Wednesday, October 5, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናየግል ዳታ ጥበቃ ረቂቅ አዋጅ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀረበ

  የግል ዳታ ጥበቃ ረቂቅ አዋጅ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀረበ

  ቀን:

  በቅርቡ እንደ ፀደቀው የኤሌክትሮኒክስ ትራንዛክሽን አዋጅ ሁሉ የግል ዳታ ጥበቃ ረቂቅ አዋጅም ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅረቡ ታወቀ፡፡ 

   

  በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር አብዮት ባዩ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ እንደ ኢትራንዛክሽን አዋጅ ሁሉ እኩል አስፈላጊ የሆነው የግል ዳታ ጥበቃ የሚባለው አዋጅ ነው፡፡

  አብዮት (ዶ/ር) ጨምረው እንደገለጹት፣ ይህን አዋጅ የማርቀቅ ሒደቱ ተጠናቋል፡፡ ይህም ሲባል ባለድርሻና የሚመለከታቸው አካላትን በማወያየት ረቂቁ ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የተላከ መሆኑን፣ በረቂቁ ላይ የተሰጠውን ግብረ መልስ መሠረት በማድረግ ማሻሻያዎች ተደርገው የመጨረሻው ቅጂ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መላኩን ተናግረዋል፡፡

  ቀጣዩ ሥራ የሚሆነው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ረቂቅ አዋጁን ከተመለከተ በኋላ በማፅደቅ ወደ ፓርላማ  እንደሚልከው ያስታወቁት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ምናልባትም የሚኒስትሮች ምክር ቤት በረቂቁ ላይ መሻሻል ይገባዋል የሚላቸው ጉዳዮች ካሉ ሒደቱን ተከትሎ እንደሚከናወኑ አስረድተዋል፡፡

  የግል ዳታ ጥበቃ አዋጅ ዋና መሠረቱ አንድ ግለሰብ ወይም ግለሰቦች መረጃ በኦንላይን ትራንዛክሽን በሚሰጡበት ጊዜ፣ መረጃው ለሰጡት ጉዳይ ብቻ እንደሚውል የሚያረጋግጥ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡ ለምሳሌ በሆስፒታል ሕክምና ወቅት የሚሰጡ መረጃዎች ካለባለቤቱ ፈቃድ ውጪ ለሌላ ጥቅም እንደማይውሉ መረጋገጥ አለባቸው የሚለውን የሚመለከት እንደሆነ ተገልጿል፡፡

  በሌላ በኩል የግለሰቦችን መረጃ ማንቀሳቀስ ቢፈለግ እንዴት ነው መንቀሳቀስ ያለበት? የሚለውን ጉዳይ ረቂቅ አዋጁ የሚመለከት ሲሆን፣ አንድ ግለሰብ የሕክምና፣ የትምህርት፣ የፍርድ ቤትና የመሳሰሉት መረጃዎቹ በሦስተኛ ወገን እጅ ስለሚገኙ እነዚህ መረጃዎች ያለ ግለሰቡ ፈቃድ አገልግሎት ላይ እንዳይውሉ፣ ግለሰቡ የሚፈቅድበት ሁኔታም ካለ መረጃው በተገቢ መንገድ እንዲንቀሳቀስ ለማድረግ የሚያስችል እንደሆነ አብዮት (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

  የግል ዳታ ጥበቃና ኢትራንዛክሽን አዋጆች በሳይበር ዓለም መረጃዎች በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲጠበቁ በማድረግ፣ የዲጂታል ኢኮኖሚው እንዲሳለጥ የሚያደርጉ መሠረታዊ ሕጎች እንደሆኑ አብዮት (ዶ/ር) ጨምረው አስታውቀዋል፡፡

   የኤሌክትሮኒክስ ትራንዛክሽን አዋጅ በፓርላማ ፀድቆ ወደ ሥራ መገባቱን ያስታወሱት አብዮት (ዶ/ር)፣ የአዋጁም ዋነኛ ግብ በወረቀት ሲከናወኑ የነበሩ ሥራዎች በዲጂታል በመከናወናቸው ብቻ ሕጋዊነት አያሳጣቸውም የሚል ነው፡፡ ይህም እኩል ተቀባይነት አላቸው የሚል እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ በተለየ ሁኔታ ካልተደነገገ ለምሳሌ እንደ ኑዛዜ ዓይነት ካልሆነ በስተቀር ዋጋቸውና ተቀባይነታቸው እኩል ነው፡፡

  የመንግሥት አገልግሎቶችን በኤሌክትሮኒክስ መስጠት እንደሚቻል በአዋጁ ተደንግጓል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ማንኛውም የመንግሥት መሥሪያ ቤት አገልግሎት ሲሰጥ ካልተቸገረ በስተቀር የመጀመርያ ምርጫው ኤሌክትሮኒክስ መሆን አለበት ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ከዚህ በፊት በነበረው አሠራር በሕግ ያልተደገፈ የነበረ በመሆኑ፣ አሁን ግን ሕጋዊነቱ በግልጽ መደንገጉን አስታውቀዋል፡፡

  የኤሌክትሮኒክስ ፊርማን ጨምሮ ሌሎች ኮንትራቶችና አገልግሎቶች በዲጂታል መንገድ ሲከናወኑ፣ ከመደበኛው የወረቀት አገለግሎት እኩል የሕግ ጥበቃ እንዲኖራቸው ከማድረጉ በሻገር፣ ሰዎች ወደ ዲጂታል ዓለም እንዲሄዱ የሚያደፋፍር እንደሆነ አብዮት (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

  የፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ አስቀድሞ በወረቀት ብቻ እንደነበረ ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ የነጋሪት ጋዜጣ በኤሌክትሮኒክስ በሚወጣው የነጋሪት ጋዜጣ ተግባራዊ እንደሚደረግ በአዋጁ ላይ የሠፈረ እንደሆነ አስታውቀው፣ ኢትራንዛክሽን አዋጁ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ በጣም ዝርዝር ማድረግ ስለሚያስፈልግ ደንቦችና መመርያዎች እየተዘጋጁለት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

  የአዋጁ ደንብ እንደተጠናቀቀ ያስታወሱት አብዮት (ዶ/ር)፣ ሌሎች ዝርዝር የሆኑ መመርያዎች በተለይም የኤሌክትሮኒክስ ግብዓቶች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው እንዴት ነው መመራት ያለበት? የደንበኞች ጥበቃ እንዴት ነው መሆን ያለበት? የሚሉና ተያያዥ ጉዳዮችን የመዘርዘር ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img