ኢትዮጵያ በተለያዩ አጋጣሚዎች ያገኘቻቸው ዕድሎች ሲበላሹ የኖሩት አንድ ላይ ለመሥራት ጥረት ከማድረግ ይልቅ፣ ጥቃቅን ልዩነቶችን ከመጠን በላይ በመለጠጥ ቅራኔ የመፍጠር ልማድ በመንሰራፋቱ ነው፡፡ የአንድ አገር ልጆች በተለያዩ ጉዳዮች መለያየታቸው ተፈጥሯዊ ቢሆንም፣ ልዩነቶቻቸው ግን አብረው ከመሥራት እንደማያግዷቸው መረዳት የግድ መሆን ነበረበት፡፡ ኢትዮጵያዊያን ያለፈውን አሳዛኝ የታሪክ ምዕራፍ በመዝጋት ለሰላማዊ ውይይት፣ ክርክርና ድርድር ከመዘጋጀት ባለፈ፣ መለስተኛ ልዩነቶችን ይዞ ለአገር አብሮ መሥራት ይቻላል ማለት አለባቸው፡፡ የኢትዮጵያ ችግሮች የሚፈቱት ለልዩነቶች ዕውቅና ሰጥቶ ተባብሮ በመሥራት እንጂ፣ በጠመንጃ አፈሙዝ እንዳልሆነ ማንም አይስተውም፡፡ በአዲሱ መንግሥት ካቢኔ የተፎካካሪ ፓርቲዎች አመራሮች እንዲካተቱ የመደረጋቸው መልካም ጅምር መበረታታት አለበት፡፡ አብሮ መሥራት እየተቻለ ፋይዳ በሌላቸው ምክንያቶች መተናነቅ የኋላቀርነት እንጂ፣ የሥልጣኔ ማሳያ እንዳልሆነ መተማመን ያስፈልጋል፡፡ የኢትዮጵያ የዘመናት ችግሮች በቅደም ተከተል እንዲፈቱ የሚፈልጉ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ፣ አዲሶቹ ተሿሚዎች የተሰጣቸውን ኃላፊነት በገቡት ቃል መሃላ እንዲያከናውኑ ዕገዛ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ አሁን የሚያስፈልጋት ሰላም እንዲሰፍን በአንድነት የመሥራት አስፈላጊነትን አፅንኦት መስጠት የግድ መሆን አለበት፡፡ አገርን በቅንነት ማገልገል ያስከብራል፡፡
በኢትዮጵያ ረዥሙ ታሪክ ውስጥ ለሥልጣን ተቀናቃኝ የሚሰጠው ምላሽ ዱላ፣ እስር፣ ግዞት፣ ማሳደድ፣ ባስ ሲልም ግድያ እንደነበር የሚካድ አይደለም፡፡ በነገሥታቱ ዘመንም ሆነ ከዚያ በኋላ ለዘመናት የሚታወቅ ነው፡፡ ይህ አስከፊ ድርጊት በዚህ ዘመን ሲፈጸም ለመኖሩ ደግሞ፣ ከሕወሓት መራሹ ኢሕአዴግ በላይ ምስክር አይኖርም፡፡ ረቡዕ መስከረም 26 ቀን 2013 ዓ.ም. በስድስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንደኛ መደበኛ ስብሰባ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የአዲሱን ካቢኔያቸውን ዕጩ ተሿሚዎች ሲያፀድቁ፣ ሦስት የተፎካካሪ ፓርቲዎች አመራሮችን ማካተታቸው ከፍተኛ የሆነ ድጋፍ ሊቸረው ይገባል፡፡ እሳቸው እንዳሉት የአዲሱ ካቢኔ አወቃቀር ሙሉ በሙሉ ከእንከን የፀዳ ባይሆን እንኳን፣ ለአገር ከሚኖረው ትልቅ ፋይዳ አኳያ ተፎካካሪዎች ለሥልጣን መብቃታቸው የታሪካችን አዲስ ምዕራፍ ተደርጎ መወሰድ አለበት፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ውሳኔ መደገፍ ያለበት ጥላቻና ቂም በቀል በነገሡበት የአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዋር ውስጥ በመከናወኑ ነው፡፡ እርግጥ ነው ለፀጉር ሰንጣቂዎች ይህ ዓይነቱ ታላቅ ዕርምጃ እንደ ተራ ነገር ሊታይ ይችላል፡፡ ነገር ግን አስተዋይ ለሆኑ በሳል ሰዎች ግን ትርጉሙ ላቅ ያለ ነው፡፡ አገርን በቅንነት ማገልገል መለመድ አለበት፡፡
አንድ በሚገባ መታወቅ ያለበት የኢትዮጵያ ህልውና ከግለሰብም ሆነ ከፓርቲ ፍላጎት በላይ መሆኑን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ እጅግ አስከፊ ከሆነው ድህነት ተገላግሎ በዕድገት ጎዳና ላይ ለመጓዝ ሰላም ያስፈልገዋል፡፡ ዘመኑን ከማይመጥን ኋላቀር አስተራረስ ተላቆ የተትረፈረፈ ምርት እንዲያገኝ መረጋጋት መፈጠር አለበት፡፡ ልጆቹ ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኙና የቴክኖሎጂ ባለቤት እንዲሆኑ ግጭትና ፍጅት መቆም አለበት፡፡ ከጎስቋላ ኑሮና ከተመፅዋችነት ተላቆ አንገቱን ቀና አድርጎ እንዲኖር ሰላማዊ የፖለቲካ ምኅዳር መኖር ይኖርበታል፡፡ የአገሩ የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ተከብሮ በነፃነት እንዲኖር፣ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶቹን የሚያስከብርለት ሥርዓት መገንባት አለበት፡፡ በኢትዮጵያ ምድር መንግሥት የሚመሠረተው በሕዝብ ነፃ ድምፅ እንጂ፣ በጉልበት መሆን እንደሌለበት መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ እነዚህና ሌሎች መሠረታዊ ፍላጎቶች የሚሟሉት፣ ኢትዮጵያዊያን ልዩነቶቻቸውን አጥብበው ለጋራ አገራቸው ለመሥራት በአንድነት ሲቆሙ ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን ሲስማሙና በጋራ ብሔራዊ ጉዳዮቻቸው ላይ መነጋገር ሲጀምሩ፣ ከታሪካዊ ጠላቶች በላይ የሚከፋው እንደሌለ መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የምታተርፈው ልጆቿ ልዩነቶቻቸውን ውበት አድርገው በጋራ ሲያለሟት እንጂ፣ ጎራ ለይተው በጦር መሣሪያ እየተጨፋጨፉ ንፁኃንን ሲፈጁና ንብረት ሲያወድሙ እንዳልሆነ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ጠመንጃ አምላኪነት ለውድመት ካልሆነ በስተቀር ለልማት አይበጅም፡፡ በሕዝብ ስም እየማሉና እየተገዘቱ ከዕልቂትና ከውድመት በስተቀር ምንም ነገር የማይታያቸው ከታሪክ ይማሩ፡፡ አገር የምትፈልገው ልጆቿ ተባብረው እንዲያሳድጓት ነው፡፡ ሕዝብ እየፈጁና እያፈናቀሉ፣ እንዲሁም የአገር አንጡራ ሀብት እያወደሙ ማንንም ማታለል አይቻልም፡፡ አገርን በቅንነት ማገልገል ነው የሚበጀው፡፡
በኢትዮጵያ ከጠመንጃ አምላኪነት የተላቀቀ ሰላማዊ ሥርዓት መፈጠር አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ የፖለቲካ ምኅዳሩን በሰፊው መክፈት አስፈላጊ ነው፡፡ በዚህ ዓውድ ውስጥ ለብሔራዊ መግባባት የሚያግዙ የውይይትና የክርክር መድረኮች በብዛት እንዲፈጠሩ በማድረግ፣ ለአመፅና ለትርምስ የሚያነሳሱ ሰበቦችን ማክሰም ይገባል፡፡ ኢትዮጵያዊያን በእኩልነት ሲነጋገሩና ሲደማመጡ ማኅበራዊ ፍትሕ ይሰፍናል፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ይረጋገጣል፡፡ አንዱ ባለቤት ሌላው መጤ እንዲሆን የሚያደርጉ ብልሹ አሠራሮች ይወገዳሉ፡፡ በዘርና በእምነት በመቧደን አገር መዝረፍ ነውር ይሆናል፡፡ ከሕዝብና ከአገር በላይ ለመሆን የሚደረግ ሥርዓተ አልበኝነት ይመክናል፡፡ ዜጎች በሕግ ፊት እኩል መሆናቸው በተግባር ይታያል፡፡ በብሔርና በእምነት እየተከለሉ ሥልጣን መያዝና ያለ ልፋት ሀብት ማግበስበስ ይቀራል፡፡ ለዕውቀት፣ ለልምድና ለሥነ ምግባር ከፍ ያለ ቦታ ይሰጣል፡፡ ሁሉም ማንነቶችና እምነቶች በእኩልነት የሚስተናገዱበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ይለመልማል፡፡ ያኔ ልዩነቶች ጌጥ ሆነው በነፃነት መኖር ባህል ይሆናል፡፡
ኢትዮጵያዊያን በዚህ ወሳኝ ጊዜ ጠንካራ፣ ደፋር፣ አርቆ አሳቢና አሰላሳይ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ በስሜት ሳይሆን በምክንያት የሚመራ ሕዝብ የማንም መጫወቻ አይሆንም፡፡ ለአገር ደንታ የሌላቸው እየተሰባሰቡ ወጣቱን የመንጋ ፖለቲካ ቅርቃር ውስጥ የሚከቱት፣ በምክንያት ሳይሆን በስሜት መነዳት በመለመዱ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን አገራቸው በሕግ የበላይነት ስትተዳደር ሥልጣን መባለጊያ እንደማይሆን ማወቅ አለባቸው፡፡ ሥልጣን የሕዝብ ማገልገያ እንጂ ራስንና ቢጤዎችን ማበልፀጊያ መሆን እንደሌለበት ሽንጣቸውን ገትረው መሟገት የሚችሉት፣ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ክርክር ለማድረግ አቅም ሲገነቡ ነው፡፡ ጥቂቶች እየተቧደኑ ራሳቸውን ከአገር በላይ ለማድረግ ሲሞክሩ በሕግ ማለት የሚቻለው፣ የሴረኞችን ብልጣ ብልጥ የፖለቲካ አካሄድ መገንዘብ ሲቻል ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በኢትዮጵያ ምድር የውይይትና የክርክር ባህል እንዲለመድ መትጋት ይገባል፡፡ ከሐሜት፣ ከአሉባልታ፣ ከጥላቻና ከአላስፈላጊ ድርጊቶች በመታቀብ ለልማትና ለዕድገት በጋራ መነሳት የግድ ይላል፡፡ ለሐሳብ ልዕልና ትኩረት በተሰጠ ቁጥር ለአገር የማይጠቅሙ መናኛ ጉዳዮች ሥፍራ አይኖራቸውም፡፡ ኢትዮጵያን የታሪካዊ ጠላቶች ተጋላጭ የሚያደርጉ ከንቱ ጭቅጭቆችና ትንቅንቆች ፈላጊ ያጣሉ፡፡ በሕዝብ ስም መነገድም ሆነ መቆመር ጊዜ ያለፈበት ፋሽን ይሆናል፡፡ ይህ ምኞት ዕውን ይሆን ዘንድ ኢትዮጵያን ለአገራቸው በአንድነት ይቁሙ፡፡
ለአገር ሲባል ልዩነትን ማለዘብና መቀራረብ የሚበረታታ ነው፡፡ ኢትዮጵያም ወደፊት መራመድ የምትችለው በመደነቃቀፍ ሳይሆን፣ በመተባበር እንቅፋቶችን በማስወገድ ነው፡፡ ልዩነት መቼም ቢሆን የሚኖር ነው፡፡ ልዩነት የተሻሉ ሐሳቦች ነጥረው እንዲወጡ ማገዝ አለበት እንጂ፣ የአንድ አገር ልጆችን ጎራ አስለይቶ ማፋጀት የለበትም፡፡ በነፃነት ስም ፍጅትን መስበክም ሆነ ተባባሪ መሆን የአገር ጠላት ከመሆን አይለይም፡፡ ዳር ሆኖ መተቸት ብቻ ሳይሆን መሀል ገብቶ አገርን ለማገልገል መነሳት፣ ወይም የሚያገለግሉትን ማበረታታት የኢትዮጵያዊያን ኃላፊነት መሆን አለበት፡፡ ጥቃቅን ልዩነቶችን በአጉሊ መነጽር እየፈለጉ እንጫረስ ማለት ዕብደት እንጂ ጤነኝነት አይደለም፡፡ በዚህ መንገድ የሚሳካ ዓላማም አይኖርም፡፡ አለ የሚሉ ካሉ ሕዝብ ከማስጨረስና አገር ከማውደም የዘለለ ውጤት አያስገኙም፡፡ አገራቸውን የሚወዱ ኢትዮጵያዊያን ግን እስከ መጨረሻው ህቅታቸው ድረስ ለአገራቸው ሰላም፣ ልማት፣ ዕድገትና ለሕዝባቸው ዘለቄታዊ ደኅንነትና ጥቅም መታገል ይጠበቅባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ በየዘመናቱ በነበሩ ልጆቿ ዕውቀት፣ ላብ፣ ደምና አጥንት ዋጋ ተከፍሎባት እዚህ የደረሰች አገር እንጂ፣ ማንም እየተነሳ የሚፈነጭባት አለመሆኗን ማስመስከር የዚህ ትውልድ ኃላፊነት ነው፡፡ ጀርባ እየተሰጣጡ የመበላላት የታሪክ ምዕራፍ ይዘጋ፡፡ ኢትዮጵያን መውደድ ብቻ ሳይሆን በቅንነት ማገልገልም ግዴታ ይሁን!