Thursday, June 8, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በምሥረታ ላይ ያሉ ባንኮች ካፒታላቸውን እንዲያሟሉ የተሰጠው ቀነ ገደብ ሊጠናቀቅ ቀናቶች ብቻ ቀሩት

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በመጋቢት ወር 2013 ዓ.ም. ባወጣው መመርያ ባንክ ለማቋቋም ይጠይቅ የነበረውን የተከፈለ ካፒታል መጠን ወደ አምስት ቢሊዮን ብር ማሳደጉን ማሳወቁ ይታወሳል፡፡ በአዲሱ መመርያ መሠረት ነባር ባንኮች በአምስት ዓመታት ውስጥ ካፒታላቸውን አምስት ቢሊዮን ብር እንዲያደርሱ ሲደነግግ፣ በምሥረታ ላይ ያሉ ባንኮች ደግሞ በመመርያው የተደነገገውን ለማሟላት እስከ ሰባት ዓመት የጊዜ ገደብ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ይኼው መመርያ በምሥረታ ላይ ያሉ ባንኮች ግን 500 ሚሊዮን ብር ካፒታል በማሟላት ባንክ ማቋቋም የሚችሉበትን ዕድል የሰጠ ነው፡፡ በምሥረታ ላይ ያሉ ባንኮች ሲሠራበት በቆየው የ500 ሚሊዮን ብር ካፒታል ባንክ መመሥረት እንዲችሉ ብቻ ሳይሆን፣ ይህንን ካፒታል ለማሟላት የስድስት ወራት ጊዜ ሰጥቷቸዋል፡፡ በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ 500 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል አሟልተው ባንኩን መመሥረት ካልቻሉ ግን፣ በአዲሱ መመርያ መሠረት የግድ ባንክ ማቋቋም የሚችሉት የተከፈለ ካፒታል አምስት ቢሊዮን ብር እንደሚሆን በማስታወቅ በዚሁ መሠረት እንዲንቀሳቀሱ አሳስቦም ነበር፡፡ ይህንን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያ በተመለከተ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (/) በተለያዩ መድረኮች በምሥረታ ላይ ያሉ ባንኮች በተሰጣቸው ጊዜ ይጠቀሙ ዘንድ ሲያሳስቡ ቆይተዋል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ከስድስት ወራት በኋላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ሊሰጣቸው የሚችለው አዲስ በወጣው መመርያ መሠረት አምስት ቢሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ሲያቀርቡ ብቻ መሆኑንም መናገራቸው ይታወሳል፡፡

 

እንዲህ ያሉ ተከታታይ መረጃዎች በሚሰጡበት ወቅት የባንክ ኢንዱስትሪውን ለመቀላቀል የአክሲዮን ሽያጭ እያደረጉ ያሉና  በምሥረታ ሒደት ላይ የሚገኙ ባንኮች ወደ 17 የሚጠጉ ነበሩ፡፡ እነዚህ ባንኮች በስድስት ወራት ውስጥ 500 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ይዘው ባንክ ማቋቋም እንዲችሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዕገዛ አደርጋለሁ ማለቱም ይታወሳል፡፡

ከሁለት ወራት በፊት የጎህ ቤቶች ባንክ ምሥረታ በተካሄደበት ፕሮግራም ላይ የተገኙት ይናገር ደሴ አጋጣሚውን በመጠቀም እንዳሳሰቡትም፣ በምሥረታ ላይ ያሉ ባንኮች በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ 500 ሚሊዮን ብሩን ካፒታል አሟልተው የማይቀርቡ ከሆነ፣ ካፒታል ለማሟላት ምንም ዓይነት የማራዘሚያ ጊዜ የማይሰጥ ስለመሆኑ አስጠንቅቀዋል፡፡ ‹‹በምንም ሁኔታ ይህ ገደብ አይራዘምም፤›› በማለትም አክለዋል፡፡ የብሔራዊ ባንክ መመርያና የተሰጠ የጊዜ ገደብ ደግሞ በሚቀጥለው ሳምንት ጥቅምት 2 ቀን 2014 ዓ.ም. የሚያበቃ በመሆኑ ባንክ ለመመሥረት የአክሲዮን ሽያጭ ላይ ያሉና የሚፈለገውን ካፒታል ያላሟሉ ባንኮች ላይ ድንጋጤ ፈጥሯል፡፡

ሪፖርተር ባገኘው መረጃ መሠረት የአክሲዮን ሽያጭ እያካሄዱ ያሉና 500 ሚሊዮን ብር ካፒታል በማሟላት ምሥረታ ያላካሄዱ ባንኮች ከአሥር በላይ የሚደርሱ በመሆኑ፣ እስከሚቀጥለው ሳምንት ካፒታላቸው ሞልቶ ካላመለከቱ ቀጣይ ጉዟቸው አጣብቂኝ ውስጥ ይገባል ተብሏል፡፡ ከአንዳንድ በምሥረታ ላይ ከሚገኙ ባንኮች አካባቢ ያገኘነው መረጃ እንደሚጠቁመውም፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በቀጣዩ ሳምንት ቀነ ገደቡን ካላራዘመላቸው ቀጣይ ዕጣ ፈንታቸው የሚያሳስባቸው መሆኑን ነው፡፡  

ሌላው ያነጋገርናቸው የአንድ በምሥረታ ላይ የሚገኝ ባንክ አደራጅ ኮሚቴ አባል እንደገለጹት፣ የቀረው ጊዜ እጅግ አጭርና በቀናት የሚቆጠር በመሆኑ፣ የተባለውን ካፒታል ለማሟላት ስለማይቻል የግድ ብሔራዊ ባንክ የተወሰነ የማራዘሚያ ሊያደርግ ይገባል የሚል አመለካከት አላቸው፡፡

ብሔራዊ ባንክ ይህንን ማራዘሚያ የሚያደርግ ከሆነ በአዲሱ መመርያ መሠረት የሚጠይቀውን አምስት ቢሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል በማሰባሰብ ባንኮቹን ማቋቋም ይኖርባቸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅ ይህንን ለማድረግ ግን ፈጽሞ የማይቻሉ በመሆኑ የእስካሁኑን እንቅስቃሴያቸውን እንዲያቋርጡ ያደርጋቸዋል የሚል ሥጋት አሳድሮባቸዋል፡፡

የኢኮኖሚ አማካሪና እየተቋቋመ ያለው የሰላም ባንክ አደራጅ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ እንደሚገልጹት ከሆነ፣ በሚቀጥለው ሳምንት ያበቃል የተባለው ቀነ ገደብ ትክክለኛ ትርጓሜ እስከ ቀነ ገደቡ ድረስ ስለሆነ፣ ከባለአክሲዮኖች የተሰባሰበው የተከፈለ ካፒታል 500 ሚሊዮን ብር በባንክ ካላቸው፣ ባንክ ማቋቋም የሚችሉበት ዕድል ያላቸው መሆኑን ነው፡፡፡

አዲስ በወጣው ሕግ መሠረት የሚቋቋም ባንክ ወይም የጊዜ ገደብ ተሰጥቶት 500 ሚሊዮን ብር ያላሟላ በመደራጀት ላይ ያለ ባንክ ካለ፣ ባንክ ማቋቋም የሚቻለው በአምስት ቢሊዮን ብር ብቻ መሆኑን ገልጸው፣ እንደ ሰላም ባንክ ግን የካፒታሉ መጠን ቀነ ገደቡ አያሳስበውም ይላሉ፡፡ 500 ሚሊዮን ወይም አምስት ቢሊዮን የሚለው ነገር ሳይሆን፣ ለእኛ ዋናው ነገር እንደ ሰላም ባንክ ከመንግሥት የምንፈልገው የቤቶችና ቁጠባ (ሞርጌጅ) ባንክን የተመለከተ መመርያ ስለመሆኑ ጠቅሰዋል፡፡ የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ኢንቨስተሮች ስናነጋግር የሚጠይቁን ‹‹በየትኛው የሞርጌጅ ሕግ ነው የምትተዳደሩት›› ብለው በመሆኑ የሞርጌጅ ባንክን ሥራ ላይ ለማዋል ራሱን የቻለ ሕግ ያስፈልጋል ይላሉ፡፡ ምክንያቱም ሞርጌጅ ባንክ ከንግድ ባንክ በጣም የተለየና እስከ 30 ዓመት የሚሆን ብድር የሚሰጥ በመሆኑ፣ እንደ ሌላው የንግድ ባንክ መታየት የለበትም የሚል እምነትም አላቸው፡፡ ስለዚህ ከመንግሥት አሁን የምንፈልገው ትብበር የማቋቋሚያ ካፒታል ይህንን ያህል ይሁን ወይም አይሁን የሚለው ሳይሆን፣ በተለየ ሁኔታ ለሞርጌጅ ባንክ የሚሆን መመርያ ወይም ሕግ ከብሔራዊ ባንክ እንዲወጣ መሆኑን አቶ ዘመዴነህ ገልጸዋል፡፡

 ብሔራዊ ባንክ የቤቶችና ቁጠባ ባንክ የሚመራበትና የሚሠራበት ራሱን የቻለ ሕግ ሊኖረው ይገባል በማለት፣ እንደ ሰላም ባንክም ከሚጠብቋቸው ነገሮች መካከል እንዲህ ያለውን ሕግ ስለመሆኑ ያብራሩት አቶ ዘመዴነህ፣ ሌላው የውጭ ኢንቨስተሮች ሞርጌጅ ባንኮች ውስጥ እንዲገቡ በመንግሥት ደረጃ የተፈቀደ በመሆኑ፣ ‹‹ብሔራዊ ባንክ ሕግ ማውጣት አለበት፤›› ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የቤት እጥረት ለመቅረፍ ተብሎ የውጭ ባለሀብቶች ጭምር የሚሳተፉበት አሠራር እንዲኖር፣ በመንግሥት ደረጃ ውሳኔ ተሰጥቶ ሳለ፣ እስካሁን ግን ይህንንም የተመለከተ ሕግ አለመውጣቱን ጠቅሰዋል፡፡ መንግሥት አሁን ያለውን የቤት ችግር ለመቅረፍ የሞርጌጅ ባንኮችን በማስፋፋት ለዚህ የሚሆን ፋይናንስ እንዲቀርብ ማድረግን እንደ ፖሊሲ የወሰደው በመሆኑ፣ የሞርጌጅ ባንክ ሕግ የግድ ያስፈልጋል ብለው ይሞግታሉ፡፡ አቶ ዘመዴነህ፣ ‹‹እንደሰላም ባንክ ከካፒታል መጠን በላይ የሚያሳስበን ለሞርጌጅ ባንክ ራሱን የቻለ ሕግ እንዲኖርና የውጭ ኢንቨስተሮች በሞርጌጅ ባንክ ውስጥ እንዲሳተፉ የሚፈቅደው ሕግ መውጣቱ ነው፤›› ብለዋል፡፡

