነቶቻችንን ለማጥበብ አካታች ብሔራዊ የውይይት መድረክ እናካሂዳለን፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የሚካሄደው ውይይት በኢትዮጵያውያን እንደሚመራና የኢትዮጵያ ወዳጅ አገሮች ደግሞ በዚህ ውስጥ ሚና እንደሚኖራቸው ገልጸዋል።
‹‹ችግሮቻቸውን ተመካክረው ይፈታሉ ብለው የሚያምኑብንን ያካተተና በኢትዮጵያውያን የሚመራ ሁሉን አቀፍ የውይይት መድረክ እናካሂዳለን፤›› ሲሉ አገረጋግጠዋል።
ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክት በማለዳው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት የጋራ ስብሰባ ወቅት፣ በፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የመክፈቻ ንግግር ላይም በግልጽ ተንፀባርቆ ነበር።
‹‹የገጠሙንን ሰንኮፎች በብሔራዊ ውይይት መፍታት ይኖርብናል፤›› ያሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፣ ብሔራዊ ውይይት የረዥም ጊዜ ሒደትን የሚጠይቅ እንደሆነና መግባባት ላይ ለመድረስም ትዕግሥትን እንደሚጠይቅ ገልጸዋል።