Saturday, December 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ቢሮ በሩብ ዓመት ከ12 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ሰበሰብኩ አለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ በተያዘው የበጀት ዓመት የመጀመርያው ሦስት ወራት፣ ከ12.2 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ፡፡

ቢሮው እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2014 .ም. ድረስ የሚዘልቅ ግብር የማሳወቅና የመሰብሰብ ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጾ፣ እስከ መስከረም 2014 ዓ.ም. መጨረሻ ሳምንት ባለው ጊዜ ከግብር አሰባሰቡ የተገኘው ገቢ ከታቀደው በላይ እንደሆነ አስታወቋል፡፡

የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊነትን አዲስ በተመረጠው የከተማ አስተዳደር እንዲመሩ በድጋሚ የተመረጡት አቶ ሙሉጌታ ተፈራ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ ገቢዎች ቢሮው በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የተጀመሩትን የከተማዋን ገቢ በተጠናከረ ሁኔታ የመሰብሰብ ሥራ ዘመናዊ በሆነ ሥርዓትና ቅንጅታዊ አተገባበር እየተከናወነ ነው፡፡

በተያዘው በሩብ ዓመት ይሰበሰባል ተብሎ የታቀደው የግብር ገቢ 11.5 ቢሊዮን ብር እንደሆነ ያስታወቁት ኃላፊው፣ ከሦስት ያላነሱ ቀናት የገቢ አሰባሰብ መረጃ ሳይካተት እስከ መስከረም 27 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ 12.26 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን ገልጸዋል፡፡

የተሰበሰበው ገቢ ከታቀደው ዕቅድ ጋር ሲነፃፀር የ105 በመቶ አፈጻጸም ታይቶበታል የተባለ ሲሆን፣ ከገቢ አንፃር አምና ተመሳሳይ ወቅት ከተሰበሰበው ጋር ሲነፃፀር በሦስቱ ወራት የተሰበሰበው ገቢ የ40 በመቶ ዕድገት የታየበት እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ገቢዎች ቢሮ በሐምሌና በነሐሴ ወራት የሚሰበስበው ግብር የደረጃእና” እንደሆነ አስታውቆ፣ ከእነዚህ የግብር ከፋይ ምድቦች የሚሰበሰበው ገቢ ጥሩ በሚባል ደረጃ እንደተጠናቀቀ ገልጿል፡፡ ቢሮው ከሁለቱ የደረጃ ምድቦች በሁለቱ ወራት ለመሰብሰብ ያቀደው 8.7 ቢሊዮን ብር እንደነበር የተገለጸ ሲሆን፣ ሆኖም በክንውኑ እንደተመዘገበው በሁለቱ ወራት ውስጥ የተሰበሰበው 10.4 ቢሊዮን ብር እንደነበረና ይህም ገቢ የዕቅዱን 119.8 በመቶ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡

በ2013 ዓ.ም. ሐምሌና ነሐሴ ወራት ውስጥ የተሰበሰበው ገቢ 7.5 በሊዮን ብር እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ በተያዘው የበጀት ዓመት ሁለት ወራት የተገኘው ገቢ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ2.9 በሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

በሩብ ዓመቱ ከተሰበሰበው ገቢ ቀጥተኛ የሚባለው ገቢ ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዝ፣ ሌሎች የገቢ ዓይነቶችን በታቀደው መንገድ ለመሰብሰብ እንደተቻለ አቶ ሙሉጌታ ተናግረዋል፡፡

በተያዘው የ2014 የበጀት ዓመት 48.5 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ ለመሰብሰብ ቢሮው ግብ ማስቀመጡ የሚታወስ ሲሆን፣ ይህንን ዕቅድ በመሠረታዊነት ለማሳካት ከሚከናወኑ ሥራዎች መካከል በአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮና በግብር ከፋዩ ኅብረተሰብ መካከል፣ እንዲሁም በሚመለከታቸው የከተማ አስተዳደሩ አስፈጻሚ አካላት መካከል ያለውን ግንኙነት ማጠናከር እንደሆነ አቶ ሙሉጌታ ጠቁመዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከሚከናወኑ ዋነኛ ተግባራት መካከል የታክስ ሥርዓቱን ማስፋት ዋነኛው እንደሆነ የጠቀሱት የቢሮው ኃላፊ፣ ይህም ወደ ታክስ ሥርዓቱ ያልገቡ አካላትን እንዲገቡ ማድረግና ከዚህ ቀደም ወደ በስፋት ያልተሠራባቸው ዘርፎች ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የሕንፃ ኪራይና የውጭ ማስታወቂያ ገቢ ከዚህ ቀደም በተፈለገው ልክ ገቢ ያልተሰበሰበባቸው ዘርፎች እንደነበሩ ያስተወቁት ኃላፊው፣ ከእነዚህ ዘርፎች ገቢን በአግባቡ ከመሰብሰብ ጎን ለጎን የንግድ ፈቃድ ሳያወጡ በንግድ ሥራ ላይ ተሠማርተው የሚሠሩ ዜጎች ሕጋዊ የንግድ ፈቃድ አውጥተው ወደ ታክስ ሥርዓቱ እንዲገቡ ማድረግ፣ ቢሮው ትኩረት ሰጥቶ እየሠራበት የሚገኝ ተግባር እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የገቢዎች ቢሮው የገቢ አሰባበሰብ ሒደቱ ዘመናዊ ሊሆን ይገባል ብሎ በደረጃ “ሀ” የጀመራቸውን የዲጂታል ሥርዓቶች፣ በቀሪዎቹ የደረጃእና” ግብር ከፋዮች በተያዘው የበጀት ዓመት በስፋት እንደሚሠራ ተጠቅሷል፡፡

የገቢ አሰባሰብ አገልግሎት በመስጠት ሒደት የኔትወርክና ሌሎች ተያያዥ እክሎች እንዳይገጥሙ ከኢትዮ ቴሌኮም፣ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትና ከባንኮች ጋር የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡

በግብር ሰብሳቢ ቢሮውም ሆነ በግብር ከፋዩ ኅብረተሰብ ከሚነሱ ተግዳሮቶች መካከል ደረሰኝን በሚመለከት የሚነሳው ችግር አንዱ እንደሆነ የተናገሩት ኃላፊው፣ ሕገወጥ ደረሰኝ፣ ሐሰተኛ ደረሰኝና ያለደረሰኝ መገበያየትን የተመለከቱት ችግሮች መፍትሔ ሊያገኙ የሚገቡ ጉዳዮች እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

ችግሩን ለመቅረፍ ኅብረተሰቡ በሕጋዊ ደረሰኝ እንዲገበያይ ግንዛቤ ከመፍጠር  አንስቶ፣ በሕጋዊ ደረሰኝ የማይገበያዩትን ለሕግ የማቅረቡ ሥራ የተያዘው የበጀት ዓመት ዋነኛ ተግባር እንደሆነ አቶ ሙሉጌታ አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች