Wednesday, June 12, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በሲሚንቶ ፋብሪካዎች ከኢትዮጵያውያን በላይ የውጭ ዜጎች ተቀጣሪ መሆናቸው ተገለጸ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ የሚገኙ በርካታ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች መንግሥት ተገቢውን ክትትል እያደረገ ባለመሆኑና ኩባንያዎች በክህሎት የበቁ ኢትዮጵያዊያን በሥልጠና ዕገዛ ባለማድረጋቸው ምክንያት፣ አብዛኛዎቹ በሲሚንቶ ፋብሪካዎች ተቀጥረው የሚሠሩት ሠራተኞች የውጭ ዜጎች መሆናቸው ተገለጸ፡፡

 

በኢትዮጵያ ምርት በማምረትና በግንባታ ላይ የሚገኙትን ጨምሮ 17 የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የሚገኙ ሲሆን፣ 12ቱ በተለያየ የማምረት መጠን ላይ ይገኛሉ፡፡ ይሁን እንጂ በበርካታ ፋብሪካዎች በተለይም ግዙፍ በሚባሉት ዳንጎት፣ ሙገርና ደርባ ኩባንያዎች ውስጥ የውጭ ዜጎች የማኔጅመንቱንና ቴክኒካል ሥራውን በበላይነት እንደሚይዙ የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ወ/ሮ ስምረት ግርማ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በዚህም በሥራ ላይ በሚገኙት የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ የውጭ ዜጎች እንዳሉ የገለጹት ምክትል ዳይሬክተሯ፣ ኢትዮጵያውያን እየሠሩባቸው ያሉ ዘርፎችም ቢሆን በዝቅተኛ ዕርከንና በጉልበት ሥራ ላይ የሚገኙ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡

በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ማዕከል ዲን የሆኑት ወርቁ ጅፋራ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ባለፉት ሦስት ወራት በሲሚንቶ አምራች ኢንዱስትሪ ውስጥ ያለውን የሰው ኃይል ስምሪትና ስብጥር ለመፈተሸ ባደረጉት የዳሰሳ ጥናት፣ ግዙፍ በሚባሉት የሲሚንቶ አምራች ፋብሪካዎች ሠራተኞች በአመዛኙ የውጭ ዜጎች ስለመሆናቸው ማየታቸውን ተናግረዋል፡፡

ለአብነትም ለዳሰሳ ጥናት በሄዱባቸው ፋብሪካዎች መካከል ‹‹በዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ አብዛኛው ሠራተኛ የውጭ አገር ዜጋ መሆኑን መረጃው ቢደርሰንም ገብተን እንዳናጣራ ተከልክለናል፤›› ብለዋል፡፡

ወርቁ (ዶ/ር) ለዚህም እንደ ዋነኛ ምክንያት የጠቀሱት በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎችም ሆነ ማሠልጠኛ ተቋማት እንደሌላው ሙያ ሁሉ በሲሚንቶ ቴክኖሎጂ የሚሰጥ ትምህርት አለመኖሩንና በታችኛው የትምህርት ደረጃም ቢሆን ወጣቶች ሥልጠና የሚያገኙበት መንገድ ባለመኖሩ፣ ካምፓኒዎች ሠራተኞችን ከውጭ እንዲያመጡ መገደዳቸውን ጠቁመዋል፡፡

ነገር ግን በርካታ የኢንጂነሪንግ ምሩቃን ለብዙ ዓመታት ያለ ሥራ ተቀምጠው ሳለ፣ በሲሚንቶ ቴክኖሎጂ ዘርፍ ምሩቃንን ማፍራት ባለመቻሉ ኢትዮጵያውያን የዚህ ዕድል ተጠቃሚ ሊሆኑ አለመቻላቸው አግባብ አለመሆኑን አክለው ተናግረዋል፡፡

ይህን በአገር ውስጥ የሠለጠነ የሰው ኃይል አለመኖር ክፍተትን ለመሙላት፣ በሥልጠናና ምክክር እንዲሁም በጥናትና ምርምር አብሮ ለመሥራት፣ የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ከሲሚንቶ አምራቾች ማኅበርና የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ጋር መስከረም 27 ቀን 2014 ዓ.ም. የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች