ሰላም! ሰላም! በቀደም ዕለት ቤት ውስጥ እየተንጎራደድኩ፣ “ካላጣሽው አካል በልቤ ላይ ተሰንቅረሽ፣ ታሰኚኝ ጀመረ ደግሞ ደግሞ እንደ ምን አለሽ?” እያልኩ ሳፏጭ ማንጠግቦሽ አልጣማትም። “እኔ ያለሁት እዚህ አጠገብህ፣ ማን ናት እሷ ተሰንቃሪዋ?” ብላ ማፋጠጥ። ጉድ እኮ ነው፣ ብለን ብለን በዘፈን ልንጣላ ነው? በስም ስንጣላ፣ በአቀማመጥ ስንጣላ፣ በአረማመድ ስንጣላ ከርመን አሁን ደግሞ በዘፈን ጭቅጭቅ። ምንድነው ጉዱ? ‘ፈራሁ የምፀናበት ልብ አጣሁ ነው’ ያለው ያ ታላቅ ባለቅኔ። አይ ሞት ሁሉን አፈር አልባሹ። “ሞት ባይኖር ኖሮ እኮ እንዲህ አንናናቅም ነበር…” ሲለኝ ነበር ምሁሩ የባሻዬ ልጅ። “ማን ከማን ሲናናቅ አየህ?” ስለው፣ “ተማሪና አስተማሪ፣ መሪና ተመሪ፣ ፈጣሪና ፍጡር ናቸዋ። አታይም እንዴ ዙሪያህን?” አለኝ። እኔ ደግሞ አንዳንዴ ነካ የሚያደርገኝ ነገር አለ። ዙሪያህን ሲለኝ ቀጥታ ወስጄው ዘወር ስል ማንጠግቦሽ ቆማለች። “ዛሬ ያቺን ስንቅር ሳታወጣ ወደ ቤት እንዳትመጣ…” ብላ ገፍትራኝ ሄደች። “ምንድነው?” አለኝ የባሻዬ ልጅ ደንግጦ። የአፍሪካ መሪዎች የመከሩንን እያስታወስኩ ታገስኩ፡፡ መታገስ መልካም ነው!
እኔ ነገሩን በጥሞና አስረዳሁት። “የወፍ ቋንቋ፣ የአሞራ ክንፍ ባደለኝ የሚባልበት ዘመን ላይ ደረስን በለኛ። ምነው ማንጠግቦሽ ያውም በሕዝብ ዘፈን እንዲህ የምትሆነው?” ብሎ ሲታዘባት ምንም ወዳጄ ቢሆን ቅር አለኝ። እንግዲህ ይኼው ነው። ሲለን በምናፍርባት ሲለን በምንኮራባት አገራችን ‘ሁለት ሞት ሙቱ’ ብሎ ሲያዝብን እንኳን፣ በዋልንበት ባልጠረጠርነው ነገር ለመኳረፍ ቅፅበት አይፈጅብንም። እናም እኔ የምላችሁ ዝም ብላችሁ ከላይ ከላይ ስታስቡት፣ ይኼ ‹የአዲሱ መንግሥት ምሥረታ› በኩነኔና በፍረጃ የደመቀ የእያንዳንዳችንን ጓዳ ሳያፀዳ እንዲያው ብቻውን ይዘልቅ ይመስላችኋል? አፌ እንዳመጣለት ባፏጨሁ ትዳሬ እንደ ቀልድ ብርድ ከገባው፣ የራሴ የሆነ አቋምና ቀኖና አርቅቄ ያፀደቅኩ ቀን ምን ሊፈጠር ነው? ብላችሁ ማሰብ እኮ ነው። አሁን ይኼ ከአገር ጉዳይ ጋር ምኑ ይገናኛል ባዮች ካላችሁ ‘በእኔ ሕይወት ቀዳዳ ብትገባ አገርህን ታያለህ’ ያለውን ደራሲ ፈልጋችሁ ጠይቁት፡፡ ፈጠን ነዋ!
