Friday, December 8, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የመስከረም ወር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ባለፉት አምስት ዓመታት ከነበሩት ወራት ከፍተኛው ነው ተባለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ በየወሩ በሚያወጣው የዋጋ ግሽበት መረጃ መሠረት በተያዘው ወር 2014 ዓ.ም. የተመዘገበው አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት፣ ባለፉት አምስት ዓመታት ከነበሩት ወራት ከፍተኛው እንደሆነ ተገለጸ፡፡

 

ኤጀንሲው ይፋ ያደረገው የመስከረም ወር 2014 ዓ.ም. አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 34.8 በመቶ መድረሱን፣ ይህም አኃዝ ከ2009 ዓ.ም. ጀምሮ ለንፅፅር ከቀረቡት ወራት በከፍተኛነቱ የሚነሳ እንደሆነና ከዚህ በፊት ከፍተኛ የተባለውና 30.4 በመቶ የደረሰው አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት የተመዘገበው፣ በነሐሴ ወር 2013 ዓ.ም. እንደነበር ሪፖርቱ ያሳያል፡፡

በመስከረም ወር 2013 ዓ.ም. የነበረው አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 18.3 በመቶ የነበረ ሲሆን፣ በተያዘው የበጀት ዓመት ይህ አኃዝ ከፍተኛ የሆነ ጭማሪ ታይቶበት 34.8 በመቶ ደርሷል፡፡

የምግብ ዋጋ ግሽበት በመስከረም ወር 2014 ዓ.ም. 40 በመቶ ሲደርስ፣ ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት የነበረው ድርሻ 21.2 በመቶ ነበር፡፡ በሌላ በኩል ምግብ ነክ ያልሆኑ የኢንዴክሱ ክፍሎች የዋጋ ግሽበት በመስከረም ወር 2014 ዓ.ም. 25.2 በመቶ የደረሰ ሲሆን፣ ይህም አኃዝ ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት 15.5 በመቶ እንደነበር ሪፖርቱ ያሳያል፡፡

ዳቦና እህሎች ተብለው በተለዩ የምግብ ዓይነቶች ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ በመስከረም ወርም በከፍተኛነቱ ቀጥሏል፡፡ የሩዝ፣ የእንጀራ፣ የዳቦ፣ የጤፍ፣ የስንዴ፣ የማሽላ፣ የበቆሎ፣ የገብስ፣ የስንዴ ዱቄት፣ የፓስታና የማካሮኒ ዋጋ እንዲሁ ፈጣን ጭማሪ እንዳሳየ ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡ በተጨማሪም ሥጋ፣ የምግብ ዘይት፣ ወተት፣ ዓይብና ዕንቁላል፣ ቅቤ፣ ቅመማ ቅመምና ቡና ላይ የተስተዋለው የዋጋ ጭማሪ በመስከረም ወር በመቀጠሉ፣ ለዋጋ ግሽበት ምጣኔ በፍጥነት መጨመር አስተዋጽኦ አድርጓል ተብሏል። ከዚህ በተጨማሪም የምግብ ዘይት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነፃፀር ከውጭ በሚገባው የምግብ ዘይት ዋጋ ላይ የታየው ጭማሪ ከእጥፍ በላይ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

አልኮልና ትምባሆ፣ ልብስና ጫማ፣ ጫት፣ የቤት መሥሪያ ዕቃዎች፣ የቤት ኪራይ፣ ሲሚንቶ፣ የቤት ክዳን ቆርቆሮ፣ የቤት ዕቃዎችና የቤት ማስጌጫዎች፣ ሕክምናና ጌጣጌጥ (ወርቅ) ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ ሌላው ምግብ ነክ ያልሆኑ የኢንዴክሱ ክፍሎች የዋጋ ግሽበት፣ በመስከረም ወር ከፍ እንዲል ካደረጉት መካከል ተጠቃሾቹ እንደሆኑ ተመላክቷል፡፡

የእርስ በርስ ግጭቶችና የሰላም መደፍረስ በምርት ሰንሰለት፣ በግብዓት አቅርቦትና በምርት ሥርጭቶች ላይ ከፍተኛ ችግር መፈጠሩ የዋጋ ንረት እንዲባባስ ተጠቃሹ እንደሆነ፣ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች የሚያወሱት ጉዳይ ሲሆን፣ የገበያ ሰንሰለት ሥርዓቱን የሚያውክ ደላላና ሕገወጥነት የሚፈጥረው ችግር ሌላው የዋጋ ንረት መባባስ ምክንያት እንደሆነ ያነሳሉ፡፡

ጦርነት፣ የኮሮና ቫይረስ ዓይነት ድንበር ዘለል ወረርሽኞች፣ የኢኮኖሚ ማዕቀቦች፣ አንበጣና ሌሎች ተፈጥሯዊ ክስተቶች በአንዲት አገር ውስጥ ለሚፈጠረው የዋጋ ንረት ዓይነተኛ መንስዔ እንደሆኑ ሪፖርተር በተለያየ ጊዜ ያነጋገራቸው የኢኮኖሚ ምሁራን ይናገራሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች