ታንዛኒያዊው ደራሲ አብዱልራዛቅ ጉራህ የ2021 የኖቤል የሥነ ጽሑፍ አሸናፊ መሆናቸውን የስዊድን አካዴሚ መስከረም 27 ቀን 2013 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል፡፡
እ.ኤ.አ. በ1986 ዎሌ ሾይንካ በሥነ ጽሑፍ የኖቤል ተሸላሚ ከሆኑ ከ35 ዓመታት በኋላ አብዱልራዛቅ ጉራህ ሁለተኛው ጥቁር አፍሪካዊ ያሰኛቸውን ክብር ተቀዳጅተዋል፡፡ በመላው አፍሪካ ደረጃ ስድስተኛ ተሸላሚ ናቸው፡፡
ቢቢሲ እንደዘገበው፣ አብዱልራዛቅ ለአሸናፊነታቸው ከስዊድኑ የኖቤል ሽልማት ድርጀት 10 ሚሊዮን ክራውን ወይም 1.14 ሚሊዮን ዶላር ያገኛሉ፡፡
የ73 ዓመቱ አዛውንት ጉራህ ጎልተው የሚታወቁትን ‹‹ፓራዳይዝ›› (Paradise) እና ‹‹ዲዘርሽን›› (Desertion) ጨምሮ የ10 ልብ ወለዶች ደራሲ ናቸው፡፡
‹ለእውነት መሰጠት›
አብዱልራዛቅ እ.ኤ.አ. በ1994 ላይ ያሳተሙት ‹ፓራዳይዝ› የተሰኘው ልብ ወለድ ታንዛኒያ ውስጥ በ20ኛው ምዕት ዓመት የልጅ አስተዳደግ ምን እንደሚመስል ፍንትው አድርገው ያሳዩበት ነው። በዚህ ልብ ወለድም ዓለም አቀፉን የ‹ቡከር› ሽልማት ለማግኘት መቻላቸውን ቢቢሲ ዘግቦታል፡፡
እንደ የኖቤል ኮሚቴ የሥነ ጽሑፍ ክፍል አገላለጽም፣ ‹‹[የእሳቸው] ገጸ ባህርያት ሁሌም ቢሆን በባህልና አኅጉራት መካከል የሚሽከረከሩ፣ በአሁን ሕይወትና በመጪው ሕይወት መካከል የሚመላለሱ ናቸው። በቀላሉ ሊያልፉት የማይችሉት ከባድ እውነታ ውስጥ ናቸው፡፡››
እ.ኤ.አ. በ1948 በዛንዚባር የተወለዱት አብዱልራዛቅ፣ እ.ኤ.አ. በ1960ዎቹ መገባደጃ አገረ እንግሊዝ የገቡት ስደተኛ ሆነው ነው። በቅርቡ ጡረታ እስከወጡበት ዕለት ድረስ በካንተርበሪው የኬንት ዩኒቨርሲቲ የእንግሊዝኛና የድኅረ ቅኝ ግዛት ሥነ ጽሑፎች ፕሮፌሰር ነበሩ።
ሽልማቱ፣ ደራሲው ያለፉበትን የስደተኞች ቀውስንና ቅኝ አገዛዝን በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ ውይይት እንዲደረግባቸው ያስችላል ብለዋል፡፡
‹‹እነዚህ በየዕለቱ ከእኛ ዘንድ ያሉ ነገሮች ናቸው። ሰዎች እየሞቱ ነው፣ ሰዎች በዓለም ዙርያ አሁንም እየተጎዱ ነው፡፡ በእነዚህን ጉዳዮች ላይ በፍፁም ቀናነትና አስተውሎት መንገድ መነጋገር መላ መምታት አለብን፤›› ብለዋል የኖቤል ተሸላሚው አብዱልራዛቅ።
ዓምና በሥነ ጽሑፍ ያሸነፉት አሜሪካዊው ገጣሚ ሊዊስ ግሉክ መሆናቸው ይታወሳል።
አፍሪካውያን የኖቤል የሥነ ጽሑፍ ተሸላሚዎች
የስዊድኑ አካዴሚ በሥነ ጽሑፍ ዘርፍ የኖቤል ሽልማት ከሸለማቸው ታላላቅ ደራስያን መካከል ከአፍሪካ አኅጉር ስድስት ደራስያን ይገኙበታል፡፡
እነርሱም ዎሌ ሾንካ (ናይጀሪያ)፣ ነጂብ ማኅፉዝ (ግብፅ)፣ ናዲን ጎርዲመር (ደቡብ አፍሪካ)፣ ጄ.ኤም ኮትዚ (ደቡብ አፍሪካ)፣ እና ዶሪስ ሌሲንግ (ዚምባቡዌ -እንግሊዝ) ይገኙበታል፡፡