ይልቅ አሁን የመንግሥት ምሥረታ ሰሞን ውስጥ ሆነን አንድ ነገር ትዝ አለኝ። መቼም እኛ ብዙ ነገር የምናከሽፈው ጠርጥረን ከዚያ በጥርጣሬ ላይ በተመሠረተ መረጃ ነገራ ነገሩን ሁላ በማራከስ ነው። ምስኪኗ አገራችን መቼም ትከሻዋ ስፋቱ ይኼው አለን። እናም መጠርጠር እያለ እርግጠኛ መሆን ብሎ ነገር መዝገበ ቃላታችው ውስጥ ሆነ ተብሎ የተዘለለ ነገር ይመስለኛል። ምነው እኔ ብቻ ሆንኩ? እናንተስ አይመስላችሁም እንዴ? እኔ ሁሌም የማምንበት ጥሩ አባባል አለ፡፡ ይህም በአገሬ ተስፋ አልቆርጥም ነው፡፡ ክብርት ፕሬዚዳንታችን፣ “እጃችን በእሾህ ተወግቶ ሲደማ ወደ ጽጌረዳዋ ተቃርበናል ማለት ነው…” ያሉት ይህንን አባባሌን ያጠናክረኛል፡፡ አፍሪካውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን “እማማ ኢትዮጵያ” እያሉ ኢትዮጵያን በኩራት ሲጠሩ፣ እኛስ እናት ኢትዮጵያን እንዴት እያደረግናት ይሆን መባባል አለብን፡፡ “እናት ኢትዮጵያ ጤናዋ ሲታወክ የእኛም ጤና አብሮ ይታወካል” ሲሉን፣ አገር ለምን ጤና እንደምንነሳ ራሳችንን መመርመር ይገባናል፡፡ “ከዘር ፖለቲካ ወደ ፍላጎትና ጥቅም ፖለቲካ የመሸጋገርን ጉዳይ አስቡበት” ስንባልም፣ እስቲ ምን እየተባልን እንደሆነ እንነጋገርበት፡፡ ምክር ነው!
አንድ ቀን ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ሳይቀር በነፈሰው ነፍሶ በነደደበት ስለሚያነደን ጉዳያችን ስንጫወት፣ “እኔ አንዳንዴ ሳስበው ግራ ግብት የሚያደርገው ባህሪያችን እንኳን ዕርምጃችንን በልተን ማደራችንን፣ የኢኮኖሚ ዕድገታችንን ቀርቶ ድህነታችንንም ለመረዳት እርግጠኛ ያደርገናል ብዬ አላስብም። ዓይናችን በቅጡ ማየቱን፣ ጆሯችን አጥርቶ ማድመጡን፣ አዕምሮአችን በሚገባ ማሰቡንና የዓላማ ፍጡራን መሆናችንን ለመገንዘብ ብዙ ይቀረናል…” አለኝ። ከነገር ሁሉ አሳቢና አሰላሳይ ለመሆናችን እርግጠኞች አይደለንም አባባሉ አስደንግጦኝ፣ ትንሽ ቆይቶ (የምሁር ነገር ምን ይታወቃል) ‘ሰው መሆናችን በጥናት ይረጋገጥ’ እንዳይለኝ ፈርቼ ዞር አልኩ። ዞር ስል ለስንት አሥርት ዓመታት በኖርኩበት ሠፈር የሚገኝ ፎቶ ቤትን አንዱ ቢጠይቀኝ፣ “ወደ ቀኝ ታጥፈህ መሰለኝ…” ብዬ መመለስ። በዚህ ዓይነት ቅንነት ከውስጣችን ተንጠፍጥፎ አልቆ ጭካኔ ይሁን መታበይ ደፍኖን ይሆን እንዴ ብዬ ማሰብ የጀመርኩት ርቄ ከሄድኩ በኋላ ነበር፡፡ የሆነስ ሆነና በዚህ ጉዳይ ላይስ ቢሆን መመካከር አያስፈልግም እንዴ ብዬ ለመጠየቅም ፈቃድ የሚያስፈልግ መስሎኝ እየተጠባበቅሁ ነው፡፡ ጥበቃ!
