Thursday, June 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሦስተኛው ከወለድ ነፃ ባንክ የምሥረታ ጉባዔውን አካሄደ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት ለመስጠት ሦስተኛው ባንክ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው ራሚስ ባንክ አ.ማ. የምሥረታ ጉባዔውን በማካሄድ የመጀመርያዎቹን የቦርድ አመራሮች መረጠ፡፡

ራሚስ ባንክ አ.ማ. ቅዳሜ መስከረም 22 ቀን 2014 ዓ.ም. ባካሄደው የምሥረታ ጉባዔ ላይ እንደተገለጸው፣ ባንኩ በ724 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል መያዙን ገልጿል፡፡ የሸሪዓ ሕግን ተከትሎ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በመስጠት የኢትዮጵያን የባንክ ኢንዱስትሪ የሚቀላቀለው ራሚስ ባንክ፣ ወደ ሥራ በሚገባበት ወቅት ‹‹ትኩረት አድርጌ እሠራበታለሁ›› ብሎ ከገለጻቸው መካከል፣ በግብርና ዘርፍ ፋይናንስ አቅርቦት አንዱ ነው፡፡ የዋቢ ሸበሌ ገባር ወንዝ በሆነው ራሚስ ወንዝ ስያሜው ያደረገው ይህ ባንክ፣ ከስድስት ሺሕ በላይ ባለአክሲዮኖች ያሉት ባንክ ነው፡፡

በቅዳሜው የባንኩ የምሥረታ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ 81 በመቶ ምልዓተ ጉባዔ ተሟልቶ ምሥረታው የተካሄደ ሲሆን፣ ተሳታፊ የጠቅላላ ጉባዔ ባለአክሲዮኖችም 13 አባላት ያሉትን የመጀመርያዎቹን የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት መርጧል፡፡

ከባንኩ አደራጆች ገለጻ ለማወቅ እንደተቻለው፣ ራሚስ ባንክ የአክሲዮን ሽያጭ ከጀመረ ሁለት ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም፣ በኮቪድ-19 ምክንያት በታሰበው ጊዜ አክሲዮኑን ሸጦ ለመጨረስ አልቻለም፡፡ አሁን ላይ ግን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያ በሚፈቅደው መሠረት ባንክ ለማቋቋም የሚያስችለውን ካፒታል በማሰባሰብና በመሙላት ምሥረታውን ሊያካሂድ መቻሉን አመልክተዋል፡፡

 በዚሁ መሠረት ቀሪ ብሔራዊ ባንክ የሚጠይቃቸውን መሥፈርቶች በማሟላት በቅርቡ ወደ ሥራ ለመግባት እየተዘጋጀ መሆኑንም አሳውቀዋል፡፡

ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቶች ጋር በተያያዘ ገና ያልተሠሩባቸው በርካታ የአገልግሎት ዓይነቶች ስላሉ ይህንኑ ታሳቢ ያደረጉ አዳዲስ አገልግሎቶችን ይዞ ወደ ገበያ የሚገባ ስለመሆኑም ከባንኩ አደራጆች ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ በባንኩ ምሥረታ ወቅትም ይኼው በሰፊው የተብራራ ሲሆን፣ በገበያ ውስጥ ጎልቶ ለመውጣት ያስችለኛል ብሎ የተዘጋጀባቸውን ስትራቴጂዎችና ዕቅዶች ለባንኩ ባለአክሲዮኖች በተሰጠው ማብራሪያ አስታውቋል፡፡

መንግሥት ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት መስጠት የሚችል ባንክ ማቋቋም እንደሚችል ከፈቀደ ወዲህ፣ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ የጠየቁ ስድስት ባንኮች የነበሩ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ ሁለቱ ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ ቀሪዎቹ ሦስት ባንኮች ግን እስካሁን ምሥረታቸውን እንኳን አላካሄዱም፡፡ ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት ከመፈቀዱ በፊት ባንኮች በመስኮት ደረጃ ከወለደ ነፃ የባንክ አገልግሎት እየሰጡ በተፈቀደው መሠረት አሥራ አንድ ባንኮች ይህንኑ አገልግሎት ለመስጠት ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ወስደው እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ እስካሁንም በመስኮትና ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰባሰበ የቁጠባ ባንክ መጠን ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች