Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊለታላቁ ህዳሴ ግድብ በሁለት ወራት ከ201 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰበሰበ

ለታላቁ ህዳሴ ግድብ በሁለት ወራት ከ201 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰበሰበ

ቀን:

የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አፈጻጸም ከ80 በመቶ በላይ በደረሰበት አጋጣሚ በሐምሌና በነሐሴ ወራት ብቻ ከ201 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን የግድቡ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት አስታወቋል፡፡

 

ጽሕፈት ቤቱ መስከረም 27 ቀን 2014 ዓ.ም ከፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ለግንባታው እንዲውል የ20 ሚሊዮን ብር ቦንድ ግዥ በፈጸመበት ጊዜ ነው የተሰበሰበው የገንዘብ መጠን የተገለጸው፡፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነትና የሚዲያ ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብርሃም እንደገለጹት፣ በ2014 በጀት ዓመትም በሐምሌና በነሐሴ ወር ብቻ ከ201 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰብስቧል፡፡ ከዚህ ውስጥም ከ101 ሚሊዮን ብር በላይ ከዳያስፖራው የተገኘ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ከግብ ለማድረስ የሁለተኛ ዙር የውኃ ሙሌትን ለማሳካት በ2013 በጀት ዓመት በተለያዩ ሁኔታዎች በተደረገው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብርም ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡንም ኃላፊው ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

የቤቶች ኮርፖሬሽን የፈጸመውን የ20 ሚሊዮን ብር ቦንድ ግዥ የግድቡ ግንባታ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር) ተረክበዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ላደረገው ድጋፍ ምስጋና ያቀረቡት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር የሚኖረው ኢትዮጵያውያን ባላቸው አቅም ሁሉ እንዲደግፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ረሻድ ከማል በበኩላቸው፣ ኮርፖሬሽናቸው ለአገራዊ ፕሮጀክት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብን ከግብ ለማድረስና ያሉትን መሠረታዊ ችግሮች ለመፍታት ተቋሙ ከመንግሥት ጎን በመቆም የሚሠራም ይሆናል ሲሉም አክለዋል፡፡

የታላቁ የህዳሴ ግድብ ጽሕፈት ቤት ላይ የሚታየውን የቢሮ ችግር ለመቅረፍ፣ ስታዲየም አካባቢ የሚገኘውን የኤርትራ ኤምባሲ በአዲስ መልክ አድሶ ለመገንባት 45 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደሚያደርግ የቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተናግረዋል፡፡

የማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን በተመለከተ የሚደረገው የውጭውን የዲፕሎማሲ ጫናን በመቋቋም የሁለተኛ ዙር የውኃ ሙሌት ማከናወን ተችሏል፡፡

ግድቡ አሁን ካለበት ቦታ ለመድረስ ሠራተኛው፣ የመከላከያ ሠራዊት፣ እንዲሁም ዳያፓስፖራዎች ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ የተደረገው ርብርብም የኢትዮጵያን ዕድገት አንድ ዕርምጃ ከፍ እንዲል ያደርጋል ብለዋል፡፡

የቤቶች ኮርፖሬሽን ከዚህ በፊት በነበረው የድጋፍ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር የ20 ሚሊዮን ብር የቦንድ ግዥ መፈጸም እንደቻለ፣ ከዚህም በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት ጽሕፈት ቤቱ ያለበትን የቢሮ ችግር ለመቅረፍ የቀድሞ የኤርትራ ኤምባሲ ሕንፃን አድሶ አገልግሎት ላይ እንዲውል ዕቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ታላቁ የህዳሴ ግድብ የሉዓላዊነትና የፍትሐዊነት ጥያቄ የሚያስነሳ መሆኑን፣ በተለይም ደግሞ አገሪቱ ከሺ ዘጠኝ መቶ ሃምሳዎቹ ጀምሮ ዕርዳታና ብድርን ተመርኩዛ የምትንቀሳቀስ በመሆኗ ግድቡ ይህንን ችግር በከፍተኛ ሁኔታ ያቃልላል በማለት ዋና ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡  

በተለይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ እናቶች ከመቀነታቸው አውጥተው የቦንድ ግዥ መፈጸማቸው የህዳሴ ግድቡ ላይ ያላቸው እምነት ከፍተኛ መሆኑን ያሳያል በማለት አክለዋል፡፡

ግድቡም ሙሉ ለሙሉ ከተጠናቀቀ በኋላ ከጥገኝነት መላቀቅ እንደሚቻል ያስታወሱት አረጋዊ (ዶ/ር)፣ ይህንንም ለማሳየት መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ጽሕፈት ቤቱ በ‹‹8100 A›› የጽሑፍ መልዕክት ከ31 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉን፣ ዘንድሮም የተሻለ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር እንደሚያከናውን ማኅበረሰቡም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ አቅርቧል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...