እንዲህ የኖርኩትን ሁሉ በዜሮ የሚያጣፋ ግራ መጋባት ሲጠናወተኝ ታዲያ መድኃኒቴን አውቀዋለሁ። እሱም በሥራ መወጠር ነው። መድኃኒት በመግዛትና መድኃኒት በማሠራት ያዳከምነው ወኔ ሥራ ላይ ውሎ ቢሆን ኖሮ ዛሬ እኛን ነበር ማየት። ከስንዴና ተመፅዋችነት ወጥነት ዓለምን እንመግብ ነበር፡፡ ማንም እየተነሳ በዚህ ግቡ በዚህ ውጡ ብሎ ትዕዛዝ አይሰጠንም ነበር፡፡ እርስ በርስ እየተፋጀን የዓለም መሳቂያ አንሆንም ነበር፡፡ እንዲህ ንድድ የሚያደርገኝ ባለፈው እየተቆጨሁ ቢሆንም፣ የነገው ጉዳይ ከመጠን በላይ ስለሚያሳስበኝ ነው፡፡ ካላመናችሁ አዛውንቱ ባሻዬ አንድ የሚሉት አባባል አለ። “ላለፈው የተበላሸ ነገር ከመቆጨት ለሚመጣው መልካም ጊዜ አስብ…” ይላሉ። ይመስለኛል እኛ ግን የምናስበው ገና ላለፈው ቂም በቀል ማስታወሻነት ስላላቆምናቸው ሐውሎቶች ነው። ካልመሰላችሁ ይህችም በልዩነት ትያዝልኝ። ይህ የባሻዬ አባባል ከዚህ በፊት የሰማነው ስለመሰለን የራሳቸው ይሁን አይሁን እርግጠኛ መሆን አንችልም’ ካላችሁ ደግሞ እንደ ፈቀደችሁ። ዋናው ቁምነገር ግን መልዕክቱ ላይ ነው፡፡ መመርመር የባለቤቱ ፋንታ ነው!
እንግዲህ አዲስ መንግሥት ምሥረታ ላይ ሆነን ስንነጋገር ከወዲህና ከወዲያ የሚያላጉ ሐሳቦች መኖራቸውን መዘንጋት ንፉግነት ነው፡፡ ከአዲሱ መንግሥት ብዙ የሚጠብቁ ተስፋ የሰነቁ በርካታ ነፍሶች አሉ፡፡ “ሺሕ ቢታለብ በገሌ” ብለው ጀርባቸውን የሚሰጡም እንዲሁ፡፡ የማይበርዳቸውና የማይሞቃቸውም አይጠፉም፡፡ “በሕይወት እያለን አዲስ መንግሥት የሚባል ነገር አናውቅም” የሚሉ የመርዝ ብልቃጦች በየሥርቻው መሸጎጣቸውን ማንም ይረዳዋል፡፡ እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ደግሞ፣ “በአገሬ ተስፋ የማልቆርጥ ከርታታ ብሆንም፣ የነገዋ ቀን ደማቅና ብሩህ የሚሆነው በብርቱ ትግል ውስጥ ነው…” እላለሁ፡፡ እየወደቀች የምትነሳ ታሪካዊት አገር መሆኗን ከታሪኳ የተገነዘብኩ በመሆኔ፣ ከእኔ የሚጠበቀውን ሁሉ በክብርና በታዛዥነት ለማድረግ ቃል እገባለሁ፡፡ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ “አንበርብር ቃል መግባትህ መልካም ነው፣ ቃል አባይ እንዳትሆን ግን ተጠንቀቅ…” ያለኝን መቼም አልረሳውም፡፡ እንዴት ይረሳል!
