ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ(ዶ/ር) መስከረም 27 ቀን 2014 ዓ .ም ለከፍተኛ የመንግስት ኃላፊነት ቦታዎች ሹመቶችን የሰጡ ሲሆን አቶ ተፈሪ ፍቅሬን በድጋሚ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈትቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር አድርገው ሾመዋል፡፡
የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ የነበሩት አቶ አደም ፋራህን በሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ዋና አስተባባሪ ፣ አቶ ተስፋዬ ቤልጅጌን በሚኒስትር ማዕረግ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ ፣ የቀድሞ የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚንስትር የነበሩትን ስለሺ በቀለ ( ዶ/ር)ን በሚኒስትር ማዕረግ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞችና የህዳሴ ግድብ ዋና ተደራዳሪና አማካሪ አድርገው ሾመዋል።
በተጨማሪም አዲስ ለተቋቋመው የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊነት ለገሰ ቱሉ ዶ/ር በሚኒስትር ማዕረግ የሾሙ ሲሆን ፤ ዶ/ር ምህረት ደበበን የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዚዳንት ፣ አቶ ፍሰሃ ይታገሱን የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፣ አቶ አብዱራህማን ሩቤ ደግሞ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አድርገው መሾማቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