የትግራይ ክልል ሰብዓዊ ቀውስ እ.ኤ.አ እስከ ኦክቶበር 2021 የመጨረሻ ቀን ድረስ ትርጉም ያለው መሻሻል ካላሳየ ማዕቀብ እንደሚጥል፣ የአውሮፓ ኅብረት አስታወቀ፡፡
የአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ ባለፈው ረቡዕ መስከረም 26 ቀን 2014 ዓ.ም. የትግራይ ክልል ሰብዓዊ ቀውስን የተመለከተ የውሳኔ ሐሳብ ያሳለፈ ሲሆን፣ በክልሉ ያለው ሰብዓዊ ቀውስ ትርጉም ባለው መልኩ መሻሻል ካልታየበት በክልሉ በተቀሰቀሰው ግጭት ተሳታፊዎች ላይ ማዕቀብ ለመጣል የጊዜ ገደብ አስቀምጧል፡፡
ባስቀመጠው የጊዜ ገደብም እስከ መጪው ጥቅምት ወር አጋማሽ ወይም እ.ኤ.አ. እስከ ኦክቶበር ወር መጨረሻ ድረስ ሰብዓዊ ቀውሱ ካልተሻሻለ የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን በክልሉ ያለው ግጭት እንዲቀጥል ባደረጉ የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት አመራር አባላት፣ በሕወሓትና በኤርትራ መንግሥት መሪዎች ላይ ማዕቀብ እንዲጣል የውሳኔ ሐሳብ አፅድቋል፡፡
የአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ ባፀደቀው በዚህ የውሳኔ ሐሳብ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታ ምክር ቤት የትግራይ ክልል ሁኔታን የተመለከተ ውሳኔ እስከዛሬ ማሳለፍ ባለመቻሉ፣ የተሰማውን ቅሬታ በመግለጽ፣ የአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮች የፀጥታ ምክር ቤቱ በትግራይ ክልል ቀውስ ላይ እንዲመክርና በክልሉ ለተፈጸሙ ሰብዓዊ ጥሰቶች ተጠያቂነትን እንዲያሰፍን ጫና እንዲያደርጉ ጥሪውን አቅርቧል፡፡
በማከልም በትግራይ ክልል ሰብዓዊ ቀውስ እንዲቆምና ሲቪል ሰዎችን ለመጠበቅ እንዲቻል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰላም አስከባሪ ጦር የሚሰማራበትን ሁኔታ እንዲያጤን ጥሪውን ለመንግሥታቱ ድርጅት አቅርቧል፡፡
የኅብረቱ አባል አገሮች ማንኛውንም ዓይነት የጦር መሣሪያም ሆነ ለወታደራዊ የቅኝት አገልግሎት የሚውሉ ቴክኖሎጂዎችን ለኢትዮጵያ እንዳይሸጡ ጥሪውን አቅርቧል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ እንዲጣል የሥራ አስፈጻሚ ትዕዛዝ መፈረማቸውን የአውሮፓ ኅብረት የሚያደንቀው ቢሆንም፣ አሜሪካ ለኢትዮጵያ መንግሥት የምታደርገው የበጀት ድጋፍ መቀጠሏ ግን ቅሬታ እንደፈጠርበትና ይህም በትግራይ ክልል ያለው ሁኔታ እንዳይሻሻል አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን አስታውቋል፡፡
አዲስ የተመሠረተው የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልልም ሆነ በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች ያለውን ግጭት ለመፍታት ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ምክክር እንዲያደርግ ጥሪውን ያቀረበ ሲሆን፣ ሁሉም ወገኖች ምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ ሳያስቀምጡ ልዩነቶቻቸውን በድርድር እንዲፈቱ አሳስቧል፡፡
በኢትዮጵያ የሚመራ አካታች የፖለቲካ ምክክር እንዲደረግ ጥሪውን ያቀረበው የአውሮፓ ኅብረት፣ የአፍሪካ ኅብረት በአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛው የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ በኩል የሚያደርገውን ጥረት እንደሚደግፍ አስታውቋል፡፡