ሥራና ኑሮ “ደርቢ” ገጥመውብኝ አዲሱን ዓመት እንዴት እንደምዘልቀው እያሰብኩ ነው። እስኪ በአንድ ወቅት ወደ አሻሻጥኩት ከባድ መኪና ገጠመኝ ልውሰዳችሁ ደግሞ። ገጠመኝ ላውሳችሁ ይባላል እንጂ ወደ ገጠመኝ ልውሰዳችሁ አይባልም ስትሉ ሰማሁ መሰለኝ። ይኼ ጭቅጭቅ መሆን ያለበት ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር መሰለኝ። እሱ ውኃ ወቀጣ ነው ካላችሁ ምንም ችግር የለም፣ ከእኔ ጋር “መቀንጠስ” ነው። መቼም በድለላ ሥራ ጥርስ ስትነቅሉ ትልቁ ወሮታችሁ በከባድ ሚዛን ከሚጫወቱ የኑሮ ተፋላሚዎች ጋር መዋል ነው። ቀላል ሚዛኑማ ጥርስ ሳታበቅሉም ታገኙታላችሁ። ታዲያ አንድ ቅጥቅጥ የሚገዛ ደንበኛዬ መኪናውን ቶሎ አስፈትሾ ቀልቡን ሰብስቦ ሊዋዋልልኝ አልቻለም። በቅርብ ሠርቶ ስላጠናቀቀው ቤት በየአቅጣጫው እየተደወለለት ያወራል። በቅርቡ ፎርብስ መጽሔት ላይ ልማቱ ያፈራው ቢሊየነር የመባል ዕቅድ የያዘ ይመስላል። አንዳንዱ እኮ!
በመርከብ አስጭኖ ከአውሮፓና ከቻይና ስለሚያስመጣቸው የቤት ዕቃዎች ይቀዳል። በዕቃ ግዥ ለሚያግዙትና ከዚያው ሆነው ለሚያማክሩት ሰዎች በስልክ ሲመልስ አንድም ርካሽ ዕቃ እንደማይፈልግና “የሰው መሳቂያ አታድርጉኝ” በሚል መኩራራት ይጋበዛል። “ያዝኩ ሲሉ መያዝ፣ አለሁ ሲሉ መቅረትን በሰው እንኳ አይቶ አልተማረም እንዴ ይኼ ሰው?” ብሎ የከባድ መኪናው ባለቤት ቢታዘበው ጓደኛው ጣልቃ ገብቶ፣ “ምን ይደረግ ገንዘብ ዕውቀትን የትና የት መርቶት እያየህ ለምን በእሱ ትፈርዳለህ?” ይለዋል። መልሶ ደግሞ በከፊል ወደ እኔ ዘወር ብሎ፣ “እንደ እኛ ያለውን ደግሞ የወረዳና የክፍለ ከተማ ጥሬ ሹመኛ ይጫወትበታል። ከሁሉ የገረመኝ ግን ሹመት የሕዝብ ማገልገያ መሆኑን የማያውቁ ሰዎች ሹመት በብሔር ሲታደላቸው ነው…” አለኝ። ይኼኔ ጓደኛው ተቀብሎ፣ “ታዲያ እኛ ከመንግሥታዊ አስተዳደርና ከአካባቢያዊ ተሳትፎ እየራቅን እንዴት ይሆናል?” ሲለው ዝምታ ሰፈነ። “ከሳሽ የተከሳሽን መልስ ቢያውቅ ኖሮ ከቤቱ ባልወጣ ነበር…” ማለት ይህም አይደል ታዲያ፡፡ እውነት ነው!
በሉ እስኪ እንሰነባበት። አንዱ በንብረት ላይ የተጣለው ዕግድ እስኪነሳ ብሎ አንዳንድ ጉዳይ ላይ አማካሪው ሆኜ ሰነበትኩ፡፡ ምክሬ መልካምና አዋጭ ሆኖ ኖሮ ወረታዬን ዘግኖ ሰጠኝ። ኪሴ ሞላ ሲል ውኃ ቅጥል አድርጎ ጠማኝ፡፡ የባሻዬን ልጅ ደወልኩለትና የተለመደችዋ ግሮሰሪያችን ቀጠርኩት። ስንገናኝ ግሮሰሪዋን ከወትሮዋ በተለየ የዋጋ ጭማሪ አድርጋ ታዳሚዎቿን ታስተናግዳለች። የግሮሰሪያችን ባለቤት ግድግዳው ላይ በደማቁ፣ “ክቡራን ደንበኞቻችን በዶላር ምንዛሪ ጭማሪ ምክንያት የፋብሪካ ምርቶቻችን ላይ ጭማሪ ስለተደረገ፣ እኛም በተለያዩ መጠጦቻችን ላይ ጭማሪ ማድረጋችንን እናስታውቃለን…” ብሎ ለጥፏል። በአቋራጭ አጋጣሚውን ለመጠቀም የተጋነነ ጭማሪ ስላደረገ በዝምታ የሚታለፍ መስሎታል። ገና አንድ መለኪያ ሳይቀምስ የዋጋ ጭማሪው ያሰከረው የዘወትር ደንበኛው ጥጉን ይዞ፣ “የት ሄደን እንብላ?’ ስንል ዝም የተባልነው አንሶ ‘የት ሄደን እንጠጣ’ በሚልም ከመንግሥት ጋር ልታቀያይመን ነው? ተው የቄሳርን ለቄሳር የእኛን ለእኛ አድርገን እየተሳሰብን…” ይለዋል። ሰሚ ሲኖር አይደል!
“አወይ ዘመን! አወይ መጨካከን! ላያችን ላይ የትርፍ ክብድት እያነሱብን ገላጋይ አጥተን እኮ ክብደት የለሾችን ሆንን ጎበዝ፡፡ ሲያዩን አንከብድ ሲቆጥሩን አንሞላ…” ይላል ሌላው። ገና ከአሁኑ በዚህ ሁኔታ እንደለመደው ተመላልሶ እየጠጣ ፀንቶ ኑሮውን የመርሳቱ ዓላማው አደጋ ላይ እንደወደቀ የተረዳው ደግሞ፣ “እሱ ምን ያድርግ? እስከ ዛሬ የተጎዳው አይበቃም? ስንት ጓደኞቹ ሕንፃ እየሠሩ በብሔር ተቧድነው ክለብ ሲከፍቱ፣ እሱ እስከ ዕለተ ሞቱ ግሮሰሪ ላይ መቅረት አለበት?” ይላል። ከዚህ ሁሉ በላይ በአገር ላይ እየደረሰ ባለ ችግር ምክንያት ይገኛሉ ተብለን፣ ዝም ይላሉ ተብለን ልንሞኝ መታሰባችን ያንገበገበው፣ “ራስህን ብቻ ብትወድ እንጂ ለእኛ ብታስብ ኖሮ ችግሩ የጋራ ይሆን ነበር፡፡ አንተ ግን ከራስ በላይ ንፋስ ብለህ እኛን የራሳችሁ ጉዳይ ማለትህ ነውረኝነት ነው…” ሲል በንዴት ይጨሳል። እኔና የባሻዬ ልጅ መለኪያችንን እያጋባን በተመስጦ ውስጥ እንዳለን አንዱ፣ ‹‹ወገኖቼ ሆይ በምድር ላይ ስንኖር ለሥጋችንም ሆነ ለነፍሳችን እኩል ማሰብ ይኖርብናል፡፡ በዚህ መሠረት አንዳችን ለሌላችን ፍቅር መስጠት አለብን፡፡ በፈጣሪ አምሳል የተፈጠርን ሰዎች ነንና እንደ ፈጣሪ ልጆች እንተሳሰብ፡፡ አንዳችን ስንጎዳ ሌላውን ይመመው፡፡ ሌላው ሲደሰት ሌላኛው አይክፋው፡፡ ልባችንን ከፍተን እንተሳሰብ፡፡ ከተሳሰብን ትንሹ ነገር ይትረፈረፋል፡፡ እስቲ እንተሳሰብ፣ እንግባባ፣ እንመካከር…›› ሲለን ‹ቃለ ሕይወት ያሰማልን› ብለን በሙሉ ልብ ተቀበልነው፡፡ አዎ! እኛ ከተመካከርን በቂ አይደል? አንዱ ተደስቶ ሌላው ለምን ይክፋው? መልካም ሰንበት!