Monday, March 4, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የዋጋ ግሽበትን መቀነስ የመንግሥት ዋነኛ ትኩረት እንደሚሆን ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ቀጣዮቹን አምስት ዓመታት አገሪቱን ለመምራት የተመሠረተው መንግሥት የዋጋ ግሽበትን መቀነስ ዋነኛ ትኩረቱ እንደሚሆን አስታወቀ፡፡

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ ሰኞ መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ለአዲሶቹ የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አባላት ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር እንዳስታወቁት፣ በኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የአገሪቱን ማክሮ ኢኮኖሚ በማረጋጋት የተጀመረው ዕድገት ወደኋላ ሳይመለስ እንዲቀጥል ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ፡፡

የሥራ ዕድል በማስፋፋት የተንሰራፋው ሥራ አጥነት እንዲቃለል ጥረት እንደሚደረጉ የገለጹት ፕሬዚደንቷ፣ ከሁሉም በላይ የዋጋ ግሽበቱን በመቀነስ የኑሮ ውድነት እንዲስተካከልና በተፈጥሯዊና በሰው ሠራሽ ተግዳሮቶች የገጠሙ ጉድሎቶችን በፍጥነት በማረም፣ ሁለንተናዊ ዕድገት እንዲረጋገጥ መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ይሠራል ብለዋል፡፡

በአገሪቱ እየጨመረ ለመጣው የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት መንስዔ የሆኑት የአቅርቦትና የፍላጎት አለመመጣጠን፣ ዝናብን መሠረት ያደረገ የግብርና ሥርዓት፣ የተዛባ የንግድ ሥርዓት ለማስተካከል በትኩረት እንደሚሠራ፣ የኑሮ ውድነቱን በዘላቂነት ለማቃለል የገንዘብና የፊስካል ፖሊሲ ቁጥጥር ሥራ አፅንኦት እንደሚሰጠውና የንግድ ሥርዓቱን የማስተካከል ሥራ የዚህ ዓመት የትኩረት አቅጣጫ ይሆናል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መስቀል አደባባይ በተካሄደው የመንግሥት ምሥረታ ንግግር፣ አዲስ የተመረጠው መንግሥት የቅድሚያ ትኩረት ሰጥቶ ከሚሠራባቸው የኢኮኖሚ አስተዳደር ሥራዎች መካከል አንዱ የዋጋ ንረትን መግራት ይሆናል ብለዋል፡፡

የመንግሥት ገቢን በ2014 ዓ.ም. 600.9 ቢሊዮን ብር ለማድረስ ግብ የተጣለ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 83 በመቶ የሚሆነው ገቢ ከታክስ ለመሰብሰብ መታቀዱ በፕሬዚደንቷ ንግግር ተመላክቷል፡፡ በ2014 የበጀት ዓመት ጠቅላላ የሸቀጦች የወጪ ንግድ ገቢ 5.25 ቢሊዮን ዶላር እንዲደርስ መታቀዱን ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ያስረዱ ሲሆን፣ በግብርና መስክ ደግሞ 592 ሚሊዮን ኩንታል የሰብል ምርት ለማምረት ዕቅድ እንደተያዘ ጠቁመዋል፡፡

ማኑፋክቸሪንግን በተመለከተ የነባር አምራቾችን ምርትና ምርታማነት በማሻሻል፣ እንዲሁም ጥራት ያላቸውን አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን በመሳብ ዘርፉ ለሥራ ዕድል ፈጠራ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት በትኩረት ይሠራል ተብሏል፡፡

ስትራቴጂካዊ የሆኑ የገቢ ምርቶችን የሚተኩ የማኑፋክቸሪንግ ውጤቶች እንዲስፋፉ እንደሚደረግና የወጪ ንግድ ምርቶችን በብዛት፣ በጥራትና በዓይነት ማምረት፣ የአገር ውስጥ ባለሀብቱ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ንዑስ ዘርፍ በስፋት እንዲሰማራ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ኢንዱስትሪው ለጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት የሚያደርገውን አስተዋፅኦ ማሳደግ፣ ንዑስ ዘርፉንም ከአገሪቱ ዘላቂ ልማት፣ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ስትራቴጂ ጋር የተጣጣመ ለማድረግ እንደሚሠራ ተመላክቷል፡፡

ፕሬዚደንት ሳህለወርቅ በንግግራቸው ማዕድናትን በዓይነት፣ በመጠንና በብዛት ለገበያ እንዲቀርቡ በማድረግ የውጭ ምንዛሪ ግኝት እንዲያደርጉ በብርቱ ይሠራል ያሉ ሲሆን፣ ለአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች የሚያስፈልጉ ማዕድናት በአገር ውስጥ እንዲቀርቡ እንደሚደረግ፣ ከፍተኛ የማዕድናት ሀብት ባለባቸው አካባቢዎች የሚስተዋሉ የፀጥታ ችግሮች እንዲቀረፉ በልዩ ትኩረት ይሠራል ብለዋል፡፡ በዘርፉ የተማራ የሰው ኃይል ልማት በጥራትና በብዛት እንዲኖር ከማድረግ በሻገር፣ ለባህላዊና ለአነስተኛ የማዕድን አምራቾችም ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ አስታውቀዋል፡፡

የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን አገራዊ አቅም በመገንባት አብዛኛው የአገር ውስጥ ፍላጎት በአገር በቀል ኩባንያዎች እንዲሸፈን ይደረጋል ያሉት ፕሬዚደንቷ፣ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ሰፊ የሥራ ዕድል እንዲፈጥርና የኮንስትራክሽን ግንባታዎች የጥራት፣ የወጪና የጊዜ ተወዳዳሪነትን ማሻሻል እንደሚያስፈልግ አስምረውበታል፡፡

የመንገድ መሠረተ ልማትን የተቀናጀ፣ ፍትኃዊና ተደራሽ በማድረግ የከተሞች ልማትና የገጠር ዕድገትን የሚያፋጥን እንቅስቃሴ በከተማና በገጠር በተመጋጋቢ መንገድ በመተግበር የከተማ ምጣኔ ያድጋል የተባለ ሲሆን፣ ከተሞች በተሟላ ዕቅድና በተማከለ የከተማ አስተዳደር እንዲመሩ ከማድረግ በተጨማ የከተሞችን የመሬትና የመኖሪያ ቤት አቅርቦትና አስተዳደር ሥርዓት ውጤታማነትን በማሻሻል ምቹ የመኖሪያ አከባቢ ለመፍጠር እንደሚሠራ ተገልጿል፡፡

ከቱሪዝም ዘርፍ የሚገኘውን ሀብት ለማሳደግ የቅርስ እንክብካቤና ጥበቃ ሥራ በማጠናከር የዘርፉን አገልግሎት አሰጣጥ በማሻሻል ነባር መዳረሻዎችን ማጎልበት ይገባል ያሉት ፕሬዚዳንቷ፣ በተጨማሪም አዳዲስ የቱሪስት መስህቦች እንዲለሙ ከማድረግ ባሻገር፣ በገበታ ለአገር ፕሮጀክት የተጀመሩ የጎርጎራ፣ የወንጪና የኮይሻ የቱሪስት መዳረሻ ልማቶች በዕቅዳቸው መሠረት ክንውናቸው እንዲቀጥል ይደረጋል ብለዋል፡፡

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተጀመሩና ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን በተያዘው ዓመት በማጠናቀቅ ለሕዝብ ጥቅም እንዲውሉ እንደሚደረግ፣ የመጠጥ ውኃ፣ ሳኒቴሽንና ኃይጅን አቅርቦትን በማስፋፋት የአገልግሎቱ ተደራሽ ያልሆነውን ሕዝብ ተጠቃሚ እንደሚደረግና ንፁህ ኢነርጂና ቴክኖሎጂ ለገጠሩ ኅብረተሰብ እንዲዳረስ፣ ጥራት ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት እንዲቀርብ በትኩረት እንደሚሠራ በፕሬዚደንቷ ንግግር ተመላክቷል፡፡

በሌላ በኩል የሚታለሙትና እንደ ግብ የሚቀመጡት በጎ ዓላማዎች ትርጉም የሚኖራቸው ባለው የማስፈጸምና የማድረግ አቅም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ደግሞ አዲሱ መንግሥት የሚያስብ፣ የሚያቅድና የሚከውን እንጂ በጎ የሚመኝና ህልመኛ ብቻ ሊሆን እንደማይገባ በመግለጽ፣ ‹‹እስከ ዛሬ ታቅደው ከጠረጴዛ ላይ ያልወረዱና ተጀምረው የተሰናከሉ ውጥኖች ባለንበት የምንረግጥና አንዳንዴም ወደኋላ የምንሸራተት እንድንሆን አድርገውናል፤›› ብለዋል፡፡

በዜጎች ላይ የሚደርሰውን ምሬትና መንገላታት ለመቅረፍ፣ ጀምሮ የመጨረስን ባህል በመላበስ በቴክኖሎጂ የታገዘ ግልጽና ቀልጣፋ የአገልግሎት አሰጣጥና ምቹ የሕዝብ አስተዳደር እንዲኖር አበክረን እንሠራለን ያሉት ዓብይ (ዶ/ር)፣ በተለይ ሌብነትን እንደ ቀላል ድክመት ሳይሆን እንደ ከፍተኛ የደኅንነትና የህልውና አደጋ በማየት፣ በቀጣዩ ዓመታት ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ አስታውቀዋል፡፡

የኢኮኖሚ ምሁራን የዋጋ ግሽበትንና የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ መከናወን ይገባቸዋል የሚሉ ምክረ ሐሳቦችን ይሰነዝራሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ መንግሥት ሰላምና መረጋጋትን በመፍጠር ሥጋት በማስወገድ ማኅበረሰቡ የተረጋጋ ኑሮ እንዲኖር ማድረግ፣ በከተሞች አካባቢ በዕቅድ የሚመራ የምርቶች አቅርቦት ሊኖር እንደሚገባ፣ የአምራቾችና የሸማቾች ማኅበራት በመንግሥትና በሌሎች ባለድርሻ አካላት መጠናከር እንዳለባቸው፣ መንግሥት ሕገወጥ ነጋዴዎችን የሚቆጣጠርበት ሥርዓት ማበጀት እንደሚገባውና የመሳሰሉት ተጠቃሽ ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች