የግል ድርጅቶች ከሠራተኞቻቸው የሰበሰቡትን የጡረታ መዋጮ በወቅቱ ለመንግሥት ወይም ለጡረታ ፈንድ የማያስገቡ ከሆነ፣ ባንኮችና መሰል የፋይናንስ ተቋማት የሚፈለገውን ዕዳ ከድርጅቶቹ የባንክ ሒሳብ ቀንሰው ለፈንዱ እንዲያስተላልፉ ግዴታ ሊጣልባቸው ነው።
ይህንን እንዲያደርጉ የተጠየቁ ባንኮችና ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ የመተግበር ኃላፊነት እንዲጣልባቸው፣ ይህንን በማይተገብሩት የፋይናንስ ተቋማት ደግሞ ዕዳውን የመክፈል ግዴታ ሊወድቅባቸው ይችላል።
የተገለጹት ግዴታዎች በፋይናንስ ተቋማቱ ላይ እንዲጣሉ የሚያስችለው አሠራር የቀረበው ከሁለት ሳምንት በፊት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀድቆ፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተላከው የግል ድርጅቶች ሠራተኞች የጡረታ ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው።
‹‹ማንኛውም ባንክ ወይም የፋይናንስ ተቋም በፈንዱ ሥልጣን የተሰጣቸው ተቋማት ወይም የጡረታ መዋጮ እንዲሰበስብ ውክልና በተሰጠው አካል ሲጠየቅ፣ ከግል ድርጅቱ የሚፈለገውን የጡረታ መዋጮ ወለድና ቅጣት ዕዳ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ከግል ድርጅቱ ሒሳብ ላይ ቀንሶ ለጡረታ መዋጮ ገቢ በተከፈተው የባንክ ሒሳብ ገቢ የማድረግ ግዴታ አለበት፤›› የሚል ድንጋጌ ይዟል፡፡
የግል ድርጅቶች ሠራተኞች ጡረታ ኤጀንሲ ወይም የጡረታ መዋጮ ገቢ እንዲሰበስብ ውክልና የተሰጠው አካል ተገቢውን የጡረታ መዋጮ ለጡረታ ፈንዱ ገቢ ሳያደርግ ከሦስት ወራት በላይ የቆየን የግል ድርጅት ዕዳ፣ በባንክ ወይም በፋይናንስ ተቋም ካለው ሒሳብ ላይ ተቀንሶ ገቢ እንዲሆን የማስደረግ ሥልጣን እንደሚኖራቸው የረቂቅ አዋጁ ድንጋጌ ያመለክታል።
በዚህ መሠረት ትዕዛዝ ወይም ጥያቄ የቀረበለት ባንክ ወይም የፋይናንስ ተቋም ከግል ድርጅቱ የሚፈለገውን የጡረታ መዋጮ ዕዳ፣ ወለድና ቅጣቱን ጨምሮ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ከግል ድርጅቱ ሒሳብ ላይ ቀንሶ፣ ለጡረታ መዋጮ ገቢ በተከፈተው የባንክ ሒሳብ ገቢ የማድረግ ግዴታ የሚጣልበት እንደሚሆን ረቂቅ ድንጋጌው ያመለክታል።
ከግል ድርጅቱ የባንክ ሒሳብ ላይ የጡረታ መዋጮ ዕዳውን ቀንሶ ለጡረታ ፈንዱ ገቢ እንዲያደርግ ሥልጣን ወይም ውክልና በተሰጠው አካል በጽሑፍ ጥያቄ የቀረበለት ባንክ ወይም የፋይናንስ ተቋም ጥያቄው ከቀረበለት በኋላ፣ ዕዳው እስከሚከፈል ድረስ የድርጅቱ ሒሳብ እንዳይንቀሳቀስ የማድረግ ግዴታ እንደሚጣልበትም ረቂቅ አዋጁ ያመለክታል።
“ከድርጅቱ ሒሳብ ላይ ገንዘብ ወጪ ሆኖ ቢገኝ ወጪ በተደረገው ገንዘብ መጠን ልክ ወይም እንደ አግባቡ በቀረው ዕዳ መጠን፣ ባንኩ ወይም የፋይናስ ተቋሙ ኃላፊ ይሆናል” የሚል ድንጋጌም በረቂቁ ተካቷል፡፡
በግል ድርጅት ሠራተኞች ጡረታ ዕቅድ ለተሸፈኑ ሠራተኞች ደመወዝ የሚከፍል አሠሪ፣ ገንዘቡ የሚገኝበትን የባንክ ቅርንጫፍና የሒሳብ ቁጥሩን ለፈንዱ በጽሑፍ የማሳወቅ፣ የባንኩ አድራሻና የሒሳብ ቁጥሩ ሲለወጥም ለውጡ ከተከሰተበት ቀን አንስቶ በ15 ቀናት ውስጥ ለፈንዱ በጽሑፍ የመግለጽ ግዴታ እንደሚኖርበትም ረቂቅ አዋጁ ያመለክታል።
እያንዳንዱ የግል ድርጅት የሠራተኞቹን የጡረታ መዋጮ ከደመወዛቸው ቀንሶና የራሱን መዋጮ ጨምሮ ለጡረታ ፈንዱ በየወሩ የመክፈል ግዴታ ያለበት ሲሆን፣ ይህንን ግዴታውንም ለሠራተኞች የወር ደመወዝ ከሚከፈልበት ወር መጨረሻ ቀን አንስቶ በ30 ቀናት ውስጥ ለጡረታ ፈንዱ ገቢ ማድረግ እንዳለበት ረቂቁ ይደነግጋል።
የወሩ ደመወዝ ከሚከፈልበት ወር ቀጥሎ ባለው 30 ቀን ውስጥ የጡረታ መዋጮውን ገቢ ያላደረገ የግል ድርጅት፣ ገቢ ባልሆነው የጡረታ መዋጮ ላይ፣ የባንክ ማስቀመጫ ወለድና በየወሩ አምስት በመቶ ቅጣት እንደሚጣልበት የረቂቁ አዋጁ ድንጋጌ ያመለክታል።
ነገር ግን የሚጣለው ቅጣት ድርጅቱ ከሚፈለግበት ውዝፍ የጡረታ መዋጮ አጠቃላይ ዕዳ ሊበልጥ እንደማይችልም ረቂቁ አዋጁ ይገልጻል።
ይህ ረቂቅ አዋጅ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ተቀባይነት አግኝቶ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተላከ ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት የሥራ ዘመኑን የጀመረው ምክር ቤት በቅድሚያ ከሚመለከታቸው ረቂቅ አዋጆች መካከል አንዱ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።