እንዲህ ያለው ሁኔታ በሞርጌጅ ባንክ በኩል ብቻ ሳይሆን ከንግድ ባንክ ውጪ ለሚቋቋሙ ባንኮች የተለየ ሕግ ሊኖራቸው ይገባል ያሉት አቶ ዘመዴነህ፣ አሁን ባለው ሁኔታ ግን በኢትዮጵያ ውስጥ በልዩ ሁኔታ ለሚቋቋሙ ባንኮች ሕግ የለም፡፡ የሞርጌጅ፣ ኢንዱስትሪና ለእርሻ ባንክ የሚሆን ሕግ የለም፡፡ ዛሬ የእርሻ ባንክ ለማቋቋም ቢፈለግ፣ በምን መልክ ነው የሚቋቋመው የሚል ጥያቄ ቢነሳ መልስ የሚሰጥ ሕግ ያለመኖሩ ደግሞ፣ አሠራርና ቁጥጥር ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድር ከመቻሉም በላይ፣ የውጭ ኢንቨስተር ሊገባ ቢችል እንኳን ይህንን ሊያስተናግድ የሚችል ሕግ ያለመኖሩ አስቸጋሪ ያደርገዋል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

አሁን በመቋቋም ላይ ያሉ ባንኮች ግን በአብዛኛው የንግድ ባንኮች መሆናቸውን ያስታወሱት አቶ ዘመዴነህ፣ 500 ሚሊዮን ብሩን እስካሁን ካሏሟሉ እስካሁን በየፊናቸው ያሰባሰቡትን ካፒታል በማዋሀድና 500 ሚሊዮን ብሩን በማሟላት ባንክ መመሥረት ነው፡፡

እነዚህ በአክሲዮን ሽያጭ ላይ የቆዩት በምሥረታ ላይ ላሉ ባንኮች ሌላ አማራጭ ሆኖ የሚቀርበው፣ ተዋህደው ባንክ ሊመሠርቱ ይችላሉ የሚለው ሐሳብ ግን፣ አሁን ባለው ደረጃ ጊዜ ያላቸው ባለመሆኑ ተዋህደው ይሥሩ የሚለው ሐሳብ ብዙ ዕድል የሌለው መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ እንደ አቶ ዘመዴነህ ምልከታ ግን በምሥረታ ላይ ያሉ ባንኮች አክሲዮን ሽያጫቸውን አንድ በማድረግ እስከ ቀነ ገደቡ ድረስ 500 ሚሊዮን ብር በባንክ ካላቸው ምሥረታውን የሚከለክላቸው ነገር ያለመኖሩን ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በአዲሱ የንግድ ሕግ ውህደትን በተመለከተ የተቀመጠው ሕግ በ21 ቀናት ውስጥ በጋዜጣ ጭምር ማሳወጅን የሚጠይቅ በመሆኑ፣ የውህደቱ ጉዳይ የሚሳካ አለመሆኑን ነው፡፡ ይህም የተሰጠው የጊዜ ገደብ ከተጣለ በኋላ በቅርቡ ምሥረታቸውን ያካሄዱ ባንኮች ጥቂት በመሆናቸው አብዛኞቹ ዕጣ ፈንታቸው በብሔራዊ ባንክ ውሳኔ ላይ እንዲንጠለጠል አድርጎታል፡፡ ካለፈው ዓመት ወዲህ በ500 ሚሊዮን ብር ካፒታል ማቋቋም እንደሚችሉ ምሥረታቸውን ካካሄዱት መካከል፣ አማራ ባንክ፣ አኃዱ ባንክ፣ ራሚስ ባንክ፣ ሒጅራ ባንክ፣ ጎህ ቤቶች ባንክና ገዳ ባንኮች ይገኙበታል፡፡ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ ሁለቱን መንግሥታዊ ባንኮች ጨምሮ በይፋ ሥራ የጀመሩ ባንኮች ቁጥር 21 የደረሰ ሲሆን፣ በቀጣይ በተከታታይ ኢንዱስትሪውን ይቀላቀላሉ ተብለው የሚጠበቁ ባንኮች የኢትዮጵያን ባንኮች ቁጥር ከ30 በላይ ያደርሱታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች