Monday, March 27, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ኢትዮጵያ እንደ ዳናኢዴስ ልጆች እንስራ እስከመቼ?

በቶፊቅ ተማም

የአገራችን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ መንበረ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ እጅግ ፈታኝ አገር የመምራት ተግባር ከመከወን ትይዩ ሁለት መጽሐፎችን ማለትም ‹‹መደመር›› እና ‹‹የመደመር መንገድ›› ለአንባቢ ማድረሳቸው ይታወሳል፡፡  ይህን የመደመር መንገድ የተሰኘውን መጽሐፍ መነሻ በማድረግ እሳቸው ካነሱት አንድ ሐሳብ ተንተርሼ ጥቂት ማለትን እሻለሁ፡፡

ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በመደመር መንገድ መጽሐፋቸው ምዕራፍ አሥራ አንድ ‹‹ኢትዮጵያ ከዳናኢዴስ እንስራነት ወደ ተስፋ አድማስነት›› በሚለው ክፍል በገጽ 356 ይህን ይላሉ፡- ‹‹በጥንታዊ ግሪክ አፈ ታሪክ ውስጥ ዳናኢዴስ በመባል የሚታወቁ ያለ ፍላጎታቸው ለሃምሳ ወንዶች የተዳሩ እህትማማቾች ነበሩ፡፡ ካለፍላጎታቸው ልጆቹን የዳረው አባትም ሴት ልጆች በሠርጋቸው ቀን ባሎቻቸውን ገድለው እንዲያድሩ መከሯቸው፡፡ ከአንዷ በቀር ሁሉም የአባታቸውን ምክር ፈፀሙ፡፡ ባሎቻቸውን ገድለው አደሩ፡፡ ይህ ኃጢአት በአማልክቱ ዘንድ ከሞት በኋላ አስገራሚ ቅጣት እንዲበየንባቸው አድርጓል፡፡ ቅጣቱም ወንዝ ወርደው ውኃ በማሰሮ እያመላለሱ ሽንቁር ያለበትን ትልቅ እንስራ መሙላት ነው፡፡ ሴቶቹ ከቅጣት የሚተርፉት እንስራውን ሲሞሉ ብቻ መሆኑ ተነገራቸው፡፡ እንስራው ደግሞ ሽንቁር ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ከሥር የሚያፈሰውን ሽንቁር እንስራ ለመሙላት ዘለዓለም ውኃ በማሰሮ ካለ ዕረፍት ያመላልሳሉ፤›› በማለት የሚገልጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በተለይ የአሁኗ ኢትዮጵያ እንደ ዳናኢዴስ ልጆች እንስራ እየሆነች ትገኛለች፡፡ ሕዝቧ የማይሞላ ጉድለቷን ለመሙላት ቢተጋም ሞላች ስትባል ስትጎድል፣ ተጨበጠች ስትባል ስታፈተልክ፣ ቀን ወጣላት ሲባል ቀን ይጨልምባታል፡፡ የእኛ ኢትዮጵያውያን ሽንቁር በፍቅር አለመደመር ነው የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እንደ እህትማማቾቹ ከመገዳደል የምንድንበትን ቀን መቼ ይሆን ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡

ይኼው የመገዳደል ሽንቁራችን ዳግሞ ለመስፋቱ ማሳያ ተገደን የገባንበት በሰሜኑ ኢትዮጵያ እየተደረገ ያለው ጦርነት አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ይኼው ጦርነት ክቡር የሆነውን የዜጎቻችንን ሕይወት በግፍ እንዲጠፋ ከማድረጉ ባሻገር፣ ከሞት የከፋ በደል በዜጎቻችን ላይ ሲደርስ በዚሁ የጦርነቱ ዳፋ ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ነፍስ ከመንጠቁ በመለስ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ ያደረገ ሲሆን፣ ይህም ዜጎችን ለከፋ ችግርና ሰቆቃ ሲዳርጋቸው፣ በዓለም የአገር ውስጥ ተፈናቃይ በብዛት ካለባቸው አገሮች ከቀዳሚዎቹ አንዷ አድርጓታል፡፡ ከዚሁ ከአገር ውስጥ ተፈናቃይ ዜጎች ጉዳይ ተያይዞ ባለፉት ዓመታት በብሔር ግጭት በድርቅ፣ በጎርፍና በሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎች ይከሰት የነበረው የአገር ውስጥ መፈናቀል በዕርቅና ሌሎች በተሠሩ ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬአቸው የመመለስ ተግባራት ምክንያት ዜጎችን ወደ ነበሩበት በመመለስ ፋታ ያገኘ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን በጦርነቱ ምክንያት የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ቁጥር እጅጉን ጨምሯል፡፡ በአማራ ክልል ብቻ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ተፈናቃዮች ሲገኙ፣ በአጠቃላይ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል፡፡ ከዚሁ ከመፈናቀል ጋር ተያይዞ ሕፃናት፣ ሴቶችና አረጋውያን በስፋት ለከፋ ለጤናና ሰብዓዊ ቀውስ የተጋለጡ ሲሆን፣ ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው ሴቶች የመደፈር አደጋ ሲደርስባቸው ይህም ከፍተኛ ለሆነ የአካልና የሥነ ልቦና ጉዳቶች እየዳረጋቸው ይገኛል፡፡

በጦርነቱ ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ጉዳት የደረሰ ሲሆን፣ ለጦርነቱ ከወጣው በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በመለስ የደረሰውን የኢኮኖሚ ጉዳት ለመተካት ዓመታት የሚፈጅ ነው፡፡ ከኮቪድ-19፣ ከጦርነቱ በፊት የነበረውና በፈጣን መልኩ እያደገ የነበረው የአገሪቱ ኢኮኖሚ ክፉኛ ሲዳከም በዚሁ ጦርነት ሳቢያ ለአገሪቱ ልማት የሚያስፈልጉ ብድርና ዕርዳታዎች እየቀነሱ ሲገኙ፣ ከዚህ ባለፈም ለአገሪቱ ኢኮኖሚ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ያደርጉ የነበሩ የጨርቃ ጨርቅ፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ የግብርና ውጤቶችን ማቀነባበርና ቱሪዝምን ጨምሮ ሌሎች ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች ሥራ ማቆማቸው፣ በአሁኑ ወቅት እየተፈጠረ ያለ የዋጋ ግሽበት የፈጠረው ቀላል ሊባል የማይችል የኢኮኖሚ ቀውስ ማስከተሉ ለአብነት ሊጠቀስ ይችላል፡፡

ሌላው በምዕራባውያን ዘንድ አንገት የሚያስደፋን እነሱም ለመዘገብ የማይታክቱትን የረሃብ ታሪካችን ለመቅረፍ በምንረባረብበት ወቅት በተፈጠሩ የሰላም መደፍረሶች ሳቢያ ከሞት ያመለጠው አርሶ አደሩ ከማሳው ተፈናቅሎ ንብረቶቹ ተዘርፈው፣ የዘራው ወድሞበት ሰፋፊ የእርሻ ማሳዎች ፆማቸውን አድረው አርሶ ከመብላት ይልቅ የዕርዳታ እህል ጠባቂ ሲያደርገው፣ አሁንም የረሃብ አደጋ እያንዣበበ መሆኑን በተለያዩ የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች እየዘገቡት ሲገኙ፣ በቀጣይ የረሃብ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል የዓለም አቀፍ የዕርዳታ ድርጅቶች እየገለጹ ይገኛሉ፡፡

ሌላው አገራችንን የዳናኢዴስ እንስራ እያደረገብን ያለው ጉዳይ በጦርነቱ፣ እንዲሁም በየጊዜው በሚከሰቱ ግጭቶች ምክንያት እየደረሰ ያለው መሠረተ ልማት ላይ ያነጣጠረ ጉዳት ነው፡፡ ከሕወሓት ጋር በገጠምነው ጦርነት ሳቢያ ክፉኛ ከወደሙ መሠረተ ልማቶች በተለይ በዓለም አቀፍ ሕጎች በጦርነት ወቅት ጥበቃ የሚያሻቸው የትምህርትና ጤና ተቋማት ይህን ሕግ በጣሰ መልኩ ክፉኛ ተጎድተዋል፡፡ ቅድሚያ ጤና ነውና በጤና መሠረተ ልማት ላይ የደረሰው ጉዳት ከፍተኛ ሲሆን ወደ ሁለት ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ለጤና አገልግሎት ችግር ዳርጓቸዋል፡፡ በደረሰው ውድመት አገሪቱ በጤናው መሠረተ ልማት ዘርፍ የጀመረችውን ጉዞ ላይ ወደኋላ የመለሰ ጋሬጣ ሆኗል፡፡

ሌላው የደረሰው ጉዳት በትምህርት መሠረተ ልማት ላይ ሲሆን፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶችና ማሠልጠኛ ተቋማት ሲወድሙ፣ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ሕፃናት ከትምህርት ገበታ ውጪ ያደረገና የሕፃናቱን የወደፊት ተስፋ ያቀጨጨ ሆኗል፡፡ ይህም አገሪቱ በትምህርት ተደራሽነት ዙሪያ ያካሄደቻቸውን በጎ ጅምሮች ወደኋላ የጎተተ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ከአራት ሚሊዮን ብር በላይ አውጥቶ የሠራውና ታዳጊ ልጆችን ዳስ ውስጥ ከመማር የታደገው ትምህርት ቤት የጥቃቱ ሰለባ መሆኑን ማንሳት ይቻላል፡፡ ይህን ጽሑፍ በማዘጋጅበት ወቅት የጉና ቤጌምድር ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ በሕወሓት ሙሉ በሙሉ መውደሙን በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ለመስማት ችያለሁ፡፡ ይህም ብዛት ያላቸው ታዳጊዎችና ወጣቶች በቴክኒክና ሙያ ክህሎት ጨብጠው አገራቸውን ብሎም ራሳቸውን መጥቀም የሚችሉ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን ተስፋ አጨልሟል፡፡

በዚሁ ጦርነት ሳቢያ በመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ዘረፋና ውድመት የደረሰ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ  የፋይናንስ ተቋማት ተቃጥለዋል፣ የገንዘብም ዘረፋ ተካሂዷል፡፡ ይህም ቀላል ሊባል የማይችል የኢኮኖሚ ጉዳት በአገሪቱ ላይ ሲያሳርፍ፣ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ለአብነት ያህል በአማራ ክልል ለብዙ ወጣቶች የሥራ ዕድል የፈጠሩ ወደ 19 ሺሕ ገዳማ ኢንተርፕራይዞች ከእነ ሙሉ ንብረታቸው መውደማቸው ተገልጿል፡፡ ይህም እጅግ የከፋ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውስ አስከትሏል፡፡

በእርግጥ ከሕወሓት ጋር የገጠምነው ጦርነት አብቅቶ ኢትዮጵያ ወደ ሰላማዊ ሁኔታ ለመመለስ በማቀድ፣ እንዲሁም በወገናችን ላይ የሚደርሰውን ሁሉን አቀፍ ግፍና መከራ ቁጭ ብሎ መመልከት ያላስቻላቸው በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ ወጣቶች፣ እንዲሁም በተለያዩ ተቋማት የሚሠሩ ሠራተኞች መከላከያን መቀላቀላቸው እጅግ የሚያስመሠግን ክብር የሚያሰጥ ቢሆንም፣ ከሕወሓት ጋር የገጠምነው ጦርነት የወጣትነት ጉልበታቸውን እንዲሁም ዕውቀታቸውን ተጠቅመው ለአገሪቱ ዕድገት አዎንታዊ ሚና በመጫወት በተለያየ መስክ የአገሪቱን ሽንቁር ሊደፍኑ እንስራዋን ሊሞሉ የሚችሉ ወጣቶች ወደ ግንባር መሸኘት ግድ አስብሏል፡፡

ከላይ በጥቂቱ የጠቃቀስናቸው በጦርነቱ ምክንያት የደረሱ ዳፋዎች የጊዜ ጉዳይ እንጂ ጦርነቱ ማብቂያውን አግኝቶ ሰላም ይሰፍናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ በዚሁ ጦርነት ሳቢያ የደረሱ ጉዳቶችን፣ የፈረሱ የጤና ተቋማትን፣ ጤና ጣቢዎችን፣ ሆስፒታሎችና ትምህርት ቤቶች፣ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት፣ የፈረሱ የከተማና የገጠር መሠረተ ልማቶች፣ የመንግሥትና የግል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንደገና ለመጠገን ብሎም የተፈናቀሉትን ዜጎቻችንን መልሶ ለማቋቋም የሚወጣው ከፍተኛ ወጪ ለሌላ ተጨማሪ ልማት መዋል ሲችል፣ ዳግም የፈራረሱ ተቋማትን ለማቋቋም መዋሉ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ላይ ዘወትር ጥያቄ የሚያነሱ የውጭ ኢንቨስተሮችን አመኔታ ያሳጣል፡፡ መልሶ መገንባቱ የአገራችንን ሁኔታ እንደ ዳናኢዴስ እንስራ ሲያደርጋት ከዜሮ የመጀመር አባዜያችን እንደገና የሚያስቀጥል ይሆናል፡፡

በእርግጥ አሁን አገር ማጥ ውስጥ ብትገባም ሰፊው ሕዝብ የወገኔ ችግር የእኔም ችግር ነው ብሎ በአገር ውስጥም ይሁን በውጭ ያሉ ዜጎቻችን በተለይ ወጣቶች ማኅበራዊ ሚዲያን በመጠቀም የዕርዳታ ማሰባሰብ ተግባራትን በመከወን ከተራቡ፣ ከታረዙና መራፊያ ካጡ ወገኖቻችን ጎን በመሠለፍ የአቅማቸውን ድጋፍ እያደረጉ ነው፡፡ ወላጅ ልጆቹን መርቆ እየሸኘ፣ የእምነት ተቋማት በፆምና በጸሎት፣ በቁሳዊና ሰብዓዊ ድጋፍ ባለሀብቶች ሀብታቸውን ለወገን እየለገሱ፣ በተለያየ የሙያ ዘርፍ ያሉ ባለሙያዎች፣ በተለይ የጤና ባለሙያዎች በሙያቸው ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ከትምህርት ገበታቸው የተፈናቀሉ ሕፃናትና ታዳጊዎች ወደ ተለያዩ በአቅራቢያቸው በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የአዲሱን ዓመት የትምህርት ዘመን እንዲቀጥሉ የተደረገው ጥረት ይበል የሚያሰኝ ሲሆን፣ ቤንጃሚን ፍራንክሊን ‹‹የሰላም መጥፎ የጦርነት ጥሩ የለውም›› እንዲል፣ አሁን በተፈጠረው ችግር ሕዝቡ ያሉ ልዩነቶችን ትቶ ወደ አንድ ጎራ እየተሠለፈ ሲገኝ፣ ኢትዮጵያዊነትም ከምንም ጊዜ በላይ እየተጠናከረ ይገኛል፡፡

መቼስ ‹‹ተስፋ መቀነት ነው›› እንዲል ጸጋዬ ገብረ መድኅን አሁን ካለንበት እጅግ ፈታኝ ወቅት እንሻገራለን ብለን ተስፋ እያደረግን፣ አገራችን በየጊዜው የዳናኢዴስ እንስራ የሚያደርጋትን በየጊዜው የሚነሱ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች ፈጣሪ ያቆምልን ዘንድ እየለመንን፣ ሁላችንም አገራችንን ከዳናኢዴስ እንስራነት ለመታደግና የአገር እንስራዋን በሰላምና በፍቅር፣ በአንድነትና በጤና፣ በብልፅግናም ለመሙላት የበኩላችንን በመወጣትና ሽንቁሯን ለመድፈን በየተሰማራንበት የሥራ መስክ የበኩላችንን በመወጣትና የሰላማችን ዘብ በመሆን፣ በፍቅር በመተሳሳብና በመቻቻል በቀናነትም አብሮ በመኖር እንደ ዳናኢዴሶች ውኃ በብርታት ማመላለስ ይኖርብናል፡፡ ነገር ግን የእንስራችንን ሽንቁር ለመድፈን በብልኃት፣ በትጋትና በታታሪነት መነሳት ከሁሉም ዜጋ ይጠበቃል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles